ጉዳዩም የ”ጠንቋይ” ታምራት ነው

Ethiopia Zare (እሁድ መጋቢት 27 ቀን 2001 ዓ.ም. April 5, 2009)፦ ”በጥንቆላ መሥሪያ ቤቶቹ” ከሌሎች ስድስት ተባባሪዎቹ ጋር በመሆን ”ባለአውሊያ” እና ”ባለከራማ” ነኝ በማለት የሰው ግድያ ወንጀልና ከባድ ማታለል ፈጽሟል በሚል በአቶ አቶ ታምራት ገለታ እና በተባሪዎቹ ላይ ክስ ያቀረበው ዓቃቤ ሕግ ያሉን የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቤ ጨርሻለሁ የቀረኝ የቪዲዮ ማስረጃ ነው በማለቱ፤ በፍርድ ቤት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሜ ዕለት ተሰይሞ በዝግ ችሎት ቪዲዮ ካሴት ሊመለከት ነው።

 

ባለፈው ማክሰኞ ለተሰየመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ዓቃቤ ሕግ ክሱን የሚያስረዱለትና ቀደም ሲል የዕምነቱ ተከታዮች የነበሩ ከ55 በላይ ምስክሮችን አቅርቦ ማሰማቱን ገልጾ፤ ማስረጃዎቹን እያጠናቀቀ መሆኑንና በመጨረሻ ማስረጃነት የወንጀል ድርጊቱን ያስረዳልኛል ያላቸውን ሦስት ቪዲዮ ካሴቶች ፍርድ ቤቱ እንዲመለከትለት ጠይቋል።

 

ፍርድ ቤቱም ጉዳዩ በመርዘሙ የሌሎች ተከሳሾችን ግዜ እየተሻማ መሆኑን በመግለጽ ከሥራ ቀን ውጪ ቅዳሜ ሚያዝያ 3 ቀን 2001 ዓ.ም. እንደሚመለከታቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

 

የቪዲዮ ካሴቶቹ አቶ ታምራት የልደት በዓሉን ሲያከብር የነበሩ ሥርዓቶችን የሚያሳይ ሲሆን፣ በልደቱ ላይ የሚደረጉት ድርጊቶችና ሰዎች የሚናገሯቸው ንግግሮች የወንጀል ድርጊቱን ሊያሳይለት የሚችል ማስረጃ እንደሆነ ተናግሯል።

 

ከሥራ ቀን ውጪ ቅዳሜ ችሎት ለመሰየም ሲቀጠር ይህ የመጀመሪያው ሲሆን፣ በተከሳሹ ላይ አፋጥኖ የመወሰን ፍላጎት ሳይኖር እንደማይቀር አንዳንዶች አስተያየት ይሰጣሉ።

 

አሁን በሚገኝበት ቃሊቲ እስር ቤት ከእስረኞች በተለየ ከቀኑ 6 ሰዓት እስከ 7 ሰዓት በማንኛውም ሰው ሲጠየቅ የነበረ ሲሆን፣ ከትናንት ጀምሮ በተላለፈ መመሪያ ሚስቱና ልጆቹ ብቻ እንዲጠይቁት ተደርጓል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!