የኛ ሰው ሊቁ ... (ወለላዬ)
የኛ ሰው ሊቁ ... (Read on PDF)
ከወለላዬ
የኛ ሰው ሊቁ ...
አባ እረቂቁ ...
አጣሞ ማየት ነገር መጠርጠር
ትልቅ ዕውቀት ነው ብሎ በመቁጠር
የነገርከውን ያፍህን ትቶ
ያጣምመዋል ሌላ ደርቶ
ያላወቀውን ከሰው መረዳት
እንብየው ብሏል ሆኖበት ውርደት
ቢአጠፋም እንኳን የይቅርታ ቃል
ካፉ ላይወጣ በልቡ ምሏል
እንደው በከንቱ ሰው በመጠርጠር
መላ የሌለው ይፈጥራል ሽብር
ይችልበታል የጠላ መምሰል
የምትለውን ካንተ ሊሰልል
ነገሩን ወዶ እሱ ሲፈራ
አንተን ይልካል እንደሙከራ
የኛ ሰው ሊቁ ...
አባ እረቂቁ ...
ገራገር መስሎ ጨዋ ሳቂታ
የልቡን ሰርቶ ይገባል ማታ
አጥፊ እንዳይባል ሰው እንዳይጠላው
ሰበብ አሳቦ ሁሌ ጋባዥ ነው
ባማረ ልባስ አካሉን ከቶ
ጨዋ በመምሰል ያድራል ቀምቶ
የዋህ ነህ ብሎ ግምት ከሰጠህ
ያመሻል ቀኑን ወሬ ሲአቅምህ
የሚሰራውን ውስጡ ሸጉጦ
ላለማስቀየም ቃላት አጣፍጦ
ፊት ለፊት ባፉ ቂቤ እየቀባ
ይሰካብሃል ጩቤ በጀርባ
ላገር ለህዝቡ ሳይኖረው ደንታ
በደሉ ብሎ ይሆናል ዱታ
በአቋራጭ ገብቶ ስልጣን ሊጨብጥ
ሲጋብዝ ያድራል ያለውን ሲሰጥ
ይሄ ሞሽላቃ ብሎ እያማልህ
እጁን ይሰዳል አንተን ሊሰርቅህ
የኛ ሰው ሊቁ ...
አባ እረቂቁ ...
ሚስት ሊአገባ ሲአስብ ወደፊት
ቀድሞ ይይዛል የነገር አባት
ቀኑ ሲከፋ ሞቱ ሲቃረብ
ጠላቴ እሚለው መኖሩን ሲአስብ
መቼ ሊተወው እንዲህ በቀላል
ለልጁ አውርሶ ቂሙን ይተዋል
ይወዳል ተረት ምሳሌ መጥቀስ
አልክ እንዳይባል እንዳይወቀስ
ትሰማዋለህ በሁሉ ሲያዝን
ጎዳኝ እያለ ይሄ ሰው ማመን
አርቆ አሳቢ ስለሆነ ሊቅ
ያስገርምሃል ላገር ሲጨነቅ
በዛሬ ጊዜ እግርን መሰብሰብ
ይጠቅማል ይላል ለመራቅ ሲያስብ
እንዴት ይቻላል እሱን ለመምከር
ሁሉን አዋቂ ለራሱ ምሁር
ማየት አይሻም የደሃን እንባ
እያስለቀሰ እሱ በጀርባ
ጎርጊስን ካልኩኝ ባባቴ ከማልኩ
ፍንክች የለችም አለቀ ጨረስኩ
ብሎ ይልሃል አንዳንዴ ደግሞ
ሲአጠፋፋብህ ነገሩን ቀድሞ
የኛ ሰው ሊቁ ...
አባ እረቂቁ ...
በፌዝ ፈገግታ በውሸት ሳቁ
ሸፋፍኖ ይዞ እራሱን ሳይገልጥ
እመሃል ሆኖ ይኖራል ሲአለምጥ
ወሬ ከሰማ ጆሮውን ጥሎ
የራሱን ከቶ ትንሽ አክሎ
ላቀደው ነገር አርጎ እንዲስማማ
ያዘጋጃታል ፈጥሮ ቅመማ
መስሎ እየታየው ሁሉ ሰው ደደብ
ይታዘበኛል ብሎ ሳያስብ
እሱው ያለውን እራሱ ፈጥሮ
በወሬ ብዛት በሌላ ሽሮ
አንዱን ካንዱ ጋር አደበላልቆ
አወታትቦብህ ይሄዳል ስቆ
የኛ ሰው ሊቁ ...
አባ እረቂቁ ...
ነገር አዋቂው ሊቀ ጠበብቱ
ባገሩ ጉዳይ ባለው በወቅቱ
የረቀቀ ነው በፖለቲካ
የትም አይገኝ እሱን ሚተካ
አስር በማውራት በመዘላበድ
የተቃውሞውን ይዘጋል መንገድ
ሌላው አዋቂ ሥልጣን ጨብጦ
እላይ ከወጣ ደረጃ እረግጦ
ዘላለም ገዢ ሆኖ ሊጣበቅ
መሃላ አለበት ላይነቃነቅ
በሥልጣኑ ላይ ሥልጣን ደራርቦ
የሀገር ሀብትን በእጁ ሰብስቦ
እየገደለ አስሮ ጠፍሮ
እንደሚታየው ይኖራል ከብሮ
የገንዘብ ፍቅሩ የሥልጣኑ ጥም
ይዘልቃል ይዞት እስከራሱ ደም
ይሄን ይመስላል የኛ ሰው ሊቁ
ዘመን ያፈራው አባ እረቂቁ
ጥር 21 ቀን 2000 ዓ.ም. - ስዊድን
(January 30, 2008) – Sweden