|
ፀሐፊ - ደረጀ ደምሴ
ቋንቋ - አማርኛ አሣታሚና አከፋፋይ - Aesop Publishers & Distributors ዋጋ - 25 የአሜሪካ ዶላር “አባቴ ያቺን ሰዓት” በደረጀ ደምሴ የተጻፈና በቅርቡ በገበያ ላይ የዋለ አዲስ መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉ ፀሐፊ ደረጀ ደምሴ ስለ አባቱ ሜ/ጄ ደምሴ ቡልቶ፣ በኢትዮጵያ ሠራዊት ውስጥ በአመራር ላይ ስለነበሩት ከፍተኛ መኮንኖች፤ እንዲሁም ስለ ግንቦት 81 መፈንቅለ መንግስት የጻፈው አዲስ መጽሐፍ ነው። ደረጀ ከአባቱ ጋር በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ ያየውን እና በቦታው ከነበሩ የተለያዩ ከፍተኛ መኮንኖች ያጠናቀረውን፤ በጣፋጭ ትረካ አቅርቦታል።
በአቀራራቡ ልዩ በሆነው በዚህ መጽሐፍ ላይ ከዚህ በፊት ተደብቅው የነበሩ ምስጢሮችን የያዘ ብቻ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ሠራዊት ውስጥ የነበሩት ችግሮች ምን ነበሩ? የሌ/ኮ መንግሥቱን ሥርዓት ለመጣል የተደረገው ሙከራ ሂደት እንዴት ነበር? የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች ዓላማስ ምን ነበር? መንስዔዎቹስ ምንድን ነበሩ? የኢትዮጵያ ሠራዊትና መሪዎቹ ያጋጠሙዋቸው ችግሮች፤ በተለይም የፖለቲካ ሥርዓቱ በጦሩና በመሪዎቹ ላይ የፈጠራቸው ዘርፈ ብዙ መሰናክሎች ምን ይመስሉ ነበሩ? መፈንቅለ መንግሥቱስ እንዴት ከሸፈ? የመፈንቅለ መንግሥቱስ አሳዛኝ ፍጻሜ የሀገራችንን እጣ ወዴት አመራው? … ወዘተ ብዙ ዓመታት በፈጀ ጥናት፣ በርካታ ቃለ ምልልሶችና በፀሐፊው ገጠመኞች ተመስርቶ በሰፊው ይዳስሳል።
የመጽሐፉ አተራረክ በአባትና ልጅ ታሪክ ላይ የተመሰረት እና አንባቢን የሚስብ፣ ከገጽ ወደ ገጽ በጉጉት የሚያስተላልፍ፣ በአይነቱ ከዚህ በፊት ከወጡት መጻሕፍት የተለየ ነው። ከመጽሐፉ በስተጀርባ የተያያዘው የሜ/ጄ ደምሴ ቡልቶ የግል የጦር ሜዳ ማስታወሻ ነው። ከሐምሌ 29 ቀን 1977 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ኅዳር 3 ቀን 1978 ድረስ የባሬንቱን ከተማ ለማስለቀቅና ናቅፋን ለመቆጣጠር በተደረጉት ዘመቻዎች ጄ/ል ደምሴ ቀን በቀን የያዙት ማስታወሻ በራሳቸው እጅ ጽሑፍ እንዳለ ለታሪክ ተመራማሪዎች እንዲያገለግል ደራሲው አቅርቦታል። የ”አባቴ ያቺን ሰዓት” ፀሐፊ ደረጀ ደምሴ የጄ/ል ደምሴ ቡልቶ አራተኛ ልጅ ሲሆን፣ ነዋሪነቱም በሰሜን አሜሪካ ነው። ደረጀ ከጆርጅ ሜሰን ዩኒቨርሲቲ በመንግሥት ፖለቲካ ትምህርት በባችለር ዲግሪ፣ ቦስተን ከሚገኘው ከሳፈክ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት በሕግ የዶክትሬት ዲግሪ ተመርቋል። በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካን ሀገር በጥብቅና ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ ሲሆን፣ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነው። የመጽሐፉን ይዘት ለማመልከት ያህል ከዚህ በታች ከመጽሐፉ የተቀነጫጨቡ ትረካዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ጥቆማ፦ መጽሐፉን ኢንተርኔት ለመግዛትም ሆነ አከፋፋዩን ለማግኘት የሚከተለውን አድራሻ ይጠቀሙ። Aesop Publishers & Distributors ስልክ: 202-386-3037 www.demissiebulto.com |