ትግሉን ለህዝባዊ ድል ለማብቃት …
ፊልጶስ
አሁን ያለው ህዝባዊ አመጽ በመላው ሀገሪቱ ለመቀጣጥጠል የበቃው የብዙ ወገኖቻችን ሕይወት ቀጥፎ፣ ለእስር፣ ለስደትና ለምድራዊ ስቃይ ዳርጎ ነው።
የ'ስካሁኑ ትግል ለድል ያለበቃው፤ ወያኔ የፈነጨውና ሀገራችንን እስከማፈራረስ ደረጃ የተቃረበበት ዋና ምክንያት፤ ተደራጅተን የጋራ ኃይል ያለመያዛችንና የወያኔን ማንነት ያለመረዳታችን ነው። ወያኔን መነሻውን፣ አሁን ያለበትንና የአጭር ግዜና የረጅም ግዜ መረኀ ግብሩ ካላወቅነው፤ እንዳለፈው የትግል ዓመታት ሁሉ ዛሬም ርስ በርስ መጠላለፍ ...
ተበደልኩኝ ባዩ፣ ሎሌ - አዳሪው በዝቶ
የችግራችንም፣ ውል - ማሰሪያው ጠፍቶ፤
የሄደው - ሲመጣ፣ የመጣው - ሲሄድ
መውጫና መውረጃው፣ ሆኖ የሀገር መንገድ፤
ብዘራው አይበቅል፣ ቢበቅል አያፈራ
መጠላለፍ ሆኖ፣ ቀረ የ'ኛ ሥራ። …
አሁንም ከዳር እስከዳር የተቀጣጠለውን የህዝብ አመጽ ካልተደራጀንና ካላደራጀነው፤ ካልመራነው፣ ካላቀነባበርነው፤ ሀገራዊ ዓላማ ይዘን በአንድነት እስካልታገልን ድረስ ውጤቱን መገመት አያዳግትም። በርግጥ ከጎንደሮች ህዝባዊ አመጽ ብዙ የምንማረው አለ። ስለዚህም፤
- ማንም ኢትዮጵያዊ ማወቅ ያለበት ነገር ወያኔ የመጨረሻ ግብ ኢትዮጵያ የተባለች ሀገር በማፈራረስና ኢትዮጵያዊ የሚባል ዜጋ በማጥፋት ‘ርስ በርሳችን ተባልተን እንድንተላለቅ ነው። ለዚህ ዓላማቸው ደግሞ ማንኛውንም ሰይጣናዊ ምግባር ሁሉ በዚች ሀገርና ህዝብ ላይ ይፈጽማሉ፤ እየፈጸሙም ነው። እናም 'ርስ በርስ አባልቶና በልቶ ሀገር ሳያሳጣን ... እንተባበር! ... እንደርጅ!
- ወያኔ እንጂ ኢህአዲግ የሚባል ነገር ባለመኖሩ፤ ”የወያኔን” ስም ብቻ በማንኛውም ቦታና ጊዜ መጠቀም።
- ወያኔ ገዥ እንጅ መንግሥት ስላልሆነ መጠቀም ያለብን የኢትዮጵያ መንግሥት በማለት ሳይሆን የወያኔ ገዥዎች፤ ወያኔዎች በማንኛውም መስፈርት የኢትዮጵያን ህዝብ አይደለም፤ ታገልንለት ያሉትን ቀበሌ አይወክሉም።
- ወያኔ የሚጠቀምበትን የጎሣ (የክልል) አጠራራ አለመጠቀም፤ ምክንያቱም ዛሬም ሆነ ነገ የምንተላለቅበትንና ተያይዘን ገደል የምንገባበት የወያኔ ወጥመድ ብቻ ሳይሆን፤ ትግሉ አድነት እንዳይኖረው በአካባቢው እንዲወሰን ከማደረጉም በላይ ለወያኔ እየነጣጠለ ለመምታት ያመቸዋል።
- በየቦታው የተነሳው አመጽ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚመለከት በመሆኑ፤ ትግሉ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል መሆኑን እንቀበል። በማኅበራዊ መገናኛዎችም የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል እያልን እንጠቀም።
- የተነሳውን ህዝባዊ አልገዛም ባይነት የተለያየ ዓላማ እንዳለው አደርገን ማቅረባችንና የመንደር ወይም የጎጥ ስም በመስጠት ለወያኔ ሥራ መተባበራችንን አቁመን፤ ትግሉ የሁሉሙ ፍትህ ፈላጌ በመሆኑ ኢትዮጵያዊ ስምና አንድምታ እንስጠው።
- ህዝባዊ አመጽ ለማካሄድ ማሳወቅ እንጂ፤ ወያኔ እንዲፈቅድልን መጠበቅ የለብንም። ፈቃድ መጠየቁን የወያኔ ተቃዋሚ ነን ለሚሉ እንተወው።
- የአንድ አካባቢ ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ሲጠራ፤ የትብብር ጥሪው ወያኔ ላሰመረው ክልልና መንደር መወሰኑ ቀርቶ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ይሁን።
- የወያኔ ተቃዋሚ ነን የሚሉት በዚህ ወሳኝ ሰዓት፤ የህዝብ ደም እንደጎርፍ እየፈሰሰ፤ አንዳንዶቹ እንደሰጎን ራሳቸውን አሸዋ ውስጥ ለመደበቅ እየሞከሩ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ባህርማዶ ጉብኝት ላይ ናቸው። ሁለትም፤ ሦስትም ... በመሆን እራሳችንን በራሳችን እናደራጅ እንጂ ከነሱ ምንም አንጠብቅ።
- ከወያኔ ባልተናነስ “ተቃዋሚዎች” ትግሉን ስለሚያደናቅፉና በወያኔ ሆድ አደሮች የተሞሉ በመሆኑ፤ በምንም መንገድ ከነሱ ጋር ግንኙነት ማደረግ ወይም ራስን ከማሳወቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
- የተደራጀን ግለሰቦች በተቻለንና ጥናቃቄ በተሞላበት መንገድ በሀገሪቱ ውስጥ ከመሀል እስከዳር፤ ከዳር እስከመሀል ካሉ የትግል አጋሮች ጋር መረብ መዘርጋትና ትግሉን ማቀናጀት። በተለይም አዲሳባ ውስጥ ህዝባዊ አመጽ ማቀጣጠል ወሳኝነት አለውና በመደራጅት የተበታተነውን ህዝባዊ አመጽ ማዕከላዊነት እንዲኖረው ማድረግ ይጠበቅብናል።
- ጥላቻን ማስወገድ! … በማንኛውም መስፈርት ቢሆን ከጥላቻ የሚሰበሰብ መከር ጥላቻ ነው። ወያኔያዊነት ነው። አካባቢን ወይም አመለካከተን መሰረት ያደረገ ጥላቻን በየትም ቦታና ሰዓት ቢሆን ማስወገድ። ትግላችን ወያኔ ተወልዶ ያደገበትንና የሀገራችን ህልውና አደጋ ላይ የጣለበትን ጥላቻንና ጎጠኝነትን መታገል ነውና።
- ህዝባዊ አመጽ በምናደርግበት ወቅት በተቻል መጠን በሰው ሕይወት ላይም ሆነ በህዝብ ንብራት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ስሜታችን መቆጣጠርና ርስ-በርሳችን መጠባበቅ ይጠበቅብናል።
- በህዛባዊ አመጽ ወቅት የሚጎዱ ወጎኖቻችን ለመርዳት የሕክምና ባለሙያዎች የሕክምና መሣሪያዎችንና አስፈላጊ መድኃኒቶችን ይዘው እንዲገኙ ማድረግ።
- የገዥው ወታደሮች የሚፈጸመው ግፍ በወገናቸው ላይ መሆኑን ተረድተው በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከመተኮስና ደም ከማፍሰስ እንዲታቀቡ እና ህዝባዊ አመጹን እንዲቀላቀሉ ያልያም ገለለተኛ በመሆን የወያኔን ውድቀት እንዲያፋጥኑ በተለያየ መንገድ ጥሪ ማድረግና የውስጥ ሥራ መሥራት።
- ከዚህ በፊትም ሆነ ወደፊት ከወያኔ ጋር ሲታገሉ መሰዋዕትነት ለከፈሉና በእስር ለሚገኙ ቤተሰቦች የተቻለውን እርዳታና ትብብር የሚደረግበትን መንገድ መፈለግ።
- ህዝባዊ አመጹ እስከ አፍንጫው ከታጠቀ እንደ ወያኔ ካለ ኢትዮጵያኖችንና ኢትዮጵያን ማጥፋት ዓላማ አድርጎ ከተነሳና በገደለና ባሰቃየን ቁጥር ርካታ ከሚያገኝ መንደርተኛና ባንዳ ቡድን ጋር የሚደረግ ትግል በመሆኑ፤ ትግሉ በጦርነት ከሚካሄድ ትግል የከበደና የከፋ ቢያደርገውም፤ ለሀገራችን ከጠበጃ ኃይል ነጻ የሆነ ትግል በማካሄድ ለድል ማባቃት እንደሚቻል፤ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለመጭው ትውልድም ፈር ቀዳጅ ማድረግ መቻል አለብን።
- በየአካባቢው የሚገኙ ሆድ አደር የባንዳ ምስለኔዎችን በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ፎቶግራፋቸውንና ማነንታቸውን ማጋለጥ።
- ወያኔዎችና ሆድ አደሮቻቸው ለሚፈጥሩትና ለሚነዙት ተራ የዘረኝነና ማወናበጃ ጊዜም ሆነ ቦታ አለመስጠት።
- በቡድንም ሆነ በግል የምንታገል ዜጎች ራሳችን ለማንኛውም ለሚገጥመን ወያኔያዊ ፈተና በመንፈስም ሆነ በስሜታችን ሙሉ ዝግጅት ማድረግ፤ አልበገር ባይነታችንና ቆራጥነታችን ይረዱት።
- በየአጋጣሚው ሁሉ በወያኔ ስር ሆነው አገልግሎት የሚሰጡትን ዜጎቻችን የውስጥ ሥራ እንዲሠሩና ወያኔን እንዲቦረቡሩት ማግባባትና ሀገራችን ያለችበትን አስከፊ ሁኔታ ማስረዳት የትግሉ አጋር እንዲሆኑ ማግባባት።
- ህዝባዊ አምጽ ለማካሂድ ስንነሳ በቂ ዝግጅት ማድረግ፤ እንደችሎታንና እንደ አቅማችን የሥራ ክፍፍል ማድረግ ብቻ ሳይሆን፤ መደማመጥና መተሳሰብ ከየአንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ነው።
- ከሌላው ዓለም ምንም አንጠብቅ፤ እንዲያውም የውጭ መንግሥታት የወያኔን ዕድሜ ለማራዛም ማንኛውም ሀገራዊ ትግል ከማደናቀፍና ከማዳፈን ወደ ኋላ አይሉም። እነሱ ለነሱ የሚሰግድላቸውና ጥቅማቸው እስከተጠበቀላቸው ድረስ፤ ከቻሉ ለወያኔ “ኒውከለር” ያበድሩታል። እኛ ጠንካራና በሁለት እግራችን ከቆምን፤ ብሎም ወያኔን እንደምናስወግደው ከተረዱ፤ እኛ ሳንሆን እነሱ ወደ እኛ ይመጣሉ። ያኔ ደግሞ የሀገራችንንና የህዝባችንን ጥቅም በማስቀደም ግንጡነት ማድረግ እንችላለን።
- ትግላችን አንድነትና ሀገራዊነት እንዲኖረው ወያኔ ሰፍቶ የሰቀለውን ጨርቅ ከማውለብለብ እንታቀብ።
- መረጃ የዘመኑ አንዱና ዋና የትግል መሣሪያ በመሆኑ፤ ጠቃሚ መረጃዎችን በተገቢው ቦታንና ሰዓት መጠቀም፤ መለዋወጥ።
- የህዝባዊ አምጽ መሪዎችና አዘጋጆች፤ ሊደርስባቸው የሚችለው አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ፤ እነሱን ሊተኩ የሚችሉ በቅድሚያ ማዘጋጅት ለትግሉ ቀጣይነት ወሳኝነት አለው።
- በራስ በመተማማን ለድል እንደምንበቃና ኢትዮጵያ ሁላችንም በጋራና በኩልነት የምንኖርባት፤ የሕግ የበላይነት የሚከበርባት ሀገር እንደምናደርጋት ማመን።
- ከወያኔ ጋር ድርድርና የመሳሰሉት ነገሮች ቦታ ስለሌላቸው፤ ወያኔን መጠየቅም ሆነ መታገል ያለብን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሥልጣኑ እንዲለቅና ለህዝብ እንዲያስረክብ ነው። ለዚህ ለመብቃት ደግሞ እኛ ተደራጅተንና ብቁ ሆኖ መገኘት ይጠበቅብናል።
ኢትዮጵያ …
እናት - አራስ መሆን እወቂበትና
ማህጸንሽን ባርኪው፤ አልመከንሽምና፤
ላንች ክብር ዝና፣ ለህዝብሽ ልዕልና
ሞቼ እየተነሳው፣ ልሙት እንደገና፤
አንድ ሞት ለሀገሬ፣ አልበቃትምና
የሚል ታደርሻለሽ፣ ዛሬም ቀን አለና። …
-------//------
ፊልጶስ /ሐምሌ 2008 (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)