Fkereaddis NeqatibebeEthiopia Zare (እሁድ መጋቢት 27 ቀን 2001 ዓ.ም. April 5, 2009)፦ ከአሥር ዓመታት በላይ ”ባለአውሊያ” እና ”ባለከራማ” እንደሆነ በመግለጽ በርካታ ተከታዮችን አፍርቶ የነበረውና በስድስት ሰዎች ሞት፣ ሰዎችን በማታለልና ሴቶችን በመድፈር ወንጀል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ያለው አቶ ታምራት ገለታ የተባለው ”ጠንቋይ” ደንበኛ መሆኗን የዘገቡ ጋዜጦችን ፍርድ ቤት እንደምትገትር አርቲስት ፍቅርአዲስ አስጠነቀቀች። አርቲስት ማንአልሞሽ ዲቦ ታማ በሕክምና ላይ ብትሆንም የትም ቦታ መሄድ መብቷ መሆኑን በመግለጽ ወንድሟ ማስተባበያ ሰጥቷል። ማስተባበያው ግን ”የተባለውን ብትሰማ ታብዳለች” የሚል ሌላ ማስተባበያ ተሰጥቶበታል።

 

ከክርስትና (ኦርቶዶክስ፣ ፕሮቴስታንትና ካቶሊክ) እና ከእስልምና፤ ወጣ ያሉ እምነቶች በኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ውስጥ በግልጽ የማይኬድባቸው፣ የተወገዙና በአብዛኛው ደግሞ የተጠሉ ቢሆኑም፤ በመላ ሀገሪቱ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ራሳቸውን ”ጠንቋይ”፣ ”ባለአውሊያ”፣ ”ባለከራማ”ና … የሚሉ ስያሜዎችን በመስጠት አገልግሎት የሚሰጡና የሚቀበሉ የመኖራቸውን ያህል በርካታ ቁጥር ያለው የማኅበረሰብ ክፍል ወደነዚህ ቦታዎች በመሄድ የሚያምንበትን ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል።

 

ሰሞኑን የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያና ማኅበራዊ አጀንዳ አስረስቶ፣ በመላ ሀገሪቱ ለሥራ፣ ለትምህርት፣ ሻይ ለመጠጣት አሊያም ምግብ ለመብላት፣ እስር ቤት ወይም ሆስፒታል ሰው ለመጠየቅ፣ ለመዝናናት፣ ፀጉር ለመሠራት፣ ማኅበራዊ አገልግሎት ለማግኘት በአጠቃላይ ከሁለት በላይ ሰው በተሰበሰበበት ማንኛውም ቦታ የሚወራው አንድ አይነት ወሬ ነው።

 

እሱም ላለፉት አስር ዓመታት ጤና እናገኛለን ያሉ በርካቶች ሲያመልኩት፤ ንብረት እናገኛለን ያሉ ሲካደሙት፣ ገንዘባችንን ያበዛልናል ያሉ እንዲበዛላቸው እንደባንክ ሲጠቀሙት፣ በድምፃችን ዓለምን ያዞረናል ያሉ አርቲስቶች ሲመላለሱለት፣ እግራችን ላይ ሞተር ገጥሞ እናሸንፋለን ያሉ አትሌቶች ሲሰግዱለት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ታዋቂ ባለሀብቶች፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተምረው የወጡ ምሁራንና የኃይማኖት አባቶች ይሄዱበት ነበር የተባለው የ35 ዓመቱ ”ጠንቋይ” ታምራት ገለታ ጉዳይ ነው።

 

ልደታ አካባቢ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ሄለን ህንጻ ጀርባ፣ በናዝሬት ከተማ ልዩ ቦታው ኬላ በተባለ አካባቢና በኦሮሚያ ክልል ልዩ ቦታው ፊቼ ግራር ጃርሶ በተባሉ ቦታዎች ባለሦስት ኮከብ ሆቴል ባለቤት ከመሆን ጀምሮ የዘመናዊ ቤቶችና የበርካታ ዘመናዊ መኪኖች ባለቤት የሆነው እንደራሱ አባባል ”ባለአውሊያ” የታምራት ገለታ ”ጠንቋይ” መሆን ብቻ አልነበረም ወሬውን ያጋጋለው።

 

ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ፖሊስ ፕሮግራም ሲቀርብ፤ አገልጋዩ ነበርን ያሉ በርካታ ምስክሮች ምስክርነታቸውን ሲሰጡ፣ አርቲስቶች አትሌቶች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ታዋቂ ባለሀብቶች የአቶ ታምራት ተከታዮች ነበሩ ማለታቸው ነበር።

 

እነኚህ ምስክሮች ፍርድ ቤት ሲቀርቡም፤ በአሳበለው ዘፈኗ የምትታወቀውን ማንአልሞሽ ዲቦ፣ ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ፣ ብርቱካን ዱባለ እና የሺመቤት ዱባለ ቋሚ ደንበኞች ነበሩ ማለታቸውን ሀገር ውስጥ የታተሙ ጋዜጦች ከዘገቡ በኋላም የአርቲስቶች ጉዳይ የመወያያ አጀንዳ ሆኗል።

 

ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ ስሟ ከተነሳ በኋላ፤ ለማስተባበል በሰጠችው ቃለምልልስ አቶ ታምራትን ከአስራ ሦስት ዓመት በፊት ገና ካሴት እንደወጣች አንዲት ጓደኛዋ ልደታ አካባቢ ያለ አንድ ሀብታም ነው ብላ ልታስተዋውቃት እንደወሰደቻትና እንደማንኛውም ሰው ቤት ከመስተናገድ ወጪ የተለየ ነገር አለማየቷን፤ ከዛም ፊቼ ያለው ቤቱ ጋብዟቸው ከጓደኞቿ ጋር መሄዷንና እዛ የተለየ ነገር በማየቷ ቤቱን ጥላ እንደወጣች፤ በመጨረሻም አንድ ግዜ የምትሠራበት ክለብ በመጣበት ግዜ በጋርድ እንዳስባረረችው በመግለጽ እሷ ከእንዲህ ያለ እምነት የራቀችና በቤተክርስቲያን እንደምታምን ገልጻ ነበር።

 

ሌሎች ምስክሮች ሌላ ጉዳይ አንስተው ስለሰውየው በሰጡት የምስክርነት ቃል፤ ሰውየው ጥንቆላውን የጀመረው ከ10 ዓመት በፊት በጀመረበት ወቅት ደግሞ ወዲያውኑ ሀብታም እንዳልሆነና እንዳውም አንድ ምስክር የሥራ ድርሻውን ሲገልጽ ከሰባት ዓመት በፊት ሰውየው ገንዘብ ስላልነበረው ቡና የማፈላው ኩበት ለቅሜ ነበር ብሏል። ስለዚህ ፍቅርአዲስ የሰጠችው ማስተባበያ ከእውነታ ጋር የሚጋጭ ነው።

 

በማስተባያው ማግስትም አብሮት የተከሰሰውና በዋስ ያለው የታምራት ገለታ ወንድም አቶ በቀለ ገለታ፤ ‘ፍቅርአዲስ በጣም ጥሩ ልጅና ለቤተሰባችን አሳቢ ነበረች። ዛሬ ወንድማችን ታሰረ ብላ ውሸት መናገር አልነበረባትም። ለማንኛውም እውነቱ ፍቅርአዲስ የኛቤት ደንበኛ የሆነቸው ለሦስት ቀን ሳይሆን ለበርካታ ዓመታት ነው። ለእኔ በተለይ ሳገባ ለሠርጌ የሰጠችኝን ስጦታ አረሳውም።’ ሲል ቃለምልልስ ሰጥቷል።

 

ከዚህ በኋላም ፍቅርአዲስ ኤፍ.ኤም. ሬዲዮ ላይ ቀርባ ”እኔ እሱ ጋር ብሄድ የ2 ሚሊዮን ብር ቤት እሠራለሁ?፣ ልጆቼን በዓመት 40 ሺህ ብር እየከፈልኩ አስተምራለሁ?፣ ልጆቼን ይንሳኝ አልሄድኩም እያለች እንባ ቀረሽ ብታስተባብልም ሰሚ አላገኘችም። ይልቁንም ናዝሬት ለኮንሰርት ሄዳ መድረክ ላይ ከወጣች በኋላ ”ታምራት! ታምራት!” እያሉ ታዳሚዎች ቢያስቸግሯት ሳትዘፍን ወደ አዲስ አበባ ተመልሳለች።

 

እንደተመለሰችም ጠበቃ ቀጥራ የተሳሳተ ዘገባ አውጥተውብኛል ያለቻቸውን ጋዜጦች በሙሉ በደብዳቤ እያስጠነቀቀች ሲሆን፣ ምንጮች እንደገለጹት በቀለ ገለታ ሠርግ ላይ ተገኝታ ስጦታ ስትሰጥ የሚያሳይ ፎቶግራፍ መኖሩን ነው። በተመሳሳይ ስሟ የተነሳው ማንአልሞሽ ዲሞ ወንድም፤ በሕክምና ላይ መሆኗንና የትም መሄድ መብቷ መሆኑን በመግለጽ ማስተባበያ ቢሰጥም፤ ከማስተባበያው ቀይሎ እሷም ”ጠንቋይ ጋር ትሄዳለች መባሉን ብትሰማ ታብዳለች” የሚል ልክ እንደማትሄድ የሚያሳይ ማስተባበያ ተሰጥቶበታል።

 

ነገር ግን ማንአልሞሽ ከሱ ጋር ስትጨፍር የሚያሳይ ፎቶግራፏ ሰሞኑን በጋዜጣ ወጥቶ የነበረ ቢሆንም፤ በየትኛውም የመገናኛ ብዙኀን ማስተባበያ ባለመስጠቷ የሷ ጉዳይ እንደ ፍቅርአዲስ የገነነ አልሆነም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!