EZ Weekly digest, 9th 2012 Eth. C

ከጥቅምት 24 - 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ዘጠነኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከጥቅምት 24 - 30 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ እንደ ወትሮው ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች ተካሒደዋል። በቀደመው ሳምንት መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅታዊ ጉዳዮች መግለጫ የሰጡበት ስለነበር፤ ባሳለፍነው ሣምንትም ይህንን መግለጫ ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩበት ነበር። ብዙዎች አሁንም “ሕግ ይከበር!” የሚለውን ጠንከር ያለ አቋም እየገለጹ ይገኛሉ።

ከዚህ ሌላ ከሰሞኑ ዐበይት ኹነቶች ውስጥ የታላቁ የህዳሴ ግድብን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዋነኞቹ የተፋሰሱ አገሮች በዋሽንግተን ነጩ ቤተመንግሥት የተገናኙበት ሳምንት ነበር። ከሰሞናዊ ክስተቶች ሰፋ ያለ የዜና ሽፋን ያገኘውና አሁንም ዋነኛ ወቅታዊ የአገሪቱ አጀንዳ ወደመሆን እየተሸጋገረ ያለው የአንበጣ መንጋ ወረራ ነው። ከሰኔ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ የአንበጣ መንጋ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተዛመተ ከመምጣቱ አንጻር ጉዳዩ ከአገር አልፎ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን የገለፁበት ሳምንት ነው።

የሲዳማ ዞን ሕዝበ ውሣኔ የመራጮች ምዝገባ መጀመር የአገሪቱ አዲስ የታሪክ ክስተት ሆኖ ሳምንቱ የሚታወስበት ነው። ከአገሪቱ 20 ሚኒስትሮች ሁለቱ ከሥራ ለቀዋል የሚል ወሬ በሰፊው የተስተጋባበት ግን፤ እስካሁን ማረጋገጫ ያልተሠጠበት ጉዳይ ሆኖ ሳምንቱ አልፏል። በሰኔ 15ቱ የከፍተኛ መኮንኖች ግድያ ተጠርጣሪ የሆነውና በሕክምና ላይ የቆየው ግለሰብ ፍ/ቤት መቅረቡ የተሰማበትም ነው። ሳምንቱ የሚታወስበት ብለን ከምንጠቅሳቸው የተለያዩ ጉዳዮች ውስጥ በምርጫ ሕጉ ላይ ጥያቄ አለን ያሉ የሰባ አንድ ፓርቲዎች አመራሮች፤ የረሃብ አድማ ለማድረግ የደሱበትን ስምምነት በመተው፤ ደም እንስጥ በሚል የቀደመ ሐሳባቸውን ስለመቀየራቸው መሰማቱ አስደማሚ ብለን ልንጠቅሰው የምንችል ሳምንታዊ ወሬ ሆኗል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከምርጥ 10 የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መባሉ፣ አንድ የሱዳን ዩኒቨርሲቲ የአፋን ኦሮሞና አማርኛ ቋንቋ ትምህርት ሊጀምር ዝግጅት አጠናቋል መባሉ፣ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ሆነው መሰየማቸውም በዚህ ሳምንት ትኩረት ከተሰጣቸው ዘገባዎች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። የኢሕአዴግ ውሕደትን በተመለከተ የተለያየ አተያይ የሚሰነዘሩ ሐሳቦችም ሲስተጋቡ ሰንበተዋል። የወራት ዕድሜ የቀረው ቀጣዩ ምርጫ ጉዳይ አሁንም ለብዙዎች ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል። ምርጫው ይደረጋል አይደረግም የሚለው ጥያቄ አሁንም በእንጥልጥል ላይ ነው።

በዋሽንግተን የኢትዮጵያውያን ቀን እንዲከበር በማወጅ የሚታወቁት የዋሽንግተን ከንቲባ ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡትም በዚህ ሳምንት ነው። ሸማቸውን ጣል አድርገው ላሊበላን መጐብኘት ችለዋል።

በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ሊሠሩ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ለመሥራት መስማማታቸውም በሳምንቱ ወሬዎች መሐል ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመከላከያ ሠራዊት መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ የተገለጸው በዚህ ሳምንት ነው። ያሳለፍነውን ሳምንት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች በርከት ያሉ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን፣ የፋይናንስ ተቋማት የማሻሻያ አዋጅ ማፅደቅና የሠላም ሚኒስቴር የሦስት ወር ሪፖርት ያዳመጠበት ነበር። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የተፈፀመው አሳዛኝ ድርጊት ልብ የሚነካ ነበር። እንዲህ ያሉና ሌሎች የተለያዩ ኹነቶች የተንፀባረቀበት ሳምንት ሲሆን፣ የተወሰኑትን እንዲህ ተጠናክረዋል። (ኢዛ)

የውኃ ዳሩ ድርቅ - 35 ሺሕ ዜጐችን ለምግብ እጥረት አጋልጧል

ከሰሞናዊ ዜናዎች ውስጥ በአማራ ክልል በዋግ ሁምራ አስተዳደር ዞን ሥር የምትገኘውና ከተከዜ ወንዝ ተጐራባች ወረዳዎች መካከል አንዷ በሆነችው የሳህያ ሰላምቱ ወረዳ ድርቅ መከሰቱን የሚያመለክት ነው።

የክልሉን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያንቀሳቀሰው ይህ ክስተት የተመለከተው የክልሉ መረጃ አብዛኛው የወረዳዋ ነዋሪ ለድርቅ ተጋልጧል። በወረዳዋ ሥር 10 ቀበሌዎችና 40 ሺሕ ነዋሪዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ነዋሪዎች ውስጥ 35 ሺሕ ነዋሪዎችን በክረምቱ ወቅት ያጋጠመው ድርቅ ለምግብ እጥረት እንዲጋለጡ ዳርጓቸዋል። በእርሻና በእንስሳት እርባታ የሚታወቀው ይህ አካባቢ በምርት ዘመኑ ክረምት ላይ የዘሩት ዘር ፍሬ አልባ ሆኖባቸዋል። ያፈራል፣ ያሽታል ከዚያም አጭደንና ወቅተን ገንዘብ ይሆነናል ብለው ክረምቱ ላይ የዘሩት በድርቅ ተመትቶ በሌላ ማዶ ያሉ አርሶ አደሮች ሲያጭዱ የዚህች ወረዳ ነዋሪዎች ግን ለዚህ ያልታደሉ ኾነዋል። ለከብቶቻቸውም ለእነርሱም የሚሆን ነገር አሳጥቷቸዋል። በዚህም የተነሳ እርዳታ እንዲጠብቁ አስገድዷቸዋል።

ከብቶቻቸው መኖ ባለማግኘታቸውም እየሞቱባቸው ሲሆን፣ በሕይወት ያሉትንም ወደ ገበያ አውጥተው ለመሸጥ መቸገራቸውን ነዋሪዎቹ ሲናገሩ ተሰምቷል። ገበያውን ያጡት ደግሞ ከብቶቻቸው ስለከሱ ገዥ በማጣታቸው ነው።

አሁን ያለው ችግር ቶሎ ካልተፈታና እርዳታ ካላገኙ ትምህርት ቤቶች ከዚህ በኋላ ይዘጋሉ የሚል ሥጋትም አሳድሯል። በክልሉ እርዳታ እየደረሰ ነው ተብሏል። ይህ አካባቢ የተከዜ ወንዝና ሌሎች የውኃ አካላት ያሉት ነው። (ኢዛ)

የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በነጩ ቤተመንግሥት

የሳምንቱ ዐበይት ዜና ሆኖ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ውስጥ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ነጩ ቤተመንግሥት ገብቶ የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ጭምር እንዲያወሩበት ማድረጉ ነው።

ወትሮ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በየተራ አዲስ አበባ፣ ካይሮና ካርቱም ከሚደረገው የጋራ ምክክር በተለየ የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪዎች አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ነጩ ቤተመንግሥት አዳራሽ ታድመዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ወትሮ ውይይት ከሚያካሒዱበት ከተሞች የብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀው በዋሽንግተን የተገናኙበት ዋና ምክንያት ደግሞ፤ በህዳሴው ግድብ የውኃ አለቃቀቅና ሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያና ግብጽ ልዩነት በመፍጠራቸው አሜሪካ ላነጋግራችሁ በማለትዋ ነው። በሌላ አነጋገር እነዚህ ተደራዳሪ ወገኖች ልዩነታቸውን ፈትተው እስካሁን ሲያደርጉ እንደነበረው ምክክራቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብጽ የውጭ ጉዳዩ ሚኒስትሮች የቡድን አባት ኾነው በነጩ ቤተመንግሥት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር አጭር ውይይት በማድረግ ከዚያም የሦስቱ አገራት በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀመጡ ተደርጓል።

በሦስቱ አገሮች የቡድን አባቶችና አባሎቻቸው የህዳሴውን ጉዳይ የሚመለከተው ውይይት በተካሔደበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ባንክ ተወካዮች ተገኝተዋል። ከምሥራቅ አፍሪካ ጉዳይነት ተሻግሮ የዓለማችንን ታላላቅ ተቋማትንና ኃያሏን አገር እንዲገቡበት የተደረገው የህዳሴ ግድብ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲሠጠው ያደረገ አጋጣሚ ነው። የዋሽንግተኑ ምክክር ላይ “የዓለም ባንክና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለምን ተገኙ?” የሚል ጥያቄ ያስነሳ ቢሆንም፤ እነርሱ ከታዛቢነት ውጭ ሚና የላቸውም ተብሏል።

የውይይት መድረኩ ካለቀ በኋላ በተሠጠ መግለጫ፤ ሦስቱ የተፋሰስ አገራቸው እስካሁን ሲያካሂዱ በነበሩት የጋራ ምክክር መድረክ ላይ ውይይታቸውን እንዲቀጥሉ መወሰኑ አንዱ ነው።

በዚሁ መሠረት ቀጣዩ የሦትዮሽ ምክክር አዲስ አበባ ላይ ይካሄዳል። እንደገናም በተራው መሠረት ካይሮና ካርቱም የሚቀጥል ሲሆን፣ በእነዚህ ከተሞች የቴክኒክ ኮሚቴው በሚደረጉት ውይይቶች የማይስማሙ ከሆነ፤ ጉዳዩን ለመሪዎቻቸው እንዲያቀርቡ በዚያም የማይፈታ ከሆነ ሦስተኛ ወገን በድርድሩ መሐል ይግባ ወደሚለው ሊገቡ የሚችሉ ስለመኾኑ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን ወደሚስማሙበት መድረክ እንዲመለሱ ያደረገ ነው የተባለው የዋሽንግተኑ ውይይት ላይ፤ የሦስቱንም አገሮች ልዑካን ያገኙት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስለህዳሴ ግድብ በቂ ማብራሪያ ተሠጥቷቸዋል። ከዚህ በፊት ግን ትራምፕ ተናገሩ የተባሉት ለየት ያለ ቃል ትኩረት ስቧል። ይህም “የህዳሴው ግድብ አልቆ ለሪቫን ቆረጣው ላይ እገኛለሁ” ማለታቸው ነው።

ይህንን ንግግራቸውን አስመልክቶ ከድርድሩ በኋላ የኢትዮጵያ ልዑካን በዋሽንግተን ዲሲ በሠጡት መግለጫ ላይ፤ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለም ይህንን የትራምፕ ንግግር የሚያረጋግጥ ቃል መሥጠታቸውን አረጋግጠዋል። ይህም በአንዳንዶች ዘንድ ትራምፕ የህዳሴው ግድብ ላይ አሜሪካ ቀና አመለካከት ያላት መኾኑን ያመላከተ ነው የሚል አስተያየት እንዲሰነዝሩ ምክንያት ሆኗል።

በብዙ ንግግሮቻቸው ወዲህና ወዲያ የማለት ልምድ አላቸው የሚባሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ህዳሴው አልቆ በሪባን ቆረጣው ላይ ለመገኘት እንደሚሹ በተናገሩት አንደበት፤ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ ምን እንደሚያደርግላትና ከዓባይ ወንዝ ይልቅ ሌላ የኃይል አማራጭ ለምን አልተጠቀመችም? የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር ተብሏል። እንዲህ ላሉ ጥያቄዎች ከኢትዮጵያ ወገን ምላሽ የተሠጠ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ ይህንን ጥያቄ ማንሳታቸው ስለግድቡ የተነገራቸውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲቀረፍ ያስቻለ እድል ፈጥሯል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደገለጹትም፤ ከፕሬዝዳንቱ ጥያቄ አንፃር ስለ ግድቡ የተሳሳተ አረዳድ የነበራቸው መኾኑን የሚጠቁም ቢሆንም፤ ይህንን አረዳዳቸውን የሚቀርፍ አጋጣሚ ያስገኘ ማብራሪያ ለመስጠት አስችሏል። (ኢዛ)

የህዳሴ ግድብና የትራምፕን ፌስ ቡክ ያጨናነቁ ግብረ መልሶች

የህዳሴ ግድብ ላይ ለመምከር ዋሽንግተን መገኘት ጋር በተያያዘ ሌላው ለየት ያለ ነገር ቢኖር፤ የሦስቱ አገራት የልዑካን ቡድኖች በኋይት ሐውስ ተገኝተው ከትራምፕ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን በተመለከተ በምስል የተደገፈ መረጃ በትራምፕ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከተለቀቀበት ደቂቃ ጀምሮ፤ አጀብ የሚያሰኙ አስተያየቶች መጉረፋቸው ነበር። በተለይ ኢትዮጵያውያንና ግብጻውያን የተለያዩ አመለካከቶቻቸውንና አስተያየቶች ማስፈር የጀመሩት ወዲያው ነው። አስተያየቶቹ አንዳንዱ ፅንፍ የያዘ ዓባይ የእኛ ብቻ ነው የሚል ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ሚዛናዊ አስተያየት የተሠጠበት ነው። ትራምፕ ያደረጉትን የሚያደንቅ፣ አገሮቹ በሥምምነት መሥራታቸው ጠቃሚ ስለመሆኑና ሌሎች ብዙ አስተየየቶች የተሠጡበት ነው።

የትራምፕ ፌስቡክ ላይ መረጃው በወጣ በሦስት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከ20 ሺሕ በላይ የፌስቡክ ተከታዮች ላይክ ያደጉት ሲሆን፣ ከአንድ ሺሕ በላይ ደግሞ አስተያየት በህዳሴው ግድብ ላይ ተሠጥቶበታል። በዚሁ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ አሁንም ድረስ አስተያየቶች እየተሠጡ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ላይክ ያደረጉ ግለሰቦች ከ50 ሺሕ በላይ ደርሰዋል። አስተያየታቸውን የሠጡ ደግሞ ከ4600 በላይ ደርሷል። በትራምፕ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከተጫኑ አንዳንድ ጉዳዮች በበለጠ የህዳሴው ግድብ ላይ የተሠጡ አስተያየቶችና ምልልሶች እጅጉን የላቁ ነበሩ ማለት ይቻላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ሥራ እንደምትቀጥልና ዜጐችም አስተዋጽኦውን እንዲቀጥሉ ተጠይቋል። በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ጽ/ቤት ይፋ እንዳደረገው፤ ባለፉት ሦስት ወራት ለህዳሴ ግድብ 168 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን እስካሁንም በመዋጮና በቦንድ ግዥ ከሕብረተሰቡ የተውጣጣ ገንዘብ 13 ቢሊዮን ብር ስለመድረሱ ተጠቁሟል። በአሁኑ ወቅት ግን የህዳሴው ግድብ የወጣበት 99 ቢሊዮን ብር መድረሱም ተጠቅሷል። በኢትዮጵያ ዕቅድ መሠረት ከግድቡ የተወሰኑ ተርባይኖችን ከ2013 ጀምሮ ሥራ ለማስጀመር ነው። (ኢዛ)

የኢንተርኔት የመጠቀም ነፃነት መሻሻል

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከኾኑ ወዲህ ኢትዮጵያ ኢንተርኔት በመጠቀም ነፃነት ከ65 አገራት ከፍተኛ መሻሻል ያሳየች አገር መሆን እንደቻለች ተገለጸ። ይህንን ያስታወቀው ፍሪደም ሐውስ በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ዓለም አቀፍ ተቋም ነው። እንደ ተቋሙ መረጃ ኢትዮጵያ በኢንትርኔት ላይ ጥላቸው የነበሩ ገደቦችን በማላላቷ ትልቅ ለውጥ አሳይታለች።

ተቋሙ ዓለም አቀፍ የኢንትርኔት ነፃነትን በሚገመግምበት ዓመታዊ ዘገባው ላይ በሠጠው ተጨማሪ ማብራሪያ፤ ግምገማው 65 አገራትን ያካተተ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም አንዷ ነበረች።

ዓመታዊ ሪፖርቱ በአዎንታዊነት ከዘረዘራቸው መሻሻሎች ውስጥ በኢትዮጵያ እንዳይታዩ ታግደው የነበሩ 260 ድረ ገጾች ላይ የተደረገው ገደብ እንዲቀር መደረጉ ይገኝበታል። (ኢዛ)

የአንበጣ ጣጣ - በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ

የአንበጣ መንጋ መከሰትና ወረራውን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት መቋጫ አላገኘም። ከሰሞኑ ይበልጥ ገኖ ታየ እንጂ ችግሩ የጀመረው ከሦስትና አራት ወራት በፊት ነበር። አሁን እንደታየው ዐይነት አይሁን እንጂ፤ የአንበጣ መንጋ በተለያዩ ወቅቶች የተከሰተ ቢሆንም፤ የአሁኑን ያህል እንዳልፈተነም ይነገራል።

የወቅቱ የአንበጣ ወረራ ከሌሎች ወቅቶች በተለየ አብዛኛውን የአገሪቱን ክልሎች አዳርሷል። አሁንም ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የተቻለበት ደረጃ አልተደረሰም። መንግሥት በአውሮፕላን ጭምር በመጠቀም መንጋውን ለማጥፋት ሙከራዎቹን ግን ቀጥሏል። በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይም ተጨማሪ አውሮፕላን በማስገባት ችግሩ ጐልቶ ታይቶባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች በምልልስ እየሠራ እንዳለ ተገልጿል። እንደ ትግራይና አማራ ያሉ ክልሎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጭምር በማሳተፍ መንጋውን ማባረር ሥራ ተሠርቷል። በአፋር ክልልም ሕብረተሰቡ በተመሳሳይ እየሠራ ነው።

የጸጥታ ኃይሎችና የመከላከያ ሠራዊት ጭምር አንበጣ በመከላከሉ ሥራ ላይ ተሳታፊ የነበሩባቸው አካባቢዎችም ነበሩ። ከዚህ ጐን ለጐንም የደረሰ ሰብል በአንበጣው እንዳይበላ የመሰብሰብ ሥራዎች እንዲሠሩ በማድረግ ሰብሉ በአንበጣው እንዳይበላ ለማድረግ እየተቻለ ነው። ይህም ቢሆን በሺህዎች የሚቆጠር ሔክታር የአንበጣ ሲሳይ መኾኑ ግን አልቀረም።

ይህ ያልተጠበቀ ክስተት ከዚህ በኋላ በምን ያህል ደረጃ ጥፋት እንደሚያደርስ ባይታወቅም፤ ጥፋቱ ያስከተለው ጉዳት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተፅዕኖ ማሳደሩ እንደማየቀር ይገመታል። በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ማብራሪያ የሚሠጡ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፤ እስካሁን በአንበጣ የጠፋው ሰብል ምንም ያህል ጉዳት የሚያስከትል ያለመሆኑን፤ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉ አርሶ አደሮች ግን የደረሰ ሰብላቸው የአንበጣ ሲሳይ መኾኑንና አሁንም በቶሎ ካልተገታ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እየተሠጠም ነው።

የምርት ዘመኑ ጥሩ የአየር ንብረት ስለነበር የተሻለ ምርት የሚገኝበት ዓመት ከመኾኑ ጋር ተያይዞም፤ በተወሰኑ አካባቢዎች ሰብላቸው ከጠፋባቸው ውጭ እንደ አገር ሲታሰብ ጉዳቱ ብዙም እንደማይሆን የሚያመለክቱ አስተያየቶች እየተሠጡ ነው። ነገር ግን አሁንም የአንበጣውን መንጋ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አልተቻለም። ከችግሩ መግፋት አንጻር በተናበበ መልኩ የመከላከሉን ተግባር መሥራት ያስፈልጋል። በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ከመልክዓ ምድሩ አመቺ አለመሆን ጋር ተያይዞ የመከላከሉን ሥራ ለመሥራት እየፈተነ ከመኾኑ አንፃር ሊደርስ የሚችለውን ጥፋት ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አልቀረም። ሆኖም በተለይ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአየር፣ በአውሮፕላንና በሌሎች የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች እየተሠሩ ነው።

ከሰሞናዊ ጉዳዮች ሰፊ ሽፋን እያገኘ ያለው ጉዳይ ግን፤ ችግሩ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት መከላከል ይችላል ነበር የሚልም አስተያየት ሰጪዎች አፋጣኝ የመከላከል ሥራ አልተሠራም በማለት ይተቻሉ።

ግብርና ሚኒስቴር ደግሞ የመከላከል ሥራውን ቀድሞ የጀመረ መኾኑን ከመግለጽ አልተቆጠበም። ነገር ግን የአንበጣ መንጋው ብዛትና መንጋው ከታየባቸው አካባቢዎች ስፋት አንፃር በእጅ ባለ አቅም ማስታገስ አላስቻለም። አሁን ግን ተጨማሪ በጀትና ተጨማሪ ኃይል በመፍጠር ከክልሎች ጋር በመናበብ እየሠራሁ ነው ብሏል።

ከሰሞኑ ዘገባዎች መረዳት እንደሚቻለው የአንበጣ መንጋ ከታየባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን 14 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የሚገኝ እፅዋት ላይ ጉዳት መድረሱን የዞኑ ግብርና ጽ/ቤት መግለጹ በምሳሌነት ይጠቀሳል።

የግብርና ሚኒስቴር ጥቅምት 26 ቀን 2012 እንዳስታወቀው ደግሞ በኢትዮጵያ 60 ወረዳዎች የበረሃ አንበጣ መከሰቱን ነው። የአንበጣ መንጋ ከተከሰተባቸው በትግራይ ሰባት ወረዳዎች፣ በአማራ 10 ወረዳዎች፣ በኦሮሚያ ዘጠኝ፣ በአፋር 21 ወረዳዎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አንድ ወረዳ ናቸው። ምን ያህል ውድመት እንደደረሰ ግን በዝርዝር የተገለጸ ነገር የለም።

ጉዳዩ አሳሳቢ ከመሆኑ አንጻር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ሚኒስቴር የሩብ ዓመት አፈፃፀም በተገመገመበት ወቅት በአንበጣ መንጋው ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሠጠው አድርጓል። የግብርና ሚኒስቴር በሠጠው ማብራሪያ የበረሃ አንበጣውን ለመከላከል እንቅፋት ከኾኑት ምክንያቶች አንዱ ተደጋጋሚ የመርጫ አውሮፕላን ብልሽት ነው።

የመከላከል ሥራውን ፈታኝ አድርገውታል ተብሎ የተጠቀሰው ሌላው ምክንያት ደግሞ፤ መካከል አንበጣው ያረፈባቸው አካባቢዎች በአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ አመች ያለመሆኑ ነው።

አሁንም ከጎረቤት አገሮች ያልተቋረጠ የአንበጣ መንጋ ወደ ሁሉም ክልሎች መዛመት፣ የአየር ጠባዩ ለአንበጣው መራባት ምቹ መኾኑም የራሱ አስተዋጽኦ ነበረው። በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የወረዳና ቀበሌ አመራሮች ለችግሩ ትኩረት ማነስ ለመከላከል ሥራው እያጋጠሙ ካሉት ችግሮች መካከል መኾናቸውን፣ በዚሁ ጉዳይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኙት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ አቶ ዘብዲዎስ መግለጻቸው ታውቋል።

“ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚደርስልን የበረሃ አንበጣው ጉዳት ካደረሰብን በኋላ ነው እያለ የመረጠን ሕዝብ ይነግረናል፤ መሬት ላይ ያለውና እናንተ የምታቀርቡት ሪፖርት አይገናኝም” ሲሉ አንድ የቋሚ ኮሚቴው አባል መናገራቸውን በዚሁ ጉዳይ ላይ የወጣው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያስረዳል። ችግሩ አሳሳቢ መኾኑን የሚያመለክተው እውነት ደግሞ፤ በአገሪቱ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በበጐ አድራጐት ሥራ ወጣቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ መደረጉ ነው። ይህንን ጥሪ ያደረጉት ደግሞ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማ ናቸው።

የአንበጣ መንጋ ጉዳይ አጀንዳነቱ በአገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አልሆነም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) በኢትዮጵያ የተከሰተውና አንበጣ መንጋ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል እስከማስጠንቀቅ የደረሰበት ነው።

በኢትዮጵያ የፋኦ ተወካይ አስፈላጊውን ሁሉ በማንቀሳቀስ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል። የፋኦ መረጃ የአንበጣ መንጋው ከወራት በፊት ከየመን ወደ ኢትዮጵያ የገባ መሆኑን የሚጠቁም ሲሆን፣ የመከላከልና የማስወገድ ሥራው በቶሎ ካልተሠራ ከኢትዮጵያ ሌላ ወደ ሌሎች ጐረቤት አገሮች የመዝመት እድሉ ሰፊ መኾኑንም ይኸው የፋኦ መግለጫ አመልክቷል። (ኢዛ)

የሰላም ሚኒስቴርና ፓርላማው

ሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀማቸውን የገመገሙበትና ማሳሰቢያ የሠጡበት ነበር። ከሰሞኑ የሥራ ክንውናቸው ካቀረቡት መካከል የሰላም ሚኒስቴር አንዱ ነው። የሰላም ሚኒስቴርን የሦስት ወሮች የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለሰላምና የዜጐች ደኅንነት ቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ሲሆኑ፤ ዕቅዱ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚያስችሉ 20 ግቦች ተከፋፍሎ የቀረበ መሆኑ ታውቋል።

የሕብረተሰቡን የሰላም ባህል ለማጎልበትና በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች ለተለያዩ አካላትና ለበርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሠጠቱን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ከዚህም ሌላ በቅርቡ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች ዜጎች እንዲፈናቀሉና ሕይወት እንዲጠፋ ያደረጉ፣ እንዲሁም ንብረት የዘረፉና ያወደሙ አካላት ከፌደራል ፖሊስና ክልሎች ጋር በመሆን የማጣራት ሥራ ስለመሠራቱ ያስረዱ ሲሆን፤ ሰላምን ከማስፈን አኳያ ሌሎች ተሠሩ ያሏቸውንም በዝርዝር ያቀረቡት መድረክ ነበር። በዚሁ መድረክ ላይ በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡ መሆኑን የሚያመለክተው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣው መረጃ፤ በተለይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሡ ግጭቶች ዙሪያ ማጠንጠኑን ይጠቁማል። በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶችና መፈናቀሎች፣ እንዲሁም አጥፊዎችን አሳልፎ በመሥጠት ዙሪያ በአመራሮች የእርስ በርስ ግንኙነት መካከል ችግር መኖሩን የሚያሳይ ጥያቄም ተነስቶ ነበር። ከዚህ አኳያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ዕቅድና ቁርጠኝነት አለው ወይ? የሚል ጥያቄ በዋነኛነት ቀርቦለታል።

በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ ከሠጡት ውስጥ አንዱ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው “የፖሊስ ዋነኛ ተግባር ሕገ-መንግሥቱንና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ነው፤ ይሁን እንጂ ተቋሙ ይህን ሥራ በሚያከናውንበት ጊዜ አልፎ አልፎ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ይታያል” ማለታቸውን መረጃው ያሳያል።

“ተቋሙ አጥፊዎችን በመያዝ እንጂ የመለየት ችግር የለበትም፤ አጥፊዎች በግላቸው አጥፍተው ተጠያቂ ሲሆኑ፣ ዘርና ሃይማኖት ውስጥ ስለሚወሸቁ ሒደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል” ማለታቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል።

ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት በበኩላቸው በአገሪቱ እያታዩ ያሉ ችግሮች ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ በመሆናቸው በአንድ ጀንበር ሊፈቱ እንደማይችሉ፤ ነገር ግን ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳይደርስ በርካታ ሥራዎችን በቁርጠኝነት መሥራቱ ሊታወቅ እንደሚገባ እና ወደፊትም ከሕዝቡ ጋር በመሆን ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ምላሽ ሠጥተዋል። የቋሚ ኮሚቴውን በቀረበው ሪፖርት ጠንካራ ጐኑን አወድሶ፤ ነገር ግን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በብርቱ ሊሠራ ይገባል ያለውንም ማሳሰቢያ ሠጥቷል። የዜጐችን ደኅንነት እና ዘላቂ ሰላም የማስፈን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት። (ኢዛ)

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል የወጣው ረቂቅ ሕግ

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀው ረቂቅ ሕግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሁንታ አግኝቶ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ የተወሰነው በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ነው።

በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመሥጠት ተሰብስቦ የነበረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለይ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርጐበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወያይቶበት እንዲጸድቅ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ጉዳይ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ባሠራጨው መረጃ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት ለማኅበራዊ ስምሪት፣ ለፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ለአገራዊ አንድነት፣ ለሰብዓዊ ክብር፣ ለብዝሃነት ጠንቅ መኾኑን በመገንዘብ የተዘጋጀ ረቂቅ ስለመሆኑ ያመለክታል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያሉ ችግሮች የሐሰተኛ መረጃና ንግግሮች ለአገር ሥጋት በመሆናቸውና የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ፤ የዚህ ሕግ መውጣት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የተሰናዳ መኾኑን ለማወቅ ተችሏል። (ኢዛ)

የገንዘብ ተቋማት ማሻሻያ

ከሳምንቱ ዐበይት ኢኮኖሚያዊ ክዋኔ ውስጥ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ይተዳደሩበት ከነበሩ ሕጐች የመድንና የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትን ሕግ ማሻሻሉ ነው።

በማሻሻያው መሠረት የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵየውያን በመድንና በአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ መሳተፍ የሚችሉበትን ፍቃድ የሚሠጥ ነው። ይህ ማሻሻያ ከዚህ በኋላ በየትኛውም የፋይናንስ ዘርፍ የውጭ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን መሳተፍ የሚችሉበት ነው።

ሌላው ማሻሻያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወለድ ነፃ የኢንሹራንስ ኩባንያ ማቋቋም እንደሚቻል መፈቀዱ ነው። ሌሎችም የፋይናንስ ጉዳዮች ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል። ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ እንደ ትልቅ ማሻሻያ ከሚወሰዱ አንኳር ጉዳዮች አንዱ የሆነው እንዲህ ያለው ሕግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀውም በዚህ ሳምንት ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ