ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የመደመር መጽሐፍ ምርቃት ላይ ፊርማ ሲያኖሩ

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የመደመር መጽሐፍ ምርቃት ላይ ፊርማ ሲያኖሩ

“በርግጥ ሰውዬውም ጭብጨባ ይወዳል”

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)

ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. - የዶ/ር ዐቢይ መጽሐፍ ተመርቋል። እኔም ከዚያ በተያያዘ ራሴን ታምሜ ዋልኩ - አሁን ድረስ። የነበረኝ የEmotional Quotient አንጻራዊ የተሻለ ደረጃ ወርዶብኝ ራሴው ስቸገርና ሰዎችንም ሳስቸግር አመሸሁ። የሚገነዘብህ ሰው ሲጠፋ ራስህን ያምሃል፤ ሲያምህ ሁሉም ነገር ያስጠላሃል።

“እውነት እንደፀሐይ ናት፤ ፊት ለፊት በባዶ ዓይኖች አትታይም” ይላል ናማያራ የተባለ ሕንዳዊ ደራሲ በአንዲት አጭር ልቦለድ ትረካው። በጣም እውነት ነው። የኔ ነው የምትለውን እውነት ይዘህ ግትር ካልክና የሚቃወምህ እንጂ የሚደግፍህ ካጣህ፤ በርግጥም በቃላት ልትገልጸው የሚቸግርህ ሕመም ጭንቅላትህን ሰንጎ ይይዝህና ትሰቃያለህ።

ባመሸሁበት ሥፍራ ከማንም ሳልስማማ ተጣልቼ ወጣሁ - በሰው ቁስል እንጨት የሚሰደው ጭፍን ዜጋ እየበዛ ነው። አያቶላ ጃዋር እየቀጠቀጠ የሚገዛትን አገር ከቤተ መንግሥት ውጪ ተሰሚነት የሌለው ወይም በማወቅም ይሁን በሆነ ነገር ተገዶ አክራሪ ኦሮሞዎች እንዳሻቸው እንዲምነሸነሹበት ወዶና ፈቅዶ ሥልጣኑን ያስረከበው ዐቢይ እንደሚያስዳድራት የሚያምነው ነሆለል ዜጋ ብዙ ነው። በሰውዬው የቅፈላ ንግግር የሚማረከው የጣፋጭ ቃላት ምርኮኛ የትዬለሌ ሆነና ከአሳባጁ ሸርና ተንኮል ይልቅ፤ የጣዖት አምላኪው ጅልነት ይበልጥ እያሳረረን ተቸግረናል። የታምራት ገለታንና የእሥራኤል ዳንሳን ተሞክሮና የአብዶ አጋንንታዊ ጥበብ ለዓመታት ቀስሞ የመጣው ዶ/ር ዐቢይ ለጊዜው አልተቻለም። በለስ ቀንቶት በምትሃታዊ ቱማታው ታላላቆችን ሳይቀር በእግሩ ሥር አውሏል፤ ለነገሩ ትንቢትም ይደግፈዋል። ለማንኛውም የኔ መጣላት ትንሽ መጮህና ዝም ማለት ነው። ዝም ስል ጓደኞቼ መናደዴን ያውቃሉ - በሚነሱ ነገሮች አለመስማማቴን ጭምር። የአሁኒቷን ኢትዮጵያ እርግፍ አድርገው ካልተዉ አደጋ አለው!

በሚሊየኒየም አዳራሽ ዐቢይ “እኔ ዴሞክራት መሪ ስለሆንኩ ብቻየን የምወስነው ነገር የለም” ሲልና ጭብጨባው ሲቀልጥ የተሰብሳቢዎቹ ማንነት ገባኝ። በዚህ ንግግሩም ከንቱነቱን ከመግለጥ በስተቀር ሰውዬው እውነትን እንዳልተናገረ እረዳለሁና፤ ፖለቲካ ምን ያህል ውሸታምና ከሐዲ እንደሚያደርግ ታወሰኝ። የሚገርመው ግን የርሱ ሐሰተኝነት ሳይሆን፤ እዚያ የተኮለኮለው አጨብጫቢ የአእምሮ ዘገምተኛና አድር ባይ ነው። ዶ/ር ምሕረት ደበበን የመሰለ በጣም የማደንቀው ሰው ሳይቀር በዚያ የጨረባ ተዝካር፣ በዚያ የስብዕና ግንባታ የአምልኮት ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሌሎች ዘገምተኞች የዚያ በተግባር የሚቀንስ በቲዎሪ ግን የሚደምር አርቲ ቡርቲ መጽሐፍ ዋና አድናቂ ሆኖ ሲገኝ በሰዎች ተፈጥሮ ተገረምኩ። በአገራችን በተጨባጭ ምን እየተከናወነ እንዳለ የሚገባው ሰው በዚያ የቁጭ በሉ የሚሌኒየም ትርዒት ተገኝቶ ለነገ ሀፍረትና የሕሊና ትዝብት አይዳረግም - ሕሊና ላለው። እዚያ ለተገኙ ዜጎች በነሱ ምትክ እኔ አፈርኩ። አንዳች እርኩስ መንፈስ ቢያስገድዳቸው እንጂ በውዴታቸው እንደዚያ እጃቸው እስኪግል እንደማያጨበጭቡም ገመትኩ። ልብን ከሚሰብር ኀዘን ባለፈ ዶ/ር ዐቢይ በተለይ በዚህን ወቅት ምን የሚያስጨበጭብ ነገር አለውና?! “ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል” ይባላል። በፈርንጆች የሤራ ፖለቲካ የተገኘ ባዶ የኖቤል ሽልማትም ኃጢኣተኛ ሰው ንስኀውን ሳያወርድ በጉልበቱ ወስዶት ሣለ፤ ነገር ግን በረሃ ላይ እያጣጣረ ለወደቀና የክርስቶስን ሥጋና ደም መቀበል እንዳይችል ከቤተ መቅደስ ለራቀ ሰው ከማይገባው በሥውር ተነጥቆ ለሚገባው እንደሚደርሰው ሥጋ ወደሙ የሚመሰል ነው። ስንቶች እየተገባቸው ሳያገኙ ዐረቦችን በተለይም ግብጽን ለማስደሰት ሲባል በኛ ይጫወታሉ።

አፄ ኃይለሥላሴም ሆኑ መንግሥቱ ኃይለማርያም የዚህን ሰውዬ ያህል አላጭበረበሩም፤ አጭበርብረውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል አልተመለኩም። ሚሌኒየም አዳራሽ ውስጥ የተገኙና ሰውዬውን ሰማየ ሰማያት በመስቀል የሚለው ነገር ገና ሳይገባቸው ዐረፍተ ነገሩን በቅጡ ሳይጨርስ በቃላትና በሐረጋት ሳይቀር ያጨበጨቡ ኢትዮጵያውያን፤ የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ የማያውቁ ደናቁርት ከመሆናቸውም በተጨማሪ የአእምሮ ችግር እንዳለባቸው ለመገንዘብ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ማየት ብቻ በቂ ነው። ይህን እውነት በገሃድ የምመሰክረው የዛሬ ታሪካችን ተመዝገቦ የሚቀመጥ እንደመሆኑ በነፃነታችን ማግሥት - አንድዬ ለዚያ ካበቃኝ - አሁን እየሆኑ ያሉትን ፍጹም ተቃራኒ ኹነቶች በማነጻጸር ይሆናል። ከዚህ ዐይነቱ አምልኮ ካልወጣን ደግሞ መቼም ሰው አንሆንም።

በርግጥ ሰውዬውም ጭብጨባ ይወዳል። እውነትም እንደሚባለው የናርሲዝም ተጠቂ ሳይሆን አይቀርም - ራስን ከልክ በላይ የማፍቀርና በሌሎች የመመለክ መጥፎ ልክፍት። ይህ ዐይነቱ በሽታ በነሂትለርና ሙሶሊኒም ታይቷል። ዐቢይ አያምንበትም እንጂ ቢያምንበት ኖሮ ወደ ዘብር ገብርኤል ሄዶ አንድ ሦስት ያህል ሰባቶችን ቢጠመቅ ከዚህ ሰይጣናዊ የእዩኝ እዩኝ የፎቶና ቪዲዮ ካሜራ ፍቅር ይፈወስ ነበር። ባናውቀው እንጂ መጥፎ በሽታ ነው።

ምንም ቁም ነገር እንዳልተናገርኩ ይገባኛል። ቢሆንም ለምን ከዚህ በላይ ያልኩትን እንዳልኩ ሁሉንም በዝርዝር ስለምታውቁት ማብራራት አይጠበቅብኝም። የሰውን አድርባይነትና አጨብጫቢነት እንዲሁም ለዚህ ያበቃውን የአእምሮ ዘገምተኝነት ከገለጥኩ በቂ ነው። የኢትዮጵያን የወቅቱን ሁኔታ የሚረዳ በዚያ ልጭና ጎፈሬ ወይም ቂጥ ከፍቶ ክንንብ ዐይነት ከእውነት የሚጣረስ ዝግጅት መናደዱ አይቀርም።

ቢሆንም … ቢሆንም … በጃዋርና በበቀለ ገርባ፣ በዶ/ር ገመቹና በሕዝቅኤል ጋቢሣ የሚመለመልና በኦሕዴድ ሠልጥኖ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት አንድ ሐሙስ የቀረው አክራሪ ኦሮሞ በገነነባትና ከላይ እስከታች አገሪቱን በወረረበት ወቅት፤ አየር መንገድን፣ ባንክን፣ ትምህርት ሚኒስቴርን፣ ሌሎች የሚኒስቴርና የኮሚሽን መ/ቤቶችን፤ ማዘጋጃን፣ ክፍለ ከተማን፣ ወረዳን፣ ቀበሌን፣ ንግዱን፣ ፖለቲካውን፣ ሃይማኖቱን፣ መሬቱን፣ ኮንዶምንየሙን፣ ኮንዶሙን፣ … ሁሉንም ኦሮሞና የኦሮሞ የማድረጉ ኦነጋዊ ተግባር በተገባደደበት ወቅት፤ ይህን መሰል የተጨፈኑ ላሞኛችሁ የመደመር ፖለቲካ የሰም ለበስ ቅኔ ሲመረቅ ማየት ደግ ነው - የሚገርመው ወያኔዎች በፈራ ተባ 27 ዓመታት የፈጀባቸውን ሁሉንም ወይም ቸርነትን በተላበሰ አገላለጽ አብዛኛውን ሥልጣንና የጥቅም ምንጭ በገዢው ጎሣና በሆድ አደር ተላላኪዎች የመጠቅለል አባዜ፤ እነዚህኞቹ ንክሮች ገና ሁለት ዓመትም ሳይሞላቸው አጠናቀቁት። የኖቤል ሽልማቱ በዚህ ርዕስ ቢሆን ይልቁንስ አሣማኝ በሆነ፤ ይህን ዐይነት ርዕስ ካላቸው ሸላሚዎቹ። “ራሴን መትተው እግሬን ቢያኩኝ” አይገባኝም አለ ትግሬ - ዘርን መሠረት ባደረገ መልክ ምሥኪን ዜጎች ላይ የሚሠራው ግፍና በደል ሌላ፤ የሚመረቀው መጽሐፍ ሌላ፤ በሀፍረተቢስነትና ይሉኝታቢስነት ወያኔን የሚበልጥ እንደማይኖር ቀደም ሲል የወሰድኩት አቋም ፈተና የገጠመው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ነው። “ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ” አሉ? አንዱ ፈላስፋ “ተማሪ ከአስተማሪው ካልበለጠ ምኑን አስተማረ?” ይል ነበር። የሕወሓት ተማሪዎች ኦሕዴድና ኦነግ ፈጣሪያቸውንና መምህራቸውን በልበ-ሥውርነት አስከንድተውት ዐረፉ። “ወያኔ ማረኝ!” እንዳንል እፈራለሁ። አሸናፊው ጎልቶ እስኪወጣ አገራዊ የነፃነት ትግሉ በሦስት ቃላት ሊገለጽ በሚችል መልኩ የሚቀጥል ይመስለኛል፡- ብልጥነት፣ ሞኝነትና ብልኅነት

ላጨብጫቢዎቹም ለአስጨብጫቢዎቹም መልካም የጣዖት አምልኮት ዘመን ያድርግላቸው! ሲፈልጉ ከቢዮንሴ ቀጥለው 46ኛ ጽላት ያስቀርጹለትና ለሁለትም ለሦስትም ጌቶች የሚገዙ ዲያቆናትና ቀሣውስት ከሣሎናቸው ስለማያጡ ሠርክ ያስቀድሱለት። አንድዬ ይህን ሁሉ አፍዝ አደንግዝ እያዬ ግና ዝም አይልምና ሁሉም በቅርብ ዋጋውን እንደሚያገኝ አንጠራጠር። ቀልድ በዚህኛው እንጂ በዚያኛው የለም። ችግሩ ሞት ሲዘገይ የቀረ መምሰሉ እንጂ፤ ሌላውን ሁሉ ትተነው ምሥራቅ አፍሪቃን በፍርሀት ያምጰረጰረው መንጌ ዛሬ እርጅና ቤቱን ሠርቶበት የዝምብ መጫወቻ ሆኖ የለ? …

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ