EZ September weekly news digest

የመስከረም ፳፻፲፪ አሥራ አምስት ቀናት አንኳር ወሬዎችን በጨረፍታ

ኢዛ (ሐሙስ መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. September 26, 2019):- አዲሱ ዓመት ብለን የተቀበልነው 2012 ዓ.ም. እነሆ 15 ቀን ሆነው የአዲሱን ዓመት የመጀመሪያ ወር አጋመስነው ማለት ነው። በዚህ 15 ቀን ውስጥ በአገር ቤት ብዙ ክስተቶችን ተመልክተናል። ዓይንና ጆሮ የያዙ ድርጊቶች ተስተውለዋል።

በፖለቲካ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጥቂት የማይባሉ አዳዲስ አገራዊ ድርጊቶችም ተስተናግደዋል። በእነዚህ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ከመስከረም 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ ዕለት ድረስ አንኳር አንኩር ከሚባሉ አገራዊ ክንውኖች የተወሰኑትን እናስቃኛለን።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና የ2012 ጅማሮ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ካስተላለፉት መልዕክት ባሻገር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የተባለውንና ብዙ አድማጭ ማግኘቱ የሚገለጽለትን ቃለምልልስ ከግል ሚዲያ ጋር በማድረግ ጀምረዋል። ከሸገር 102.1 ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ ልዩ የሚያደርገው በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ለግል ሚዲያ የተሰጠ ቃለምልልስ ነበር። ይህ በተሰማ በቀናት ልዩነት በአገር ውስጥ የመጀመሪያ የተባለውን ጉዞ ወደ ቦንጋ አድርገዋል። ቀጥሎም ሆስአና በመሄድ ከሁለቱም ዞኖች ሕዝብ ጋር ውይይት አድርገዋል። በሁለቱም የውይይት መድረኮች የክልል እንሁን የሚል ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፣ በጥቅል ይህንን ጥያቄ “በደንብ አስቡበት!” የሚል አንደምታ ያለው ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት 15 ቀናት የተለያዩ ክንውኖች ውስጥ ሌላም አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር። ከተወሰኑ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በስተቀር ወደ ስምንት የሚሆኑ የአገሪቱ የመንግሥትና የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የተሠራጨው “ከቢሮ እስከ አገር የትውልድ አሻራ” የሚል ርዕስ የተሰጠው ዶክመንተሪ (ዘጋቢ) ፊልም ነው። ይህ ዘጋቢ ፊልም በወራት ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና የቤተ መንግሥት ሕንፃዎችን እድሳትን የሚያሳይ ነበር።

በማደስና ዓይነ ግቡ አድርገው ስለማሳደሳቸው የሚያመለክት ዘጋቢ ፊልም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተራኪ በሆኑበት በዚህ ዘጋቢ ፊልም ላይ የተደረገው ለውጥ በእርግጥም ማራኪ ነው። ባማረ ሁኔታ እንዲታደስ በማድረግ ለቱሪዝም መስህብ ማድረግ እንደሚቻል አስገንዝበዋል። ታሪክንም ከመጠበቅ አንፃር ይህ የማስዋብ ሥራው በመልካም የታየ ነው።

ይህንን ዘጋቢ ፊልም በተለያዩ ሚዲያዎች የተከታተሉ ወገኖች ሥራውን አወድሰዋል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ይህንን ማድረጋቸውን ሲያጣጥሉ ተሰምቶ አልፏል። ለሥራው የወጣው ወጪ የተለያዩ በጐ አድራጊዎች ባደረጉት አስተዋጽኦ ሲሆን፣ ከመንግሥት ካዝና ምንም ወጪ አለመውጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የፍቅር ከተማዋን የተፈታተነው ጠብ

በኢትዮጵያ ከሌሎች በተለየ በመቻቻል የሚኖርባት እና የፍቅር አገር በመባል የምትታወቀዋ ድሬዳዋ፣ የአዲሱን ዓመት የመጀመሪያ ቀናት የተቀበለችው በከተማ ባልተለመደ ድርጊት ነበር።

በሁለት ልጆች ፀብ የተጀመረው ኹከት ቅርፅ ቀይሮ ወደ ዘረፋና ወዳልተገባ ግጭት በማምራት ለቀናት የድሬን ሰላም እስከመንሳት ደርሷል። እስከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነዋሪዎቿን ስጋት ውስጥ ከቶ የነበረው ድርጊት፤ ምንም እንኳ አሁን ሰላም ቢሆንም፤ የአንድ ሰው ሕይወት ቀጥፎ አልፎአል። በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉ ሰዎችንም ለእስር እየዳረገ ነው።

በኹከት የተዘረፈ ንብረት መጠን እስካሁን ባይገለጽም ከፍተኛ ግምት ያለው ነው ተብሏል። አንዳንዱን የማስመለስ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስተዳደሩ ገልጿል። አንዳንዶች ግን፤ ድሬ አሁንም ስጋት ላይ ነች እያሉ ሲሆን፣ የፀጥታ ኃይሉ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል እያሉ ነው።

የኦርቶዶክሳውያን ድምፅ

ባለፉት አሥራ አምስት ቀናት የብዙዎችን ቀልብ ከሳቡ እውነታዎች መካከል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ይቁም!” በሚል የተደረጉት ሰላማዊ ሠልፎች ናቸው።

በዋናነት በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች የተደረጉት ሠላማዊ ሠልፎች በታቦት የታጀቡ ነበሩ። እንዲህ ላለው ሰፊ ሠልፍ ዋነኛ መነሻ በቅርቡ “የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እናቋቁማለን” ባሉ ጥቂት ግለሰቦች የተደረገው እንቅስቃሴ ሲሆን፤ ይህንን እንቅስቃሴ ከማውገዝ ጐን ለጐን ቤተክርስቲያኗ ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችም ይቁሙ በሚል ሰፍቶ ሠላማዊ ሠልፎቹ ተደርገዋል።

በአዲስ አበባ ከተማም በተመሳሰይ ይካሄዳል የተባለው ሠልፍ ለሌላ ጊዜ እንዲቀየር የተደረገ ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አሁንም ምክክር እየተደረገበት ነው። በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተደረጉ ሠልፎች ላይ ግን የእስልምና ተከታይ ኢትዮጵያውያን፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አትንኩ!" ብለው መፈክር ይዘው በመውጣት አጋርነታቸውን ያሳዩበት ድርጊት በተለየ የሚታይ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ 33 ለሚሆኑ አድባራት (ቤተክርስቲያናት) የይዞታ ማረጋገጫ ሠርተፍኬት ለቤተክርስቲያኗ አስረክበዋል። ሌሎች ጥያቄ የቀረበባቸው የይዞታ ማረጋገጫዎችንም በቀጣይ እንደሚሰጡ ገልፀዋል።

የኢሕአዴግ ውህደትና ሕወሓት

አዲሱ ዓመት የኢሕአዴግን ውህደት የተመለከቱ ዜናዎች በተለያየ መልክ ሲቀርብ ቆይቷል። ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶቹን ለማዋሃድ አሁንም ድረስ ውይይት እየተደረገ ያለ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ኢሕአዴግ እስካሁን በነበረው ቅርፅና ይዘት እንደማይቀጥል በይፋ የተናገሩበትም ወቅት ነው። በአንፃሩ ግን ሕወሓት በዚህ ውህደት ዙሪያ የተለየ ሐሳብ ያለው መሆኑን እየገለፀ ነው። እስካሁን በይፋ አይገለጽ እንጂ በአዲሰ መልክ በሚዋቀረው ኢሕአዴግ ውስጥ ሕወሓት እንደማይገባ እየተነገረ ሲሆን፣ ድምፂ ወያኔና የትግራይ ቴሌቪዥንም በአመዛኙ ውህደቱን የሚያጣጥል የተለያዩ ፕሮግራሞችን እያሠራጩ ነው።

በትናንትናው ዕለት ደግሞ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ለቢቢሲ አማርኛ ፕሮግራም እንደገለፁት፤ ኢሕአዴግ አንድ ወጥ አገራዊ ፓርቲ ይሆናል እየተባለ የሚነገረውን ጉዳይ፣ ሕወሓት ፈጽሞ የማይቀበለው መሆኑን ነው። ይህም ሕወሓት አዲስ ይፈጠራል ተብሎ በሚጠበቀው ውህድ ፓርቲ ውስጥ የማይካተት አለመሆኑ አመላካች እየሆነ ነው።

ኢዜማ በመቀሌ

በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ኃይል ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ፣ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ወደ ትግራይ በመጓዝ ከመቀሌ ነዋሪዎች ውይይት በማድረግ ኢዜማ የመጀመሪያው ሆኗል። ኢዜማንና አሁን ያለውን የለውጥ ኃይልን የተቹ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተነሱበት ይህ የውይይት መድረክ፣ ወደ መቀሌ የተጓዙትና የኢዜማ የአመራር አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡበትና ፕሮግራማቸውን ያስተዋወቁበት ሆኗል።

ኢዜማ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለየ በመላ አገሪቱ ከ400 በላይ አካባቢዎች ለምርጫ ዝግጁ የሆኑ አባላትን በመመልመል በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ፓርቲ ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ