Ethiopian and turism

ኢትዮጵያ በቱሪዝም መስብህነቷ ከአጎራባች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲወዳደር እምቅ ሀብት አላት።

ሥናፍቅሽ ግርማ

አገራት ለኢኮኖሚ ድጋፋቸው ከሚጠቀሙበት ስልቶች አንዱና ዋንኛው ያላቸውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብት መንከባከብ፣ መጠበቅና በተቻለ መጠንም ማሳደግ እንደሆነ ይታመናል። አገራችን ኢትዮጵያ ያሏትን በተጠቀሱት ዘርፍ የሚገኙትን ሀብቷን በአግባቡ ከተጠቀመች የኢኮኖሚ አቅሟን ለማሳደግና በዚህም የሕዝቧን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እንደምትችል አያጠያይቅም። ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ በመትጋት አገራዊና ወገናዊ ኃላፊነትን ለመወጣት የበቃን ሆነን መገኘት አለብን።

አገራችን ኢትዮጵያ ለዓለም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያበረከተቻቸው እፁብ ድንቅ የሆኑ ክንውኖች ይገኛሉ። ለዚህ ጽሑፍ መነሻ በሆነውና ‹ጢስ አልባ› ተብሎ በሚታወቀው የቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ አገራችን ከምትታወቅባቸው መስህቦች መካከል - በጎንደር የሚገኘው የፋሲለደስ ግንብ፣ የአክሱም ሐውልቶች፣ የኦሞ ሸለቆ፣ የባሌና የሰሜን ተራሮች፣ የደንከል ዝቅተኛ ቦታዎች፣ የተለያዩ የዱር እንስሳት (በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንደ ዋልያ የመሳሰሉ እንዳሉ ያጤኗል)፣ ልዩ ልዩ የአዕዋፋት ዝርያዎች … ወዘተ በዚሁ የሚካተቱ ናቸው።

ከላይ የተገለጹት ለቱሪዝም እድገት ድርሻቸው ከፍተኛ የሆኑ መስህቦች ቢሆኑም አገሪቱ በዚሁ ክፍለ ኢኮኖሚ ያገኘችው ጥቅም አነስተኛ ነው። በተለይ ከሌሎች አጎራባች ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲወዳደር ኢትዮጵያ ካላት እምቅ ሀብት አንጻር፤ በዚሁ የሙያ ዘርፍ ብዙም ተጠቃሚ እንዳልሆነች አኀዞች ይናገራሉ። ለምሳሌ እኤአ በ2015 ግብጽን 9.1 ሚልዮን፣ ኬንያን 1.3 ሚልዮን ቱሪስቶች ጎብኝተዋል። በዚያው ዓመት ኢትዮጵያን የጎበኙ ቱሪስቶች 871ሺ ነበሩ። ከዚህ በላይ ከኢትዮጵያ ጋር በማወዳደር ያቀረብኳቸው አገራትን ለማቅረብ የተገደድኩት ካላቸው የቱሪስት መስህብ አንጻር ከእኛይቱ ኢትዮጵያ ጋር የሚወዳደሩ ሆነው ያለመገኘታቸው ነው። የኬንያን ስንመለከት ዋናው የዱር እንስሳትና ይህንኑ በብቃት ለማስጎብኘት ያዘጋጀቻቸው ፓርኮች ሲሆኑ፣ በግብጽ በኩል ደግሞ ጥንታዊ ሐውልቶችና ታሪካዊ ግንቦች እንደሆኑ ይጠቀሳል። ይህም እንደ ፒራሚድና የመሳሰሉት ናቸው። ይህንን ማንሳት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ እነዚህ የተጠቀሱት የሁለቱ አገራት የቱሪስት መስህቦች ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ያላት መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ሐቅ መሆኑን ለመጥቀስ ነው።

ልንጠብቃቸውና ልንንከባከባቸው የሚገቡ ዕሴቶችና ንብረቶቻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩ ይገኛሉ። ለዚህም መሸርሸር ምክንያት ከተጠቃሾቹ ዋንኛው እኛው ኢትዮጵያዊያን ሆነን እንገኛለን። ይህንኑ በአጭር ምሳሌ ለማስረዳት - በዓለም አቀፍ ደረጃ ለውድድር በተለያዩ አገራት የሚሄዱ አትሌቶቻችን ለብሰው የሚሄዱት ቱታም ሆነ ሌላ ልብስ ላይ ስማቸውና አገራቸው ይጻፋል። እንኳን በአትሌት ደረጃ በማናቸውም ምክንያት ከአገሩ የሚወጣ ዜጋ የአገሩ አምባሳደር እንደሆነ ሊሰማው ይገባል። እነዚህ አትሌቶች በጀርባቸውና በደረታቸው የሚጻፈው በአገርኛ ፊደል ቢሆንና ሌላው ማለትም እንግሊዝኛው ቢከተል አገርን ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ መገንዘብ ያስፈልጋል። በአፍሪካ ብቸኛው ፊደል ያላት አገር የእኛይቱ ኢትዮጵያ እንደሆነች አንርሳ። አማርኛ፣ ትግሪኛ፣ ኦሮሚኛ፣ የብዙ ቋንቋዎች ባለቤት ሆነን አብዛኛዎች አትሌቶች በተለያዩ መድረኮች በሚሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ቢናገሩ ያለብዙ ችግር ሐሳባቸውን መግለጽ ሲችሉ፤ የመልአክት ቋንቋ ነው የተባሉ ይመስል በእንግሊዝኛ ሲኮላተፉ መስማት ያሳዝናል።

በሌላ በኩል የእኛ የሆኑና የብቸኛነት ባለቤትነት ያሉንን አንጸባራቂ ንብረቶቻችንን በተለያየ መልኩ እየተሰረቁ ባለቤትነታችን ፈሩን እየለቀቀ ነው። ‹ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል› እንደሚባለው ይህንንም ዘረፋ አስመልክቶ በቅርቡ የተከሰቱትን በአጭሩ እንመልከት።

ጤፍን በማምረት እንዲሁም በምርቱ በመጠቀም ብቸኛው ሕዝብ እንደሆንን ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። ዛሬ እንደምንሰማው ከባህር ማዶ የሚገኝ አገር የባለቤትነት መብቱ የእኔ ነው እያለ ይገኛል። እንዲሁም በተለያዩ የአገራችን ክልሎች ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን ፍንትው አድርጎ በሚገልጽ መልኩ የሚሠሩት የሽመናና የጥልፍ ውጤቶች ውበታቸውና ድምቀታቸው ወደር የማይገኝላቸው ናቸው። በጣም የሚያሳዝነው እነዚሁ የሽመናና የጥልፍ ውጤቶች እንዲሁም ሌሎች ቅርፃ ቅርፆች ናሙናቸው ወደ ቻይና እየተሸጋገረ የኛኑ አሠራር ከእነሱ ጋር እያደባለቁ ለሽያጭ (Export) እያቀረቡ ይገኛሉ። ከሚላክላቸው አገራት እኛም እንገኝበታለን።

እነዚህ ንብረቶቻችን እየተዘረፉ መሄድ ጉዳቱ በብዙ መልኩ ሊገለጽ ይችላል። ከጉዳቶቹም መካከል ሊጠቀስ የሚገባው እነዚህኑ ምርቶች በብዙ ልፋት የሚሠሩት ወገኖቻችን ርካሽ በሆነ ወረራ የሚደርስባቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ነው።

ታሪካዊ እሴቶቻችን - በንብረት፣ በቋንቋ፣ በባህልና በመሳሰለው የሚደረግብንን ዘረፋ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ሊታገለው የሚገባ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። አባቶቻችን፣ እናቶቻችንና አያቶቻችን አሁን የእኛ ነው ብለን የምንኮራበትን መለያዎቻችንን ለመሥራትና ለማቆየት ብዙ መሥዋዕትነትን እንደከፈሉ በማወቅ፤ እኛም ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ የበቃን ሆነን መገኘት እንዳለብን ልናምን ይገባል። ማመን ብቻ ሳይሆን ሁሉም የተቻለውን ማድረግ ይኖርበታል። የተደረገውን ይህን ዘረፋና ወረራ መንግሥትም በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሔ እንዲገኝለት ዋንኛው አካል እንደመሆኑ ሳይታክት ሊሠራበት ይገባል።

በመጠኑም ቢሆን በተነሳው በዚህ ርዕስ ላይ ‹ትራቭል ኢትዮጵያ› የተባለ ድርጅት በተመሳሳይ መልኩ ለሚመለከታቸው አካላት ያቀረበውን አስተያየት በቅርቡ ከፌስቡክ ለመመልከት ችያለሁ። ይህን የመሰለው ዐቢይ አገራዊ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶቹ ትኩረት ሰጥተው አስተያየታቸውን እንዲያካፍሉንና በመፍትሔውም በኩል ዛሬ ነገ ሳይሉ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ በአንክሮ አሳስባለሁ።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!