ከዓርብ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ከረፋድ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ጎሐጽዮን አካባቢ ቄሮዎችና የኦሮምያ ፖሊስ መንገድ ዘጉ

ከዓርብ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ከረፋድ ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ጎሐጽዮን አካባቢ ቄሮዎችና የኦሮምያ ፖሊስ መንገድ በመዝጋታቸው ወደ አማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ማለፍ ባለመቻላቸው ወደ ደጀን ከተማ ተመልሰው ለማደር ተገድደዋል

ግርማ በላይ

የአንዳንድ ስያሜዎች እውናዊ ልጨኛነት የሚገርም ነው - የአንዳንዶች ደግሞ ከማስገረምም አልፎ በለበጣ የሚያስፈግግ ነው። “ዐመለ ወርቅ” ተብላ ነጭናጫ፣ “ሽመክት” ተብሎ ባንድ ጥፊ የሚዘረር፣ “ደም መላሽ” ተብሎ ከእናትና አባቱ ገዳይ ጋር በጎን ተመሳጥሮ ባንድ መሸታ ቤት አሥረሽ ምቺው የሚል ወስላታ፣ … የመኖሩን ያህል፤ እንደስማቸው “አለልኝ”ና “ድጋፌ” ሆነው ለተመካባቸው ሰው ደጀንና ከለላ የሚሆኑ ድንቅ ዜጎች አሉ። እርግጥ ነው ስም አይገዛምና በስም ዙሪያ ብዙ ተቃራኒ ነገሮች መኖራቸው እውነት ነው።

የዓባይን በረሃ ተሻግረን ለደብረ ማርቆስ 70 ኪሎ ሜትሮች ያህል ሲቀሩን አፋፍ ላይ የምናገኛት ደጀን ከተማ፣ እንደስሟ ለወገኖቿ ደጀን መሆንዋን የተረዳንበት የሰሞኑ ዜና እውነትም በአባት ግዕዝ “ስም ይቀድሞ ለነገር” የተባለውንና ልጁ አማርኛም “ስምን መልኣክ ያወጣዋል” የሚለውን የመሳሰሉ ነባር ብሂሎች በተግባር የሚያሳይ ነው። ፈጣሪ ምድርን ጨርሶ አይበድልም።

ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመንጋ ፍርድ ተሰቅሎ ሞተ። በሦስተኛው ቀን እሁድ እኩለ ሌሊት ገደማ ሞትን አሽንፎ ተነሣ። ከዚያን ዘመን ወዲህ ዓርብ የምትታወሰን በስቃይና በሕማም ነው። የስቅሎ ስቅሎ የመንጋዎች ታሪክም ሲብስ እንጂ ሲቀንስ አልታየም። የንጹሑን የመጥምቁ ዮሐንስን አንገት ያስቆረጠው፣ እንዲሁም ወንጀለኛውን በርባንን ከእስር ያስፈታው የመንጋ ፍርድ ነው። የመንጋ ጦስ አያድርስ!።

ዓርብ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ልጄ የተሣፈረበት የሕዝብ ማመላለሻ ከአንድ የአማራ ክልል ከተማ በጧት ተነሣና ጉዞውን ወደ አዲስ አበባ ጀመረ። ጉዟቸውን በስልክ ስከታተል ግስጋሴያቸው እጅግ ፈጠነና - ዓይን ገብቷቸው መጨረሻቸው ላያምር - ስድስት ሰዓት አካባቢ ዓባይ በረሃን አቋርጠው ጎሐጽዮን ዳርቻ ደረሱ። እዚያ ሲደርሱ ግን ያልጠበቁትና ኢትዮጵያውያንን አልፎ ዓለምን ጉድ ያሰኘ የአጋች ታጋች ድራማ በኦሮሞ ቄሮዎችና በኦሮምያ ፖሊስ መርግ መርግ የሚያካክል ድንጋይ አስፋልቱ ተዘግቶ አታልፉም ተባሉ። ከብዙ መኪኖች ጋርም ተደርድረው በአሳልፉን አታልፉም ውርክብ ምሽቱ ለዓይን ሊይዝ ሆነ። መንገድ ላይ ሊያድሩ መሆናቸውን ሲያረጋግጡ ወደ ደጀን ተመለሱ። ጉዳዩን ቀድሞ የሰማው የደጀን ሕዝብ ከ3000 የሚበልጠውን ተሣፋሪና ባለመኪና በፍቅርና በወገናዊ የአለኝታነት ስሜት ተቀብሎ ካለው ብቻ ሳይሆን ያለውን ሁሉ በማውጣት በደስታ ማስተናገዱን ቀጠለ። እነዚህን ወገኖች ዘርና ብሔር፣ ሃይማኖትና አገር ሳይለይ ሁሉንም እኩል ተመልክቶ በሚቆዩባቸው ሦስት ቀናት ምንም ሳያወጡ ተራ ገብቶ ተንከባከበ። ሁለት ሌሊቶችን እዚያ ሲያድሩ ምግብም መጠጥም እያመጣ ወገኖቻችን ምንም ሳይሰማቸው ከረሙ። ማታ ማታም ወደየቤቱ እየወሰደ አልጋውን በመልቀቅ ራሱ ሰሌንና አጎዛ በማነጠፍ መሬት ላይ እየተኛ እንግዶቹን በፍቅር አስተናገደ። የኔ ልጅ ያደረበት ስምንት ሰዎችን የተቀበለ ቤት - ለምሣሌ - ሴቶች ተሣፋሪዎችን ከባለቤቱና ከሕጻናት ልጆቹ ጋር አስተኝቶ አባወራው ከወንድ እንግዶቹ ጋር መሬት አነጥፎ ተኝቷል። ይህ ነገር በየትም ዓለም የለም። ይህን ኢትዮጵያዊነት ነው እንግዲህ ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-አማራ ኃይሎች ሊበጣጥሱት እየጣሩ የሚገኙት።

ነባሩ ቱባ የኢትዮጵያዊነት ባህል እንደዚህ ነው። ይህን እውነተኛ ታሪክ ልጄ ሲነግረኝ ወደ ደጀን ወዲያውኑ ብረር ብረር የሚል ስሜት ተሰማኝ፤ ይህን ደስታየን ለመግለጽ ወደዚያው ሥራየ ብዬ እንደምሄድ ባውቅም ጊዜው ተንቀራፈፈብኝ። በዚህች እየሞተች በምትመስል አገር ይህን የመሰለ እንደብርቅዬው ዋልያ እንስሳ ሊጠፋ የደረሰ መልካም ወግና ባህል ስንመለከት፤ ውኃ እንዳገኘች የበረሃ ጽጌረዳ ነፍሳችን ትለመልማለች። ለባሰ ቀን እንዲሆነኝ ብዬ እንባየን እንደምንም በዘዴ ያዝኩት እንጂ ዓይኖቼ ተንቆርዘው ነበር።

መለስ ዜናዊ ቀድሞኝ በመናገሩና እንደተሳሳተም ብዙ ጊዜ በመዘገቡ እንጂ፤ እርሱ ያለውን አሁን ብለው ደስ ባለኝ። እርሱ የሁላችንም መሪ ሆኖ ተናገረ የተባለውን መናገሩ ከኔው የሚከፋ መሆኑን ብረዳም፤ አንዳንዴ በበጎ ጎኑ ካየነው በርግጥም ከዚህን መሰል የፍቅር ተምሣሌት ማኅበረሰብ መወለድን ቢመኙትና ምኞትንም በአደባባይ ቢገልጹ ክፋት የለውም ባይ ነኝ። ዱብቲ ላይ የተሠራውን መልካም ሥራ፣ አርሲ ነገሌ ላይ የተሠራውን መልካም ሥራ ... በሰማሁ ወቅት ይሄው ስሜት ተሰምቶኝ ነበርና፤ ቁም ነገሬ ከመልካምነት አኳያ እንጂ ከዘርና ከቋንቋ አንጻር እንዳይወሰድብኝ አደራ። በተቃራኒው አንድ ወቅት አንድ አካባቢ አንድ ዕብድ ሰው ዘሎ ገብቶበት ገጭቶት በመሞቱ ምክንያት በሕግ ጥላ ሥር የነበረን ሹፌር ከሁለቱ የፖሊስ ጣቢያው ጠባቂዎች ሕዝቡ በመውሰድ - (ጠባቂዎቹም ወደው ሠጥተው) - ቆራርጠው በገደሉበት የአንድ ኢትዮጵያዊ ከተማ ነዋሪ መኻል መወለድ ቀርቶ በዚያ በኩል ማለፍም አልፈልግም። ...

ለማንኛውም መለስ ያን ያስባለው ለክፋትና በክፋት ነው - ለሌላው ማኅበረሰብ በነበረው ጥላቻና ንቀት ኅሊናው ታውሮ ነው። እርሱ የተዋረደበት ንግግር ምንጩ ስንቅና ትጥቅ እንዲሁም ለጦርነት ግብኣት የሚሆን ተዋጊ ኃይል ነው። እኔ ብወለድበት የተመኘሁትና ስለተወለድኩበትም የምኮራበት ማኅበረሰብ ያሳዬው ተግባር ግን፤ ጆሯቸውን ቢቆርጧቸው ካለትግርኛና ኦሮምኛ የማይሰሙ ግን በበላይ ልሂቃን ተብዬዎች “ጠላቶችህ ናቸው! አጥፋቸው!” እየተባለ እስኪያንገሸግሸው የባጀበትን ወሬና አሉቧልታ ንቆ ትቶ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወገኑ ያላንዳች መድሎና መገለል እኩል ተንከባክቦ መንገዱ ሲከፈት በሰላም መሸኘቱ ነው። ሁሉም ሊማርበት የሚገባ ግሩም አርኣያነት ነውና ደጀኖች በዚህ አኩሪ ተግባራችሁ እንኳን ደስ አላችሁ። የአካባቢው የክብር ኗሪነት መብት እንዲሰጠኝ ማመልከቴ አይቀርምና፤ በተለይ ኃላፊዎች አቤቱታየን እንድትቀበሉኝ ከወዲሁ በትኅትና እጠይቃለሁ። ዕድሜ ይስጠኝ እንጂ በጡረታ ዘመኔ በዚህች ድንቅ ከተማ ውስጥ መኖር እንድችል አንድዬ እድሉን ቢያመቻችልኝ ደስታየ ገደብ የለውም።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ! አሁን ጣዕር ላይ ናትና የእምዬን የጣር ዘመን ያሳጥርልን። ትንቢትን ጨርሶ ማስቆም ባይቻልም በኢትዮጵያና በፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች መካከል የሚደረገውን አርማጌዴናዊ ጦርነት በአመክሮ እንዲያለዝብልን ሁላችን በየእምነት ቤቶቻችን ከክፋት ርቀን በቅን ልቦና ፈጣሪን እንለምነው።

ግርማ በላይ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ