Ato Chekol & Dr. Berhanu (080621 Stockholm)By Yonatan Tsegaye

Ethiopia Zare (ሰኞ ግንቦት 10 ቀን 2001 ዓ.ም. May 18, 2009)፦ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመሩት ”ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ” በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች እየተዘዋወረ ህዝባዊ ስብሰባ እያካሄደ ሲሆን፣ የመጀመሪያውን ህዝባዊ ውይይት ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 8 ቀን 2001 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት አደረገ።

 

የንቅናቄው መሥራቾች የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ ቸኮል ጌታሁን በስቶክሆልም ከተማ በተያዘላቸው የስብሰባ አደራሽ ረፋዱ ላይ በ14 ሰዓት (በኢትዮ. ሰዓት አቆጣጠር 8 ሰዓት) ተገኝተው ስለንቅናቄው ዓላማ፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዴት ማድረግ እንደሚቻልና የሕብረት ትግልን በተመለከተ ከኢትዮጵያውያን ጋር አራት ሰዓት ያህል የፈጀ ውይይት አድርገዋል።

 

በዚሁ የውይይት ላይ አቶ ቸኮል በመክፈቻ ንግራቸው ግንቦት 7 ላደረገው ጥሪ የመጡትን በማመስገን፤ ከዚህ በፊትም ”እኔ ለወገኔ” በሚለው ጥሪ የስዊድን ነዋሪ ኢትዮጵያዊ ያደረገው ምላሽ ከማንኛውም ቦታ የላቀ የሚያስመሰግንና የሚያኮራ መሆኑን ገልጸዋል። አሁንም ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ በገንዘብ፣ በእውቀትና በጉልበት በማንኛውም አቅም በፈቀደው ሁሉ በመተባበር ህዝቡን ነፃ የማውጣት ትግል የሁላችንም መሆን አለበት በማለት አሳስበዋል።

 

ከአቶ ቸኮል በመቀጠልም የግንቦት 7 ንቅናቄ መሪ የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ብዙ ጊዜ ስዊድን በመምጣታቸው ቤተኛ ሊሆኑ መቻላቸውን በመግለጽ ስለሕብረት ትግል አስፈላጊነትና በተለያዩ አርዕስተ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ መግለጫና ማብራሪያ ለተሰብሳቢው ሰጥተዋል።

 

ዶ/ር ብርሃኑ ባደረጉት ንግግር የተሰብሳቢውን ቀልብ ለመሳብ ስለቻሉ በአድራሹ የሞላው ህዝብ አድናቆቱን በጭብጨባ ሲገልጽላቸው ቆይቷል።

 

ግንቦት 7 የአቶ መለስን መንግሥት ለመታገል ቆርጦ መነሳቱን የገለጹት ዶ/ር ብርሃኑ፤ እረፍት በማይሰጥ ሁኔታ ወያኔን ወጥረን በመያዝ መግቢያና መውጫ አሳጥተን ትግሉን በድል አድራጊነት እንደምንወጣ ምንም ጥርጥር የለንም ብለዋል።

 

በተጨማሪ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውንና የሀገራቸውን ህዝብ ለመታደግ የሚያደርጉትን ትግል እንደሚያደንቁና አኩሪም እንደሆነ ገልጸው፤ አሁንም ሕብረታቸውን በማጠንከር በጽናት እንዲቆሙ በማሳሰብ፤ ለዚህም ግንቦት ሰባት በያሉበት ከጎናቸው በመሆን ትስስሩን እንደሚያጠናክር ቃል ገብተዋል።

 

በዚሁ ህዝባዊ ውይይት ላይ በተደረገው የአስተያየት መስጫና የጥያቄና መልስ ወቅት የስዊድን የምክር ቤት አባል ስለሆኑት ስለ ካሪና ሄግ ከተገለጸላቸውም በመነሳት ከኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ጋር በመቆም ወ/ሪት ብርቱካን እንድትፈታ እያደረጉ ያሉትን ጥረትና የትግል አጋርነት አድንቀው፤ አሁንም አውሮፓ ምክር ቤት ለሚያደርጉት የምርጫ ውድድር ኢትዮጵያዊው ያልተቆጠበ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው አሳስበዋል። ግንቦት ሰባትም የበኩሉን ቅስቀሳ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

 

ከተሰብሳቢው በሀገራችን ሁኔታና በግንቦት 7 ዙሪያ በርካታና የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

 

በመጨረሻም ለንቅናቀው መርጃ እንዲሆን የገንዘብ ማሰባሰቢያ ተደርጎ በርከት ያለ ገንዘብ ተሰብስቧል። ከዚህም ውስጥ ለጨረታ የቀረበ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በ26 ሺህ ክሮነር (ሦስት ሺህ ዶላር) በጨረታ ተሽጧል። ስብሰባው ሞልቶት የነበረው ህዝብ ከአራት ሰዓት ቆይታ በኋላ ሲወጣ በውይይቱ ተደስቶ ነበር።

 

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ትናንት እሁድ ግንቦት 9 ቀን 2001 ዓ.ም. በኖርዌይ ኦስሎ ህዝባዊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት 15 ቀን 2001 ዓ.ም. (ሜይ 23 ቀን 2009 እ.ኤ.አ.) በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ፣ እሁድ ግንቦት 16 ቀን 2001 ዓ.ም. (ሜይ 24 ቀን 2009 እ.ኤ.አ.) በስዊዘርላንድ ዙሪክ፣ ቅዳሜ ግንቦት 22 ቀን 2001 ዓ.ም. (ሜይ 30 ቀን 2009 እ.ኤ.አ.) በሆላንድ አምስተርዳም፤ እንዲሁም የመጨረሻውን ህዝባዊ ውይይት እሁድ ግንቦት 23 ቀን 2001 ዓ.ም. (ሜይ 31 ቀን 2009 እ.ኤ.አ.) በእንግሊዝ ሎንዶን ከተማ እንደሚያደርጉ ታውቋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!