Happy Ethiopian Newy Year! መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልዎ!

Jawar Mohammed

አክቲቪስት ጃዋር መሐመድ (በግራ)

“ለሁሉም በሚበጅ ጉዳይ ላይ ተቀራርቦ ያለመታከት መነጋገር ያስፈልጋል፤ በግራ እጅ እየካቡ በቀኝ መናድ ኪሳራ ነው - በፍቃዱ ሞረዳ (ጋዜጠኛ)

የውጭ አገር ዜግነት ባላቸው ሰዎች የሚተዳደሩ ሚዲያዎችን አስመልክቶ ዐቢይ አሕመድ ለኢሕአዴግ ፓርላማ ያሰሙትን ንግግር/ዛቻ፣ አንዳንድ ቅን ልቦች "ጃዋርን የሚመለከት አይደለም" እያሉ ሊያረጋጉ እየሞከሩ ነው። "እንደአፋችሁ ያድርግልን" እንላለን።

ደግሞም እንዲህ እንላለን።

የዐብይ አሕመድ ነፍስ በግራም በቀኝም፣ ከፊትም ከኋላም፣ ከውስጥም ከውጭም፣ በጠላትም በወዳጅም … ተወጥራ የተያዘች ናት። ባተሌ ምስኪን ነፍስ።

የሰሜን አጋሮቻቸው የአማራ ክልል ሹምምንትና አንዳንድ ሽፍቶች ጃዋርንም ሆነ ሚዲያውን አስመልክቶ በይፋ እየተናገሩ ያሉትን ግምት ውስጥ አለማስገባት ለዐቢይ ትልቅ ኪሳራ ነው የሚሆነው። ቢያንስ አጋሮቹን ማረጋጋት ይኖርበታል። የመደመር ሐሳብ በገነነበት በአሁኑ ሰዓት፤ ርቀው ያሉትን እነአብንን ለማቅረብም ማሽኮርመሚያ ሊያስፈልግ ይችላል።

"ስለዚህ ሰውዬ አንድ ነገር በል እንጂ …" የሚለው የውስጥ ግፊት ምን ያህል ሊበዛ እንደሚችል እንገምታለን። እናም ከፓርላማ ስብሰባ የተወረወረው ቀስት በቀጥታ ጃዋር ሲራጅን የሚመለከት መሆኑን ሙትም አይስተውም።

ጃዋርን በግል ማስፈራራትም፣ ሚዲያውን መዝጋትም ይቻላል። አዲስ የሚቀሰም ልምድ የለም። ትናንት ሲደረግ የነበረውን እንደገና መሞከር ነው። እንደገና ከሠራ።

ጃዋር ሁለት ምርጫ አለው። አንድም የአሜሪካ ፓስፖርቱን ለባለቤቶቹ መልሶ፤ "ከዛሬ ጀምሮ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ እኔ ኦሮሞ ነኝ" ብሎ ልበሙሉ ዜጋ ሆኖ ፊት ለፊት መጋተር። የሚያስፈልገውንም ዋጋ ለመክፈል ኅሊናዊና አካላዊ ዝግጅት ማድረግ። ካልሆነም አገሩን ጥሎ በመውጣት ላለፉት ዓመቶች ሲያደርግ እንደነበረው ትግሉን ከውጪ መቀጠል።

ሁለቱም ምርጫ ለኢሕአዴግ መንግሥት የሚፈልገውን እፎይታ ሊሰጠው አይችልም። ዛሬ በኦሮሚያ ውስጥ የጃዋርን ጎራ በመግፋት ሰላምን ማግኘት መቻል ባይታሰብ ይሻላል። ይህንን የምንለው ደጋፊ ከመሆን ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን ሐቅ ስለምናውቅ ነው። ጃዋር ቢያንስ ቢያንስ ነፃ የአርሲ መንግሥት መሥርቶ ማንም በዋዛ የማይነቀንቀውን ባንዲራ ጭላሎ ላይ መትከል ይችላል።

እናም … ከኦነግ ጋር ተላትሞ፣ ከእነጃዋር ጋር ተላትሞ፣ ከሕወሓት ጋር ተላትሞ፣ ከኦፌኮ ጋር ተኳርፎ … አንድን ወገን ብቻ አስደስቶ የዚያችን አገር ችግር ለመፍታት ማሰብ አዳራሽ ሙሉ ደጋፊን ሰብስቦ የማስጨብጨብን ያህል ቀላል አይደለም።

በተለይ በሚዲያ ጉዳይ በማንኛውም ሰበብ የሚደረገውን ተፅዕኖ መታገስ የማይቻለው፣ ትናንት ነፃውን ሚዲያ ሲያፍኑና ሲያሳፍኑ የነበሩ አንጎበሪያም ካድሬዎች፤ አሁንም አርፈው ስላልተቀመጡ ነው። በጋዜጠኛ ጆሮ ላይ ስልክ በመዝጋት የጀግንነት ካባ የሚደረብላቸው ፀረ-ዴሞክራሲ እንወደድ ባዮች ሞልተዋል። ሚዲያን ማፈን፣ የዜጎችን ብሶት ማፈን ነው። "ስለቅማንት፣ ስለአፋር፣ ስለሶማሌ፣ … ለምን ትዘግባላችሁ?" ማለት ሳይሆን፤ "ያልተመቸኝ ነገር አለ፣ ጥያቄ አለኝ …" የሚለውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተጠግቶ ማነጋገር ነው ሥልጡንነት። "አሸባሪ ነው፣ ፅንፈኛ ነው፣ ክንፈኛ ነው" እያሉ ከመፎከር። ሚዲያውን ቀድሞ ቀዳዳዎችን መዝጋት። በርህን ክፍት አድርገህ፣ ነውርህን አደባባይ አስጥተህ፤ "ሚዲያ እንዲህ አድርጎኝ …" አትበል። ወይ ከሚዲያው ጋር ተባብሮ ለጋራ ዓላማ መሥራት … አልያም በማለቃቀስ መትጋት።

ለማንኛውም የጠቅላይ ሚንስትሩ ዛቻ ማንንም ይመልከት ማንን ድርጅታቸውንም፣ ደጋፊዎቻቸውንም የሚጠቅም አይደለም። ለሁሉም በሚበጅ ጉዳይ ላይ ተቀራርቦ ያለመታከት መነጋገር ያስፈልጋል። በግራ እጅ እየካቡ በቀኝ መናድ ኪሳራ ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እንኳን በጊዜ ብጫ ምልክት አሳዩን። እኛም ወደአገራችን ተመልሰን በሚዲያ ለአገራችን በጎ አስተዋጽኦ ለማበርከት የጀመርነውን ሥራ እንደገና እናየዋለን። ፕሮጀክታችንንም ወደ ዶሮ እርባታ እንቀይረዋለን። የውጭ አገር ፓስፖርት ይዞ “ኩኩሉ …" ማለት ይቻላል አይደል?

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!