ከመኮንን ልጅ

27 ዓመታት ሲታገል የኖረው
ሲታሰር ሲገደል ሲሰደድ የከረመው
በወያኔውም በአሽከሩም ሲታምስ ሲታመስ
ትግሉን አርግዞ ምጡ ላይ ሲደርስ

ከወያኔው ሰፈር ካሽከሮቹ መንደር
ትግሉ ጫፍ መድረሱን እጅግ በመጠርጠር
ከሉሌነት ይልቅ ሰው መሆን የመረጡ
ሲመሽ ተቀላቀልው መሪ ኹነው መጡ

ቆንጆ ቃል ተናግረው ትልቅ ተስፋ ሰጥተው
ደምረው አስደምረው አፍዘው አስፈዝዘው
የወያኔውን ወንበር ለራሳቸው አዙረው
የትግሉን እንጀራ መጀምርያ ቆርሰው
አስጨበጨቡትና ያን መኸረኛ ሕዝብ
"ኢትዮጵያ" አሉትና ዙፋኑ ላይ ጉብ

ወያኔ ያሰረውን እስረኛ ፈቱና
ተሰዶ የሄደውን ኑ አሉትና
ንግግር አሳምረው ተደመሩ ብለው
የኢትዮጵያዊነት ሱስ መሆኑን ሰብከው
የወሬ ጠጅ ቢያጠጡት ቀንና ለሊት
ሰዉ ሰከረና ሁሉንም መርሣት

ወንበር ሳያጋሩ ብቻቸውን ይዘው
አሸጋጋሪዎች ነን ብለው አሳውጀው
የፖለቲካ ኤሊቱን አስቀው አስደስተው
ዲያስፖራውን አፍዘው አሳብደው
ምስኪኑን ሕዝብ ፈጽመው ረስተው
መንግሥት መሰረቱ ለውጥ መጣ ብለው
ሌላ ተረኛ ግዜው የሱ ነው ብለው

ከፋፋይ ዘረኛውን እንዲጋልብ ፈቅደው
ድሀን አስገድለው፣ ድሀን አፈናቅለው
በወሬ ኢትዮጵያ እናትህ ናት እያሉት
ቤቱና ንብረቱን በሌቦች አዘርፉት

ወያኔ አስቸግሯቸው ነው ብለን ስንከራከርላቸው
ሳንቃወማቸው ግዜ ብንሰጣቸው
ስናጨበጭብላቸው ስንደግፋቸው
እየሞቃቸው መጣና እየጣማቸው
በምርጫ ያሸንፉ እየመሰላቸው
አዲስ ንጉሥ ኾነው ዙፋን መያዛቸው

በወሬ ቤት አይቆምም
ቀልድም ሲደገም አይጥምም
የሕዝቡን ትግል ውጤት አትስረቁ
ይልቅ አደብ ግዙና አገር አስታርቁ
ሰላማዊው ሰው ላይ ጦርነት አታውጁ
በሸፈተው ጎጠኛው ላይ ድል ተቀዳጁ

ከጎጠኝነቱ ውጡና የሰበካችኹትን በተግባር አውሉት
በሰላም የሚሞግታችኹን (እስክንድርን) ማስፈራራቱን ተዉት
ሽፍታውን ኃይለኛውን ዘረኛውን ግጠሙት

ምላስ ወሬ ምላስ ብቻ ኾናቸሁ
እግዜሩ ትልቅ ጆሮ ይስጣችሁ
ደግሞም መልካም ጥርስ ያውጣላችሁ

ለምርጫ ሩጫ ከመንደርደራችሁ
እርቅ ቀድሞ ያስፈልጋል ሰላም የሚሰጣችሁ
የመነጋገርን የመቀራረብን ፍቅርን አውጁ
የይቅርታ መድረክ በአገር ምድር አዘጋጁ

የበደለም ይቅርታ ጠይቆ፣ የተበደለም ይቀር ብሎ
በመላ አገራችን መልካም ፍርድ ተጥሎ
ይቅር ተባብለን ያለፈውን ኃጢያት ትተን
መኖር ይሻለናል የወደፊቱን ዜግነትን ኢትዮጵያዊነትን መርጠን
ካልኖርበት የመቶ ዓመት ታሪክ ውስጠ ዲስኩር ወጠተን
በፍቅር ባንድነት አገራችንን አቅንተን
‘ያ መሬት የኔ ነው፣ ያ ያንት ነው' ማለት ትተን
አዲስ ሕገ-መንግሥት ቃልኪዳን አድርገን
ፍትሕና እኩልነት ያለባት አገር መሥርተን
የጎጥ አጥሩን ወሰኑን ኬላውን ሰብረን
ቋንቋ ባሕላችንን የጋራ ጌጥ አድርገን
የሕዝብ ምርጫ ያለው መንግሥትን መሥርተን።

04th April 2019

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!