Ethiopia Zare's weekly news digest, week 17, 2012 Ethiopian calendar

ከታኅሣሥ 20 - 26 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አሥራ ሰባተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከታኅሣሥ 20 - 26 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ያሳለፍነው ሳምንት ከፖለቲካዊ ጉዳዮች አንፃር ለየት ያለ ክስተቶችን ያስተናገደ ነው ሊባል የሚችል ነው። በጣት የሚቆጠሩ ወራት የቀሩትን አገራዊ ምርጫ የተመለከቱ ቅስቀሳና ይፋዊ የምረጡኝ ዘመቻ ተጀመረ ማለት ነው? የሚል ጥያቄ የሚጭሩ እንቅስቃሴዎች ጐልተው የታዩበት ሳምንት ነበር ማለት ይቻላል።

ለቀጣዩ ምርጫ ተፎካካሪ ለመኾን እየተሰናዱ ስለመኾናቸው አመላካች የኾኑ ክንውኖችን ከአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ እየታየ ነው። የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ እንደ ኦነግ፣ ኦፌኮ፣ ኢዜማና የመሳሰሉ ፓርቲዎች እዚህም እዚያ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ከፓርቲዎቻቸው ደጋፊዎች ጋር ከወትሮ ለየት ባለ ሁኔታ ተገናኝተው እየመከሩ ነው።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተደጋጋሚ ስሙ የሚነሳው አቶ ጀዋር መሐመድ ደግሞ በይፋ ኦፌኮን ስለመቀላቀሉ የተሰማበት፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኦፌኮ በትብብር ለመሥራት ማስታወቃቸው ከሳምንቱ ቀዳሚ ወሬዎች መካከል አንዱ ኾኗል። ታዋቂው የፖለቲካ ሰው ፕ/ር መረራ ጉዲና ፓርቲያቸው አቶ ጃዋርን ስለመቀበሉና በቀጣዩ ምርጫ ከጃዋርና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ኾነው ምርጫውን አሸንፎ ለመውጣት ስለመሰናዳታቸውም መግለጻቸው፤ ፓርቲዎች ዓይናቸውን ምርጫው ላይ ማሳረፋቸውን አመላክቷል።

በውሕደት ከተፈጠረው ብልጽግና ፓርቲ ራሱን አግልሎ የቆየው ሕወሓት ቀጣይ ጉዞውን የሚያመላክትበት ይኾናል የተባለውና፤ በታሪኩ የመጀመሪያውን አስቸኳይ ስብሰባ ያካሔደውም በዚሁ ሳምንት ነው። በድርጅታዊ ጉባዔው መጨረሻ ላይም ሕወሓት ከብልጽግና ጋር እንደማይዋሐድ አስታውቋል። ከሁሉም በላይ ግን ብልጽግና ፓርቲ እውቅና ካገኘ ወዲህ የመጀመሪያውን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ በማድረግ ግልጽ አቋሙን ያስታወቀበትና በዚሁ ጉዳይ መግለጫ የሠጠው በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባሳለፍነው ሳምንት ከወቅታዊ ፖለቲካ ጉዳዮች አንፃር በተለየ ሊገለጽ የሚችለው ከዚሁ ምርጫ ጋር ተያይዞ ፓርቲዎች እያደረጉ ያሉት እንቅስቃሴ ነው።

ከሳምንቱ ወሬዎች ውስጥ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ከወረደ በኋላ የመጀመሪያው አምባሳደር በመኾን የተመደቡት አቶ ሬድዋን ሑሴን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኾነው መሾማቸውና ከአንድ ሳምንት በፊት ከትምህርት ሚኒስትርነታቸው የለቀቁት ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ በዩኔስኮ ሥራ መጀመራቸው የተጠቀሰበት ነው።

በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ራስ ምታት ኾኖ የዘለቀው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች የመማር ማስተማሩን ሒደት እየተገዳደረ መኾኑን ባለማቆሙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ተጠቃሽ ናቸው። የችግሩ ምንጭ ናቸው የተባሉት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ሲሆን፣ በተለይ የጐንደር ዩኒቨርሲቲ በመምህራን ላይ ያሳለፈው ውሳኔ በተለየ የሚታይ ሲሆን፣ በእነዚህ ተቋማት ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከዚህ ቀደሙ የተለየ መኾኑ የተስተዋለበት ነው።

ከንግድና ኢንቨስትመንት አንፃር ባሳለፍነው ሳምንት የአዲሱ ኤክሳይዝ ታክስ ጉዳይ ጥርት ያለ ማብራሪያ የተሠጠበት ነው ማለት ይቻላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ አስፈላጊነትን ያብራሩበትና በተለይም ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ከፍ ያለ ታክስ የተጣለበትን ምክንያት ሕዝብ እንዲያውቀው ያደረጉበት ነው።

በተመሳሳይ ዘመናዊ አሠራርን ለመፍጠር የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች አገልግሎታቸውን በአንድ መስኮት ለመሥጠት ይችሉ ዘንድ ዝግጅት ሲደረግበት የነበረው አሠራር በይፋ መጀመሩም ከንግድና ኢንቨስትመንት አንፃር እንደ ትልቅ ጉዳይ የሚታይ ነው።

እንዲህ ባሉ ሰሞናዊ ጉዳዮች ላይና ሌሎች ዜናዎችን የተመለከተው የሳምንቱ ቅኝት እንደሚከተለው ቀርቧል።

የብልጽግና ምርጫ ምርጫ ነው

የብልጽግና ፓርቲ ከኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ የእውቅና ሰርተፍኬት ከወሰደ ወዲህ የመጀመሪያውን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ አከሒዷል።

በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የተካሔደው ይህ የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባው ለሁለት ቀናት የተካሔደ ሲሆን፣ ዋነኛ አጀንዳው በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳይ መምከር እንደኾነ ቀድሞ ተጠቁሞ ነበር። ስብሰባውን በተመለከተ የፓርቲው የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም የሠጡት መግለጫም በተለይ በመጪው ምርጫ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ያመለክታል።

የ2012 ብሔራዊ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ እንዲካሔድ ፓርቲያቸው ብልጽግና ጠንካራ አቋም መያዙን ጠቅሰዋል። ብልጽግና ፓርቲ በምርጫው ዙሪያ የአቋም ለውጥ ያለማድረጉን የገለጹት አቶ ብናልፍ ፓርቲያቸው ምርጫው በዚህ ዓመት መካሔድ አለበት የሚል እምነት እንዳለው በገለጹበት መግለጫቸው፤ ይህ ማለት ግን ፈታኝ ነገሮች የሉም ማለት አይደለም፣ ሥራ አስፈፃሚው በስብሰባው የምርጫው ሥጋቶችና መልካም እድሎች ዙሪያ በስፋት መክሮ መፍትሔ ይኾናል ያላቸውን ውሳኔዎችን እንዳሳለፈም አመልክተዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ኾኑ ሕብረተሰቡ ከምርጫው መካሔድ ጋር ተያይዞ የሚያነሷቸው ሥጋቶችን እንደተወያየባቸው ይኸው የኃላፊው መግለጫ ያመለክታል። የምርጫው መካሔድ ወይም መራዘም ላይም ሥራ አስፈፃሚው ስለመወያየቱ የገለጹት አቶ ብናልፍ “ምርጫው ወቅቱን ጠብቆ የአገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እውን ለማድረግ ያግዛል፣ ሕብረተሰቡ የመረጥኩት መንግሥት ነው የሚያስተዳድረኝ የሚል እምነት እንዲኖረውም ያደርጋል” ብለዋል።

በብዙ መለኪያዎች ምርጫው ቢካሔድ የተሻለ መኾኑ የተገመገመ ሲሆን፣ በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያሉት ችግሮች ግን በቀላሉ የማይታዩ መኾናቸውን ይገልጻሉ። በኃላፊው መግለጫ የተካተተው ሌላው ሐሳብ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አባላትና ደጋፊዎቻቸውን ሰላምን ከሚያውኩ ተግባራት እንዲያርቁ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የጠየቁበት ሲሆን፣ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል አጥፊዎችን ማጋለጥና ለሰላም መትጋት ይኖርበታልም ብለዋል።

ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ ምርጫው ቢራዘምም ችግሩ የመቀጠል እድሉ ሰፊ መኾኑን ያስታወሱት አቶ ብናልፍ፤ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ አገሪቱን ወደተሟላ መረጋጋት ለመመለስ በየደረጃው ያሉ የጸጥታ መዋቅሮች ጸጥታ የማስከበር ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡ አቅጣጫ ስለማስቀመጡም የኃላፊውን መግለጫ አመልክቷል። (ኢዛ)

በዩኒቨርሲቲዎች ለተፈጠሩ ግጭቶች እጃቸውን አስገብተዋል በተባሉት ላይ እርምጃ ተወሰደ

ከ450 በላይ ተማሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል፤ መምህራንም ይገኙበታል

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለተፈጠሩ ግጭቶች እጃቸው አለበት ተብለው በተጠረጠሩ ከ450 በላይ ተማሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ። ጐንደር ዩኒቨርሲቲ ብቻ በ73 ተማሪዎች፣ አስተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ እርምጃ ወስዷል።

የፌዴራል ፖሊስና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር በጋራ በሠጡት መግለጫ፤ እርምጃ ከተወሰደባቸው ከ450 ተማሪዎች በላይ ውስጥ ከ170 በላይ ተማሪዎች ከአንድ ዓመት እስከ መጨረሻው ድረስ እንዲታገዱ ውሳኔ ሲወሰን፤ ከ280 በላይ በሚኾኑት ላይ ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሠጥቷቸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ 11 ተማሪች ሙሉ በሙሉ ከዩኒቨርሲቲው እንዲባረሩ የተደረገ ሲሆን፣ 39 ተማሪዎች ለሁለት ዓመት፣ ሁለት ተማሪዎች ደግሞ ለአንድ ዓመት ከትምህርታቸው ማገዱንም የዩኒቨርሲቲው መረጃ ያስረዳል።

ብቁ ዜጋን የመገንባት ኃላፊነታቸውን ወደ ጎን በመተው በዩኒቨርሲቲው ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን ኹከትና ግጭት በማስነሳት ሚና የነበራቸው 13 መምህራንም አስተዳደራዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተገልጿል።

ቀደም ሲል በዩኒቨርሲቲው ተፈጥሮ በነበረ ግጭት በአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፍና በሌሎችም መቁሰል፤ እንዲሁም በንብረት ጉዳት የተጠረጠሩ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞችም በፖሊስ ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ እንደሚገኝ ይኸው የጐንደር ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያመለክታል። (ኢዛ)

ባገለገሉ መኪኖች ላይ ሊጣል የታሰበው ኤክሳይዝ ታክስ መተግበሩ አይቀሬ ሆኗል

ባለፉት ሳምንታት አነጋጋሪ ከኾኑ ጉዳዮች አንዱ አዲሱ የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ነበር። ረቂቅ አዋጁ በተለይ ባገለገሉት መኪኖች ላይ ሊጣል የታሰበው የኤክሳይዝ ታክስ መጠን ከፍተኛ ነው በሚል በየአቅጣጫው ብዙ ተብሎበታል።

ረቂቁ የተለያዩ ምርቶች ላይ ዋጋ ለመጨምር መንሥኤ ሊሆን ይችላል የሚሉም አስተያየቶች ሲሰነዘሩ የነበረ ሲሆን፣ በረቂቁ ላይ ታኅሣሥ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. የተደረገው የውይይት መድረክ ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችን ያፍታታ ሆኗል። የገቢዎችና የገንዘብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች ላይ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትና የመገናኛ ብዙኀን በታደሙበት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የኤክሳይዝ ታክስ ከዚህ በፊት የነበረ እንጂ አዲስ ታክስ ካለመኾኑ፤ በተጨማሪ ኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው እቃዎችና ሸቀጦች ከዚህ በፊት የነበሩና በሌሎች አገሮች የሚጣልባቸው እንደኾነ ተብራርቷል።

በሌሎች አገሮችም እንደሚደረገው ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው ኤክሳይዝ ታክስ የሚኖረውን ጠቀሜታም በሰፊው ተብራርቷል። ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ በተጣለው አዲስ ተጨማሪ ታክስ ምክንያት ዜጎች የሚያወጡትን ተጨማሪ ወጪ ከማስቀረቱ በተጨማሪ፤ አገራችን የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ብክነት እንደሚቀንስ እኒሁ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል። የነዳጅና መለዋወጫ ወጪዎችን በመቀነሱ ረገድም ያለውን ጠቀሜታ በምሳሌ በማመላከት አብራርተዋል።

በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ሁለት ቢሊየን ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙ የሚጠቅሰው በዕለቱ የቀረበ ትንታኔ፤ እነኚህ ተሽከርካሪዎች የአገልግሎት ጊዜያቸው ሲያልፍ እንደማስወገጃ ወይም ማሳረፊያ ተደርገው የሚታዩት የአፍሪካ አገሮች እንደኾኑም ያስታውሳል። ነገር ግን ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ወደ አገራቸው መግባት ቀስ በቀስ የሚደርሰውን ጉዳት ተገንዝበው ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካና ሱዳን ሙሉ በሙሉ፤ እንዲሁም ኢትዮጵያን ጨምሮ 20 ያህል አገራት በከፊል ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ እገዳ ጥለዋል።

እ.ኤ.አ. በ2017 የአገራችን ጉምሩክ መረጃ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 88 በመቶዎቹ ያገለገሉ ናቸው። እነዚህ ተሽከርካሪዎች አብዛኞቹ የቴክኒክ ችግር ያለባቸው ሲሆን፣ ከ100 ሺዎቹ ውስጥ 5ሺ የሞት አደጋዎች በማድረስ ኢትዮጵያን ከዓለም አምስተኛ ደረጃን እንድትይዝ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተመላክቷል። ይህንን ለመለወጥ ጭምር የዚህ ረቂቅ መዘጋጀት አግባብ ነው ተብሏል።

ካገለገሉት ተሽከርካሪዎች አንፃር ረቂቁ ጠቃሚ መኾኑን በተለይ የገቢዎች ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊ ያብራሩ ሲሆን፣ እስካሁን ይሠራበት የነበረውን አሠራር በመለወጥ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች እድለ የሚሠጥ ነው። እስካሁን በነበረው የኤክሳይዝ ታክስ አሠራር እስከ 1 ሺሕ 300 ሲሲ 30 በመቶ፣ ከ1ሺ 301 እስከ 1ሺ 800 ሲሲ 60 በመቶና ከሺ 801 በላይ ከ100 በመቶ ይጣል ነበር። ይህ አመዳደብ ለአዳዲስም፣ ላገለገሉትም ተሽከርካሪዎች ተመሳሳይ ስለነበር በርካታ አሮጌ መኪኖች ወደ አገር እየገቡ ችግር አስከትለው እንደነበርም ያመለክታል።

ይህ አሠራር የአገር ውስጥ አምራቾችን ካለማበረታታት አልፎ የፍትሐዊነት ጥያቄንም ያስነሳ ነበር። አሁን ግን ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የኤክሳይዝ ታክስ መጣሉ፤ አገር ውስጥ ለሚያመርቱትም፣ አዳዲስ መኪኖችን ከውጭ ለሚያስገቡትም ትልቅ እፎይታን እንደሚሠጥም የተሠጠው ማብራሪያ ያመለክታል። ይህም የአሁኑ ማሻሻያ እንደየሲሲያቸውና እንደየአገልግሎት ዘመናቸው እስከ 500 በመቶ ታክስ ስለሚጥልባቸው ነው። ለዚህ ማሳያ ሆኖ የቀረበው፤ የሲሊንደር ይዘቱ ከ1300 ሲሲ ያልበለጠ አዲስ መኪና 30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ሲጣልበት መኪናው ከሰባት ዓመት በላይ ካገለገለ 430 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይከፍላል የሚል ነው።

ውይይቱ እንዲህ ያሉ ማብራሪያዎችን በመሥጠት ረቂቅ ሕጉ ለተሻለ አገልግሎትና ጥቅም የተሰናዳ መኾኑን በውይይት መድረኩ ላይ አመላክተዋል።

ከዚሁ ውይይት ጋር ተያይዞ የገቢዎች ሚኒስቴር ያስተላለፈው መልእክትም ነበር። በረቂቅ ላይ ያለው አዋጅ ዋጋ ጭማሪ ያስከትላል በማለት በተለይም በመሠረታዊ የፍጆታዎች እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ የሚገኙትን የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያልተገባ ተግባር መኾኑን በመግለጽ እንዲህ የሚያደርጉት እርምጃ ይወሰድባቸዋል ብሏል።

ከዚህ ውይይት ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኤክሳይዝ ረቂቅ አዋጁ ጠቀሜታው የጐላ መኾኑንና በተለይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች እየደረሱ ያሉትን ችግር ጭምር በምሳሌ በመጥቀስ አብራርተዋል። ይህን የአገር ችግር ለመቅረፍ አዋጁ ተፈፃሚ የሚደረግ መኾኑንም አረጋግጠዋል። (ኢዛ)

የአቶ ሬድዋን ሁሴን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ መኾን

ከለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያና ኤርትራ ባሰፈኑት ሰላም በኤርትራ የመጀመሪያው አምባሳደር በመኾን የተሾሙት አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኾነው መሾማቸው የተሰማው ባሳለፍነው ሳምንት ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከታኅሣሥ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኾነው መሾማቸውን አስታውቋል።

አቶ ሬድዋን በኤርትራ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኾነው ከመሾማቸው በፊት በአየርላንድ አምባሳደር በመኾን ማገልገላቸው ይታወሳል። አቶ ሬድዋን በአምባሳደርነት ከመሥራታቸው ቀደም ብሎ በተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በሚኒስትርነት የሠሩ መኾኑ አይዘነጋም። የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር፣ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር እንደነበሩ ይታወሳል። አቶ ሬድዋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የኾኑት በቅርቡ ከኃላፊነታቸው በለቀቁት አቶ ማርቆስ ተክሌ ምትክ ነው። (ኢዛ)

ወጣቶችና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት

ባለፈው ዓርብ ታኅሣሥ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ወጣቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ መድረክ ላይ ታድመው ነበር። እርሳቸው የታደሙበት ይህ መድረክ ደግሞ “በህብር ወደ ብልጽግና” የሚል መሪቃል የያዘና የብልጽግና ፓርቲን ፕሮግራምና ሕገ ደንብ ዙሪያ ሲካሔዱ የነበሩ ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች መጠናቀቃቸውን በማስመልከት የተሰናዳ የማጠቃለያ ዝግጅት ነው።

ውይይቱ የተካሔደው በሚሊኒየም አዳራሽ ሲሆን፣ 10 ሺሕ ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል በተባለው በዚህ ፕሮግራም ላይ አንዱ ተናጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ነበሩና፤ ብልጽግና ፓርቲን የገለጹበት መንገድ ጆሮ ያገኘ ነበር ማለት ይችላል። “የብልጽግና አስተሳሰብንና አሠራርን በቀጣይ 50 እና 60 ዓመታት ማሸነፍ ከባድ ነው፤ ማንም እኔን ቢያሸንፍ ከብልጽግና ሐሳብ ወዲያ ግን ኢትዮጵያን ለወራትም ቢሆን ማስተዳደር ይከብደዋል” በማለት እስከ መግለጽ ደርሰዋል።

“ብልጽግናን በመክሰስ ሳይሆን፤ ከብልጽግና በመማርና የብልጽግና እሳቤዎችን በማሻሻል ብቻ ነው ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራው” ያሉት ጠቅላይ ማኒስትሩ፤ አክለው ያስተላለፉት መልእክት “ወጣቶች በምርጫ ወቅቶች ለተወዳዳሪዎች ድምፃቸውን እንጂ ሕይወታቸውን መገበር አይገባቸውም” የሚል ነበር።

ወጣቶች ሕልማቸውን ሊነጥቁ ከተዘጋጁ ጉዳዮች በመራቅ፤ የብልጽግና ጎዳናን መከተል እንደሚገባቸው በማመልከትም፤ ሰውን አጋድሎና አጣልቶ ሥልጣን ለመያዝ ያለመ ካለ፤ አስተሳሰቡ ራሱ የቆሸሸ ነውና ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፤ ስለዚህ ወጣቶች መንቃት ይኖርባቸዋል በማለት መክረዋል።

በተለይ ወጣቶችን ጠቅሰው ይህንን መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሚከሰቱ ግጭቶች ወጣቶች እየተጎዱ ስለመኾኑ አስረድተዋል። ወጣቱን ተገፋፍቶ ወዳልተፈለገ ነገር የሚያስገቡ ኃይሎች ሲሞቱ እንደማይስተዋል በማሳሰብ፤ ወጣት ስለኾናችሁ ለማናችንም ቢሆን ካርዳችሁን እንጂ ሕይወታችሁን አትስጡ በማለት መልእክት አስተላልፈዋል። “የአዲስ አበባ ወጣቶች ብልጽግናን ከወደዳችሁ ድምፅ ሥጡት፤ ካልወደዳችሁት ግን በድምፅ ቅጡት፤ ለማንም ቢሆን ሕይወታችሁን አትሥጡ” በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለወጣቶች ካስተላለፉት መልእክት ውስጥ መሥራት፤ ከሌብነት መጠበቅ፣ በቅንነት ማገልገል ብቻ ነው የሚል የሚገኝበት ሲሆን፤ ከእንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራው ይህ ብቻ መኾኑንም ገልጸዋል። “ዛሬ ኦሮሞና አማራን አጋድሎ ሥልጣን ለመያዝ የሚፈልግ ኃይል ካለ፣ ዛሬ እስላምና ክርስቲያንን አጋድሎ፣ ቤተክርስቲያንና መስጅድ አቃጥሎ ሥልጣን ለመያዝ የሚሻ ግሩፕ ካለ አመጣጡ ራሱ የቆሸሸ ነውና ለኢትዮጵያ አይበጃትም” በማለት እምነታቸውን ገልጸዋል። (ኢዛ)

የባሌ ዞን ለሁለት መከፈል

ከሳምንቱ ዜናዎች ለየት ባለ መልኩ ሊታይ የሚችለው የኦሮሚያ ክልል ካቢኔ ያሳለፈው ውሳኔ ነው። የተለየ የሚያደርገው እንዲህ ያለ ውሳኔ ያልተለመደ ከመኾኑ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፤ ካቢኔው ባካሔደው ስብሰባ የባሌ ዞን በሁለት ዞኖች እንደ አዲስ እንዲደራጁ ወስኗል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ጨፌ ኦሮሚያ እንዲጸድቃቸው መርቷቸዋል።

ካቢኔው እንዲህ ያለውን ውሳኔ የወሰነው ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ለካቢኔው ባቀረበው ጥናት መሠረት ነው። ይህም በባሌ ዞን ባለው የመሠረተ ልማትና የቦታ መራራቅ ችግር የተነሳ አገልግሎት በፍጥነት ማቅረብ ካለመቻሉ ጋር የተያዘ ነው። በዚህም ምክንያት ለረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ችግር መንሥኤ ኾኖ መቆየቱን የቀረበው ጥናት ማመልከቱን በዚህ ውሳኔ ላይ የተሠራጩ መረጃዎች አመልክተዋል። ካቢኔው የቀረበለትን ጥናት በመንተራስ ውይይት ካካሔደ በኋላ የባሌ ዞንን ምሥራቅ ባሌ ዞንና ምእራብ ባሌ ዞን ሆኖ እንደ አዲስ እንዲደራጁ በሙሉ ድምፅ ወስኗል። በዚህ ውሳኔ መሠረት የምዕራብ ባሌ ዞን በሚል እንዲደራጅ የሚደረገው ዞን ዋና ከተማ ሮቤ እንዲሁም የምሥራቅ ባሌ ዞን ዋና ከተማ ደግሞ ጊኒር እንዲሆን ተወስኗል። (ኢዛ)

ኦፌኮ፣ ጃዋርና አዲሱ ጥምረት

ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከተሰሙት ወሬዎች አንዱ አቶ ጃዋር መሐመድ ኦፌኮን ስለመቀላቀሉና ኦፌኮም ይህንን ያረጋገጠ መረጃ መሥጠቱ ነው።

ከለውጡ ወዲህ በኢትየጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስሙ የሚነሳው አቶ ጃዋር ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ በየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ እንደማይገባ በመግለጽ፤ ሚናው በያዘው ሚዲያ ላይ ስለመኾኑ ያስታወቀ መኾኑን ላስታወሰ፤ በዚህ አቋሙ ይጸናል የሚል አስተያየቶች ሲዘነዘሩ ቢቆዩም፤ ባለፈው ሳምንት ግን ከዚህ በተቃራኒ በኾነ መንገድ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የአንድ ፓርቲ አባል መኾኑን በኦፌኮ በኩል ሊታገል መኾኑን ገልጿል። ብዙዎችን ያነጋገረው ጉዳይ አቶ ጃዋር በኦሮሚያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መካከል ኦፌኮን የመምረጡ ጉዳይ ሲሆን፤ የኦፌኮን መሪ ፕ/ር መረራ ጉዲና አቶ ጃዋር ቀድሞም ቢሆን ከፓርቲያቸው ጋር ግንኙነት እንዳለው በመጥቀስ እንደ ምሳሌ ያነሱት እርሳቸው ለእስር ዳርጓቸው በነበረው የክስ መዝገብ ላይ አንዱ ተከሳሽ ጃዋር ነበር በማለት ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኦነግ፣ ኦፌኮና ኦብኮ በትብብር ለመሥራት ስለመስማማታቸው የተሰማውም በዚህ ሳምንት ነበር። ይህ ስብስብ በመጪው ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ ለማሸነፍ የሚሠራ መኾኑን፤ ይህ እንኳን ባይኾን ሊመሠረት ይችላል ተብሎ በሚጠበቀው ጥምር መንግሥት ውስጥ ኹነኛ ቦታ ለመያዝ የሚሠራ ስለመኾኑ ፕሮፌሰር መረራ ገልጸዋል።

እነዚህ ፓርቲዎች ተጣምረው ለመሥራት መስማማታቸው አንድ ጉዳይ ኾኖ፤ ጃዋር መሐመድ ዜግነትና የፖለቲካ ተሳትፎው ጉዳይ አነጋጋሪ መኾኑ አልቀረም። ከሰሞኑ ጃዋር መሐመድ በሠጠው መግለጫ ደግሞ፤ አሜሪካዊ ዜግነታቸውን ለመቀየር የጀመሩት እንቅስቃሴ መኖሩ ነው። ይሁንና አሁን በኦፌኮ አባልነት ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ነው መባሉ ከሕግ አንፃር አከራካሪ ይኾናል የሚሉ ወገኖች አሉ። (ኢዛ)

የብልጽግናና የሕወሓት መጨረሻ

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ረዥም እጅ የነበረው ሕወሓት ከማዕከላዊ መንግሥት በብዙ ኪሎ ሜርት ርቀት ላይ እንዲወሰን ከተደረገ ወደ ሁለት ዓመታት እየተጠጋው ነው።

የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን በመፍጠር የሚጠቀሰው ሕወሓት፤ ኢሕአዴግን ለማዋሐድ ሲደረጉ ከነበሩ እንቅስቃሴዎች ራሱን አግሎ የቆየ ሲሆን፣ ሦስቱ የኢሕአዴግ እኅት ድርጅቶችና አምስቱ አጋር ድርጅቶች ተዋሕደው ብልጽግና ፓርቲን ለመፍጠር ሲስማሙ፤ ሕወሓት መክሬበት ውሳኔዬን አሳውቃለሁ ብሎ ቆይቶ ነበር።

ይህንንም በዚህ ሳምንት በሚያካሒደው አስቸኳይ ጉባዔ ይወስናል ተብሎ ሲጠበቅ ቆይቶ፤ የውሳኔው ድምዳሜ ከብልጽግና ጋር አልዋሐድም የሚል ኾኗል።

ከዚህ ውሳኔ ቀደም ብሎ የሕወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ፓርቲያቸው ከብልጽግና በተቃራኒ በመኾን የሚንቀሳቀስ መኾኑን በይፋ የገለጹ ሲሆን፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችንም እስከ ማስጠንቀቅ ደርሰው ነበር። ይህ መግለጫቸው በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን አስቆጥቷል። ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ጭቆና የሚያብስ ሥራ እየሠራ መኾኑንም በመግለጽ የዶክተር ደብረጽዮን ንግግርን ፓርቲዎቹ ተቃውመዋል። ይህም ቢሆን ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ያወጣው መግለጫ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የሚያስማሙ ነገሮች ስለሌሉ ብልጽግና ፓርቲን እንደማይቀላቀል በይፋ በማስታወቅ ከሌሎች የፌደራሊስት ኃይሎች ጋር እሠራለሁ ብሏል።

ለሁለት ቀናት ያካሔደውን አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባዔ ካጠናቀቀ በኋላ፤ ታኅሣሥ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በሕገ መንግሥቱና በሕግ ብቻ እንዲኾን መደረጉን ጠቅሷል።

ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የዓላማና የመስመር ልዩነት ስላለው ውሕደቱ ውስጥ እንደማይገባ ያስታወቀው የሕወሓት መግለጫ፤ የኢሕአዴግንም ንብረት እካፈላለሁ ብሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ