ስደት ተወኝ

ከወለላዬ

(Read on PDF)  

ተገላገኩ እሰይ ቀናኝ

ካገር አገር ያዟዟረኝ

ያከሰለ ያጠቆረኝ

አበሳዬን ያስቆጠረኝ

ለብዙ ዓመት ያስጨነቀኝ

እፎይ አረፍኩ ስደት ተወኝ

 

የታባቱ ይሄ አሲዳም

መጦ መጦ ሲአጣብኝ ደም

አለ ዕድሜዬ አሸምግሎ

ክስት አርጎ አሰልስሎ

እጅና እግሬን አቆላልፎ

ሰጠኝ ለሞት አሳልፎ

 

መልኬ ጠፋ ወዜን አጣሁ

ድክም አለኝ አንቀላፋሁ

ሸመቀቀኝ ቀጥ አለ እግሬ

ተወጥሮ ቀረ ስሬ

አቅም አጣሁ ለመላወስ

ተጣበቀ ጉንጨ እርስ በእርስ

አላይ አለኝ ዓይኔ ፈዞ

ድፍን አለ አይናር ይዞ

አዬ ስጋ ይሄ ባዳ

ገሸሽ አለ እንደ እንግዳ

እፊቴ አመድ የተነፋ

መስሎ ታዬ ወዜ ጠፋ

ጥርሴ አለቀ ፀጉሬ ነጣ

ተናነቀኝ ሞቴ መጣ

ይሄን አይቶ አቶ ስደት

ትቶኝ ጠፋ ከባዶ ቤት

 

የታባቱ ይሄ አሲዳም

መጦ መጦ ሲአጣብኝ ደም

እጅና እግሬን አቆላልፎ

ሰጠኝ ለሞት አሳልፎ

ፈጣሪ ሆይ ተቀበለኝ

በጥፋቴ ይቅር በለኝ

ስደተኛ አላገሩ

ላይኮነን በምግባሩ

ባላነብም ይኖራል ቃል

እንዳትከተኝ እኔን ሲኦል

ይቅር በለኝ በድፍረቴ

ስምክን አሁን በመጥራቴ

በጭንቅ አይደል የምንወድህ

መች አጣኸው ታውቀዋለህ

ለነገሩ እኔም በቃኝ

አልልህም ሞት ይራቀኝ

ከስደት ጭንቅ ከዓለም ማጥ

ይሻለኛል ልሂድ ላምልጥ

 

እናቴ ሆይ ይሄን ሰምተሽ

አደራሽን እንዳታለቅሽ

ደስ ይበልሽ እሰይ አረፍኩ

ስደት ተወኝ ተገላገልኩ

ይልቅ ትንሽ እየቆጨኝ

ልብ ልቤን እየበላኝ

አሁን ድረስ ያለቀቀኝ

ያራራቀን እኔና አንችን

ያለያየን ከቤታችን

ሄዶ ጠፍቶ ተወግዶ

ባገራችን ሰላም ወርዶ

እንደዱሮው እንደጥንቱ

ሳንበላ ከሌማቱ

ሳንተያይ ሳንገናኝ

ሳልደግፍሽ ሳትመርቂኝ

መቅረታችን አስጨንቆኝ

እኖር ነበር ተገላገልኩ

ከናፍቆትሽ እሰይ አረፍኩ

እፎይ አልኩኝ እሰይ እኔ

እናት ሆይ ይስጥሽ መጥኔ

አንችም የኔ እኔ እምልሽ

ባትለምጅኝም የለመድኩሽ

ባታውቂኝም እኔ እማውቅሽ

ቃልኪዳኔ ይቅለልልሽ

አንተ ከፊት ወይ ከኋላ

ተከትለህ እንደጥላ

ያለቀከኝ ስደተኛ

መሆንህ ነው በል ተረኛ

እንካ ትግሌን ከኔ ውሰድ

ማስረከቤ ሆኗል የግድ

እኔማ እሰይ ተገላገልኩ

እሩጫዬን በቃኝ ጨረስኩ

 

ካገር አገር ያዟዟረኝ

ያጠቆረ ያከሰለኝ

አበሳዬን ያስቆጠረኝ

ለብዙ ዓመት ያስጨነቀኝ

እፎይ አረፍኩ ስደት ተወኝ

እፎይ አረፍኩ ስደት ተወኝ

 

የካቲት 27 ቀን 2000 ዓ.ም. - ስዊድን

March 7,2008 - Sweden

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ