Yoweri Kaguta Museveni  (Ugandas president) & Omar Hassan Ahmad al-Bashir (former Sudanese president)

ላለፉት 33 ዓመታት በሥልጣን ላይ የተዘረፈጡት የኡጋንዳው መሪ ዩሪ ሙሴቪኒና በሕዝብ ግፊት ከ30 ዓመታት ከሥልጣን የተወገዱት የሱዳን መሪ የነበሩት አል በሽር

ነፃነት ዘለቀ

በዜና ስከታተላቸው ለጊዜው “ብው” ያልኩባቸውን መጥቀሴ እንጂ፤ አፍሪካዊ መሆን በተለይ ከቅርብ ዘመናት ወዲህ የሚያኮራ ወይም የሚመኙት ሆኖ አይደለም - ርዕሴን እንደዚያ የሰየምኩት። አፍሪካ በሚገርም ሁኔታ ዓለምን እያሳቀችና ጥቂት የማይባሉ ዜጎቿን እያሳቀቀች ትገኛለች።

1. የኛው ጉድ በየሚዲያው እንደልብስ ተሰጥቶ ፀሐይ እየሞቀው ስለሆነ፤ አሁን እዚህ ገብቼበት አልዳክርም። ሠለጠነ በተባለ ዓለም ውስጥ የዘርና የጎጥ ፓርቲና ድርጅት መሥርቶ መጃጃል ከየት እንደመጣ ማወቅ ስለማይቻል፤ የኛን አለማንሳት ነው። ተስማምቶና ተዋኅዶ የሚኖርን ሕዝብ እያጣሉ እንደ አዲስ ለማስታረቅና ለማስማማት የሚደረገውንም በየወንዙ የሚማማሉ የማይተማመኑ ጓደኛሞች ዐይነት ነገር እንተወው።

2. ዩጋንዳ ትገርማለች። ዮሪ ሙሴቪኒ የተባለን በዕድሜም ባይሆን ሥልጣን ላይ ሙጭጭ ከማለት አኳያ በአምባገነንነት የጃጀ ሽማግሌ ለማስመረጥ ፓርላማው ሕጉን ጠመዘዘው አሉ። ይህን ስሰማ በውነቱ አፈርኩ። አፍሪካ ወዴት እየሔደች እንደሆነ በግልጽ የሚናገር እጅግ አሣፋሪ ክስተት ነው። “የራሷ አሮባት ...” እንዳልባል ፈርቼ እንጂ፤ ብዙ ያስብላል። ይህ ሰው ዩጋንዳን መምራት ከጀመረ ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ ነው። ይሄ ሁሉ የሥልጣን ዘመን አላጠገበውም። በዚህ ሁሉ የፈላጭ ቆራጭነት ዘመን የሥልጣን ሐራራው ጋብ አላለለትም። በሚገርም ሁኔታ አሻንጉሊቶቹም አጸደቁለት። የግብጽ ፓርላሜንታዊ አሻንጉሊቶችም ልክ እንደዚሁ ለአልሲሲ የሥልጣን ዘመን መራዘም ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሳያደርጉለት የቀሩ አይመስለኝም - ባለፈው ሰሞን ሲወራ ሰምቻለሁ። እነሱ እንኳን በሥልጣኔና በአስተሳሰብ ከሌሎቻችን የተሻሉ ናቸው የሚባሉ ነበሩ። በውነት አፍሪካውያንን ምን ነካን? ከዚህ ከዚህስ የይሉኝታን ገመድ በጣጥሶ የጣለው የኤርትራው መሪ ኢሣይያስ አፈወርቂ ይሻላል። አንድ ጊዜ ስለምርጫ ተጠይቆ ምን አለ አሉ - “እንደ ኢትዮጵያ ያለ ምርጫ ከፈለጋችሁ በየስድስት ወሩም ማድረግ እንችላለን።” እውነቱን ነው! እውነቱን ተናግሮ እመሸበት ማደር። የርሱ በስንት ጣሙ!

3. የሱዳኑ መሪ ቤት ሲፈተሸ አንድ አገር ሙሉ ዶላርና ዩሮ በየከረጢቱ ታጭቆ ተገኘ አሉ። እንዲህ ነው “የሕዝብ ሰው” ማለት። መቼና የት ሆኖ ሊጠቀምበት ያን ሁሉ ሶልዲ እንዳከማቸ እርሱን ራሱን መጠየቅ ነው። ግን ጭንቅላት የሚባል ነገር በተለይ ተማሩና ዐወቁ በተባሉ የአገር መሪዎች ዘንድ እንዴት ጠፋ? አውነትም ምን ነካን?

እንዴ! ሰው ወዴት እየሄደ ነው!! ያስጨንቃል እኮ። ታዲያ ከነዚህ ሰዎች ጋር እንደሰው ተቆጥሮ በዚህች አፍሪካ መኖር ልክ ነው? እንደኔ እንዲህ ዐይነት መሪዎችና “ሲጠሯቸው አቤት፣ ሲልኳቸው ወዴት” የሚሉ ሁሉንም ትእዛዛቸውን ያለማንገራገር የሚፈጽሙ ሆዳም አጃቢዎቻቸው ባሉባት ምድር መኖር ወርቃማ ጊዜን እንደማባከን እቆጥረዋለሁ። የአሁኑ ዘመንስ በርግጥም አጃኢብ ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!