ጠንቋዩና ስድስት ግብረአበሮቹ የተከሰሱት በ9 ሰዎች ሕይወት ማጥፋት፣ የሰው ገንዘብና ንብረት በማታለልና በማጭበርበር፣ ሴቶችን በመድፈር ነው

ከዕድሜ ልክ እስራት እስከ የሞት ቅጣት ሊቀጡ ይችላሉ

ጠንቋዩን ታዋቂ ግለሰቦችና ባለሥልጣኖች ያመልኩታል

ማንአልቦሽ ዲቦ፣ ብርቱካንና የሺመቤት ዱባለ፣ ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ ደንበኞቹ ነበሩ

Ethiopia Zare (ዓርብ መጋቢት 18 ቀን 2001 ዓ.ም. March 27, 2009)፦ ከአሥር ዓመታት በላይ ”ባለ አውሊያ” እና ”ባለ ከራማ” እንደሆነ በመግለጽ በርካታ ተከታዮችን አፍርቶ የነበረውና በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ያለው አቶ ታምራት ገለታ የተባለው ”ጠንቋይ” ጉዳይ በመዲናዋ አዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ የሰሞኑ የመነጋገሪያ አጀንዳ (Hot issue) ሆኗል። መነጋሪያነቱ የጨመረው ታዋቂ አርቲስቶች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አትሌቶች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ታዋቂ ባለሀብቶችና የኃይማኖት አባቶች በጥንቆላ ቤቶቹ ተጠቃሚ ነበሩ የሚሉ ምስክሮች ፍርድ ቤት በመቅረባቸው ነው።

 

በኦሮሚያ ክልል ፊቼ ከተማ ተወልዶ በትምህርቱ ብዙም ሳይዘልቅ ብሔራዊ ውትድርና የሄደው አቶ ታምራት፣ ከዚያ ሲመለስ ፊቼ ከተማ ላይ ”ባለአውሊያ” በመሆን ከሚታወቁት እናቱ ላይ “የአውሊያውን” ሥልጣን ተረክቦ፤ በሀገሪቱ ሦስት የተለያዩ አካባቢዎች “የጥንቆላ” መሥሪያ ቤቶች ከፍቶ የ”ጥንቆላ” ሥራውን በስፋት ሲያከናውን ቆይቷል። በአዲስ አበባ ውስጥ ልደታ አካባቢ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ሄለን ሕንጻ ጀርባ፣ በናዝሬት ከተማ ልዩ ቦታው ኬላ በተባለ አካባቢ፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ልዩ ቦታው ፊቼ ግራር ጃርሶ በተባለ ቦታ ላይ ለጥንቆላ ሥራ የሚያገለግሉ ግንባታዎችን አከናውኖ በቁጥር የማይታወቁ በርካታ ተከታዮችን አፍርቷል።

 

አቶ ታምራት በጥንቆላ መሥሪያ ቤቶቹ ከሌሎች ስድስት ተባባሪዎቹ ጋር በመሆን ”ባለ አውልያ” እና ”ባለ ከራማ” ነኝ በማለት የሰው ግድያ ወንጀልና ከባድ ማታለል ፈጽሟል በሚል ክስ የቀረበበት ሲሆን፤ ይህንኑ ክሱን የሚያስረዱለትና ቀደም ሲል የዕምነቱ ተከታዮች የነበሩ ከ55 በላይ ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል።

 

እነዚህ ምስክሮች ታምራት፤ ማንኛውንም በሽታ እንደሚያድን፣ ለሰዎች ሀብት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ፣ ዕድሜ እንደሚያስረዝም እና የእግዚአብሔርና የአላህ መልዕክተኛ እንደሆነ በተለያየ ምክንያት ሰምተው በቤት ውስጥ ሲያገለግሉት፣ ንብረታቸውን ሲሰጡትና እንደአምላክና እንደ ወልይ ሲያመልኩት እንደነበሩ ገልጸው፤ የሰው ሕይወት ሲጠፋ፣ ሲታመም፣ ንብረታቸው ሲወድም ከመመልከታቸው ውጪ ያገኙት ነገር እንደሌለ መስክረዋል።

 

ጠዋት ጠዋት ቆብ አጥልቆ ካባ ለብሶ መነኩሴ፤ ከሰዓት በኋላ ደግሞ የሙስሊም ልብስ ለብሶ ሃጂ ይሆናል የሚሉት ምስክሮቹ፤ ‘ክንፍ አለኝ እበራለሁ፣ በአርባ ቦታዎች ላይ ተቀምጬ እፈርዳለሁ፣ የሞተ አስነሳለሁ፣ በኤች.አይ.ቪ. በሽታ የተያዙትን እፈውሳለሁ፣ ሀብታም አደርጋችኋለሁ፣ …’ እያለ ተከታዮቹን ሲያሰባስብና ገንዘብ ሲሰበስብ እንደኖረ ገልጸው፤ በዚህ ምክንያት ከሚሰበስበው ገንዘብ ባለ ሦስት ኮከብ ሆቴል፣ ከአምስት ቦታ በላይ መኖሪያ ቤት፣ በርካታ ውድ መኪኖችን ገዝቷል ብለዋል።

 

በዚህ ቦታ ላይ ታዋቂ አርቲስቶችን፣ የሕግ ባለሙያዎችን፣ አትሌቶችንና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦችን ሲያዩ ለእኛ ይሠራል ብለው በማሰብ መታለላቸውን የገለጹት ምስክሮች፤ “ከታዋቂ አርቲስት ማንን አይታችኋል?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በአሳበለው ዘፈኗ የምትታወቀውን ማንአልቦሽ ዲቦ፣ እህትማማቾቹ ብርቱካንና የሺመቤት ዱባለ፣ እንዲሁም ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ ቋሚ ደንበኛ መሆናቸውንና፤ እንዳውም በያመቱ ለሚከበረው የልደት በዓሉ ስጦታዎችን ይዘው በመምጣት ባንድ አቁመው ዘፈን ይዘፍኑለት እንደነበር መስክረዋል።

 

በአሳበለው ዘፈኗ የምትታወቀውን ማንአልቦሽ ዲቦ በአቶ ታምራት የልደት በዓል ላይ ተገኝታ ”አባባ ታምራት በዘፈንሽ ዓለምን ትዞሪያለሽ ብለውኝ ነበር፤ ይኸው ዓለምን ዞሬ መጣሁ” በማለት በርካታ ተከታዮቹ በተሰበሰቡበት ምስክርነቷን ስትሰጥ የተቀረጸችው ቪዲዮ ታይቷል።

 

በጠንቋዩ ቤት መገኘቷ ስሟ በምስክሮች የተጠቀሰው አርቲስት ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ በተለያዩ ጋዜጦችና ኤፍ.ኤም. ራዲዮኖች ላይ እየቀረበች፤ አቶ ታምራትን የምታውቀው የዛሬ 12 ዓመት ካሴቷን አውጥታ ታዋቂ መሆን ስትጀምር በአንዲት ጓደኛዋ አማካኝነት አንድ ሀብታም ሊተዋወቃት እንደተፈለገች ተነግሯት መሄዷንና ፊቼ በሚገኘው ቤቱም ከጓደኞቿ ጋር ተጋብዛ እንደሄደች በመግለጽ፤ ከዛን በምሽት ጭፈራ ቤቷ ሲመጣ በሰዎች እንዳስወጣችው ተናግራለች። ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በእግዚአብሔር ብቻ እንደምታምን እንዲረዳት ጠይቃለች።

 

ነገር ግን በየመገናኛ ብዙኀኑ ላይ የድምፃዊ ፍቅርአዲስን ቃል የሰማውና ያነበበው የአቶ ታምራት ገለታ ወንድም አቶ በቀለ ገለታ፤ ፍቅርአዲስ ፊቼ ከሚገኘው እናቱ ቤት ጀምሮ ተከታያቸው እንደነበረች ገልጾ፤ ‘ለቀለበቴ ቀን ገጠር ድረስ መጥታ የሰጠችኝን ስጦታ እንኳን አልረሳውም’ ሲል በመግለጽ ደንበኝነቷ አረጋግጧል።

 

ዓቃቤ ሕግ አቶ ታምራትን ጨምሮ በስድስት ክሶች ውስጥ በአንደኛው ክስ በአንደኝነት ዋናውን ተከሳሽ አቶ ታምራት ገለታ ያስቀመጠ ሲሆን፣ አቶ ደረጀ ስሜ፣ አቶ አዲሱ ሱልጣን እና ወ/ት ፍሬገነት ማርዬ ጨምሮ ክስ አቅርቧል።

 

በወንጀሉ ዝርዝር ላይም “ተከሳሾቹ ሆን ብለው በግብረአበርነት ከ1992 ዓ.ም. እስከ 1999 ዓ.ም. ባለው ግዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 22 ልዩ ስሙ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ሄለን ሕንጻ ጀርባ፣ አዳማ ከተማ ልዩ ቦታው ኬላ በተባለ አካባቢ፣ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ቦታው ፊቼ ግራር ጃርሶ በተባለ ቦታ በሚገኙና ለጥንቆላ መሥሪያ በተዘጋጁ ቤቶች ውስጥ፤ ከተባባሪዎቹ ጋር በጋራ በመሆን አቶ ታምራት ማንኛውንም በሽታ እንደሚያድን፣ ለሰዎች ሀብት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ፣ ዕድሜ እንደሚያስረዝም እና የእግዚአብሔርና የአላህ መልዕክተኛ እንደሆነ በመግለጽ ኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ተጽዕኖ በማሳዳር የተለያዩ ግለሰቦች በእምነቱ ስር እንዲወድቁ በማድረግ የግለሰቦቹን ገንዘብና ንብረት ለመውሰድ እንዲመቻቸው፤ ከተቀቀለ ጫት፣ ከአመድ፣ ከሰልፈር፣ ከሽቶ እና ሌሎች ምንነታቸው ያልታወቁ ነገሮች የተቀመመ እና ሃውዛ የሚሉትን ውኅድ ከብሽታቸው ለመዳን የመጡ ግለሰቦች እንዲጠጡ በማድረግና ወደ ሌላ ሕክምና ከሄዱ እንደሚሞቱ በመግለጽ እና በማስፈራራት ተከሳሾች ተግባራቸው ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት እያወቁና እየተረዱ የሆነው ይሁን ብለው የሰው ሕይወት እንዲጠፋ አድርገዋል” ሲል ይከሳቸዋል።

 

የአቶ ታምራት ጥንቆላ እምነት ተከታይ የነበሩና በተለያየ ግዜ ከበሽታቸው ለመዳን ወደ ስፍራው በመሄድ ሕይወታቸውን አጥተዋል ያላቸውን ሟቾች ዓቃቤ ሕግ ሲዘረዝር፤ ተስፉ ተሾመ፣ ኢብራሂም ባርጌቾ፣ ፈጠነ፣ መሐመድ አረጋ፣ ተስፋዬ ታዬ እና መካ አብዱላሂ ይባሉ የነበሩ ስድስት ግለሰቦች ወደ ሕክምና እንዳይሄዱ በመከልከል ውኅዱን አጠጥተው ለመሞት ዳርገው ንብረታቸውን ወርሰዋል ሲል፤ በዚህ ድርጊታቸው በ1949 ዓ.ም. የወጣውን የወ/መ/ሕ/ቁ32/1/ሀ/ለ፣ 58/1/፣ 522/1/ሀ/ሐ የተመለከተውን ተላልፈዋል ሲል አንቀጽ ጠቅሶባቸዋል። በተጠቀሰው አንቀጽ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ዕድሜ ልካቸውን በጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣሉ።

 

ሁለተኛው ክስ፦ በአንደኛው ክስ የተከሰሱት አራቱም ተከሳሾች የተከሰሱ ሲሆን፤ ወሰኔ ፈረደ ትባል የነበረችውን የጥንቆላ እምነቱ ተከታይ የምትሠራው የመጠጥ ግሮሰሪ ሥራ እንደማይሳካላትና መድኃኒት እንደተደረገባት በማሳመን የግሮሰሪዋን ቁልፍ በ80 ሺህ ብር ሸጣ ወደ ቤቱ እንድትገባ ካደረገና ገንዘቡን ላስቀምጥልሽ በሚል ዘዴ ተቀብሎ ወደ ሐኪም ቤት እንዳትሄድ በማሳመን ውኅዱን በተደጋጋሚ እንድትጠጣ ካደረጉ በኋላ ሕመሙ ሲጸናባት አዳማ ወስደው ቤት ተከራይተው እንድትቀመጠጥና እዛው እንድትሞት በማድረጋቸው በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ፣ 58/1/ለ እና 539/1/ሀ/ሐ የተመለከተውን በመተላለፋቸው በዚህ አንቀጽ ስር ጥፋተኛ ተብለው እንዲቀጡለት ይጠይቃል። በዚህ አንቀጽ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ደግሞ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት እንደሚቀጡ ተደንግጓል።

 

ሦስተኛው ክስ፦ በ1995 ዓ.ም. አራቱ ተከሳሾች ሄለን ሕንጻ ጀርባ እና አዳማ በሚገኙ የጥንቆላ ቤቶች ውስጥ የኤች.ኤይ.ቪ. ሕመምተኛ የሆነች አንዲት ግለሰብ የምትወስደውን መድኃኒት አቋርጣ ከሱ ጋር ጫት በመቃም ወደ ጥንቆላው ቤት ብትመላለስ እንደሚያድናት በማሳመን በአቶ ታምራት ትዕዛዝ በወ/ት ፍሬገነት ቀማሚነት ተበጥብጦ የተሰጣትን ውኅድ በመጠጣቷ ሕመሟ ተባብሶ ሰውነቷ ሽባ ሆኖ ልትሞት ስትል በቤተሰቦቿ ጥረት ውጭ ሀገር ሄዳ ብትታከምም ልትሞት ችላለች ያለው ዓቃቤ ሕግ ለዚህ ከባድ የሰው አገዳደል የወንጀል ሙከራ በ1949 ዓ.ም. የወጣውን የወ/መ/ሕ/ቁ32/1/ሀ/ለ፣ 58/1/፣ 522/1/ሀ/ሐ የተመለከተውን ተላልፈዋል ሲል፤ ዕድሜ ልካቸውን በጽኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣቸውን አንቀጽ ጠቅሶባቸዋል።

 

በአራተኛው ክስ፦ አራቱ ተከሳሾችና በመሞቱ ምክንያት ክሱ የተቋረጠው አምስተኛው ተከሳሽ በጋራ ሆነው በካንሰር በሽታ የተያዘች እህቱን ለማዳን ገብቶ የነበረን አቶ መንግሥቱ የተባለ ግለሰብ በጥንቆላው እምነት ስር እንዲወድቅ ካደረጉት በኋላ፤ ከደምወዙ አስር ከመቶ ለስምንት ዓመት እንዲከፍል፣ ለአቶ ታምራት ልደት በየዓመቱ የሁለት ሺህ ብር ኬክ እንዲያቀርብ፣ ለመንታ ልጆቹ ልደት በየዓመቱ አንድ ሺህ ብር ለአራት ዓመት እንዲሰጥ፣ በየዓመቱ ለድግስ 200 ብር እንዲያስገባ እና 50 ሺህ ብር ላስቀምጥልህ በሚል ወስደውበት ለአባቱ ቀብር ሄዶ ሲመጣ እንዳይገባ ተከልክሎ መባረሩን ክሱ ይዘረዝራል።

 

አቶ አረጋ ይማምና ወ/ሮ ራህማ ሰይድ የተባሉ ግለሰቦች፤ ልጃቸውን ሟች መሐመድ አረጋን ለማዳን እንደገቡ በዛው እንዲቀሩ ተደርገው ሴት ልጃቸውን ውጪ ለመላክና ቤታቸው መድኃኒት ስለተደረገበት እንዲሸጡት በማሳመን እና ከሽያጩ ላይ አስራት እንዲከፍሉ በማሳመን 55 ሺህ ብር ለልጃቸው መላኪያ 13 ሺህ ብር ወስዶ በሀብታቸው ላይ ጉዳት እንዲደርስባቸው በማድረጋቸው፤

 

ከአንድ ግለሰብ 20 ሺህ ብር፣ ከሌላኛው 400 ሺህ ብር፣ ንግድ ውስጥ እንገባለን በሚል ከሦስተኛው ሰው 150 ሺህ ብር፣ አንዱን ውጭ እልከዋለሁ በሚል 35 ሺህ ብርና ከሆድ ሕመም እፈውሰዋለሁ ያለውን ሌላኛውን 60 ሺህ ብር፤ በድምሩ 95 ሺህ ብር በመውሰዳቸው በቀላል እስራት ወይም እንደነገሩ ከባድነት እስከ አምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና መቀጮ የሚያስቀጡለት ዓቃቤ ሕግ አንቀጽ ተጠቅሶባቸዋል።

 

አምስተኛ ክስ፦ አቶ ታምራትና ወ/ሮ አልሳቤጥ ሆነው አንዲት ግለሰብን አታለው በማስፈረም የሰው ቤት የራሳቸው በማድረጋቸው በከባድ አታላይነት ተከሰዋል። በዚህ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከአስራ አምስት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና እስከ ብር 50 ሺ በማይበልጥ መቀጮ የሚያስቀጣቸው አንቀጽ ተቅሶባቸዋል።

 

በስድስተኛው ክስ፦ በዚህ ክስ አቶ ታምራት ብቻ የተከሰሰ ሲሆን፤ ከሕመማቸው ለመዳን የመጡ ሦስት ሴቶችን አስገድዶ ደፍሯል የሚል ክስ ቀርቦበታል። በዚህም እስከ አስር ዓመት ሊያስቀጣ የሚችል አንቀጽ ተጠቅሶበታል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!