ከሣምንት በኋላ ጠይቁን ተብለዋል

Ethiopia Zare (ዓርብ ሚያዝያ 9 ቀን 2001 ዓ.ም. April 17, 2009)፦ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት ተቀጥረው ሥራ የጀመሩት መለስካቸው አምሃ እና እስክንድር ፍሬው የተባሉት የአሜሪካ ድምፅ ጋዜጠኞች ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጣቸውንና መዘገብ የሚያስችላቸውን ፈቃድ መቀማታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ። መንግሥት በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ዘገባ አለመደሰቱን ከመግለጽ ውጭ የተባሉት ነገር የለም።

 

በትናንትናው ዕለት ጠዋት በአቶ በረከት ስምዖን ስር አዲስ ወደ ተቋቋመው የመንግሥት ጉዳዮች ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ጋዜጠኛ መለስካቸው አምሃ ተጠርቶ መሄዱንና መንግሥት ቪ.ኦ.ኤ. በሚያቀርበው ዘገባ እንዳልተደሰተ እንደተገለፀለት ምንጮች ጠቁመዋል።

 

ከሰዓት በኋላ የሥራ ባልደረቦቹን ጋዜጠኞች እስክንድር ፍሬውን እና የእንግሊዘኛ ዘገባ የሚሠራውን ፒተር ሔይንሊንን (Peter Heinlein) ጨምረው ሲሄዱ ዝርዝር ጉዳዩ ሳይገለጽላቸው የመለስካቸው አምሃና የእስክንድር ፍሬው ፈቃድ (accreditation) መቀማቱ ታውቋል።

 

ማንኛውም የውጭ ሀገር ሚዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ዘገባ ለመሥራት ከመንግሥት የሚሰጥ ፈቃድ (accreditation) የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ይህም በየዓመቱ እየታደሰ ለሥራ የሚያገለግል ነው። ይህ ፈቃድ የሌለው የውጭ ጋዜጠኛ ምንም አይነት ዘገባ ማቅረብ አይችልም።

 

ጋዜጠኞቹን ያነጋገራቸውና ፈቃዳቸው እንዲቀማ ያደረገው በመንግሥት ጉዳዮች ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት አዲሱ ሚንስትር ዴታ አቶ ኤርሚያስ ሲሆን፣ የመጨረሻውን ውሳኔ ከሣምንት በኋላ እናሳውቃችኋለን እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!