ካሣን አትቀስቅሱት!! (ወለላዬ)
ካሣን አትቀስቅሱት!! (Read on PDF)
ከወለላዬ
ተዉት ይተኛበት! ካሣን አትቀስቅሱት!
ተዋግቶ ተዋግቶ ስላረፈ ደክሞት።
መይሳውን ተዉት! ያንን ዳልጋ አንበሳ፣
ተራውን ይተኛ! ዳግም አይነሳ።
አገር ሲያማት - ሲያመው፣ ስትደማ - ሲደማ!
ቆይቷል ሲደክም አሁንስ አይስማ
እሱ አካሉ ይጥና ቁስሉ ይድረቅለት፣
የሱን ኑሮ ኖረን ሞቱን እኛ እንሙት
ስቃይዋ ስቃዩ! ህመምዋ ህመሙ! ጠላቷ ጠላቱ፣
ሆኖ ላገር ሞቷል የለው ያንድ ብርቱ
አለግዜው በርቶ የቋራው ነበልባል፣
አሮ! ተኮማትሮ! ተቃጥሎ በቅቶታል።
ሳይታሰብ ጠፍቷል! ውስጡን ጨሶ ጨሶ
ውስጡን ጨሶ ጨሶ፣
አገሩን አኑሮ እራሱን ጨርሶ።
ታዲያ ለምን ይንቃ! በሱ ቁጣ ንዴት፣
እኛው እንወጣው እሱን አትቀስቅሱት።
ስንት ጊዜ ይሙት? ስንት ጊዜ ይድማ?
ስንቱን ደባ ይየው? ስንቱን ወሬ ይስማ?
በማን ላይ ደስ ብሎት በማን ላይ ይቆጣ?
የቱን ሹመት ሾሞ፤ የትኛውን ይቅጣ?
በየቱ ተናዶ፤ በየትኛው ይሳቅ?
አትቀስቅሱት በቃ! መዩ ከሚጨነቅ።
መዩ ከሚጨነቅ ከሚከፋው ይቅር፣
እኛው እንመልሰው የመጣውን ችግር
መዩ አምጦ አምጦ ካሣ ቃቶ ቃቶ፣
ለኢትዮጵያ አንድነት አርፏል ዋቶ ዋቶ
ስለዚህ ደክሞታል አባ ታጠቅ ይረፍ፣
ላሁን ችግራችን እኛው እንሰለፍ።
ሰላማዊ ትግሉ ለውጥ ካላመጣ፣
ለወሳኙ ፍልሚያ ባንድ ላይ እንውጣ
ማለዳ ተነስተን ፈጥነንም እንገስግስ፣
መዩ ባንተ ወኔ ካሣ ባንተ ፈረስ
ሰይፍህን እንምዘዝ ጦርህን እንስበቅ፣
አረፍ በል አንተ ጥና አባ ታጠቅ
ብዙ ሽህ ካሣዎች ብዙ ሽህ መይሳ፣
ሆነን ላገራችን እኛው እንነሳ
በደል የበዛብን የምንገኝ በቋፍ፣
ብዙ ስለሆንን ግፈኛን እናራግፍ
ካሣን ግን እንተወው መዩን አንቀስቅሰው፣
አንበሳው ተኝቷል ደክሞታል እንደሰው
ስለዚህ ለሀገር ለህዝብ እኩልነት፣
ለኢትዮጵያ ክብር ለኢትዮጵያ አንድነት፣
የሱን ትግል ታግለን እንብቃ ለውጤት።
መጋቢት 21 ቀን 2000 ዓ.ም. ስዊድን
March 30,2008 Sweden