By Matias Ketema

May 15, 2009 World wide rally, Sweden, Stockholm
 

Ethiopia Zare (ዓርብ ግንቦት 7 ቀን 2001 ዓ.ም. May 15, 2009)፦ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስምንት ከተሞች የአሜሪካን መንግሥት በጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያደርግ የተጠራ ዓለም አቀፍ ሰልፍ ተካሂዷል። በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ሰልፈኛውን ለመቀላቀል ከከተማዋ እንብርት ብዙም ሳይርቅ ከሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ የደረስኩት ሰልፉ በተጠራበት 14፡00 ሰዓት (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 8 ሰዓት) ላይ ነበር።

የኤምባሲው ጽ/ቤት ህንጻ ከፍ ካለ ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ከሌሎች ህንጻዎች ጎላ ብሎና ተኮፍሶ ጉብ ብሏል። ስቶክሆልምን አረንጓዴ እንደለበሰ ሠራዊት ወርረዋት የሚገኙት የጥድና ሌሎች ዛፎች ውበት ሰጥተው እንዳደመቋት ሁሉ፤ ኤምባሲውም የራሱን ድርሻ ወስዶ እጅብ ብለው በሚታዩት ዛፎች መሃል ግርማ ሞገሱን ለብሶ ይታያል።

 

ከኤምባሲው በግራ በኩል ባለው ገላጣ ቦታ ላይ ለተቃውሞ የወጡት ኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ የተወጠሩና በእጅ የሚያዙ መፈክሮች ይዘው፣ የኢትዮጵያንና የስዊድንን ሰንድ ዓላማዎች፣ የተለያዩ መፈክሮችና ምስሎች ያሉባቸውን ልብሶች ለብሰው በስፍራው ላይ ተሰብስበዋል።

 

ፖሊሶች ቀድሞውኑም የኢትዮጵያውያኑን ጨውነት ስለሚያውቁ ይመስላል፣ ራቅ ብለው በተዝናና ሁኔታ መኪኖቻቸውን ተደግፈው ቆመዋል።

May 15, 2009 World wide rally, Sweden, Stockholm

 

የሥራ ቀን በመሆኑና ከሥራም የሚወጣበት ሰዓት ስላልሆነ የሰልፈኛው ቁጥር አነስተኛ ነበር፣ ቀስ በቀስ ግን ቁጥሩ መበርከት ጀመረ።

 

በድምፅ ማጉሊያ ተለቆ ይሰማ የነበረውን የሻምበል በላይነህን ዘፈን፣ ቴዲ አፍሮ ተረክቦ በመሰማት ላይ እንዳለ የሰልፉ ፕሮግራም መሪ አቶ ስሜነህ ታምራት መናገርሪያውን በመጨበጥ የሰልፉን ፕሮግራም አብራሩ። ፕሮግራሙንም ከመምራታቸው በፊት የፕሮፌሠር አስራትን አስረኛ ሙት ዓመትና አርቲስት ጥላሁን ገሠሠን እንዲሁም ሰሞኑን ተከታትለው ያረፉትን እውቅ ሰዎች በማሰብ የኅሊና ጸሎት እንዲደረግላቸው አደረጉ።

 

ከዚህ በኋላ መፈክሮች መሰማታቸውን ቀጥለው በተደጋጋሚ ከሰልፈኛው የሚወጣው ድምፅ ኤምባሲው ጽ/ቤት እየደረሰ ተስተጋብቶ ወደቦታው ይመለስ ነበር። የኅሊና እስረኞች ይፈቱ!፣ ብርቱካን ሚደቅሳ ትፈታ!፣ ቴዲ አፍሮ ይፈታ!፣ ነፃ ሚድያ ይኑር!፣ የሕግ የበላይነት ይከበር!፣ የገንዘብ ድጋፍ ለዲክታተሮች አይደረግ!፣ መለስ አሸባሪ ነው!፣ ነፍሰ ገዳዮች ለፍርድ ይቅረቡ!፣ ... እያለ።

 

በመቀጠልም በስዊድን የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ራስወርቅ መንገሻ ለሰልፈኛው ባደረጉት ንግግር የሠላማዊ ሰልፉ ዓላማ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ረገጣና ሕገ ወጥ አገዛዝ እየተባባሰ በምጣቱን ለመቃወም፣ ወ/ሪት ብርቱካንና ቴዲ አፍሮን ጨምሮ ብዙ ንጹኀን ዜጎች በእስር በመንገላታት ላይ ስለሚገኙ የአሜሪካን መንግሥት በዚህ አንባገነን መንግሥት ላይ ጫና እንዲያደርግ፣ የዘር ማጥፋት ምርመራውም ተጠናቆ ለፍርድ እንዲቀርብ ነው በማለት አብራርተዋል። በዚሁ ንግግራቸው መግቻ ላይ መላው ዜጋ በሀገራችን እንዲሰፍን ለሚፈለገው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለሚደረገው ህዝባዊ ትግል የበኩሉን እገዛ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

 

በመጨረሻም ከአቶ ራስወርቅ ጋር በመሆንም ሁለት ሰዎች ተጨምረው ለፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የተጻፈውን ደብዳቤ ራሳቸውን የኤምባሲው ሴኩሪቲ ኦፊሰር በማለት ላስተዋወቁት ሰው ያስረከቡ ሲሆን፣ ኦፊሰሩም ይሄ ደብዳቤው ሥርዓቱን ጠብቆና ደረጃውን ተከትሎ ለፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እንደሚደርስ ገልጸዋል።

 

የደብዳቤ ይዘት ወ/ሪት ብርቱካንና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና መንግሥት ባደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል ፍርዱን እንዲያገኝ የአሜሪካ መንግሥት ግፊት እንዲያደርግ፣ ለጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መንግሥት የሚሰጠውንም ዕርዳታ እንዲያቆም፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎንም እንዲቆም የሚጠይቅ ሲሆን፤ ሰልፈኛው የዚህን ደብዳቤ ሙሉ ቃል በንባብ ካዳመጠ በኋላ በ16፡00 ሰዓት (በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 10 ሰዓት) ላይ ሰልፉ ተጠናቋል።

 

የዛሬው ዓለም አቀፍ ሰልፍ በዓለም በሚገኙ ስምንት ታላላቅ ከተሞች እንደሚደረግ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ዋና ከተማ ዋሽንግተን ዲሲ በዋይት ኃውስ፣ በስዊዘርላንድ ጄኔቭ ከተማ በተ.መ.ድ. (የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት) ዋና ጽሕፈት ቤት፣ በአሜሪካን ሚሽን፣ በተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ ባለሥልጣን ዋና ጽ/ቤት፣ በስዊዘርላንድ በርን ከተማ አሜሪካ ኤምባሲ፣ እንዲሁም በእንግሊዝ ለንደን፣ በኖርዌይ ኦስሎ፣ በጣሊያን ሮም፣ በስዊድን ስቶክሆልም እና በጀርመን በርሊን ከተሞች የአሜሪካ ኤምባሲዎች እንደሚደረግ ይታወቃል።

May 15, 2009 World wide rally, Sweden, Stockholm

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!