የፖለቲካውን ምስቅልቅል ተረድተህ ጽንፈኛ፣ ቁርጠኛ ብሎም ጦረኛ እስክትሆን፤ አገርና ሕዝብ ከቶም አይኖርህም

ዐፄ ቴዎድሮስ
ሸንቁጥ አየለ
የፖለቲካው ምስቅልቅል
አሁን ያለው የፖለቲካ ምስቅልቅል እውነትና ገጽታው ምን ይመስላል?የጠላት አቋሙስ ምን ይመስላል? ወያኔ ምን እየሰራች ነው? አጠቃላይ የፖለቲካው ትርምስምሱ እንዴት ይገለጻል ብለህ እራስህን ጠይቅ። ከአንድ እስከ አስር ያሉትን ነጥቦች አንድ በአንድ በስፋት እያብራራህ ከእውነተኛ የትግል አጋሮችህ ጋር ብቻ እጅግ ጥልቅ ውይይት አድርግባቸው። እዚህ በደምሳሳው የተሰጡትን ነጥቦች በምሳሌ እያሰፋፋህ የፖለቲካውን ምስቅልቅል መጀመሪያ አጥብቀህ ተረዳ።
ወያኔ ድርጅቶችን ጠልፋ በመጣል፣ የሕዝብን አመጽ ጠልፋ በመደምሰስ፣ ውዥንብር እና ሐሰተኛ ተቃዋሚዎችን በማፍራት የተዋጣለት ስትራቴጅ ትከተላለች። አሁንም ወያኔ በብዙ አቅጣጫ የሕዝቡን ትግል የመጠለፍ እና ትግሉን የመቆጣጠር ስልት ነድፋለች። እጅግ ብዙ ቢሊዮን ብሮችም ወደ ተቃዋሚ መሰል አምታች ኃይሎች ኪስ እየፈሰሰ ነው።
1ኛ. ኦህዴድ እና ብአዴን የሚባሉ አሽከሮቿን የኢትዮጵያዊነት ፕሮፖጋንዳ አልብሳ ወደ አደባባይ አውጥታቸው አንድ ሰሞን ልፍስፍስ ተቃዋሚዎችን ልባቸውን መማረክ ችላለች። ወያኔ ግን መቼም ቢሆን ጸረ ኢትዮጵያዊ ሥራዋን እንደማትዘነጋው በወያኔ ላይ ጽንፍ የያዙ እና ቁርጠኛ ጠላትነት የመሰረቱ ብቻ ያውቁታል። መሃል ሰፋሪዎች የሐሰት ከበሮ በተመታ ቁጥር እስክስታ መች ናቸው እና ሕዝባዊ ጠላት ናቸው። በወያኔ ፕሮፖጋንዳ ያለ ምክንያት አይወሰዱም ልባቸው በከፊል ከወያኔ ጋር ስለሚተባበር ነው።
2ኛ. በአሁኑ ወቅት በውጭ አገር የሚኖሩ (በተለይም በአሜሪካ የሚኖሩ) እና ከወያኔ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን እየተኮናተሩ አብረው የሚሰሩ ሰቃጢ እና አስመሳይ ፕሮፌሰሮች በተቃዋሚዎች እና በወያኔ መሃከል ድርድር እናደርጋለ እያሉ የሐሰት ሽንገላ ለዋላላ እና ደንበርባራ ተቃዋሚዎች በአገር ቤትም በውጭ አገርም ተስፋ እየሰጡ ነው። ወያኔ ሁሌም ይሄን ነገር ማድረግ በደንብ የተካነበት አሰራሩ ነው። ልክ የደርግን ሰንካላ ጀነራሎችን ሻቢያዎች እና ወያኔዎች ሆነው "እንቅፋት የሆነብን መንግሥቱ ኃይለማርያም እና ደርግ ናቸው። እነሱን ከጣልን ዲሞክራሲ እንዲሰፍን እናደርጋለን። ሕዝባዊ መንግሥት እንመሰርታለን" እያሉ እንዳታለሏቸው መሆኑ ነው። በአሁኑ ሰዓትም እነዚህ አደራዳሪ ፕሮፌሰሮችም፣ ምሁራን ተብዬዎች እና የሐሰት ተቃዋሚዎች አሁን ዲያስፖራው እና አገር ቤት የሚኖረው ተቃዋሚ መሃከል መደናገርን እንዲፈጥሩ ወያኔ ልኳቸዋል። እጅግ ብዙ ብርም ተመድቦላቸው እየሰሩ ነው።
3ኛ. ወያኔ በአሁኑ ሰዓት በአገር ቤት የለበጣ ድርድሩን እራሱ ከጠፈጠፋቸው የተቃዋሚ አመራሮች ጋር በማስመሰል እያከናወነው ሲሆን መሃል ሰፋሪዎች እና አስመሳይ ተቃዋሚዎች እንዲሁም ወደ ጽንፍ መምጣት ያልቻሉት ተቃዋሚዎች የሚዋልል አቋም ይዘው ወያኔ በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ይለቃል የሚል ለበጣን እያራመዱ ነው።
4ኛ. ወያኔ በአንድ መልኩ ኢትዮጵያዊነትን አራመድኩ ሲል ቢደመጥም በሌላ መስመር ደግሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከተሰለፉ ኃይሎች ጋር እጅግ ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ውስጣዊ ድርድር እያደረገ እና አገሪቱን አፈራርሶ እንደሚያስረክባቸው ቃል እየገባ ነው። ወያኔ ማንኛውንም አይነት ድርድር ያደርጋል። ማንኛውንም አይነት ማታለያ እና ማዘናጊያ ስልት ይጠቀማል። ግን ወያኔ አንድም ጊዜ አላማውን አይስተውም።
5ኛ. አንዳንዱ መሃል ሰፋሪ እና ዋላላ ተቃዋሚ ወያኔ እርስ በርሱ ተባላ፣ መስማማት አቃተው፣ የወያኔዎች ስብሰባ ልዩነት በመሃላቸው ፈጠረ በማለት ወያኔን በፕሮፖጋናዳ እና በግርግር ሊጥላት እንዲሁም ሕዝቡንም በከንቱ ተስፋ ሊሸነግል መከራውን ያያል። ሆኖም ይሄ ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ሕዝቡን በማይሆን ተስፋ በመሙላት እውነቱ እየተገለጸ ሲመጣ ሕዝቡ ተስፋ እንዲቆርጥ እና ለመራራ ትግል እንዳይዘጋጅ በማድረግ የአቋራጭ አሸናፊነት እንዳለ በማሰመሰል ነገሮችን ያለዝዛቸዋል። መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅ "ኢህአዴግ የሾላ ፍሬ አይደለም። በድንጋይ አይወርድም" ያለው በጦር እንደመጣን የምንወርደው እና የሚያወርደን እውነተኛ ጦረኛ ብቻ ነው ማለቱ ነው።
6ኛ. የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች እርስ በራሳቸው መባላትን አሁንም እንደመረጡ ነው። እርስ በራሳቸው ከመተማመን ይልቅ የኢትዮጵያን ጠላቶች በማመን የኢትዮጵያን እጣ ፋንታ በኢትዮጵያ ጠላቶች እጅ ላይ አኑረውታል። ሌላው ቀርቶ ከአንድ ጎሳ ወጣን በአንድ ጎሳ ስም ድርጅት መስርተናል የሚሉ የተቃዋሚ ሱቅ በደረቴ ፓርቲዎች ጮህው በአደባባይ እንደሚናገሩት ወያኔን አምርረው ከመጥላት ይልቅ እርስ በርሳቸው በመራራ ጥላቻ ታንቀዋል።
7ኛ. ተቃዋሚዎች በአንድ ጉዳይ ላይ በጥለቀት እና በትእግስት ከመከራከር እና ከመወያዬት ይልቅ በግልብልብ እና በግብታዊነት እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ከመተማመን እና እርስ በርስ ከመምከር ይልቅ በውጭ አገራት ምክር ላይ የመንጠልጠል አባዜ ውስጥ ተቀርቅረዋል። ይሄም አልበቃ ብሎ የኢህአፓነት፣ የደርገነት፣ የመኤሶንነት፣ የንጉሣዊነት ማንነት እየመዘዙ እርስ በርሳቸው አሁንም ለመጠፋፋት የሚያደቡት ምሁራን ብዙ ናቸው። ከውጭ አገር እስከ አገርቤት ያላቸው የፖለቲካ ተሳትፎም ቀላል አይደለም። አገር ለማዳን እና ሕዝብን ለመታደግ ከቶም ይቅር ለእግዚአብሔር ለመባባል ምንም ፍላጎት የላቸውም። ከኢትዮጵያ ሕመም እና መከራ ይልቅ የእነሱ የግል የልብ ቂም እርስ በርስ እንዲጠፋፉ አሁንም እንዲጠላለፉ አሁንም ቁርጠኛ አድርጓቸዋል። እርስ በርሳቸው አብረው ቆመው አገሪቱን እና ሕዝቡን ከመታደግ ይልቅ አንዳንዱ ከወያኔ አሁንም እንደወገነ ሌላው ደግሞ አሁንም ከሻቢያ እንደተተለለ ብሎም እርስ በርስ ለመጠፋፋት እንደወሰነ አሁንም አገሪቱ መራራ የፖለቲካ አዘቅት ውስጥ እንድትወድቅ አድርገው ያንኑ ዲያቢሎሳዊ ሥራቸውን ቀጥለዋል። ጥላቻ ወደ ቀውስነት ደረጃ አድርሷቸዋል ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያዊነት ማማም ላይ አውርዷቸዋል። ከነዚህ አጋር ከቶም ምስጢር መሥራት አይቻልም።
8ኛ. ኩርፊያ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ፣ እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ የሚለው የኢትዮጵያ ምሁራን አባዜ እንዳለ ሆኖ በርካታ የኢትዮጵያ ምሁራን የአሜሪካ መንግሥት እና የምዕራብ አገራት ወያኔን ታግሎ እንዲጥሉላቸው ወይም ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት እንዲያነሳላቸው እና እነሱን እንዲሰይማቸው የመማለል ከንቱ የትግል ስልት ላይ ተንጠልጥለው ቀርተዋል። ሆኖም ይሄ አካሄድ ከቶም የሕልም እሩጫ መሆኑን የሚያውቁት ምሁራን ድምጻቸውን ከማሰማት እና ተሰባስቦ ወደ መራራ እርምጃ ከመሄድ ይልቅ፤ በእነዚህ የምዕራብ መንግሥታት አጎብዳጅ ምሁራን ጩኸት ተደናግረው ዝም ብለዋል።
9ኛ. የወያኔ ተላላኪዎችን ወደፊት ለማምጣት እና ተቃውሞውን ለመቆጣጠር እውነተኛ እና ቁርጠኛ ታጋዮችን በሕዝብ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው አጠብቀው ይሠራሉ። ከዚያም ዘለው በውጭ አገር በሚንቀሳቀሱ፣ በአገር ቤት በሚንቀሳቀሱ እና ወያኔ በሚስጢር በቀጠራቸው ተቃዋሚዎች እውነተኛ ተቃዋሚዎችን የማስጠፋት ሥራ በስፋት ይሰራል። እነ እከሌን እንዴት እናጥፋቸው? ለነገ እንቅፋት ናቸው በማለት ብዙ ጥናቶች ይደረጋሉ። እውነተኛ ተቃዋሚዎች በአንድ በኩል በወያኔ ይሳደዳሉ፣ ይገደለላሉ፣ ይታሰራሉ፣ በረሃብ ይጠበሳሉ፣ ብዙ መከራዎችን ይቀበላሉ። ሆኖም አስመሳዮች፣ ተገለባባጮች፣ የወያኔ አገልጋይ የነበሩ መርህ አልባ ፖለቲከኞች ደግሞ ወደ ሰማዬ ሰማያት ከፍታ ላይ በሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ይሰቀላሉ። ሕዝቡ እራሱ ማስተዋሉን የተነጠቀ ይመስል ድል እና አሸናፊነት ከእንደዚህ አይነት አስመሳዮች ይጠብቃል። ለነገሩ ኢትዮጵያ ልማዷ ነው። በላይ ዘለቀን ሰቅላ ባንዳዎችን የምትሾም። ሕዝቡም አይገርመውም። ያረዱትን፣ ያስገደሉትን፣ ያሳደዱትን እና የሰደቡትን መልሶ ነጻናት እና ብልጽግናን ያመጡለት ዘንድ አንጋጦ ያስተውላቸዋል። ተስፋም ያደርጋቸዋል።
10ኛ. አሁን ያለውን የፖለቲካ ምስቅልቅል በተጨባጭ ለመረዳት ጎንደርን እንደማሳያ እንውሰዳት እና አንድ አስቀያሚ እውነትን እንመልከት። የተቃዋሚ ፖለቲከኛው የእርስ በርስ መከፋፈሉን ጥልቀት ለማዬት በአሁኑ ሰዓት ከጎንደር የተሻለ ማሳያ የለም። ሰባት የጎንደር ተወላጆችን ብትወስድ እና ሰባቱም ሰዎች ሰባት ድርጅት ውስጥ እንደሆኑ ብታውቅ ብሎም ከሰባቱም ጋር በጋራ ስለመታገል ምክክር ብታደርግ የሚገርም እና የሚያስደምም እውነታን ታገኛለህ። ምናልባትም አራቱ ሰዎች አማራ ድርጅቶች የሚባሉ ፓርቲዎች ውስጥ አራት ቦታ መሽገዋል ብለህ አስብ። እንዲሁም ምንአልባትም ሁለቱ ሰዎች ደግሞ ህብረ ብሄራዊ እሆኑ ሁለት ፓርቲዎች ውስጥ መሽገዋል። አንዱ ደግሞ በጎንደር ስም እተዋቀር ድርጅት ውስጥ የመሸገ ነው ብለህ አስብ። እነዚህ ሰባት ድርጅቶች ውስጥ የመሸጉ ሰባት ሰዎች ወያኔን እንደሚታሉ ቢነግሩህም ዋናው ጥላቻቸው ግን እርስ በርሳቸው ነው። በመሃላቸው ያልተጨበጠ እና የተወናበደ አሉባልታ እንደጉድ ይርመሰመሳል።
ምናልባትም ሰባቱም ድርጅቶች በትጥቅ ትግል የሚያምኑ እና ወያኔን በኃይል መወገድ አለበት የሚሉህ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም እነዚህን ኃይሎች ጠጋ ብለህ የመረመርሃቸው እንደሆነ ስለሕዝቡ ማዘንህ አቀርም። ጉልበት እና አቅም ቢኖራቸው ምናልባትም ልክ ቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር በማለት በደርግ ድንቁርና እንዲሁም በሻቢያ እና በወያኔ ተንኮል እንደተቀነባበረው የእርስ በርስ ፍጅት አሁንም በጎንደር ሕዝብ ላይ ከማምጣት የማይመለሱ መሆናቸው ቀስ ብሎ ይገለጽልህ ይሆናል። እርስ በርስ በጣም ስለሚጠላሉም እነሱ እርስ በርስ ለመጠፋፋት በሚወስዱት እርምጃ አንተ እገሌን ትደግፋለህ እያሉ ሕዝቡን እና ወጣቱን እንደሚያጠፉት ግልጽ የሚሆንልህ ሁሉንም በጣም ደጋግመህ የሚሰሩትን ሥራ ቀርበህ የመረመርህ እንደሆነ ነው። የሚገርመው ደግሞ እነዚህ ከአንድ አካባቢ የወጡ ሰዎች አንዳንዶቹ የኢትዮጵያ ጠላትም የአማራ ሕዝብ ጠላትም የሆነውን ኢሳያስ አፈወርቂን እንደ ፈጣሪያቸው እና እንደ አምላካቸው በመውሰድ የራሳቸውን የጎንደር ሰው እና ታጋይ ግን መደምሰስ እንዳለበት የሚሰብኩ ሆነው ታገኛቸዋለህ። እድሉ የቀናቸው እንደሆነም አቢዎታዊ እርምጃ እርስ በርሳቸው ከመወሳሰድ እንደማይመለሱ በደንብ ይገባሃል።
ጽንፈኛ፣ ቁርጠኛ ብሎም ጦረኛ እስክትሆን፤ ትግል እንዳልጀመርክ እወቅ። አገርና ሕዝብም ከቶም እንደማይኖርህ ተረዳ
እናም በዚህ ሁሉ ትርምስምስ ውስጥ እውነተኛ ሕዝባዊ ትግል የያዘው ሕዝብ በበርካታ ውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ በሚሸረብ እና በሚከወን ፖለቲካ ታንቆ ተይዟል። እና መፍተሄው ምንድን ነው ብለህ ከጠየቅህ ጠላትህን እወቅ፣ ጽንፈኛ ተቃዋሚ ሁን ብሎም ለመስዋዕትነት እራስህን ከመሰሎችህ ጋር ብቻ ሆነህ አዘጋጅ የሚል ነው። አገር እና ሕዝብ እንዲኖርህ ከፈለግህ መስዋዕትነት ወሳኝ ነው። በጦር የመጣው ወያኔ ያለ መራራ ውጊያ ከቶም ስልጣኑን ለሕዝብ አያስረክብም። መራራ ጦርነት ደግሞ መራራ አሰራሮችን እና መራራ መርሆችን መከተልን ይጠይቃል። በየትኛውም የትውልድ ፍሰት ውስጥ ይሄ ሀቅ ነው። ጽንፈኛ እና ቁርጠኛ እስክትሆን ጠላትህን አታጠፋውም፤ አገርና ሕዝብም አይኖርህም። እናም የሚከተሉትን ነጥቦች በልብህ እያንሰላሰልህ ወደላቀ ድርጅታዊ መርህ አሳድጋቸው።
1ኛ - የጠላት ረድፉ እና መደቡ አንድ ነው። ጠላትህን ያለ እርህራሄ ለይተህ ካላወቅህ ከቶም ሕዝብህን ነጻ አታወጣውም። ሌላው ቀርቶ ይሄን እስክታደርግ ትግል እንዳልጀመርክ እወቀው።
2ኛ - የወዳጅ ረድፉ እና መደቡ አንድ ነው። ወዳጆችህን እና የመደብ አጋሮችህን ማስተባበር እስክትችል ከቶም ጠላትህን መደምሰስ አትችልም። የወዳጆችህን ጥንካሬ መቁጠር ካልጀመርህ ደግሞ ከቶም ወዳጆችህን ወደ አንድ ልታመጣቸው አትችልም። መሃል ሰፋሪዎቹ ጠላቶችህ መሆናቸውን እስክታውቅ እና ከለዘብተኞች ጋር መሞዳሞድህን እስክትተው ድረስ ከቶም ትግል እንዳልጀመርክ እወቅ። የገጠመህ ጠላት እጅግ ጽንፈኛ እና ቁርጠኛ ብቻ ሳይሆን በመራራ ጥላቻ ተረግዞ በመራራ ጥላቻ ውስጥ እየኖረ ያለ መሆኑን ለማወቅ መከራ የተሸከመውን ሕዝብ ቀርበህ አነጋግረው።
3ኛ - ሕዝብ እና አገር እንዲኖርህ ከፈለግህ ጠላቶችህን መደምሰስ አለብህ። ከዋናው ጠላትህ በላይ ደግሞ መሰረታዊ ጠላቶችህ ከጠላትህ ጋር ተባባሪዎቹ እና መሃል ሰፋሪዎቹ መሆናቸው እስካላወቅህ ድረስ በጠላት ወጥመድ ውስጥ የመያዝ እድልህ ሰፊ ነው። ጠላት ለመደምሰስ ከመሃል ሰፋሪዎች ጋር የቆምክ እለት ተደምሳሽ ነህ። በተለይም አማራ ነኝ ብለህ በወያኔ የተጠፈጠፈ ብአዴንን ውስጥ የሚልከሰከስ/የተልከሰከሰ/ አማራ ያመንክ እንደሆነ ወይም ኦሮሞ ነኝ ብለህ ኦህዴድ ውስጥ የተልከሰከሰ/ወይም የሚልከሰከስ/ ኦሮሞ ያመንክ እንደሆነ ያኔ ፈጽሞ በወያኔ መረብ ውስጥ እንደወደቅህ እወቅ። ትግሉ የብሄሮች ትግል ብቻ ሳይሆን የመደብ ትግል ባህሪም እንዳለው አልገባህም እና እራስህን መርምር። እንኳን የአለም ስነ መንግሥት የሰማዩ ስነመንግሥት ያለ ተጋድሎ አይወረስም። ሥነ መንግሥትን መመሥረት፣ ሕዝብህንም ነጻ ማውጣት እና አገር እንዲኖርህ ከፈለግህ እጅህን ወደ ቀስቱ ላይ ዘርጋው። ስልጣን የጨበጠን ኃይል በሐሜት፣ በሐሰት እና በፕሮፖጋንዳ ማውረድ ከቶም አይቻልም። የአንዲት አገር ሕዝብ ምድራዊ ሰቀቀን እና መከራ እንዲፈወስ ለመሰዋዕትነት እራሳቸውን የሚያቀርቡ ጀግኖች ወሳኝ ናቸው። እነዚያን ጀግኖች ፈልገህ እስክታገኝ ከቶም ሕዝብህን ነጻ እና የተከበረ ሕዝብ ማድረግ አትችልም
4ኛ - በዚህ ዘመን ዶክትሬት እና ፕሮፌሰርነት አንጠልጠልጥለው የአንድ አርሶ አደር ያህል የፖለቲካ ስሌት ማንሰላሰል የማይችሉ ሆኖም ዶክተር እና ፕሮፌሰር ስለተባሉ መሪ፣ የፖለቲካ አማሳይ፣ አስታራቂ፣ እና የፖለቲካ ፈራጆች መሆን ያለባቸው የሚመስላቸው በርካታ ቀውሶችን ሕዝባችን ማፍራቱን አትርሳ። እነዚህ የሕዝባችን ዋና ሕመም እና ስቃይ ናቸው። ስለሆነም እውነተኞቹን እና ቁርጠኞቹን ምሁራን፣ ዶክተሮች እና ፕሮፌሰሮች ፈልገህ እስግታገኝ በስመ ምሁር አብረሃቸው አትግበስበስ።
5ኛ - አስመሳይ እና ሐሰተኛ አዎንታዊነት አነብናቢ ምሁራን፣ ተናጋሪዎች፣ የሃይማኖት ሰው ነን የሚሉ ሀሳውያን እና በገንዘብ ልባቸው የነቀዘ ባለ ሀብቶች ኢትዮጵያን ተብትበው ይዘዋታል። ስያፍሩ ወያኔን በአደባባይ ላይ እድሜ እንዲሰጠው የሚጸልዩ ሞልተዋል። ግን የሚነግዱት በሃይማኖት ስም ነው። ሆኖም ስለሚፈሰው ሕዝባዊ ደም፣ ስለወገናቸው መከራ፣ ስደት፣ ርሃብ እና ጭቆና ከቶም ግድ አይሰጣቸውም። ነገ በኢትዮጵያ ምድር የሚከሰተው የርስ በርስ ፍጅት እና ትርምስ ከቶም አያሳስባቸውም። የወያኔን ጎሰኝነት እየባረኩ፣ በአዳራሾቻቸው በጌታ ስም ወያኔን እየባረኩ እየጮሁ የሚለፈልፉ ሞልተዋል። ስለዚህም የሐሰትኛ አዎንታዊ እና ጠጋጋኝ ቅላት እና የአረፍተ ነገር ኳኳታ ሲያሰሙ የሰማህ እንደሆነ ከነዚህ እራቅ። እንኳን የምድሩ ስነ መንግሥት፣ እና ሕዝብ ድህነት ቀርቶ የሰማዩ መንግሥት ውርስ በመራራ መስዋዕትነት እንጅ በሐሰተኛ አዎንታዊ የቃላት ለበጣ አይገኝም እና።
6ኛ - ነገሮች በጣም ተስፋ አስቆራጭ ሆነዋል። የኢትዮጵያም ሕልውና እጅግ አሳሳቢ እና ፈታኝ ሆኗል። ሆኖም እውነተኛ ሕዝባውያንን የምታገኛቸው በመከራው ሰዓት መሆኑን አትርሳ። እሳቱ በጣም ሲግፈጠፈጥ ወርቁ እየነጠረ እንደሚመጣው ማለት ነው። እናም በተስፋ አስቆራጩ በዚህ ዘመን ጀግኖቹን በርትተህ ማሰስህን ቀጥል።
7ኛ - ኢትዮጵያ ከቶም አትጠፋም ብለህ እመን። ሆኖም መራራ መስዋዕትነት ከፊት ለፊትህ እንዳለ አትርሳ። ታላቁን ባለ ራዕይ ንጉሠ ነገሥት አጼ ቴዎድሮስን በዚህ ዘመን አስበው። ኢትዮጵያ ለ179 ዓመታት ተከፋፍላ ኖራ ሳለ ታላቁ ባለ ራዕይ ቴዎድሮስ ግን ከቲንሿ አንዲት የጎንደር ቀበሌ ውስጥ ሆኖ እንዲህ ሲል አለመ። "የኢትዮጵያ ባል፣ የእየሩሳሌም እጮኛ እኔ አጼ ቴዎድሮስ ተከፋፍሎ መከራ እየወረደበት ያለውን ሕዝቤን በአንድ አደርገዋለሁ"። እናም የተከፋፈለውን ሕዝብ አንድ አደረገው። አገር እና ሕዝብ በኃይል ይሰበሰባል። መጽሐፍ እንደሚልም በጥበብ ይጸናል። ኃያሉ ንጉሠ ነገሥት ቴዎድሮስ በኃይል የሰበሰበውን አገር እና ሕዝብ ጠቢቡ ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ደግሞ በጥበብ አጸናው። አንተ የነዚህ ነገስታቶች ልጅ መሆንህን አትርሳ። በመክራ እና በእሳት መሃከል የሚራመዱ። ሽህ ዓመታት የተዋጉ። ሽህ ዓመታት በነጻነት የኖሩ። በመከራ እና በጠላት ብዛት ተበትኖ እና መክኖ ያልቀረ የሀያላን ምድር ያፈረሃ መሆንህን እመን። ኃያል ኢትዮጵያዊ መሆንህን እንዳትረሳ። ይሄን ጽንፍ ያዝ። በዚህም ጽንፍ ጠላትህን ሁሉ ደምስስ። ያኔም አገር እና ሕዝብ ይኖርሃል።