አቶ በረከት ከጋዜጠኞች ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ ይዘናል

Ethiopia Zare (ረቡዕ ሚያዝያ 28 ቀን 2001 ዓ.ም. May 6, 2009)፦ መንግሥት ከግንቦት ሰባት ጋር በተያያዘ ”የግድያና የሽብር ተግባር ሊፈጽሙ ሲሉ ያዝኳቸው” ያላቸውን በሥራ ላይ የነበሩና የተባረሩ ጄኔራሎችና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ክሳቸው በመደበኛ ፍርድ ቤት ይታይ ወይስ በጦር ፍርድ ቤት የሚለውን ለመወሰን እየተወያየ መሆኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ምጮች ገለጹ።

 

ምንጮች ለኢትዮጵያ ዛሬ እንደገለጹት፤ ከግንቦት ሰባት ጋር በተያያዘ ስድስት በሥራ ላይ የነበሩ እና ወደ አምስት የሚጠጉ ደግሞ ቀደም ሲል የተባረሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በግድያና በሽብር ተግባር ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ ለዓቃቤ ሕግ ካስረከበ በኋላ ክሱ ሲመሰረት በጦር ፍርድ ቤት ይሁን በመደበኛ የሚለው ገና ውሳኔ አለማግኘቱ ታውቋል።

 

በሥራ ላይ ያሉት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጉዳያቸው ሊታይ የሚገባው በጦር ፍርድ ቤት መሆኑ እንዳላከራከረ ምንጮቻችን ጠቅሰው፤ ቀደም ሲል የተባረሩትን ግን በየትኛው ፍርድ ቤት መከሰስ እንዳለባቸው አለመወሰናቸው ታውቋል። የተባረሩት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጉዳያቸው የት መታየት እንዳለበት ከተወሰነ በኋላ ተከሳሾቹን ለሁለት ከፍለው ክስ እንደሚመሰርቱባቸው የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ጠቁመዋል።

 

የመንግሥት ጉዳዮች ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሚንስትር አቶ በረከት ስምኦን፤ ”የተጠርጣሪዎቹ ጉዳይ በጦር ፍርድ ቤት ይታይ አይታይ የሚለው ወደፊት የሚወሰን ይሆናል። አሁን ባለው ሁኔታ በመደበኛ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ነፃና ገለልተኛ በሆነ መልኩ ይታያል።” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

 

ጅማሮ

ቅዳሜ ሚያዝያ 17 ቀን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌደራል ፖሊስ የጋራ ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ "በሀገራችን ሠላማዊ ትግል አብቅቷል በማለት የደም ማፋሰስን መንገድ እንደ ብቸኛ የትግል ስልት ያወጀው ራሱን ግንቦት 7 ብሎ የሚጠራውና በውጭ ሀገር በእነ ብርሃኑ ነጋ የተቋቋመው የፀረ-ሠላም ቡድን ሕገመንግሥታችንንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓታችንን በኃይል ለመገርሰስ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር ወጪ በማድረግ የወታደራዊ ንዑስ ቡድንና የሲቪል ንዑስ ቡድን በሚል በሀገር ውስጥ ያደራጀው የሽብር መረብና እንቅስቃሴ በፀጥታ ኃይሎች ከሸፏል" የሚል መግለጫ አወጣ።

 

በሌላ በኩል ግንቦት 7 መንግሥት ያወጣውን መግለጫ በመቃወም ። ”የመለስ አገዛዝ በዛሬው ዕለት ሚያዝያ 17 ቀን 2001 ዓ.ም. ’ራሱን የግንቦት 7 ብሎ የሚጠራው ቡድን የሽብር ሴራ ከሸፈ’ በማለት ያወጣውን መግለጫ አንብበነዋል። የመለስ አገዛዝ በተለያዩ ወቅቶች በህዝብ ውስጥ ተቃውሞ ሲበዛበት፣ የተቃዋሚ ድርጅቶች አፋጠው ሲይዙት፣ በገዛ ሠራዊቱና በሲቪል አስተዳደሩ ውስጥ ችግር በገጠመው ቁጥር፣ ህዝብን ለማደናገር ወይም የሚፈልጋቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ለማጥቃት ሲፈልግ እንዲህ አይነቱን መግለጫ ማውጣትና ህዝብን ማደናገር፣ መግለጫውን ተከትሎ የሚፈልገውን መግደል፣ ማሰር፣ ከሥራ ማባረር፣ ከቀየው ማፈናቀልና ማሳደድ ባለፉት አስራ ስምንት ዓመታት ዕድሜው ደጋግሞ ሲፈጽመው የኖረ ነውረኛ ድርጊቱ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ በዛሬው ዕለት ግንቦት 7 ንቅናቄን በሚመለከት ያወጣው መግለጫ ከዚህ በፊቱ ወያኔ ሲያወጣው ከነበሩት መግለጫዎች ልዩነት የሌለው መሆኑን ንቅናቄያችን ይገልፃል።” የሚል መግለጫ ወዲያውኑ አወጣ።

 

መንግሥት ከግንቦት ሰባት ጋር በተያያዘ መጀመሪያ 35 ተጠርጣሪዎችን፣ ቀጥሎ ተጠርጣሪዎቹ 40 መድረሳቸውን ካስታወቀ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ በቀጣይ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡና መንግሥት ክሱን በማስረጃ እንደሚያረጋግጥ አስታውቀዋል።

 

ይህን ዜና የሰሙ በርካቶች፤ መግለጫው የመንግሥት የተለመደ ተራ መግለጫ ነው፣ ዶ/ር ብርሃኑ በአጭር ግዜ ወደ ሥራ እገባለሁ ብለው እንደዛቱ ሥራ ጀመሩ፣ ከ1997 ምርጫ ወዲህ ሁለት የብአዴን አባል የሆኑ ጄነራሎች በአፈንጋጭነት ስም መታሰራቸው፤ በኢህአዲግ ውስጥ ጤናማ አመለካከት እንደሌለ ያመለክታል፣ ምን አልባትም የመለስ ዜናዊ ካቢኔ፤ ከህወሓት ክፍፍል በኋላ ወደ ብአዴን መጠጋቱን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፣ ህወሓቶች ብአዲኖችን መምቻ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው ምንያቱም እየታሰሩ ያሉት ከአንድ ብሔር የወጡ በመሆናቸው፣መከላከያ ውስጥ እንዲህ አይነት ነገር መፈጠሩ ለኢህአዴግ መንግሥት መፈረካከስ አመላካች ነው፣ ... የሚሉና ሌሎች በርካታ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው።

 

ሌላ ጊዜ እንዲህ ያለ የፖለቲካ ጉዳይ ሲያጋጥም አስተያየት ለመስጠት የሚሽቀዳደሙት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ብዙዎቹ ዝምታን የመረጡ ሲሆን፣ የኦፌዲን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፤ ”እኔ በእውነቱ ይሄ ዜና እውነት ነው ብዬ አላስብም። የኢትዮጵያ መንግሥት ሰዎችን ለማሰር እንዲህ አይነት ክሶችን በየጊዜው ይጠቀማል። ምርጫ እየደረሰ ነው። ለመወዳደር ብቃት ያለው የተቃዋሚ አባል ሁሉ በዚህ መረብ ይያዛል” ሲሉ ጉዳዩን በጥርጣሬ መመልከታቸውን ለቪኦኤ ተናግረዋል።

 

ከታሰሩት ሰዎች መካከልም፤ የመከላከያ ሠራዊት አባል የሆኑት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ፣ የአንድት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሰሜን ቀጠና አደራጅ አቶ መላ ተፈራ፣ የ80 ዓመቱ አዛውንት የአቶ አንዳጋቸው ጽጌ አባት፣ የዶክተር ብርሃኑ የቅርብ ዘመድ አቶ ጌቱ ወርቁ፣ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ባደረገው ግምገማ ማዕረጋቸውን እንዲገፈፉ ተወስኖ ከሠራዊቱ እንዲሰናበቱ የተደረጉት የቀድሞ ብርጋዴል ጄኔራል አሳምነው ፅጌ የሚገኙበት ሲሆን፤ መንግሥት ባለፈው አርብ በሰጠው መግለጫ የታሰሩት ሰዎች 40 መድረሳቸውን፣ አራት ለጊዜው የተሰወሩና እየተፈለጉ ያሉትን ሳይጨምር የአሸባሪ ቡድኑን አባላት በቁጥጥር ስር የማስገባቱ ሥራ በወሳኝነት መጠናቀቁን፣ ምናልባት ምርመራው ቀጥሎ በሂደት የሚገኝ ተጨማሪ አዲስ ማስረጃ ካለ እንደነገሩ ተጨባጭነት እየታየ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማስገባቱ ሥራ መቀጠሉ ዝግ ባይደረግም ለአሁኑ ሥራው ከሞላ ጎደል መጠናቀቁን ገልጧል።

 

የአቶ በረከት ጥያቄና መልስ ከጋዜጠኞች ጋር

 

ጥያቄ፡- የቡድኑ ዓላማ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ ነበር? ይህን ለማድረግ ካቀደ ጥንካሬ ነበረው ማለት ነው? መከላከያ ውስጥ ግምገማ ነበር የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ በዚህ ተግባር ተሰማርተው መገኘታቸው የግምገማው ውጤት ነው? የፋይናንስ ምንጫቸው ምን ነበር? በቅንጅት ስም በውጭ ሀገር የተሰበሰበውንና በኋላም ከአንድነት ጋር የተጣሉበትን ወስደው ነው? መንግሥት ራሱ ባመቻቸው ነገር የግንቦት ሰባት ተደማጭነት ጨምሯል ይባላል? የአሜሪካ መንግሥት ዶ/ር ብርሃኑን እንዲሰጣችሁ ትጠይቃላችሁ? የዶ/ር ብርሃኑ ይቅርታቸው አልተነሳም ወይ? ከግንቦት ሰባት አመራሮች ጋር ዝምድና አላቸው የተባሉ ሰዎች ተይዘዋል ይባላል ...

 

መልስ፡- ይህ የቀቢጸ ተስፋ ቡድን ከተዋጽኦው ለማየት እንደሚቻለው መፈንቅለ መንግሥት የማካሄድ ችከሎታም ዝግጁነትም የነበረው ኃይል አይደለም። በኢትዮጵያ መፈንቅለ መንግሥት የሚካሄድበት የፖለቲካ ሁኔታ ካለመኖሩም በላይ ከቡድኑ ተዋጽኦውም ሆነ በተጨባጭ ከተገኙበት ማስረጃዎች ለማረጋገጥ የተቻለው ቡድኑ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያሉ ግለሰቦችን በተከታታይ በመግደልና የህዝብ መገልገያ ተቋማትን በማውደም ለነውጥ ቅድመ ሁኔታ ለመፍጠር የተዘጋጀ ኃይል ነበር። መንግሥት በዚህ የቀቢጸ ተስፋ ቡድን ተጠርጣሪ አባላት ላይ የቅርብ ክትትል ሲያካሂድ ከቆየ በኋላ የቡድኑን አባላት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል። ጠንካራ ነው ደካማ ነው የሚባልና ሀገርን ስጋት ላይ የሚጥል አይደለም። በየትኛውም ዓለም ተስፋ የሚቆርጡ ኃይሎች የሚያተኩሩት አሸባሪ የሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ ነው። እንደሚታወቀው እንዲህ ያለ የአሸባሪዎች ድርጅት መሪዎቹን ብንመለከት አንዳችም እሳት ውስጥ ገብተው አብረው ለመንደድ የተዘጋጁ አይደሉም። ቡድኑ ከፍተኛ ቅንጅት ነበረው እንዳይባል ከጀመሩ ጀምሮ ለአንድ ዓመት ያህል ቡድኑ የት እንዳለ፣ ምን እየሠሩ እንደነበር መረጃው እጃችን ላይ አለ።

 

መከላከያ ሠራዊቱን በሚመለከት - መከላከያ ሁሌም አቅሙን መፈተሽ አለበት። መከላከያ ካስቀመጠው ዓላማ አንፃር ግቡን ለመምታ የሚያደርገው የሪፎርም እንቅስቃሴ አልዋጥ ያላቸው ናቸው በእንዲህ ያለ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ያደረጋቸው። የጄነራሉ መገኘትን ደግሞ የፍተሻው ውጤት እንደሆነ ነው የሚገባን።

 

እንዲህ ያሉ አባላት ደግሞ፤ በየደረጃው ያለውን የመንግሥት እንቅስቃሴ በመደገፍ ወደፊት እንዲራመድ በማድረግ ሥራ ላይ ሳይሆን ሪፎርም የማደናቀፍ ሥራ ላይ የተሰማሩበት ሁኔታ ነው የነበረው። ይኼ ይታወቃል ስለዚህ ይህንን መነሻ በማድረግ እንደነዚህ አይነት ሰዎች የሚገለሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ መከላከያ ከነዚህ ሰዎች መወገድ ወይም ደግሞ ከነዚህ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋል በኋላ በመሠረቱ ይበልጥ የሚጠናከርበት ሁኔታ ተመቻችቷል እንጂ የተዳከመበት ሁኔታ አለ ማለት አይቻልም። እንዲህ ብለው የሚያስቡ ኃይሎች አሉ፤ እነዚህ ኃይሎች እነማናቸው ብለን ብናስብ ሁል ጊዜ የሚያስቡት ነገር ሆኗል ብለው የሚገምቱ ሰዎች ናቸው። በዚህ አይነት ብዥታ ላይ ተነስተው በተደጋጋሚ በተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም እርምጃ በመውሰድ የሚያዘወትሩ ሰዎች ናቸው። ከኤርትራ መንግሥት ጅምሮ በሀገር ውስጥም እንዲህ አይነት አስተሳሰብ የሚቀናቸው ሰዎች ያሉበት ሁኔታ አለ። እንግዲህ እነዚህ ሰዎች መከላከያን የመገምገም መብት አላቸው። ከዚህ ግምገማ ተነስተው ሌላ ተግባር ላይ እስካልተሰማሩ ድረስ። የዚህ አይነት አቋም ለምን ያዛችሁ ልንል አንችልም፤ ነገር ግን እውነታው መከላከያ ከመቸውም ጊዜ በተሻለ የጥንካሬ ሁኔታ ላይ እንዳለ ነው የሚያመለክተው።

 

በአንድ በሔር ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ - እንደዚህ የሚሉ ሰዎች አሉ፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ በብሔር ላይ ያነጣጠረ እርምጃ የሚወሰድበት ዘመን ከተሻረ 18 ዓመት አልፎታል። ከ18 ዓመት በፊት እንደዛ ቢባል ያስኬዳል፤ ይሄ ሀገር ይሄ መንግሥት ብሔርን ማዕከል አድርጎ የሚንቀሳቀስ መንግሥት ነው። ኢትዮጵያ የብዙ በሔር ብሔረሰቦች ሀገር ነች። እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ላይ እንዳችም የመብት ረገጣ የሚደርስበት ሁኔታ የለም ብሎ የሚንቀሳቀስና መብታቸውን ያስከበረ መንግሥት ነው። ስለዚህ በማናቸውም የተለየ ቡድን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የሚሠራ መንግሥት አይደለም። በኃይማኖትም በብሔርም በፆታም በመሳሰለው ይሄ መንግሥት ኢትዮጵያ የብዙ ኃይማኖቶች የብዙ ብሔሮች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያቀፈች ሀገር መሆኗን መነሻ አድርጎ እነዚህ ተቻችለውና ተከባብረው መኖር አለባቸው ብሎ የሚንቀሳቀስ መንግሥት ነው። ስለዚህ ብሔር ላይ ነው ያነጣጠረው የሚለው ነገር ከመንግሥት ፖሊሲ ጋር አጣጥሞ ሲታይ መሠረት የሌለው ነው። እነዚህ የተባረሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች በአጋጣሚ ከአንድ ብሔር የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። በአጋጣሚ የአንድ መንደር ልጆች ሊሆኑ ይችላሉ። ከአንድ መንደር የወጡ ሰዎች ወንጀል ፈጽመው ሲገኙ በቁጥጥር ስር ሊውሉ ይችላሉ። የዚህ መንደር ስለሆንን ነው የታሰርነው የሚል ማብራሪያ መስጠት ወንጀልን ለመከላከል ዕድል አይሰጣቸውም። የዚህ ብሔር አባል ስለሆኑ ወንጀል ላይ ተሰማርተው ቢገኙ አይያዙም የሚባል ሕግ የለም። ስለዚህ ማንኛውም ወንጀል የፈጸመ ሰው በወንጀል የተጠረጠረበት ጉዳይ በማስረጃ ተረጋግጦ እስከቀረበበት ድረስ የዚህ ብሔር ነኝ፣ የዛ ኃይማኖት ነኝ በሚል መንገድ ለማምለጥ የሚደረገው ጥረት መሠረትና ተቀባይነት የሌለው ነው ብሎ መውሰድ ተገቢ ነው የሚመሰለኝ። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ እነዚህ ሰዎች ማንንም አይወክሉም ሁሉንም እናቃቸዋለን ራሳቸውን ብቻ የሚወክሉ ሰዎች ናቸው። በጥፋቱ ላይ ገብተው የተገኙትም የራሳቸውን ጥቅም ለማሳካት አስበው ነው በጥፋት ውስጥ ተዘፍቀው የተገኙት። ስለዚህ በመሠረቱ ይሄን ብሔር በመጥቀም እንደዚህ አድረገው ሠርተዋል የሚባል ነገር አይደለም። ስለዚህ ከየትኛውም ብሔር ጋር የሚያያዝ ጉዳይ አይደለም።

 

የፋይናንስ መሠረቱ ምን ነበር? ለተባለው አንድ የውጭ ኃይል እንደሆነ ማየት የሚቻልበት ሁኔታ አለ። ዝርዝሩ ወደፊት በማስረጃችን ተቀምሮ የሚቀርብበት ሁኔት እንደሚኖር ማየት ይቻላል። ነገር ግን ውጭ ያለው ኃይል ቡድኑን ከማንቀሳቀስ በተጨማሪ በተለያዩ አጋጣሚዎች ገንዘብ በመላክና ገንዘብ በማሰማራት ማንቀሳቀስ ለማድረግ የሞከረበት ሁኔታ አለ።

 

የግንቦት ሰባት ተደማጭነት ጨምሯል ለተባለው፤ ይኼ እንግዲህ አንድ የጥፋት ቡድን ጥፋት ላይ ተሰማርቶ በመገኘቱ ስሙ ተደጋግሞ በሚዲያ ሊነሳ ይችላል። ይኼ ግን ሰው ከዚህ ቡድን ጋር አዎንታዊ በሆነ መንገድ እንዲሳካለት መንገድ ከፍቷል ሊባል የሚችል አይመስለኝም። ጥሩ የሆነ ግንኙነት ሊፈጠር የሚችል ነው ብሎ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም አሸባሪ ቡድን ነው። ይሄን ቡድን የሚመሩት ሰዎቹ ይታወቃሉ፤ በ1997 በተካሄደ ምርጫ ህዝብ ትመሩናላችሁ ብሎ የመረጣቸው ናቸው። ህዝብ ትመሩናላችሁ ብሎ ከመረጣቸው በኋላ ኃላፊነቱን ወስደው በመሪነት ኃላፊነት ተቀምጠው የገቡትን ቃል ማክበር እንደማይችሉ ሲያውቁ ወደ ወንጀል የገቡ ናቸው። ስለዚህ በዚህ ደረጃ አሁን ሄደው ሄደው ወደ ሽብር ስልቶች የተረማመዱበት ሁኔታ እንዳለ በግልፅ ይታያል። ይሄ ተደማጭነትን የጨመረ አይደለም፤ በመሠረቱ የፖለቲካ ክስረት ውስጥ ያለ ኃይል ነው ብሎ መውሰድ የሚቻል ነው የሚመስለኝ።

 

የአሜሪካ መንግሥት ዶ/ር ብርሃኑን አሳልፎ እንዲሰጣችሁ ትጠይቃላችሁ - ለተባለው እስካሁን አላቀረብንም። ወደፊት በዚህ ሁኔታ ምን እንደሚደረግ ከፍርድ ቤት ውሳኔው ጋር ተያይዞ የሚታወቅ ነገር ይሆናል ማለት ይቻላል። ይቅርታቸው አልተነሳም ወይ? የሚለውን በቅድመ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የተሰጠ ይቅርታ ስለሆነ ዶ/ር ብርሃኑ ከተለቀቁት የቅንጅት አመራሮች ጋር ፈርመው የወጡ ናቸው። በመጣ ጊዜ የተሰጠው ይቅርታ ማናቸውንም ጥፋት ፈፅሞ ቢገኝ ይቅርታው ወዲያውኑ ውድቅ የሚሆንበት ሁኔታ የሚያረጋግጥ ይቅርታ ነው የተሰጠው በዚህ መሠረት ግለሰቡ ግንቦት ሰባትን አደራጅቶ ትጥቅ ትግልን ያወጀ ቀን በጥፋት ላይ ተሰማርቶ የተገኘበት ሁኔታ ስላለ ይቅርታ የተነሳበት መሆኑ አውቶማቲክ ነው። በድጋሚ ማንሳት የሚያስፈለገው አይመስለኝም።

 

ዝምድና አላቸው የተባሉ ሰዎች ተይዘዋል ይባላል - ለሚለው እነዚህ ሰዎች ዝምድና ያላቸው ስለሆኑ አይደለም የተያዙት፣ በተጨባጭ ወንጀል ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ነው። ዝምድና ያለው ሰው ተፈልጎ የሚታደንበት ሀገር አይደለም ይሄ ሀገር። ወንጀል የፈፀመ ሰው ለፈጸመው ወንጀል ማስረጃ እስከተገኘ ድረስ በተጠርጣሪነት የሚያዝበት ሁኔታ ይኖራል። ስለዚህ ሁኔታው የሚየሳየው በዝምድና ማሰርን ሳይሆን ተጨባጭ ወንጀል ላይ ተሰማርተዋል በሚል ጥርጣሬ ነው ሰዎች በቁጥጥር ስር የገቡት በዚህ ረገድ መንግሥት ማስረጃዎች እንዳሉት እያረጋገጠ ነው ማስረጃዎችን ይዞ ፍርድ ቤት ይቀርባል።

 

ሁለተኛ ዙር ጥያቄ

 

ጥያቄ፦ እኔ እንደሚገባኝ ራሱን በጣም ያጋለጠ ኃይል ነው። በጣም ተራ የወንበዴ ሥራ የሚሠራ ነው የሚመስለው መከላከያ ሠራዊት ውስጥ እንዲህ ያለ ጄነራል ነው ያለው የሚል ጥያቄ አያስነሳም? ሊገደሉ የነበሩት የመንግሥት ባለሥልጣናት የመገደያ መስፈርታቸው ምንድነው? ገዳዮች ያወጡት የግድያ መስፈርት ምንድነው? ከተገደዮቹ ውስጥ አንዱ ነበሩ ተብሏል ይህን ያስተባብላሉ? መንግሥት አሸባሪ ብሎ የሚጠራው ቡድን አንዱ ያነጣጠረው የኢኮኖሚ ተቋማት ላይ ነው። በእናንተ አስተሳሰብ የገዘፈ የኢኮኖሚ ተቋማቱን የማውደሙ የመጨረሻ ውጤት ምንድን ነበር ያሰቡት ማለት ይቻላል?

 

ጥያቄ፦ ይሄ ቡድን ዋና ያነጣጠረው ግለሰቦችን ለመግደል ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል እና ምናልባት በጋራ መደራጀቱ አላዋጣ ካላቸው እና ከዚህ በኋላ ከዚህ ቡድን ጋር ተያይዞ የሚወሰድ የግል ጥረቶች ወይም እንደዚህ አሸባሪ እንቀስቃሴዎች ካሉ ይሄን ተያይዞ የሚኒስትሮችንም ሆኑ ታርጌት ተደርገዋል ተብሎ የታሰቡ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተሻለ ጥበቃ ለማድረግ መንግሥት የሚወስናቸው ርምጃዎች አሉ ወይ?

 

ጥያቄ፦ ሰኞ ዕለት አካባቢ እነዚህ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡና 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ እንዲጠየቁባቸው አንድ ሪፖርት ላይ አንብቤያለሁ፤ መንግሥት እነዚህ ሰዎች ምን እያደረጉ እንደነበር እየተከታተለ ነበር? ብሔራዊ ደህንነት ኤጀንሲያችንም ሆነ ፌደራል ፖሊሳችን መረጃዎች እንዲህ ተጠናክረው በቀረቡበት ሀኔታ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለምን አስፈለገ?

 

ጥያቄ፦ ምርጫ 97ትን አስመልክቶ የተነሳውን ረብሻ ለማብረድ መንግሥት ሕጋዊም ፖለቲካዊም እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል ይህንንስ አስመልክቶ ምን ታስቧል?

 

ለሁለተኛው ዙር ጥያቄ አቶ በረከት የሰጡት ምላሽ

 

እንዲህ አይነት ጄኔራል ነው ወይ ያለን የሚለውን ጥያቄ ከሁለት መንገድ ብንመለከተው ጥሩ ይሆናል። መጀመሪያ እውነታውን የተመለከተ ነው፤ እነዚህ ሰዎች የገቡበትን ደረጃ መነሻ በማድረግ ከግለሰቡም ከማዕከላዊ የመከላከያ ኃይላችን አማራጭም በመነሳት መመለስ ይቻላል። ግለሰቡን በተመለከተ እኔ እስከማውቀው ድረስ ማሰቡ እስከታመነ ጊዜ ድረስ ጥሩ ተዋጊና አዋጊ እንደሆነ ይታወቃል። ነገር ግን ይኼ ለማንኛውም ሰው ለአንዴና ለዘላለም የተሰጠ ፀጋ ነው ሊባል አይችልም። ጥሩ ተዋጊነትና አዋጊነት ፖለቲካዊ አቋም ላይ ይመሰረታል። ለህዝብ ማገልገል አስተሳሰብ የራስን ግላዊ ፍላጎት ብቻ ማየት ሰትጀምር ጥንካሬ ወይም ደግሞ ጥሩ ነገር የሠራኸውን መልሰህ መድገም የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስለዚህ ግለሰቡ በሂደት በመዝቀጥ አቅጣጫ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ነው ያለው። ይኼ ለማንኛውም በዚህ መስመር ለሚጓዝ ሰው ሊሠራ የሚችል አገላለጽ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። በሂደት ወደዝቅጠት የገባን ጄነራል መነሻ አድርጎ የመከላከያ ሠራዊቱን የአመራር አካላት በዚህ ደረጃ ለመውሰድ መሞከር ትክክል አይመሰለኝም። የመከላከያ ሠራዊት አካላትም ሆኑ መሪዎች ምን አይነት ተዓምር መሥራት እንደሚችሉ ሁላችሁም የ10 ዓመት ሂደት ማስታወስ ትችላላችሁና ምን አይነት ተዓምር ሊሠሩ እንደሚችሉ የኢትዮ ኤርትራን ምሳሌ መውሰድ ትችላላችሁ። ግዝፉን የደርግ ሥርዓት በማንበርከክ ዙሪያ በተካሄደ ትግል በጣም ብዙ አስታዋሽ ነገሮች ማንሳት ይቻላል። አሁን ያለውን የመከላከያ ሠራዊት ወደ ከፍተኛ የጥንካሬ ደረጃ እንዲሸጋገር በማድረግ አመራሮችን በመስጠት ላይ ያለ ኃይል ነው። ስለዚህ ጥርጣሬ ሊገባን አይገባም። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአስተማማኝና ብቁ ኃይል የሚመራ ሠራዊት ነው። አንድ ፍራፍሬዎች የመወከል አይሆንም ብሎ መውሰድ ነው ተገቢ የሚሆነው።

 

የመግደያ መስፈርታቸው ምንድነው? ሽብር ፈጣሪዎችን በቀቢፅ ተስፋ የሚራመዱ ሰዎች ማንኛውንም ዓላማውንም ማሳካት ያስተችለኛል ብሎ ያሰበውን ለመምታት ይሞክራል። በዚህ ደረጃ እከሌ ከከሌ የሚባል ነገር ላይኖር ይችላል። ሲሄድ እከሌ ነው የታሰበው እከሌ ናት የታሰበችው ሊባል አይችልም። ፕላናቸው በሥርዓቱና በመንግሥት ላይ ነው፤ ስለዚህ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያለ ሰው አመቺ ሆኖ ቢያገኙት ማንም ላይ እርምጃ ለመውሰድ የማይችሉበት ምክንያት የለም፤ ለዚህ ነው ጥያቄውን በዚህ መልኩ መመለስ የመረጥኩት።

 

የግል እርምጃ እንዳይወስድ ምንድነው የሚደረገው ላይ - መንግሥት አሸባሪዎች ወይም ቀቢፅ ተስፋዎች አንዳንድ ሙከራ ባደረጉ ቁጥር ሲደናበር የሚያድር መንግሥት አይደለም ይሄ መንግሥት፤ ስለዚህ የተለመደ ሕይወት ይቀጥላል ማለት ነው። የተለየ ነገር የሚያደርግበት ሁኔታ ያለ አይመሰለኝም።

 

14 ተጨማሪ ቀን የተጠየቀበት ምክንያት መንግሥት የራሱን ክትትል አድርጎ ያገኛቸው የስብሰባቸው ማስረጃዎች አሉት። ይሄ የሆነው ሰዎቹ ከመያዛቸው በፊት ነው። ከተያዙ በኋላ ሕጋዊ የሆነ ምርመራ ይካሄዳል፤ ሰብዓዊ መብታቸው በተጠበቀበት ማለት ነው። በዚህ ምርመራ የሚገኙ ተጨማሪ ማስረጃዎች ካሉ እነዚህን በውስጡ አሰባስቦ ለፍርድ ማቅረብ ያለበት በችኮላ የያዘውን ይዞ ለመሮጥ አይደለም የፈለገው። ለዚህ ነው ተጨማሪ የ14 ቀን ጥያቄ ውስጥ የገባው።

 

ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል ለሚለው ነገር - መንግሥት ሁል ጊዜም ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን ማስቀደም አይቀርም የመንግሥት ዓላማ ማሰር መቅጣት ቀዳሚው ዓላማ አይደለም። የመንግሥት ዓላማ ችግሮችን በሠላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ በውይይት መፍታት ነው። ስህተት ከተገኘና ከተፈፀመ በኋላ ይሄ ዕድል ካለ ሁሌም ይሄ ዕድል ለመመልከት የሚዋክርበት ሁኔታ እንዳለ ያያል። ይሄ ማለት ግን ወንጀለኛ ሁሉ ምህረት ይደረግለታል ማለት አይደለም። አንደኛ በሕግ የሚጠየቁበት ሥርዓት መኖር አለበት። ይሄን ታሳቢ በማድረግ ለፍርድ የሚቀርቡበት ሁኔታ ይኖራል ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው። ነገር ግን መንግሥት ሁሌም እንደሚያደርገው የፖለቲካዊ መፍትሔዎች ምንጊዜም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች እንደሆኑ በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የነበረው ፕሮሰስ ቢሆን ይሄ ሁኔታ የነበረበትን ሁኔታ ነው የሚያሳየው።

 

ጄነራሉ ለምሳሌ እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር ያልቀረበበት ምክንያት ብዙ ምክሮች ተሰጥተውታል፤ የሚያውቀው ሰው ሁሉ በጥፋት መንገድ መሄድ እንደሌለበት ምክር ሲሰጠው ነው የነበረው። ስለዚህ ፖለቲካዊ ሁኔታ ለማስያዝ ጥረት ሲደረግ ነበር። ስለዚህ ይሄ የመንግሥት አካሄድ ፖለቲካን እንደምርት የሚያስቀድም መንግሥት መሆኑን የሚያሳይ ነው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ