ፕሮፌሠሩ በህወሓት ሰዎች ተተቹ
የመጽሐፉ ገምጋሚ ፕ/ር ባሕሩ ዘውዴ የነበሩ ሲሆን፣ አወያዩ ፕ/ር እንድርያስ እሸቴ ነበሩ። በውይይቱ ጄኔራል ጻድቃንን ጨምሮ የቀድሞ ጄኔራል አበበ ተ/ኃይማኖት (ጆቤ)፣ የቀድሞ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የአሁኑ የአ.አ.ዩ መምህር ሙሉጌታ ገ/ሕይወት (ጫልቱ)፣ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ እና ዶ/ር ሠለሞን እንቋይ ተሳትፈዋል።
መጽሐፉ በደርግ ጄኔራሎች የተወደሰ ሲሆን፣ በህወሓት ጄኔራሎችና ባለስልጣናትግ ከፍተኛ ወቀሳና ትችት ቀርቦበታል። የቀድሞው የህወሓት ጄኔራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ “የህወሓት ህዝባዊነት፣ በህወሓት እና በሻዕቢያ መካከል የነበረውን ግንኙነት እና የቀድሞ ኢህዲንን አስመልክቶ የቀረበው መረጃ የተዛባ ያልተሟላና ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ ነው” በማለት ሲተቹ፤ ፕ/ሩ በበኩላቸው “የሰጠኋቸውን መጠይቆች እንኳን ለመመለስ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መጽሐፉ የተሟላ ነው አይደለም ለማለት የሚያበቃ ሞራል የላቸውም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የኢህአፓ (ዓሲምባ) አመራር የነበሩት ፕ/ር ገብሩ “ህወሓት የትግራይን ህዝብ በፀረ-ደርግ ትግል ያሰለፈው በኃይልና በብልጣ ብልጥነት እንጂ፤ የትግራይ ህዝብ ስለደገፈውና ዲሞክራሲያዊ ስለነበረ አይደለም ያሉ ሲሆን፤ ጄኔራል ፃድቃን ደግሞ “በብልጣ ብልጥነት እና በኃይል ህዝብን ማሰለፍ የሚቻል ቢሆን ድርጅትዎ (ኢህአፓ) እና ሌሎች ባሸነፉ ነበር” ብለዋል።
ለደርግ ሠራዊት አክብሮት እንደነበራቸው የገለጹት ፕ/ር ገብሩ፤ “የኢትዮጵያ ሠራዊት (ደርግ) የተሸነፈው በአማጽያን (የህወሓት እና የሻዕቢያ) ወታደራዊ ጥበብ ሳይሆን፤ በፖለቲካዊ አመራር ውድቀትና ደርግ ከኢትዮጵያ ህዝብ በመነጠሉ ነው” ብለዋል።
የደርግ ጄኔራል የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ካሣዬ ጨመዳ የቀይ ኮከብ ዘመቻን አስመልክቶ መጽሐፉ ላይ የሰፈረው ሃሳብ፤ ማለትም የቀይ ኮከብ ዘመቻ ሻዕቢያ ያለ ህወሓት እርዳታ ሕልውና አልነበረውም” ብለዋል። አያይዘውም ሠራዊታቸው የተሸነፈው በወታደራዊ ታክቲክ ሳይሆን በፖለቲካ አመራር ድክመት መሆኑን አምነውበታል።
ደራሲው በማግስቱ በሸገር ኤፍ.ኤም. ባደረጉት ቃለምልልስ “ማንም ጫት ቃሚ እየተነሳ የኔን ትውልድ ሊተች አይችልም፤ እኛ የሀገር ፍቅር ወኔ የነበረን ጠንካራ ትውልዶች ነበርን” በማለት በስሜት የተናገሩ ሲሆን፤ ለደርግ ጄኔራሎች የነበራቸውን ከፍ ያለ ግምትም አሳይተዋል። በተለይም ከሚቆጫቸው ነገር አንዱ የሆነውን ሲናገሩ፤ “በህወሓት በኩል ኃየሎምን በደርግ በኩል ኮሎኔል ሠረቀ ብርሃንን አገናኝቼ በመጽሐፌ ዙሪያ አለማነጋገሬ ነው” ብለዋል። ሁለቱም የየድርጅታቸው ጀግኖች ነበሩ። ሁለቱም በአካል አይተዋወቁም። በዝና ግን ይደናነቁ ነበር። ኃየሎምን ጠይቄው የሚያደንቀውና ማሸነፍ ያልቻለው የ3ኛው አንበሣ ክፍለ ጦር አዛዥ የነበረውን ኮሎኔል ሠረቀ ብርሃንን ጦር መሆኑን፣ ኮዱንም መበጠስ እንዳልቻለ ሲነግረኝ፤ ኮሎኔል ሰረቀብርሃን ጠይቄው ኃየሎምን እንደሚያደንቀውና ኮዱን ይበጣጥሰው እንደነበር ነግሮኛል።” ብለዋል።