ክብርት ካሪና ሄግ Carina Häggለኢሚግሬሽን ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል

Ethiopia Zare (ሐሙስ ግንቦት 27 ቀን 2001 ዓ.ም. June 4, 2009)፦ ለአውሮፓ ፓርላማ እየተወዳደሩ የሚገኙት የስዊድን ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የፓርላማ አባል የሆኑት ክብርት ካሪና ሄግ ከስዊድን እንዲባረሩ የተወሰነባቸው የኢትዮጵያን ስደተኞች ጉዳይ እንዳስጨነቃቸውና እንዳሳሰባቸው ገልጸው፣ ለኢሚግሬሽን ሚኒስትሩ ቶቢያስ ቢልስተረም የስደተኞቹን ጉዳይ ትኩስ መረጃን መሠረት በማድረግ እንዲታይ ጥያቄ አቀረቡ።

 

ክብርት ካሪና ከምርጫ 97 ወዲህ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ መበላሸቱንና በመልካም ሁኔታ ላይ እንደማይገኝ ገልፀው፤ የስዊድን መንግሥት በጉዳዩ ላይ ትኩረት በመስጠት የኢትዮጵያውያኑን ስደተኞ ጉዳይ ሊያጤነው እንደሚገባ ለሚኒስትር ቶቢያስ በፃፉት ደብዳቤ አስረድተዋል።

 

በ2002 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ የስዊድን መንግሥት ከወዲሁ ትኩረት ሰጥቶት በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ተነሳሽነቱን በመውሰድ ሕብረቱ የምርጫ ታዛቢ እንዲልክ ለስዊድን ፓርላማ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።

 

ምንም እንኳን በ1986 በፀደቀው ሕገመንግሥት የሰው ልጅ የሰብዓዊ መብት መከበርን ቢያሰፍርም፤ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት እስካሁን ድረስ እየተጣሰ እንደሚገኝ፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዳልሰፈነና ሀገሪቱ የኢኮኖሚ ችግር መኖሩን ክብርት ካሪና ሄድ ጠቅሰዋል። ሕገ-መንግሥቱ ለእኩልነት ከፍተኛ ሥፍራ ሰጥቶት የሚገኝ ቢሆንም፤ በተግባር ግን ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ ዝቅተኛና ደካማ ነው ብለዋል። ለዚህም ምሳሌ ሲሰጡ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በሚገርም ፍጥነትና ሁኔታ ወደ እስር መወርወራቸውን ጠቅሰዋል።

 

ክብርት ካሪና ለስዊድን ኢሚግሬሽን ሚኒስትር ቶቢያስ ቢልስትረም ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ስደተኞችን በሚመለከት ጥያቄ አቅርበውላቸዋል። ክብርት ካሪና ሚኒስትር ቶቢያስ ከላይ የጠቀሷቸውን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዩ እውነቶችን ለስዊድን ፓርላማ በማስረዳት ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ስደተኞች ጉዳይ የሚታይበት መሠረታዊ ሚዛን እንዲቀየር አበክረው ጠይቀዋቸዋል።

 

”በመላው አውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በጭንቅ ውስጥ እንደሚገኙና በስዊድን ካሉት ውስጥ በርካቶቹ እንዲባረሩ ተወስኖባቸዋል። የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ድረ ገጽ ከ2007 እ.ኤ.አ. ወዲህ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አስመልክቶ ያወጣ ምንም አይነት ሪፖርት የለም። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ፍርድ ቤቶች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡና በራስ መተማመን እንዲሰሩ አዳዲስ መረጃዎች እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ናቸው። የፖለቲካ ስደተኞቹ ጉዳይ እየታየና ውሳኔ እየተሰጠበት ያለው ግን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ያለችበትን እውነታ በመንተራስ ባለመሆኑ ያሳዝናል።” ሲሉ ክብርት ካሪና ሄግ ገልጸዋል።

 

ከ1995 እ.ኤ.አ. ጀምሮ የስዊድን ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርላማ አባል የሆኑት የ52 ዓመቷ ክብርት ካሪና ሄግ የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ተወካይ ሲሆኑ፣ የፊታችን እሁድ ጁን 7 ቀን 2009 እ.ኤ.አ. በስዊድን በሚደረገው የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ምርጫ ፓርቲያቸውን ወክለው ለእጩነት ከቀረቡት ውስጥ አንዷ ናቸው።

 

በዚህ የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ምርጫ ላይ ትውልደ ኢትዮጵያ የሆኑ ስዊድናውያን ለክብርት ካሪና ሄግ ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ክብርት ካሪና በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍንና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ከሚታገሉ ነዋሪነታቸው በስዊድን ከሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን ጋር ተቀራርበው ከሚሠሩ የስዊድን የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ውስጥ ግንባር ቀደሟ መሆናቸው ይታወቃል።

 

ክብርት ካሪና መጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን እስር ቤት በመሄድ ለመጎብኘት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የኢህአዲግ መንግሥት ግን ሳይፈቅድላቸው መቅረቱንና የወ/ት ብርቱካንን ልጅ እና እናት ጎብኝተው ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ መዘገባችን አይዘነጋም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!