በማትያስ ከተማ

Ethiopia Zare (ሰኞ ጥር 4 ቀን 2001 ዓ.ም. January 12, 2009)፦ የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን፣ የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንን፣ የአቶ በቀለ ጅራታን እንዲሁም በፖለቲካ ምክንያት በእስር እየማቀቁ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን እንዲፈቱ የሚጠይቀውንና ረቡዕ ጥር 6 ቀን (January 14) ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የተቃውሞ ሠልፍ በስዊድን ቅድመ ሁኔታው መጠናቀቁ ተገለጸ።

 

በተለያዩ ሀገራት ሊካሄድ ዕቅድ የተያዘለትን ይህንን የተቃውሞ ሰልፍ ለማዘጋጀት በስዊድን የተቋቋመው ጊዜያዊ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ምትኩ የሱፍ በዕለቱ የተያዘው ዕቅድ ምን እንደሚመስል አብራርተዋል። ሰልፈኛው በዕለቱ ከቀኑ በ13:00 ሰዓት በሰልቨስትሬ ተገናኝቶ ወደ ሚንቶርየት በማምራት ለፓርማው የተዘጋጀ ደብዳቤ እንደሚሰጥ ገልፀዋል።

 

በዚህ ሰልፍ ላይ የስዊድን የሶሻል ዲሞክራት ፀሐፊ ማሪታ ኡልቭስኩግ እና ልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላትና ለሰልፉ ድምቀት የሚሰጡ የኪነት ባለሙያዎች እንደሚገኙ ከአቶ ምትኩ ገለፃ ለመረዳት ችለናል።

 

በተጨማሪም ስለሰልፉ ሲያብራሩ፤ ይህንን ሰልፍ የጠራው የተለየ የፖለቲካ ደርጅት ሳይሆን ስለሀገራችን ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያውያን እና ድርጅቶች በመነሳሳት እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሰልፍን ልዩ ስለሚያደርገው ደግሞ የማሪታ ኡልቭስኩግ በሰልፉ ላይ መገኘት ሲሆን፣ የስዊድን የሶሻል ዲሞክራት አባላት ከዚህ በፊት በእንዲህ አይነት ሰልፍ ላይ የተገኙት በቬትናም ወረራ ተቃውሞ ጊዜ ብቻ እንደነበርም አስታውሰዋል። የስዊድን የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ በሀገሪቱ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ያለው ፓርቲ እንደሆነ ይታወቃል።

 

ሰልፈኛው ድምፁን እያሰማ ቆይታ በሚያደርግበት አደባባይም ማሪታ ኡልቭስኩግ እና የአዘጋጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ምትኩ የሱፍ ንግግር እንደሚያደርጉ እንዲሁም ጽሑፎችና ግጥሞችም እንደሚቀርቡ ለማወቅ ተችሏል።

 

ይኸው ”ዓለም አቀፍ ሰልፍ ለፍትህና ለሰብዓዊ መብት መከበር” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ዓለም አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲ ከሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ውስጥ ”በሕግ ሥም የሚፈፀሙ ወንጀሎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ በሰበብ አስባቡ ለእስር የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን በአስቸኳይ ይፈቱ፣ በግሉ ሚዲያ ላይ የሚደረገው ማዋከብ ይቁም፣ በኡጋዴን ወገኖቻችን ላይ ግፍ የሚፈጽሙ ለፍርድ ይቅረቡ፣ ...” የሚሉ እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል።

 

ዓለም አቀፉ የተቃውሞ ሰልፍ ዋና ከተማዋን ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ በበርካታ የአሜሪካ ከተሞች፣ ቤልጂየም ብራስልስ፣ ጀርመን ፍራንክፈርት፣ ስዊዘርላንድ ጄኔቭ፣ እንግሊዝ ሎንዶን፣ ኖርዌይ ኦስሎ፣ ስዊድን ስቶክሆልም ረቡዕ ጥር 6 ቀን (January 14) እንደሚካሄድ ታውቋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!