Ethiopia Zare (ቅዳሜ ኅዳር 20 ቀን 2001 ዓ.ም. November 29, 2008)፦ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 10 ክፍለ ከተሞች መካከል በድህነት ደረጃ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13/14 እንደሚመራ አንድ ጥናት አመለከተ። አራዳ፣ አዲስ ከተማና ልደታ ክፍለ ከተሞችም የተጨናነቀ የህዝብ ብዛትና ከፍተኛ የገቢ ማነስ የሚታይባቸው ክፍለ ከተሞች መሆናቸው ተገልጧል።

 

ኅዳር 18 ቀን 2001 ዓ.ም. "የድህነት ገጽታ በአዲስ አበባ" በሚል ርዕስ የማኅበራዊ ጥናት መድረክ፣ ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት ባደረገው ጥናት፣ በአራቱም ክፍለ ከተሞች የሚታየው የድህነት ገጽታ አስከፊ መሆኑንና በተለየ ሁኔታ ግን ሴቶች ተጠቂ መሆናቸው ተመልክቷል።

 

አቶ ካሳዬ አማረ የዜጋ ለዕድገት ሀገር በቀል ድርጅት ተወካይ፤ በጥናታቸው ላይ እንደገለፁት ድርጅታቸው በሚንቀሳቀስበት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13/14 የሚገኘው ኅብረተሰብ የድህነት ደረጃ፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙ ሌሎች ክፍለ ከተሞች የባሰ መሆኑን ተናግረዋል።

 

እንደ አቶ ካሳዬ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተወሳሰቡ የድህነት አረንቋ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ያሉበት መሆኑን ጠቁመው፣ ከነዚህም ውስጥ ሥራ አጥነት በከፍተኛ ደረጃ የሚታይበት ከመሆኑ ባሻገር፣ ንጽኅና የጎደላቸው ቤቶች፣ ከኤች.አይ.ቪ. ቫይረስ ጋር የሚኖሩ በርካታ ሰዎችና የመኖሪያ ቤት እጥረት ያለበት ክፍለ ከተማ እንደሆነ ገልጸዋል። በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አብዛኛው ኅብረተሰብ በእማወራ የሚተዳደር በመሆኑም፣ እናቶች ልጆቻቸውን ለመመገብ የሚኖሩባቸውን ላስቲክ ቤቶች ለሴተኛ አዳሪዎች በማከራየት፤ አልያም ጥቃቅን በሆኑ የጉልት ንግድ ላይ መሠማራት ግድ እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

 

በኤች.አይ.ቪ. ሥርጭት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች የሚገኙበት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ካሳዬ፣ በአካባቢው አስገድዶ መድፈር፣ የጫትና ሺሻ ንግድ የተስፋፋበት መሆኑን አመልክተዋል። ድህነቱ ባስከተለው ማኅበራዊ ቀውስ ሳቢያ የአካባቢው ሴቶች፣ በምርጫ 1997 እንዳይመርጡ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን ያስታወሱት አቶ ካሳዬ፤ እናት አባት የሌላቸው በርካታ ሕፃናትና ጧሪና ደጋፊ ያጡ አዛውንቶች የሚኖሩበት ክፍለ ከተማ መሆኑን ተናግረዋል።

 

"ድህነትና በጊዜ ሂደት የሚያሳየው ተለዋዋጭነት በአራዳ፣ በአዲስ ከተማና በልደታ ክፍለ ከተሞች" በሚል ርዕስ ጥናታቸውን ያቀረቡት ወ/ት ነፃነት ተክለኃይማኖት በበኩላቸው፤ በሦስቱ ክፍለ ከተሞች ማለትም በአራዳ፣ በአዲስ ከተማ እና በልደታ ክፍለ ከተሞች የሚኖረው ህዝብ ከከተማው ነዋሪ 44 በመቶ የሚይዝ መሆኑንና ህዝብ ተጨናንቆ ከሚኖርባቸው ክፍለ ከተሞች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ።

 

እንደ ወ/ት ነፃነት ላለፉት አምስት ዓመታት፣ በሦስቱም ክፍለ ከተሞች ባደረጉት ጥናት፣ በልደታ 53 ከመቶ፣ በአራዳ 29 ከመቶ፣ በአዲስ ከተማ ደግሞ 47 ከመቶ ህዝብ በድህነት ውስጥ ይገኛል።

 

እንደ ጥናት አቅራቢዋ ከሆነም በነዚህ ክፍለ ከተሞች በዋነኛነት ሴቶች የድህነት ተጠቂ መሆናቸውን አመልክተው፣ በቁጥር ደረጃ ሲቀመጥ ሴቶች 51.1 ከመቶ ሲሆኑ፣ ወንዶች ግን 48.8 ከመቶውን ይይዛሉ።

 

በሦስቱም ክፍለ ከተሞች በተደረገው ጥናት፣ በየጊዜው የሚያጋጥመውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ጥናቱ ከተደረገባቸው ዜጎች ለመረዳት እንደተቻለው፤ ቀደም ሲል በቀን ሦስቴ ይበሉ የነበሩት ወደ ሁለት ጊዜ፣ እንዲሁም ከዚያ በፊት የማይመገቧቸውን ምግቦች ለመመገብ መገደደቸው ተመልክቷል።

 

አንዳንድ ቤተሰቦች ደግሞ የቤት ዕቃዎቻቸውን በመሸጥ፣ መሠረታዊ የምግብ ፍላጎታቸውን ማሟላታቸውንና በሦስቱም ክፍለ ከተሞች የሚኖረው ኅብረተሰብም በተጨናነቁ ቤቶች፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነዋሪና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች እንደሚገኙ ተገልጧል።

 

ወ/ት ነፃነት ጥናታቸውን ለማካሄድ በርካታ መረጃዎችን መጠቀማቸውንና በጥናት ናሙናነት ከቀረቡ 300 አባወራዎች ውስጥ በጾታ፣ በብሔረሰብ፣ በኃይማኖትና በትምህርት ደረጃ ያለውን ሁኔታ ታሳቢ እንዳደረጉ ገልጸዋል። በዚህም መሠረት በክፍለ ከተሞቹ በተደረገው ጥናት አብዛኛዎቹ በድህነት ገጽታ ውስጥ ያሉት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ሲሆኑ፣ በመቀጠል ደግሞ የሙስሊምና የፕሮቴስታንት ተከታዮች እንደሆኑ ተናግረዋል።

 

ጥናቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት ንግግር ያደረጉት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የልማት ዕቅድና ጥናት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አደም እንደተናገሩት፤ የጥናት ውጤቶቹ መንግሥት በብሔራዊ ደረጃ ድህነትን ለመቅረፍ ከያዘው እንቅስቃሴ ጋር ተቀናጅቶ ለዜጎች የተሻለ ኑሮ መምጣት መተባበር እንደሚገባ አመልክተዋል።

 

በመጨረሻም ከየክፍለ ከተሞቹ የተገኙ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት፣ ጥናቱ ለየክፍለ ከተሞቹ ፖሊሲ አስፈጻሚዎች እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ