ከበደ ኃይሌ

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ኢትዮጵያውያን ወላጆች በአሁኑ ጊዜ ኢኮኖሚና ቴክኖሎጂ ባሳደረባቸው ተጸዕኖ ልጆቻቸውን እንደባህላቸው ተቆጣጥሮ ለማሳደግና በኢትዮጵያዊነት ሊያስጠራ የሚያስችል ባህላቸውን ለማውረስ ባለመቻላቸው ልጆቻቸውን እንደባዕድ ሲያዩ እየታዘብን እናልፋለን እንጂ የወላጅነት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ያልቻሉበት ምክንያት ምን እንደሆነ የሚረዱላቸው በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ወጣት ልጆች የሚያሳድጉ ብቻ ናቸው ለማለት ያስደፍራል።

 

በአገር ውጭ የሚኖሩ የትውልደ- እትዮጵያውን ልጆቹ የወላጆቻቸውን ቋንቋ የማይናገሩበት ወይም ስለባህላቸው ብዙም የማያውቁት በውጭ አገር ስለተወልዱ ወይም በሕጻንነታቸው ከአገር ወጥተው ስላደጉ ነው።ስለሥነ-ምግባራቸው መጉደል ደግሞ ወላጆቻቸው ስለማይቀጧቸው/ስለማይቆጣጠሯቸው ነው በሚል የአዝማሚያ መልስ ሰጥተን እንደመድማለን።በመሠረቱ ልጆቻቸው በጥሩ ምግባር አድገውላቸው ወላጆቻቸውንና ህብረተሰቡን በጥሩ ስም እንዲያስጠሩ በግላቸውም ሆነ የማህበራዊ ኑሮ ወደሚካሄድባቸው ስፍራ በመውሰድ ለማስተማር ቢጥሩም ወጣቱ በዘመኑ ቴክኖሎጂና በአካባቢው ተጽዕኖ በሚተላለፉ ባህሪያት አዕምሮው ስለተበረዘ ወደ ሃይማኖት ማምለኪያ ሥፍራዎች መሄዳቸው ቀንሷል። ስለዚህ “ፈሬሃ እግዚአብሄር መሆን የጥበብ መጀመሪያ ነው፤ ወላጅን ማክበር ደግሞ የልጆች መልካም ባህርይ ምልክት ነው” የሚለውን ግብረገባዊ አባባል ዘንግተውት ከወላጆቻቸው/ከአሳዳጊዎቻቸው ይልቅ ለሚገለገሉበት ቱክኖሎጂ ከበሪታ ይሰጣሉ፤እራሰ ወዳድ ሆነው የግል ፍላጎታቸውን ይመለከታሉ።ይህ በመሆኑ ወላጆች ድካማቸው መና ቀርቶ ተሰፋቸው መንምኖ በልጆቻቸው ባህሪ መበላሸት ምክንት የሚጉላሉና የሚበሳጩ ወላጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ አየጨመረ መሄዱን በውጭ አገርና በአገር ቤት የሚታይ የማህበራዊ ችግሮች እየጎሉ መምጣቱን ያሳያል።

 

ይህ ርዕስ ሰፊ በመሆኑ የወላጆችን ኃላፊነ ት ችግር ከእነ መፍትሄያቸው በዚህ ርዕስ አማካይነት ዘርዝሮ ለማስፈር አዳጋች ስለሆነ ኢኮኖሚ፤ፖለቲካ፤ ቴክኖሎጂና ሕግጋቶች በየትኛውም አገር ባለ ሕዝብ የማህበራዊ ኑሮ ዘርፍ ላይ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ስለሆነ ለልጆች አስተዳደግና አያያዝ መልኩን እንዲለውጥ ለማድረግና የወላጆች የኃላፊነት የስራ ድርሻም ወሰን የለሸ ሊያደርገው እንደቻለ በእነዚህ ርዕሶች ላይ ያተኮረ ሃሳብ በአጭሩ እንዳስሳለን።ስለርዕሱ የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት የሚፈልጉ አንባቢያን ካሉ “የኢትዮጵያውያን ልጆች አስተዳደግ ችግር በአሜሪካ” በሚል ርዕስ በ2012 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ታትሞ የወጣውን መጽሐፍ አግኝቶ ማንበቡ ይመከራል።

 

በስደት ዓለም እየኖሩ ልጆች የሚያሳድጉ ወላጆች የልጆቻቸውን ህጋዊና ማህበራዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ኢኮኖሚው ከመውደቁ በፊት አንድ ስራ ሰርተው በሚያገኙት ክፍያ ሙሉ ቤተሰብ ለማስተዳደር በቅቶ በአገር ቤት ያሉትን ተረጂ የቤተሰብ አካል ለመርዳት ይቻል ነበር።አሁን በዓለም ዙሪያ በደረሰው ኢኮኖሚ መቀወስ ሳቢያ የደረሰውን የዋጋ ግሽበት ለመቋቋም በቂ ገንዘብ ለማፍራት ወላጆች ሁለት ስራ ወይም ፈረቃ ደርበው ሰርተውና ደክመው ወደ ቤት ሲመለሱ ልጆቻቸው እቤት በሰላም ወጥተው መግባታቸውን ከማረጋገጥ በስተቀር የሚታያቸው በቂ እረፍት አድርገው ለሚቀጥለው የሥራ ቀን እራሳቸውን ማዘጋጀት ነው። የሥራቸው ፈረቃና የልጆቻቸው ትርፍ ጊዜ ያለመመቻቸት ከልጆቻው ጋር ያላቸውን የግንኙነት ጊዜ ቀንሶት ልጆቻውን በፈለጉት መንገድ ተቆጣጥረው ለማሳደግና የትምህርታቸውን አያያዝ በየዕለቱ ተከታትሎ የሚጠበቅባቸውን ያህል ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ኢኮኖሚው፤ቦታውና ወቅቱ አልፈቀደላቸውም።

 

በዚህ የተነሳ ልጆቹ ከትምህርት ቤት መልስ ብቻቸውን ስለሚሆኑና በቅርብ የሚቆጣጣራቸው ሰው ስለሌለ ከምግባረ ብልሹ የጎረበት ልጆች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፤ ለዕድሜያቸው የማይመጥኑ መጽሔቶችን፤በቴሌቪዥንና በኮምፕይተር የሚተላለፉትን ፕሮግራሞች ይመለከታሉ።ልጆችን በርቀት ለመቆጣጣር የሚያስችል የቴክኖሎጂ መሣሪያ መኖሩን ወላጆች ቢያውቁትም መሣሪያውን ለመግዛት የኢኮኖሚ አቅማቸው ስለማይፈቅድና የአጠቃቀም ችሎታም ስለሚያንሳቸው ልጆች የሚፈልጉትን ፕሮግራም እየተመለከቱ ጸረ-ባህል ባህርይ መልዕክት በመቀሰም ጊዚያቸውን ስለሚያማሳልፉ ለባህሪያቸው መለወጥ ምክንያት ሆኗል።

 

አንዳንድ ወላጀች የሚኖሩበትን አገር ህግጋትና የማህበራዊ ኑሮ ሥርዓቱን ባለማወቅ ባህል-ተኮር የድስፕሊን እርምጃ ወስደው የልጆቻቸውን ባህርይ ለማስተካከል ሲሞክሩ ጎረቤትና ልጆቻቸው እያጋለጧቸው ልጆችን አጎሳቁላችኋል በመባል በህግ የመጠየቅ ደረጃ ላይ ስለደረሱ ልጆቻቸው ህጋዊ ዕድሜ እስከሚሞላቸው ድረስ ወላጆች የተቻላቸውን እያደረጉ የአካባቢ ተጽዕኖውን በመፍራት የተጣለባቸውን የማህበራዊና ህጋዊ ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ከብዷቸው ልጆቹ እንደፈለጉ በመኖርና ወላጆችን በማስቸገር ተግባር ላይ ይገኛሉ።

 

ለልጆች ጠባይ መበከል ወላጆች የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ቢኖር ኢትዮጵያውያን ወላጆች እንደ አገራቸው የት/ቤት አመራር ሥርዓት እየመሰላቸው ልጆቻቸውን አንዴ ት/ቤት ካሰገቡ በኋላ አይከታተሉም፤ ከቋንቋ ማነስ የተነሳ በት/ቤታቸው ውስጥ በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አይሳተፉም፤ ጥሪ ካልደረሳቸው በቀር ከአስተማሪዎቻቸው ጋር ግንኙነት በማድረግ ስለልጆቻቸው አጠቃላይ ጉዳይ በቅርብ ስለማይከታተሉ ነው።

 

መንግስታዊ ድርጅቶች የተለያዩ መመሪያዎችን እያወጡ በህግ ከለላ በቤተሰብ መካከል ጣልቃ እየገቡ የወላጆችንና የልጆችን ግንኙነት የሚያራርቅ ሁኔታን በመፍጠሩ ወላጆች ልጆቻቸውን እንደፈለጉት ሊቆጣጠሩና ሊመሩ እንቅፋት ስለሆነባቸው የቤተሰባዊ ኑሮ ትስስሩን ለማላላት እንደቻለ ጥናቶች ያመለክታሉ።በመሆኑም ህዝባዊ ድርጅቶች በወላጆች ላይ ስለሚያተኩሩና ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ያላቸውን የመቆጣጠር ሙሉ ሥልጣን ስለገደበው ልጆች በወላጆች፤ወላጆች በልጆች ላይ ያለውን ከበሬታና መተማመን ቀንሶት ልጆቻቸው ከውጭ የቀሰሙትን ባህርይ በወላጆች ፊት ካለእፍረት ሲተገብሩት ይታያሉ።

 

በወጣት ልጆች ሥነ-ምግባር መበላሸትና ወላጆችን ሃሳብ ላይ የመውደቁ ጉዳዩ በውጭው ዓለም ተሰድዶ በሚኖረው ወጣት እትዮጵያውያን ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ቸግሩ ዓለም አቀፋዊነት ይዘት ያለው እየሆነ መጥቶ ባህልና ድንበር ሳይገታው ኢትዮጵያም ዘምቶ የወጣቱን ባህርይ ስለበከለው ወላጆችንና መንግሥትን በእጅጉ አፋጧል።

 

ታዲያ በውጭ የሚኖረው ወላጅ ኃላፊነት የተጫነው የሚኖሩበት አገር ህጉና የማህበራዊ ኑሮ ሥርዓቱ ነው ከተባለ በአገር ቤት የሚኖረው ወላጅ የኃላፊነት ድርሻውን ለምን አልተወጣም ወደሚለው ጥያቄ ስነመለስ ደግሞ ካላይ የተጠቀሱት ክስተቶች እንደተጠበቁ ሆኖ፤ በኢትዮጵያ በሚኖረው ህዝብ ላይ ኃላፊነቱ ይበልጥ ሊባባስ ከቻሉበት ምክንያቶች መካከል የኑሮ ውድነት፤የሥራ አጥነት፤የዘመኑ ቴክኖሎጂና ጠባይ በካይ ባህል ወደ አገር ውስጥ ስለሚገቡ የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

 

በመንግስት በጀት የሚተዳደደሩ መ/ቤቶች አትራፊ አልሆኑም በማለት ስለተዘጉ/ ስለተሸጡ በውስጡ ያገለገሉ የነበሩ ሠራተኞችን ካለሥራና ካለክፍያ ስለተባረሩ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደርና ለመቆጣጥር ተስኗቸው ወጣት ልጆች በወላጆቻቸው መቸገር ምክንያት ትምህርታቸውን እያቋረጡ ወላጆቻቸውን ለመርዳት፤እየሰሩ ለመማርና ኑሮውን ለመቋቋም ሲሉ ባገኙት ሥራ ላይ ለመሰማራት ተገድደዋል።

 

አገሪቷ የአፍሪካ አንድነት ጽ/ቤት ዋና መዲና በመሆኗ ብዛት ያላቸው የውጭ ድርጅቶችና የውጭ ዜጋ በአገር ውስጥ ገብተው ስለሚኖሩ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ግንባታ አጋዥ በመሆን ለህዝቡ የስራ ዕድል መፍጠር ሲገባቸው ርካሸ ባህል ከማሰራጨት፤ዕቃ እያስገቡ ነግደው በሚያገኙት የአገር ውስጥ ገንዘብ ተዝናንቶ ከመኖር በቀር የቤት ሠራተኛ ለመቅጠር ፍላጎት ያለው ጥቂቱ የውጭ ዜጋ ነው።

 

የአገሪቱ የኢኮኖሚ የሚመራው በቅይጥ የኢኮኖሚ ሥርዓተ-አመራር ላይ የተቀየሰ ነው ተብሎ መዋዕለ-ነዋ ተስፋፍቷል ይባል እንጂ ባልሃብቶች የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፤የሥራ ዕድል ፈጥረው ሞያና ልምድ ለህዝቡ ማስተላለፍ ሲገባቸው ሸቀጣሸቀጣቸውን ካለገደብ እያስገቡ በገበያ ላይ በማዋል ገበያውን እየተሻሙት ለአገር በቀል ነጋዴዎች እንቅፋት ሆነው ፍክክሩን ሊቋቋሙት ስላልቻሉ ድርጅታቸውን ለመዝጋት ተገድደወዋል። ለውጭ አገር ነጋዴዎች ይህን የንግድ ዕድል የከፈተላቸው በውጭ ዜጎች ላይ በቂ ክትትል ስለማይደረግባቸው፤የአገሪቱ የውጭና የአገር ውስጥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አመራር ፖሊሲ በብሄራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን በፖለቲካ ህልውና ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ነው።

 

በአንጻሩም ወደ አገር ውስጥ ካሰገቡትመዋለ-ነዋይ ጋር ያስገቧቸው ዜጎቻቸው የድርጅቶቻቸው አካል ናቸው በሚል ሽፋን ለራሳቸው ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር መንገድ ከፈቱ እንጂ ለአገሩ ዜጋ ሰራ ፈጣሪ ሆነው አልተገኙም።አልፎ ተርፎም ከአገሬው ሥራ ፈላጊ ሰው ጋር በመሰለፍ በተለያዩ መንግስታዊና የግል ድርጅቶች ውስጥ ገብተው ለመስራት በቅተው የስራ ዕድሉን አጣብበውታል።

 

ወጣቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ቀልቡ በመያዙ ለምዕራቡ አገር የነጻነት አኗኗር ባህርይ ለመጋለጥ ስለበቃ፤ በአገር ውስጥ ለማሰራጨትና ለቅስቀሳ ወጣት ተማሪዎች በቀደኝነት ስለሚጠረጠሩ መንግስት ለሚያካሄደውና ለሚቀይሰው የፖለቲካ አቅጣጫ እንቅፋት እንደሚሆንበትና በወጣቱ በኩል የፖለቲካ ንቅናቄ ቢነሳ ይህን አፍላ ጉልበት ያለውን ህዝብ ተቆጣጥሮ ሊገታ የሚቻለው በወላጆች በኩል ብቻ መሆኑን ሰለተገነዘበ የህዝቡን የኑሮና የማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ከህዝቡጋር በቅርብ እተገናኘ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ልጆቻችሁን ተቆጣጠሩ እያለ ወላጆችን በልዩ ልዩ መንገድ ተጠያቂ ማድረግ፤ ወጣት ልጆቹን ማሳደድና ወላጆችን ማስጨነቅ በሥልጣን ላይ ያሉ የአገር አስተዳዳሪዎች አንዱ ስልታቸው ነው።ወላጆች ከተጠያቂነት ለመራቅ ልጆቻቸው የትና ከማን ጋር እንደሚውሉ፤ ምን እንደሚሰሩና እራሳቸውን ከወንጀል ስራ እንዲቆጠቡ በምክር ለመቆጣጠር ቢጥሩም ትምህርታቸውን እያቃረጡ ባአልባሌ ስራ ላይ በመሳተፍ የሚያፈሩት ገንዘብ ለመጠጥና ለዕጽ ሱሰኝነት ዳርጓቸዋል።

 

ልጆቹ ወላጆቻቸውን ጠልተው ሳይሆን ስለተቸገሩ ገንዘብ አምጡ እያሉ ማስቸገርና የባዕድ አገር ባህል አስተናጋጅ ለመሆን ሰለበቁባቸው፤ በወንጀል ተጠይቀው ከሚታሰሩ፤ በሥራ ፍለጋ ሲጉላሉና ሲበሳጩ ከመመልከት፤የጎረቤት ተወቃሸ እንዳይሆኑና ከቁጭት ለመዳን እያሉ ልጆቻውን ከከአገር ወጥተው እድላቸውን ይሞክሩ በማለት በህጋዊና ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከአገር እንዲወጡ ማመቻቸት የወላጆች ዋንኛ አማራጭ መንገድ አድርገው ይዘውታል።

 

በውጭና በአገር ቤት የሚኖረው ወላጅ በልጆች አያያዝ በጊዜው ኢኮኖሚ፤በወስጥ እስተዳደርና በቴክኖሎጂ ሳቢያ የገጠማቸው ችግሮች በአጭሩ ይህንን ይመስላል።ይሁንና የልጆች ግብረገብ ሲጓደል በተግሳጽና በቅጣት ምግባራቸውን ለማስተካከል ጥረት ይደረጋል። የአገር ኢኮኖሚ፤ የፖሊቲካ አመራር አቅጣጫና የማህበራዊ ችግሮች ሲደፈርሱ ግን በህዝብና በመንግሰት ትብብር ካልተስተካከለ በቀር ለወላጆች ጭንቀት ለአገር አስተዳዳሪዎች ደግሞ ከሰላም የራቀ አመራር ይሆንባቸዋል።አገሪቷ በኢኮኖሚ እራሷን ችላ እስከምትተዳድር ድረስ የባለሃብቶች ባህል አስተናጋጅ ከመሆን አትላቀቅም።የወጣቶች ባህርይ ችግር ከላይ የተጠቀሱት ምክንቶች የጥምር ኃይል አስተዋጽኦ ስለሆነ መልኩን እየለዋወጠ የሚስፋፋ እንጂ በአሁኑ ጊዜ ወጣቱ የሚከተለውን አጓጉል ባህርይ ለመለወጥና የወላጆችን ጭንቀት ለማቅለል ቀላል መስሎ አይታይም።

----------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የጽሁፍ አቅራቢ ነፃ ጸሀፊና በውጭው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውንን የሚመለለከቱ መጽህፍቶችን አሳትሟል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ