በማትያስ ከተማ

Ethiopia Zare (ኀሙስ ጥር 7 ቀን 2001 ዓ.ም. January 15, 2009)፦ ረቡዕ የካቲት 6 ቀን 2001 ዓ.ም. ተለዋዋጩን የስዊድን የአየር ሁኔታ ደፍሮ ለመናገር ባያስተማምንም ዕለቱ ከሰልፈኛው ጋር የተባበረ ይመስል ነበር። በስቶክሆልም ዝናብ አልነበረም። በስዊድን ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ሊገናኙ ከተቃጠሩበት በስቶክሆልም በሰርገልስ ቶርየት አደባባይ የደረስኩት ከሰዓቱ ቀደም ብዬ ነበር። በቦታው ላይ መጠነኛ ሰዎች የነበሩ ሲሆን ቀስ በቀስ ግን አደባባዩ ባንዲራ በለበሱ ባነገቱና በተከናነቡ ልዩ ልዩ ጽሑፎችና ፎቶዎች በያዙ ኢትዮጵያውያን ተሞላ።

 

ለዚህ ሰልፍ መነሻ የሆነው የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እና የአቶ በቀለ ጅራታ አላግባብ መታሰር ሲሆን፣ ለፍትህና ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚል ዓለም አቀፋዊ ስያሜም ይዟል።

 

በቦታው ላይ ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ ልዩ ልዩ የቅስቀሳ ሙዚቃዎችና መፈክሮች ሲስሙ ቆይተው ስለሰልፉ ሁኔታ ማብራሪያና ገለጻ ለሰልፈኛው ተሰጥቷል። እንዲሁም ለስዊድናውያኑ እንዲገባ በማሰብ በሀገራቸው ቋንቋ ስለሰልፉ ዓላማ መግለጫ ተሰጥቷል። አቶ ዳንኤል አበበም አጠር ያለ ግጥም ካሰሙ በኋላ ሰልፈኛው በ8 ሰዓት ፓርላማው ወደሚገኝበት ሚንቶርየት አደባባይ ልዩ ልዩ መፈክሮች በማሰማት ሲጓዝ የአካባቢውን ህዝብ ትኩረት ስቦ ነበር።

 

ሰልፈኛው ካነገባቸው ጽሑፎችና በተደጋጋሚ ከሚላቸው መፈክሮች መሃል ”እነመለስ ኢትዮጵያን አይወክሉም፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ባደረሱት በደል ለፍርድ ይቅረቡ!፣ እነብርቱካን ሚደቅሳ በአስቸኳይ ይፈቱ!፣ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ መብት ይከበር የፕሬስ አፈና ይቁም! ...” የሚሉ ነበሩበት።

 

 

በዚህ ጉዞ ላይ የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ ፀሐፊ ማሪታ ኡልቭስኩግ ሰልፈኛውን አጅበው አብረው የተጓዙ ሲሆን፣ ፓርቲያቸው በእንዲህ አይነቱ ሰልፍ ላይ ከቬትናም ጦርነት ወዲህ ለተቃውሞ የወጣው አሁን ብቻ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

 

በ8:30 ሰዓት (14:30) ፓርላማው በሚገኝበት አደባባይ የደረሰው ሰልፈኛ መፈክሮችና የቅስቀሳ ዘፈኖች ሲያሰማ ቆይቶ ለፓርላማው ጽ/ቤት ሁለት ደብዳቤዎች ከሰጠ በኋላ የሰልፉ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ምትኩ የሱፍ በቦታው ላይ የነበሩትን የሶሻል ዲሞክራት ፓርቲ ፀሐፊን እንዲሁም የፎልክ ፓርቲን ተወካይ ጉናር አንድሬን ንግግር እንዲያደርጉ ጋበዙ።

 

ማሪታ ኡልቭስኩግ ወ/ሪት ብርቱካን ስዊድንን በጎበኙበት ጊዜ እንዳነጋገሯቸው ጠቅሰው፤ ለዲሞክራሲ መገንባት፣ ለሕግ እኩልነት የቆሙ ጠንካራ መሪ መሆናቸውን መረዳት እንደቻሉና ስዊድን ሀገር ተናገሩ በተባሉትም መታሰር እንደማይገባቸው በማብራራት ይህ አይነቱም ሕግን የጣሰ እስራት በሳቸው ብቻ የተፈጸመ ሳይሆን በሌሎችም ዜጎች በመፈጸም ላይ መሆኑ ያሳሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል። ይህንንም ሁኔታ እንደሚቃወሙት ገልጸው ለወደፊቱም በተቃውሞው ከኢትዮጵያውያኑ ጋር እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

 

የፎልክ ፓርቲ ተወካይ ደግሞ በበኩላቸው ኢትዮጵያን እንደጎበኙ ዋና ከተማውን ብቻ ሳይሆን ክልሎችንም ጭምር ዞረው እንደተመለከቱ አስታውቀው፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ አክብሮትና ፍቅር እንዳላቸው በማስረዳት የሀገሪቱ መንግሥት ግን ሕግን በመጣስ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ተቃውመዋል። ይህንንም ከመንግሥት መሪዎች ጋር ለመነጋገር ሞክረው አጥጋቢ መልስ እንዳላገኙ በመግለጽ፤ ኢትዮጵያውያኑ የሚያደርጉትን ተቃውሞ እንደሚደግፉና እንደሚረዱ አስታውቀዋል።

 

ከዚህ በኋላም አቶ ምትኩ ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል። በንግግራቸውም ላይ ሀገራችን በሕጋዊ ምርጫ የተቋቋመ መንግሥት እንደሚያስፈልጋት ኢህአዲግ የህዝብ ወኪል እንዳልሆነ ባሁኑ ጊዜም የፓርቲ ጥያቄ የምናራምድበት ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማዳን በአንድነት የምንነሳበት ወቅት በመሆኑ የጓዳ ኩርፊያ በመተው እጅ ለእጅ ተያይዘን ትግላችንን እናጠናክር በማለት መድረኩን ለአንድነት ተወካይ ለአቶ መላኩ ለቀዋል።

 

አቶ መላኩ በበኩላቸው የወይዘሪት ብርቱካንንና የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንን እስራት አውግዘው የቀድሞው ቅንጅት ወራሽ የሆነው የአንድነት ፓርቲ የድጋፍ ማኅበር ለፍትህ ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የሚያደርገውን ትግል ማጠናከር እንደሚገባው አሳስበዋል።

 

በመጨረሻም "የነፃነት እልህ" የሚልና ሌላ በማራኪ የተዘጋጀ ከወቅቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተያያዥነት ያለው ግጥም በየፀሐፊዎቹ ተነቦ በአስር ሰዓት (16፡00) የሰልፉ ፍጻሜ ሆኗል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ