ጆሴፍ ኮኒ በኡጋንዳ ከ60 ሺህ በላይ ሕፃናትን ጠልፏል

Ethiopia Zare(ዓርብ የካቲት 30 ቀን 2004 ዓ.ም. March 9, 2012)፦ የኡጋንዳው የጎሬላ ተዋጊዎችና "የጌታ ተጋዳይ ሠራዊት" (Lord’s Resistance Army - LRA) መሪ የሆነውን ጨካኙንና አረመኔውን ጆሴፍ ኮኒን ለማደን በኢንተርኔት የተሰራጨው የ30 ደቂቃ ቪዲዮ በአራት ቀን ውስጥ በዩቲዩብ ብቻ ወደ 60 ሚሊዮን ተመልካቾችን ማግኘቱ ታወቀ። የቪዲዮው ዓላማ ጨካኙን በዓለም ላይ ታዋቂ በማድረግ በቁጥጥር ስር ለማዋል ነው።

ጆሴፍ ኮኒ ላለፉት ሃያ ዓመታት ሕፃናትንና ወጣቶችን አስገድዶ ሴቶቹን ለወሲብ ባርነት በመዳረግ፣ ወንዶቹን ደግሞ ለወታደርነት በማሰማራት፣ ሰው በማፈንና በመግደል፣ ... በዓለም ላይ በአሁኑ ሰዓት ቁጥር አንድ ታዳኝ ከሆኑት ጨካኝና አረመኔ ሰዎች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። ጆሴፍ ኮኒ ከ60 ሺህ በላይ ሕፃናትን መጥለፉ ታውቋል።

”ኮኒ 2012” የተሰኘውን ቪዲዮ ያሰራጨው መሰረቱን ሳንዲያጎ ያደረገው "ኢንቪዚብል ችልድረን" የተሰኘው ድርጅት ሲሆን፣ የፊልሙ ዳይሬክተር የድርጅቱ መስራች ጄሰን ሩሰል ናቸው። የቪዲዮው ዓላማ ጆሴፍ ኮኒን በዓለም ላይ እጅግ ታዋቂ ለማድረግ ሲሆን፣ ታዋቂነቱ ግን እንዲወደስና እንዲፈቀር ለማድረግ እንዳልሆነ የፊልሙ አዘጋጅ ይገልጻል። ይልቁንም ጆሴፍ ኮኒን በዓለም አቀፍ ደረጃ ግለሰባዊ ማንነቱን በማሳወቅ የዓለምን ህዝብና መንግሥታት ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በማብዛት፤ ግለሰቡን አድኖ በመያዝ ለዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ እና በኡጋንዳ ሕፃናት፣ ወጣቶችና ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን የጭካኔ ሥራ ለመታደግ እንደሆነ ታውቋል።

ይህ ዜና በሚጠናከርበት ሰዓት ቪዲዮው በዩቲዩብ ከተለቀቀ አራት ቀናት ያልሞላው ቢሆንም፣ የተመልካቹ ቁጥር 60 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ በቪምዮ እና በመሳሰሉትም የቪዲዮ ድረ ገጾች ከ20 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾችን ቪዲዮው ማግኘቱ ታውቋል። ትዊተርና ፌስቡክም ጭምር ለዚህ ቪዲዮ በሰፊውና በፍጥነት መሰራጨት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። እንዲህ ያለውን ክብረወሰን በዓለም ላይ ያሉ ታዋቂ አርቲስቶችና ግለሰቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ አግኝተውት የማያውቁ መሆኑ ብዙዎችን አስገርሟል።

ቪዲዮው የበርካቶችን ድጋፍ ያገኘ ቢሆንም፤ አንዳንድ ወገኖች ግን ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ከተቃውሞዎቹ ነጥቦች መካከል አንኳሮቹ ”ቪዲዮው ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካንን ብቸኛዋ የዓለም ሠላም አስከባሪና መፍትሄ ሰጪ አድርጎ አቅርቧታል፤ በዚህም በዓለም ላይ ፈላጭ ቆራጭነትን ያከናንባታል”፣ ”አፍሪካውያን የራሳቸውን ጉዳይ ራሳቸው መጨረስ ይገባቸዋል”፣ ... የሚሉት ይገኙበታል።

የቪዲዮውን መለቀቅ ተከትሎ የኡጋንዳ መንግሥት ጆሴፍ ኮኒን ከገባበት ገብቶ በሕይወትም ይሁን አስከሬኑን ለመያዝ የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ በዛሬው ዕለት ከሰጠው መግለጫ ለማወቅ ተችሏል።

አንዳንድ ኡጋንዳውያን እንደሚሉት ከሆነ ጆሴፍ ኮኒ በአሁኑ ሰዓት በጭራሽ በኡጋንዳ ውስጥ እንደሌለ ይናገራል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!