Ethiopia Zare (ቅዳሜ የካቲት 15 ቀን 2000 ዓ.ም. February 23,2008) የ"ሰለፊያ" ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ኢብራሂም መሐመድ እና የ"አልቁዱስ" ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ኢዘዲን መሐመድ የካቲት 8 ቀን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አንድ ዘገባ ጠቆመ።

የአልቁዱስ አሣታሚና የአቶ ኢዘዲን መሐመድ ባለቤት ወ/ሮ ማሪያ ቃዲም ከባለቤታቸው ጋር ታስረዋል።

ኢስላማዊ ይዘት ያላቸው "ሰለፊያ" እና "አልቁዱስ" ጋዜጦች ዋና አዘጋጆችና አሣተሚ የታሰሩበት ምክንያት በትምህርት ሚኒስቴር የወጣውን "የትምህርት ተቋማት የአምልኮ ሥርዓት" ረቂቅ መተዳደሪያ በተመለከተ በጋዜጦቹ ላይ ካወጧቸው ጽሑፎች ጋር በተያያዘ መሆኑን ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል። ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ ከፖሊስ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን አልቻለም።

"ሰለፊያ" ጋዜጣ ጥር 30 እና የካቲት 7 ቀን የትምህርት ሚኒስቴርን የአምልኮ ሥርዓት የሚመለከተውን ረቂቅ አስመልክቶ ዘገባዎች አቅርቧል። በቀረቡት ዘገባዎች የሐረር እስልምና ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የትምህርት ሚኒስቴርን ረቂቅ ሕግ በመቃወም ጻፈው የተባለውን ደብዳቤ የተመለከተ ጽሑፍ አቅርቧል። ከዚህም በተጨማሪ በዚሁ ዕትም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከአሜሪካ ከመጡ ልዑካን ጋር ያደረገውን ስብሰባ በመንቀፍ ሌላ ጽሑፍ አስፍሯል።

በ"አልቁዱስ" ጋዜጣ ላይ በሪፖርተርነት የሚሠራው ሙሃጅር ዲኖ እንደሚገልጸው አዘጋጁ የታሰረው "ኢትዮ ሙስሊምስ ዶት ኮም" ከተባለ ድረ-ገጽ የተገኘና ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ወጣ የተባለ ደብዳቤን በፊት ገጹ ላይ በማውጣቱ ነው።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ጽፎታል በተባለው እና በድረ-ገጹ የተበተነው ደብዳቤ ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው ረቂቅ እንዲጸድቅ የሚደግፍ እና ነገሩን የሚያናፍሱ ጋዜጦችን የሚኮንን እንደሆነ በጋዜጣው ላይ ከወጣው ጽሑፍ ለመረዳት ተችሏል።

የጋዜጦቹ ዘገባ እንደሚለው ከሆነ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የትምህርት ሚኒስቴርን ረቂቅ ደንብ ይቃወማል።

የ"አልቁዱስ" ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ኢዘዲን እና የጋዜጣው አሣታሚ የሆኑት ወ/ሮ ማሪያ ቃዲ ከታሰሩ በኋላ ለጋዜጣ ሥራ ይጠቀሙበት የነበረው ኮምፒዩተር፣ ፕሪንተር፣ ካሜራ፣ እና ሌሎች የጽሕፈት መገልገያዎች በፖሊስ ተጭነው እንደተወሰዱ ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።

የጋዜጦቹ ዋና አዘጋጆች እና አሣታሚዎች ሰኞ የካቲት 10 ፍርድ ቤት ቀርበው ለየካቲት 21 ቀን መቀጠራቸውን አቶ ሙሃጅር ዲኖ ጨምረው ገልጸዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ