Ato Tamerat LayneEthiopia Zare (ኀሙስ ታህሳስ 9 ቀን 2001 ዓ.ም. December 18, 2008)፦ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ፤ ለ12 ዓመታት በእስር ከቆዩ በኋላ ነገ ጠዋት ዓርብ ታህሳስ 10 ቀን 2001 ዓ.ም. ቃሊቲ ከሚገኘው የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንደሚለቀቁና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደሚቀላቀሉ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለፁ። 

 

የኢህአዲግ አንጋፋና ታዋቂ ታጋይ የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ በተከሰሱባቸው ክሶች 18 ዓመት እንዲታሰሩ ተፈርዶባቸው፣ ከ12 ዓመታት እስር በኋላ ከእስር የሚፈተቱት በአመክሮ መሆኑን ለማወቅ ችለናል። ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት የአመክሮ ጥያቄ ያቀረቡት አቶ ታምራት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግንቶ እንደነበር ባለፈው ሣምንት መዘገባችን አይዘነጋም።

 

አቶ ታምራት በሦስት ጉዳዮች ክስ ተመስርቶባቸው፣ በአንዱ ክስ ነፃ ተብለው፤ በሁለቱ ግን “ጥፋተና” ከተባሉ በኋላ የ18 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው እንደነበር አይዘነጋም። ጥፋተኛ ተብለውባቸው የነበሩት ክሶች “ለተለያዩ ክልሎች የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ግዥ ያለ ጨረታና ያለተወዳዳሪ ሰጥተዋል” እንዲሁም “የጣልያን ኩባንያዎች ለተወሰኑ የጨርቃ ጨርቅ ድርጅቶች ያቀረቡትን ጥሬ ዕቃ ዕዳ መክፈያ በሚል በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጣ ቡና እንዲሰጥ አደርገዋል” በሚሉት እንደሆነ ይታወሳል።

 

በነገው ዕለት የአቶ ታምራት ላይኔ እህትን ጨምሮ ቤተሰቦቻቸው ቃሊቲ ሄደው እንደሚቀበሏቸው ለማወቅ ችለናል። የአቶ ታምራት ላይኔ ባለቤትና ሁለት ሕፃናት ሴቶች ልጆቻቸው ነዋሪነታቸው በአሜሪካ ሲሆን፣ በነገው ዕለት ቃሊቲ እንደማይገኙ ለመረዳት ችለናል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ