Ato Bereket SemeonEthiopia Zare (ማክሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2001 ዓ.ም. April 7, 2009)፦ በሚንስትሩ አቶ በረከት ስምዖን የሚመራው የመንግሥት ጉዳዮች ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት በሣምንት ውስጥ በመንግሥት የሚከናወኑ ታላቅቅ ጉዳዮች ላይ ለመንግሥት፣ ለግልና ለውጭ ሚዲያዎች በየሣምንቱ መግለጫ ለመስጠት መወሰኑን አስታወቀ። በዚህም መሰረት በሣምንቱ የተከናወኑና የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው ባላቸው ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

 

በመግለጫው ላይ ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፤ “ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከለንደኑ ስብሰባ በኋላ በራቸውን ለሚዲያ ዝግ አድርገው ነበር። ይህ ደግሞ ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ ጥያቄ እንዳይነሳባቸው ሸሽተው ነው በሚል እየተነገረ ነው፤ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አሎት?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ በረከት ስምኦን ሲመልሱ፤

 

“ጠቅላይ ሚንስትሩ ለውጭ ሚዲያ በብዛት መግለጫ ሰጥተዋል። ለምሳሌ ለአልጀዚራ፣ ለቢቢሲ፣ ለፋይናሽያል ታይምስ፣ ለቻናል ፎርና ለበርካታ ሚዲያዎች የሰጡበት ሁኔታ ነው ያለው ሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ሽሽት ነው የሚለው እኔ ለምን እንደሚሸሽ አይገባኝም፤ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ የሚያሳፍር ትራክ ሪከርድ አለን የሚል እምነት የለንም። የሚያኮራ ትራክ ሪከርድ ነው ያለን ብለን እናምናለን። ጠቅላይ ሚንስትሩም በዚህ ያምናሉ። ስለዚህ በሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች ላይ መንግሥት አንገቱን ደፍቶ እንዲሄድ የሚያደርገው ነገር አለ ብለን አናምንም። አንገቱን ቀና አድርጎ ማንኛውንም ጥያቄ ለመመለስ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ታሪክ ያለው መንግሥት ነው ብለን ነው የምናምው። ትናንትም ዛሬም እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን ለመመለስ ችግር አልነበረብንም ወደፊትም አይኖርም።” ሲሉ ጥያቄውን አስተባብለዋል።

 

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለንደን ላይ በነበሩበት ግዜ ስለገጠማቸው ተቃውሞ ተጠይቀው፤ “በተቃውሞ ደረጃ ተሰለፉ የተባሉት የኦነግና የኦብነግ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች 10 እና 15 ሆነው ነው የተሰለፉት፤ ያን ያክል ትልቅ የሚባል አይደለም። ባጠቃላይ መልኩ እንደዚህ አይነት የጂ8 እና የጂ20 የመሳሰሉ የዓለም ታላላቅ ፎረሞች በሚካሄዱበት ግዜ፤ ከተለያዩ ዓለሞች ተጠራርቶ የሚመጣ በጣም ሰፊ ተቃውሞ የሚያጋጥምበት ግዜ አለ። ይሄ ብሶታቸውን ለዓለም መንግሥታት የሚያሰሙበት ነው። ከዛ ጋር ተዳምረው ሲታዩ ትልቅ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ብዙም የጎላ ነገር ነበራቸው ማለት አይቻልም።” ብለዋል።

 

“ለንደን ላይ ኢትዮጵያዊያኖች ከእርሶ ጋር ባደረጉት ውይይት ሰዎች እየተመረጡ ነበር የሚገቡት ይህ ለምን ተደረገ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፤ “ስብሰባውን ኤምባሲው ነው ያዘጋጀው። ኤምባሲው የስብሰባ አጠራር ሥነሥርዓት አለው። የተዘጋጀው ቦታ 250 ሰው የሚይዝ የስብሰባ አዳራሽ ነው። በዛ ስብሰባ ላይ ገንቢ በሆነ መንገድ ሊወያዩ ይችላሉ ተብለው የታመነባቸው ደጋፊዎች፣ተቃዋሚዎችና ነፃ የሆኑ ሰዎችን ኤምባሲው ጋብዟል። ስለዚህ አጠራሩ ምንም ስህተት ያለው ነገር አይደለም። በመድረኩ ያልተጠሩ ሰዎች የራሳችን ጉዳይ አለን ብለው መጥተው ነበር። ግን በጥሪ የተጋበዙ ሰዎች ስላልነበሩ አልተፈቀደላቸውም፣ አልገቡም።” ሲሉ አቶ በረከት ምላሽ ሰጥተዋል።

 

የመንግሥትን የቀጣይ ሣምንት ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት ቅዳሜ ሚያዝያ 3 ቀን 2001 ዓ.ም.፤ የኢህአዲግ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ስብሰባ እንደሚያካሂዱና የስብሰባቸው ዋነኛ አጀንዳም፤ “… ለአራተኛ ጊዜ ለሚደረገው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የተነደፈውን ስትራተጂ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴው የመግባቢያ ውይይት ያደርግበታል። በስትራተጂው መነሻ ላይ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ስትራተጂውን ለማጽደቅ የኢህአዲግ ምከር ቤት በበቅርቡ ተሰብስቦ የሚመክርበት ሁኔታ ይኖራል።” ካሉ በኋላ “… ይህንን የምርጫ ስትራተጂ ሲነድፍ ምርጫው ዲሞክራሲያዊና ሠላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ ለማድረግ መላ የሀገራችን ህዝቦች የሚያምኑበትና የሚቀበሉት ታማኝነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ መከተል ያለበትን ስትራተጂ በትክክል ለመንደፍ እንዲቻል ተደርጎ ነው።” ብለዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!