ሕገወጥ ዘይት መያዙ ብቻ ሳይሆን የተያዘውን ዘይት በሕገወጥ መንገድ እንዲሠራጭ ማድረጉም ሌላ ሕገወጥነት ነው

ሕገወጥ ዘይት መያዙ ብቻ ሳይሆን የተያዘውን ዘይት በሕገወጥ መንገድ እንዲሠራጭ ማድረጉም ሌላ ሕገወጥነት ነው

የዘይቱ መዘዝ ገና ብዙ ነገር ያሳየናል

ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - አገርን እንደ አገር ለማስቀጠልና የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ ለማስረከብ እጅግ በርካታ ሥራዎች ከፊታችን ይጠብቁናል። እድገትን ቀጣይ ለማድረግና ለዜጐች ምቹ የኾነች አገር ለመፍጠር ከሚያስፈልጉ ወሳኝ ጉዳዮች መካከል ለሕግ መገዛት፣ በሕግ አግባብ መጓዝና አድሎ የሌለው የፍትሕ ሥርዓትን ማስፈን ቁልፍ ጉዳዮ ናቸው።

ሕግ ማስከበር፣ ለሕግ መገዛት ያለ አድሎ መዳኘት፣ ፍትሕ እንዳይጓደል መሟገትና በአጠቃላይ ከፍትሕ ሥርዓቱ ጋር የተሳሰሩ ማንኛቸውም ተግባራት በአግባቡና በሥርዓቱ መፈጸም፤ የተወሳሰቡ ችግሮቻችንን ለመፍታት ጭምር የሚያግዝ ነው። ለዴሞክራሲ ሥርዓት መጐልበት ለዜጐች የሰብአዊ መብት መከበርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በትክክል ለመተግበር አሁንም የፍትሕ ሥርዓቱ ጉልህ ድርሻ አለው።

ከኢኮኖሚ አንጻርም ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዲኖር፤ በአግባቡ ነግዶ በማትረፍ ተገቢውን ግብር ከፍሎ ራስንም አገርንም ለመጥቀም ከተፈለገ አሁንም ሕግ መከበር ይኖርበታል።

አሁን ላይ ሕግን ከማክበርና ከማስከበር አንጻር ግን የምናያቸው የበዙ ችግሮች፤ ውንብድናና ሌብነት እየሰፉ መሔዳቸውን አመላካች ናቸው።

በቡድንና በግለሰብ ደረጃ የሚፈጸሙ ፀያፍ ተግባራት፤ አገርን እያራቆቱ፤ ጥቂቶችን እያበለፀገ ስለመኾኑ በግልጽ እያየን ነው።

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምንሰማቸው የሌብነት ዐይነቶች መብዛት፤ ሕግን ከማክበርና ካለማስከበር ጋር የተያያዙ ናቸው ማለት ይቻላል። የሌብነት ዐይነቱና ብዛቱም እየሰፋ ለመምጣቱ ብዙ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል። የመሬት ወረራና ዘርፋ፣ አንድን ቡድን ለመጥቀም ሲባል በጨረታዎች ላይ የሚፈጸም አሻጥር፣ ሥልጣንን መከታ በማድረግ የሚፈጸም ምዝበራ፣ … እያልን ብዙ ሕገወጥነትን የሚገልጹ ተግባራትን መዘርዘር ይቻላል።

ኮንዶሚንየም ተሰረቀ፣ ያለአግባብ ለሌላ ተላለፈ የሚሉት ወሬዎችን ጆሯችን ለመዳቸው እንጂ፤ የከፋ ውንብድናና ሕገወጥ ተግባራት ናቸው። ችግሩ ግን ለጆሮ የሚከብዱ የሌብነት ተግባራትን እግር በእግር ተከታትሎ በተገቢው መንገድ ሕግን ማስከበር አለመቻሉ የዚህችን አገር ፈተና አብሶታል።

ሕግን ለማስከበር አዳጋች ከሚኾንባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፤ ሕዝብ እንዲያገለግሉ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያሉ ተሿሚዎች ያለአግባብ ለመበልጸግ ከሚሹ ግለሰቦች ጋር መመሳጠር ነው። መመሳጠር ብቻ ሳይኾን ለሌብነቱ ተባባሪ ኾነው የአገርን ሕመም ማባሳቸው ነው።

ሥልጣናቸውን ተጠቅመው የሕግ የበላይነትን ለመቆልመም ይሉኝታ የሌላቸው ኾኖ መገኘትና ለሕገወጦች በሚሰጡት ከለላ ምክንያት፤ አገር ስትዘረፍ፣ ሕዝብ ሲመዘበር፣ ተገልጋይ ሲጉላላ፣ ኢኮኖሚው ሲመታ ይታያል። በአጠቃላይ ሕገወጥ አሠራሮች ሌብነትን አስፋፍተዋል። የችግሩ ስፋት፤ በበጐ ሊሠራ የሚነሳሳውን ሁሉ እየኮረኮመ፣ በሕግ አግባብ ከመሥራት ይልቅ፤ በመሞዳሞድ መክበርን ሕጋዊ እንዲመስል እያደረገው ጭምር ነው። የአደጋው ስፋት ሔዶ ሔዶ አገር እስከማፍረስ ሊደርስ ይችላል። ስለዚህ ሕግ በመንግሥትም፤ በዜጐችም ዘንድ መከበር አለበት።

በተለይ በገበያ ሥርዓት ውስጥ የሚፈጸም አሻጥር እየሰፋ መምጣት አደገኛ የሚኾነው፤ የዜጐች በአቅም ሸምቶ የመኖር መብትን የሚጋፋ በመኾኑና ቀጥሎም ሕዝብ ጥያቄ እንዲያነሳ የሚያስችል በመኾኑ ጭምር ነው። ከሰሞኑ ወደ ሁለት ሚሊዮን ጄሪካን (አንዳንዴም ሁለት ሚሊዮን ሌትር የተባለው) በሕገወጥ መንገድ የተከማቸ የምግብ ዘይት ጉዳይ፤ በአገራችን ያለውን ፍጹም ውንብድና የተሞላበትን የገበያ ሥርዓት የሚያመለክት ብቻ ሳይኾን፤ ሕግና ሕጋዊነት የተፈተኑበት ነው።

ጉዳዩ በሕገወጥነት ድርጊት ብቻ የሚገለጽ አይደለም። በመንግሥት ተደጉሞ ከሌለ የውጭ ምንዛሪ ላይ ተቀንሶ የተገዛ የምግብ ዘይት፤ እንደዋዛ በአንድ የግለሰብ መጋዘን ውስጥ ሁለት ሚሊዮን ሌትር/ጄሪካን ዘይት ተሸሽጐ ተገኘ በሚል የሞቀ ወሬ የሚታለፍ አይደለም። እንደ አገር አስደንጋጭ ዜና ነው።

ይህንን ያህል መጠን ያለው ዘይት እንደ ቀላል ከውጭ ወደ አገር፤ ከዚያም ወደ መጋዘን ገብቶ ሲደበቅ ሕግ አስከባሪዎች የት ነበሩ? ሌላው ቢቀር ዘይቱ በድጎማ እንዲገባ የውጭ ምንዛሪ እንዲፈቀድለትና ለሕብረተሰቡ እንዲዳረስ ኃላፊነት የወሰደው የመንግሥት አካል በጭንቅ እንዲገባ ያደረገው ዘይት፤ “የት ደርሰ?” ብሎ አለመጠየቁም፤ ጉዳዩን ማወሳሰቡ አይቀርም። ባለሥልጣን ከሌለበት እንዲህ ያለ ትልቅ ውንብድና አይፈጸምም የምንለው ለዚህ ነው።

ከተማው በዘይት እጥረትና ዋጋ ንረት ሲታመስ፤ ይህንን ዘይት የሸሸጉ አካላት ጸጥ ብለው መቀመጣቸው በራሱ የዚህን ሕገወጥ ተግባር በጭካኔ የተሞላ ጭምር መኾኑን ያሳያል።

እንዲህ ዐይነቱ ድርጊት በስግብግብ “ነጋዴዎች” ብቻ የተፈጸመ ነው ተብሎ አይታመንምና ድርጊቱ በተዋረድ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጡ ተሿሚዎችን ይሁንታ ያገኘ ጭምር በመኾኑ እነዚህን ስግብግብ ሕግ ፊት ማቅረብ ለነገ የሚባል መኾን የለበትም።

የሁለት ሚሊዮን ጄሪካኑ/ሌትሩ ዘይት ጉዳይ ሌላም ጥያቄ የሚያስነሳ ስለመኾኑ ልብ ሊባል ይገባል። ይህም ዘይቱ ተገኘ እንደተባለ፤ “ማን ሸሸገው?” የሚለውን ጥያቄ ወዲያው ለመመለስ ያለመፈለጉ ነው። የመጋዘኑ ባለቤት ከታወቀና መጋዘኑን ለዚህ ዓላማ ያዋለውን ሰው ለመለየት ይህንን ያህል የሚከብድ አይኾንም። መጋዘኑ ጥበቃ ያለው መኾኑንም መርሳት የለብንም። ስለዚህ ይህንን በአገርና በሕዝብ ላይ የተሠራው ሸፍጥ የፈጸመ አካል ማንነቱን በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። ነገር ግን አሁን ላይ ይህንን ብርቱ ጉዳይ ገሃድ ለማውጣት የተፈለገ አይመስልም። ይህንን አለመግለጽ ደግሞ ሌላው ሕገወጥነት ተግባር ነው። ወንጀል ነው ከተባለ የወንጀሉን ፈጻሚ ለሕግ ማቅረብ የግድ ነው። ይህ አደባባይ የወጣ ውንብድና እንዲሁ ተደፋፍኖ ከታለፈ፤ ፍትሕ አደጋ ላይ መኾኗን በደንብ የምንረዳበት ትልቅ መረጃ ይኾናል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሕግን ያለማክበርና ያለማስከበሩ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሌላው አስደንጋጭ ሁኔታ ደግሞ፤ ተሸሽጐ የተገኘውን ዘይት በማግሥቱ “በአስተዳደሩ ውሳኔ ለሸማቾች መከፋፈል ጀመረ” መባሉ ነው።

የተፈጸሙው ሕገወጥ ድርጊት ሳያንስ፤ እንደገና አስተዳደሩ ዘይቱን በአንድ ቀን ልዩነት ማሠራጨት የጀመረው በምን ሒሳብ ነው?

በግምት የተሰላውን የታሸገ ዘይት በየትኛው የሕግ አግባብ ነው እንዲሠራጭ ያደረገው? ብቻ ሳይኾን፤ የትኛውን ሕጋዊ መሠረት ተከትሎ ነው፤ በሕገወጥ መንገድ የተከማቸውን ዘይት የሚቸበችበው? “ካለው ችግር አንጻር ዘይቱን ለሕብረተሰቡ ሊያደርስ ሆዱ ባብቶ ወይም ሽቶ ነው” ከተባለ፤ የዘይቱ ሽያጭ በየትኛው አካውንት፤ ለማን የሚገባ ነው?

የሽያጩ ገቢ፣ ወጪ እንዴት ተሰልቶ ነው ይሠራጭ የተባለው? ዘይቱ ምን ያህል ጊዜው ነው በመጋዘኑ ከተከማቸ? የመጠቀሚያ ጊዜውስ መቼ ነው የሚያልፈው ወይም ያለፈው? የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈ ወይንም እጅግ በጣም በቅርቡ የሚያልፍ ከኾነ፤ እንዴት ለሕዝብ እንዲደርስ ሽያጭ ላይ ይቀርባል? እነዚህንና የመሳሰሉ ከሕግ፣ ከሕዝብና ከአገር ጥቅም ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ ነው ዘይቱ እንዲሠራጭ የተደረገው።

ስለዚህ ሕገወጥ ዘይት መያዙ ብቻ ሳይሆን የተያዘውን ዘይት በሕገወጥ መንገድ እንዲሠራጭ ማድረጉም ሌላ ሕገወጥነት ነው። ይህም ሕገወጥ ተግባርን በሕገወጥ መንገድ ለማከም መሞከር ተደርጐ ይቆጠራል። ስለዚህ የተሸሸገውን ዘይት ማን እንዳስቀመጠ ታውቆ በሕግ ይጠየቅ። አስተዳደሩ በሕገወጥ መንገድ የተገኘውን ዘይት በምን አግባብ እንዳከፋፈለ ያሳውቅ። ከዚህ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለማን በየትኛው አግባብ ገቢ እንደተደረገም መገለጽ አለበትና፤ የዚህ ዘይት መዘዝ ብዙ ነገር ያሳየናል።

ኢትዮጵያ ዛሬ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!