"ከ602 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለምግብ መግዣ ያስፈልጋል" አቶ ምትኩ ካሣ (የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር ዴኤታ)

Ethiopia Zare (ማክሰኞ የካቲት 17 ቀን 2001 ዓ.ም. February 24, 2009)፦ በኢትዮጵያ አራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ህዝብ መራቡን በዛሬው ዕለት የገለፀው የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ከ602 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለምግብ መግዣ እንደሚያስፈልገው አስታውቋል። ከዚህ ውስጥ 148 ሚሊዮን ዶላር በእጁ እንደሚገኝና፣ 455 ሚሊዮን ዶላሩን ከለጋሾች እንደሚጠብቅ ይፋ አደረገ።

 

ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች በዛሬው ዕለት ይህንን ይፋ ያደረጉት የግብርናና ገጠር ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት አቶ ምትኩ ካሣ ናቸው። እንደ አቶ ምትኩ ገለፃ ከሆነ የተራቡት ወገኖች 591 ሺህ ሜትሪክ ቶን የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

 

አራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ህዝብ መራቡንና ለሚቀጥሉት አስር ወራት የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ እና የለጋሽ ሀገሮችና ድርጅቶች ጋር በመሆን በጋራ በተደረገ ጥናት የመስክ ጥናት መረጋገጡን ገልፀዋል።

 

የሚኒስትር ዴኤታው አቶ ምትኩ የምግብ እጥረቱ የተከሰተው ባለፈው ዓመት የበልግ ዝናብ እጥረት በመኖሩና በመዛባቱ እንደሆነና የምግብ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመናሩ መሆኑን አስረድተዋል።

 

አክለውም ጥናቱ እንደሚያሳየው ከሆነ የተራቢው ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቀንሷል ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአንዳንድ አካባቢዎች የግጦሽ እጥረት ስለነበረ የእንስሳት ዋጋ መቀነስ ለምግብ እጥረቱ ምክንያት መሆኑን ጥናቱ እንደሚያሳይ ገልፀዋል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን እያጠቃ ያለውን ድርቅ አስመልክቶ የተለያዩ የውጭ ሀገር የመገናኛ ብዙኃን፣ ሀገር በቀልና የውጭ የዕርዳታ ድርጅቶች የሚሰጡትን አኀዝ ሲያጣጥሉ እንደነበር አይዘነጋም። ባለፈው ዓመት ነኀሴ ወር ላይ ጠ/ሚ/ር መለስ ከታይም መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ ”በኢትዮጵያ ረሃብ የለም” ማለታቸውን መዘገባችን አይዘነጋም።

 

በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትና ባለሥልጣናት ከቃላትና ከቁጥር ጦርነቱ ወጥተው በተደጋጋሚ ሀገሪቱንና ህዝቧን ከሚያጠቁበት ድርቅና ረሃብ ለማላቀቅ ዘላቂ መፍትሔ መሻት እንደሚሻል በርካቶች ሲተቹ ይደመጣል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!