እሳቱን እናጥፋ (ወለላዬ)
እሳቱን እናጥፋ (Read on PDF)
ከወለላዬ
ተዛምቶ በሃገር እያደረ ሰፋ
ጠብሶ ሳይጨርሰን እሳቱን እናጥፋ
ጠንክሯል እሳቱ በርትቷል ቃጠሎ
ማጥፋት ይገባዋል ስው ሁሉ ሆ ብሎ
ከጨማመርንበት እሳቱ ላይ ቅጠል
ነደን እናልቃለን አንበቃም ለትግል
በወገን ተካፍለን እኛው ስንዋጋ
ወያኔ ተረሳ ህዝቡ ተዘነጋ
ባለቅኔው በፊት ቀድመው ሲናገሩ
ብለውን ነበረ ባንድነት አብሩ
ካልሆነም ጨርሶ ወይ ተሰባበሩ
ስለዚህ ይሄንን ወሬ ቀመስ እሳት
እንዳንበታተን ይገባናል ማጥፋት
አይጎዳም ይጠቅማል ቀርቦ መነጋገር
መለወጥ አለብን ጥላቻን በፍቅር
እሷ/እኮ እሱ እኮ አሁን መባባሉ
ከጉዳት በስተቀር አይጠቅመንም ቃሉ
እንግዲህ ለሃገር ለወገን በማሰብ
ባንድነት ጥላ ስር አለብን መሰብሰብ
ካንዱ ቤት አንዱ ቤት ዘለን እንዶ ጦጣ
ጸቡን አባብሰን ለኳኩሰን አንውጣ
በዚሁ ጉዳይ ላይ ሁሉም ይረባረብ
በመጥፎ ጥላቻ አገር አይለብለብ
ጸቡ ከዚህ በላይ እንዳሄድም ገፍቶ
አንተም ተው አንተም ተው ብሎ ሽምጋይ ገብቶ
በእምነት ደረጃም ወይ ቄሱ ገዝቶ
ከዚህ ከከበደም ታቦት ይዞ ወጥቶ
ሰላም እንዲሰፍን ጸብ ጥላቻ እንዲርቅ
ከጥፋት ያድነን ይገላግለን በእርቅ
አለዛ ወያኔ አርማችንን ገፎ
መውሰዱ ሳያንሰው ከዚህ በላይ አልፎ
መጠቀሚያ አድርጎ የኛን መለያየት
አይቀርም ማምጣቱ መሪዎች ላይ ጥቃት
በነደብሪቱና በጓንጉል በአሽኔ
ባሽብር በግዛው አሳበን በአንቶኔ
ነገር ስናራግብ እኛ ስንፋተግ
ለወያኔ መንግስት ሆኗል የሞቀ ሰርግ
እንዳለፈው እንኳን አብሮ ለመቃወም
ይሄው ተለያይተን እያጣን ነው አቅም
የነአስካለ ወገን የዱባለ ሆኗል
ጥርጥር የለውም ከገሌ ጋር ቆሟል
ብለን ስንፋተግ እኛው ስንናከስ
ላጭቶ ይጎርሰናል አይምረንም መለስ
ያንግዜ በለቅሶ ባዘን ከመታረቅ
አፍጦ እያየነው ሞትን ከመጠበቅ
ያቀጣጠልነውን ይሄን የጸብ እሳት
ለራሳችን ስንል በቶሎ በማጥፋት
ባንድነት እናቁም ነገር በማቀዝቀዝ
ጸቡን እንፍታና እንደፊቱ እንጓዝ
መቼም ውሎ አያድር በኛ ጓዳ ፍቅር
ደግሞ ካስካለ ጋር ዱባለ ሲቃቃር
ወልደየስ ከገብሬ ሲለይ በመናናቅ
እምን ቦታ ይሆን እኛ ምንወሸቅ
ያንግዜ የማነን የጓንጉል የጥዱ
አቅጣጫ ሲቀይር ሲበተን ሴት ወንዱ
ማንን ይሆን ያኔ ከበን ምናዋልድ
መቼም የኛ ነገር የምንሆነው አይገድ
ስለዚህ ከመጪው አስችጋሪ ጉዳይ
መዳን እንድንችል በመሆን አንድ ላይ
ይሄንን ነበልባል ወሬ ጨመር እሳት
ከመካከላችን ይገባናል ማጥፋት