እኔን ስቀሏት!

“እኔን ስቀሏት!” ወለላዬ ከስዊድን

ወለላዬ ከስዊድን

“እኔ”፣ “የእኔ” ማለትን ውገሯት፣

ጣር ፍዳ ሞቷን አሳዩአት፣

መቀጣጫ አድርጋችሁ ስቀሏት፣

አርቃችሁ ቆፍራችሁ ቅበሯት።

በእኔ መቃብር ላይ “እኛ”

በቅሎ ይገኝ ይሁነን መዳኛ

እኛነት ስትለመልም

ትወልዳለች ሕዝበ ሰላም

አገር ምድሩ ያብባል

በአንድነት አንድ ይሆናል

ፍዳ መዓቱ ይጥፋል

ሞትም በሕይወት ይሞታል

እናም “እኔ” ማለትን እንናቅ

ጉያዋ ስር አንወሸቅ

ከጀርባዋ አንደበቅ

“እኔ” ናት እኛነትን የበላችው

ጠባብነትን የዘራችው

ወንጀል ክፋት ያፈራችው

“እኔ” ናት ሞታችን

“እኔ” ናት ፍዳችን

“እኔ” ናት ጠላታችን

“እኔ” ናት የመከራ ዘራችን

በክፋት በተንኮል በጠብና በቂም

ተተባትበን ተያይዘን በዘር ቆጠራ አዚም

በ“እኔ እበልጥ”፣ “እኔ እበልጥ”

ነጋ ጠባ ስንበጣበጥ

ነገር ከነገር ስናገላብጥ

ወሬ ከወሬ ስናቀያይጥ

የእኛ መናቆር ሳያንሰን

ጠላት ገብቶ እንዳያምሰን

እባካችሁ! “እኔ”፣ “የእኔ” ማለትን ውገሯት

ጣር ፍዳ ሞቷን አሳዩአት

መቀጣጫ አድርጋችሁ ስቀሏት

አርቃችሁ ቆፍራችሁ ቅበሯት

“እኔ” ናት የዘር ካባ ለብሳ

ፊቷን በጎሣ ቅባት አብሳ

በየቀየው ራሷን አንግሣ

እንዲህ የጣለችን አዋርዳ

እንዲህ ያስቆጠረችን ፍዳ

አንድነታችንን እኛነታችንን የዋጠችው

ፍቅራችንን የበላችው

አገር ክልል ያጠረችው

መተሳሰባችንን የሻረችው

“እኔ” ናትና እናዋርዳት

ጥንብ እርኩሷን እናሳያት

ድብቅ ምስጢሯን እናውጣባት

የጥፋት ጦሯን እንንጠቃት

የደም ግብሯን እንንፈጋት

“እኔ” ማለትን ለልጆቻችን አናውርስ

“እኔ”ን በኛነት እናድስ

“እኔ” ካመጣብን ጣጣ

“እኛ” ብለን እንወጣ

“እኔ”፣ “የእኔ” የማለትን ፍዳ

የራስ ማስቀደምን ዕዳ

“እኔ” ከማለት የጉራ ወጉ

ወገብ አቅንቶ ከመውረግረጉ

በእኔነት አጎንብሶ ከማደግደጉ

እንድንድን “እኔ” ማለትን እንጣለው

በእኛነት እንተካው

አዳሜ “እኔ” ብሎ ተንስቶ ነው

ስንቱን ጥፋት ያስከተለው

“እኔ” ብሎ ነው ዓይኑን ጨፍኖ

እኛታችንን ያሳጣው መቅኖ

አሁንም በ“እኔ እበልጥ”፣ “እኔ እበልጥ” ፉክክር

መልኳ እንዳይገረጣ እንዳትወይብ አገር

በለቀቃት ክፉ መንፈስ

በዲያቢሎስ የሞት ምላስ

እንደገና እንዳትላስ

የነፃነት ብርሃናችን እንዳይጋረድ

የአንድነት ርብርባችን እንዳይናድ

የሰላም ጉዞው ደፍርሶ

እንዳይሆንብን መራራ ኮሶ

የመሰባሰቢያችን በር እንዳይዘጋ

ከንቱ እንዳይቀር የከፈልነው የደም ዋጋ

የሚታየን ብሩህ ተስፋ

እንዳይጨልም እንዳይጠፋ

“እኔ”፣ “የእኔ” ማለትን ውገሯት

ጣር ፍዳ ሞቷን አሳዩአት

መቀጣጫ አድርጋችሁ ስቀሏት

አርቃችሁ ቆፍራችሁ ቅበሯት

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ