ለጥበብ ሰው እዘኑለት (Read on PDF)

ከወለላዬ

(ለድምፃዊ ታምራት ሞላ እና ለጥበብ ሰዎች)


 

ዝነኛ ነው ድምፀ መልካም

አቤት ደግሞ ሲጽፍ ግጥም

ሰዓሊ ነው የረቀቀ

ባገር ዙሪያ የታወቀ

ደራሲ ነው ስመጥሩ

የገነነ በብዕሩ

ታዋቂ ነው ባለቅኔ

አትበሉኝ ይቅር ለኔ

 

ከዛ ጥበብ በስተጀርባ

ተደብቆ እያደባ

ህዝብ ሳያውቅ ሰው ሳይሰማ

የሚጠብሰው እንደሳማ

አለው እጅግ ክፉ ጠላት

ለጥበብ ሰው እዘኑለት

ካለው ዝና ተነስታችሁ

ደስተኛ ነው እያላችሁ

አትመኑት እባካችሁ

ችግር ቤቱ ዓይን አፍጦ

ተቀምጧል ተዘርፍጦ

አቤት ለዛው ጨዋታ ሲያውቅ

አቤት ድምፁ ሠርግ ሲያሞቅ

አቤት ቃላት አወጣጡ

አይ ሠላምታ አሰጣጡ

አቤት መድረክ ሲቆጣጠር

ደግሞ መልኩ ገጹ ሲያምር

ሽቅርቅር ነው ባለባበስ

ማንም የለ ከሱ እሚደርስ

ከገጠመ ከጻፈማ

ለሁሉ ነው የሚስማማ

የሚል ዝና በማላበስ

ለችግሩ ቀድመን ሳንደርስ

ያንን ስሙን ተሸክሞ

ስንቱ ቀረ ሳይድን ታሞ

ሃቅ ሲያምጥ ጥበብ ሲጭር

ማጣት ገብቶ እጎጆው ስር

እላዩ ላይ አድሮ ውሎ

ጠርቦ ጥሎት አጥመልምሎ

ተሰቃይቶ ያ ወንድሜ

ሀብት ነፍጎት ተርፎት ዕድሜ

በእጁ ሳይተርፍ ትንሽ ቅሪት

ፍግም ሲል በባዶ ቤት

ተመልክቷል ሁለት ዓይኔ

አትንገሩኝ የሱን ለኔ

ለኛ ደስታ ጮማ እንዲቆርጥ

አለልኩ ግተን መጠጥ

አስጨፍረን አስደንሰን

ለለት ውሎ ሆዱን ሞልተን

ሸኝተነው በጭብጨባ

ባዶ ኪሱን እየገባ

ቀን ሲጨምር ወር ሲገፋ

ችግር ውጦት አጥቶ ተስፋ

እዛ እሮጦ እዛ በሮ

ቀን ተጠብሶ ሲመሽ አሮ

ይቆይና ሲይዝ አልጋ

ሳንሰጠው ምንም ዋጋ

ጥሎን ያልፋል ማቆ ማቆ

ጠያቂ አጥቶ ሁሉን ናፍቆ

ይሄ ጉዳይ ይሄ ድርጊት

እንደመጣ ባሁን ሰዓት

አድርጋችሁ አትንገሩኝ

ድሮም አለ አውቃለሁኝ

አይቻለሁ ፊትም ከጥንት

ደራሲውን ችግር ውጦት

አይቻለሁ የጥበብ ሰው

በባዶ ቤት ሞት ሲልሰው

አይቻለሁ ፊቱ ቆሜ

ተቆራምዶ ያ ወንድሜ

እኔን ተዉኝ አትንገሩኝ

በዚህ ጉዳይ ቤተኛ ነኝ

ያቺ ቆንጆ ሙዚቀኛ

ያ ሸበቶ ጋዜጠኛ

ብዙዎቹ ጥበበኞች

የተባሉ ሕይወት ኮትኳች

በዛን ጊዜ በሰዓቱ

እንዴት ሆነው እንደሞቱ

አይቻለሁ ምስክር ነኝ

እባካችሁ አታንሱብኝ

ያሳለፉት ውጣ ውረድ

እንደሆነ እጅግ ከባድ

ተመልክቷል ሁለት ዓይኔ

አትንገሩኝ ያንን ለኔ

እናንተ ግን አደራችሁ

የጻፈውን አንብባችሁ

ድምጹን ከሩቅ አዳምጣችሁ

እንደደላው እንዳትቆጥሩት

ለጥበብ ሰው እዘኑለት

ያሁኑ እንኳን ያውቅበታል

ጊዜው ጥሩ ሆኖለታል

በአስዮ በቤሌማ

በቀን እና በጭለማ

በእቴሜቴ በአቦጊዳ

ቀሎለታል የኑሮ ዕዳ

የድሮው ግን ተንከራቶ

ለአርባ ዓመታት ለፍቶ ለፍቶ

ይሄው ቀረ ሁሉን አጥቶ

እሱ ለሰው ሲያጨበጭብ

ሰዉ ለሱ ሲያጨበጭብ

በኡኡታ በቸብቸብ

በብርቱካን በአልማዜ

በትዝታ ውዝዋዜ

በእሹሩሩ በኔ ፍቅር

ሽቅብ ቁልቁል ሲውተረተር

ለፋሲካ ለእንቁጣጣሽ

እዛው ውሎ እዛው ሲያመሽ

ለልደት ቀን ለድል በዓል

ወይ ሲያቅራራ ወይ ሲሸልል

ይውልና ዋቶ ዋቶ

ድፍት ይላል ጎጆው ገብቶ

ደራሲውም ገንዘብ አጥቶ

ማሣተሚያ ዕዳ ገብቶ

ካንዱ ወስዶ ላንዱ ሰጥቶ

በአንድ ክፍል በጠባብ ቤት

ተጨናንቆ በመጻሕፍት

በሷው ውሎ በሷው አድሮ

ይገኛታል እዛው ከሮ

ይሄንን ሰው አስጊጣችሁ

እሰማይ ላይ አውጥታችሁ

ታዋቂ ነው ድምፀ መልካም

አይ ችሎታው ሲጽፍ ግጥም

ሰዓሊ ነው የረቀቀ

ባገር ዙሪያ የታወቀ

ደራሲ ነው ስመጥሩ

የገነነ በብዕሩ

ዝነኛ ነው ባለቅኔ

አትበሉኝ ይቅር ለኔ

ከጥበቡ በስተጀርባ

ተደብቆ እያደባ

ህዝብ ሳያውቅ ሰው ሳይሰማ

የሚጠብሰው እንደሳማ

አለው እጅግ ክፉ ጠላት

ለጥበብ ሰው እዘኑለት


ሚያዚያ 7 ቀን 2000 ዓ.ም.

15 April 2008

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ