ዳግም ትንሣኤ

ዳግም ትንሣኤ

ለዳግማይ ትንሣኤ እሁድ የተለየ አዋጅ የወጣ ይመስል ነበር

(ማህደር ዳ. | ኢዛ) ባለፈው እሁድ ሚያዝያ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው። በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ዳግማይ ትንሣኤ ነበር። በዚህ ዕለት ዘመድ አዝማድ የሚገናኝበት፤ አክፋይ ይዞ እንኳን አደረሳችሁ፣ እንኳን አደረሰን የሚባባልበት ቀን ነው። እንዲህ ያለውን የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትና መልካም ምኞት ለመግለጽ አገር አቆራርጠው ወላጆችና አማች ቤት የመሔዱ ልምድ በአብዛኛው የአገሪቱ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚከናወንበት ነው። የቆየ ወግና ልማዳችን ኾኖ ለዘመናት እየኖርነው እስካሁን ደርሰናል።

ወትሮ ልክ ዳግማይ ትንሣኤ የሚውልበት ዕለት በየትኛውም አካባቢ በተለየ የሚስተዋለው ቤተሰብ ሰብስቦ ለአክፋይ የሚያዘውን ስጦታ ሸክፎ የሚንቀሳቀስ ማየት በዘንድሮው ዳግማይ ትንሣኤ ብርቅ ኾኗል።

በዕለቱ የአዲስ አበባን ጐዳናዎች በተለያዩ ሰዓታት ለመቃኘት እንደሞከርኩት በዳግማይ ትንሣኤዎች ወቅት ልጆች አስከትለው፤ አባወራው በጋዜጣ የተጠቀለለ አረቄ ወይም ወይን ይዞ፤ እማወራ በዳንቴል የተሸፋፈነ ዳቦ አዘል አድርገው ወደ አንዳቸው አማች ቤት ሲሔዱ የለመደ ዓይን፤ በዘንድሮው የዳግማይ ትንሣኤ መመልከት አይታሰብም።

ኾነ ብዬ እንዲህ ያለውን ነገር ለመመልከት ያደረግኩት ጥረት አልተሳካልኝም። ግን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ፤ በተለይ ዳቦ አዝለው፣ የሚቀማመስ ነገር አስጠቅልለው፣ ባላቸው አቅም የአገር ባህል ልብስ ለብሰው፣ ታክሲ ሲጠብቁ ወይም ከታክሲ ወርደው አክፋያቸውን ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ እናያቸው የነበሩ የቤተሰብ አባላት፤ ዛሬ እግራቸው ተሰብስቧል። ለዓመታት ያስለመዱትን ዘንድሮ መከወን አልቻሉም። ይህ ሁሉ የኾነው ደግሞ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እንዲህ ያሉ ማኅበራዊና ቤተሰባዊ ክንውኖችን ከማድረግ መቆጠብ ግድ በመኾኑ ነው።

እንደ ዘንድሮ የትንሣኤ በዓል ሁሉ በዳግማይ ትንሣኤም ወትሮ ሲከናወኑ የነበሩ ክንውኖችን ማድረግ አልተቻለም። መንገዶች ከወትሮ በተለየ ጭር ብለዋል። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ የግል ተሽከርካሪዎች በፈረቃ እንዲሽከረከሩ በመደረጉና እሁድ ግን ከዚህ ከልካይ አዋጅ ውጭ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ሞላ ጐደለ የሚለውን ታርጋቸውን ሳያስቡ የሚንቀሳቀሱበት ቢሆንም፤ እንደ ዳግማይ ትንሣኤዋ እሁድ የከተማችን መንገዶች ጭር ብለው አልታዩም።

ለዳግማይ ትንሣኤ እሁድ የተለየ አዋጅ የወጣ ይመስል ነበር። እንዲህ መኾኑ በመልካም የሚታይ ነው። በፋሲካ ዋዜማ የገበያ ቦታዎችንና መንገዶቻችንን ለተመለከተ፤ የኮሮና ወረርሽኝ ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ያሳየ ነበር። አሁንም የዛ ሰሞን ያልተጠበቀ የግብይት ሥርዓታችን ምን ይዞብን እንደሚመጣ ባናውቅም፤ በዳግማይ ትንሣኤ ዕለት ግን ከዚያ በተለየ እንቅስቃሴዎች መገደባቸውንና ብዙዎች በቤት መኾናቸውን መንገዶቻችን ነግረውናል።

ነገም ከነገ ወዲያም በተቻለ አቅም ሰብሰብ የማለት ልምዱን ማዳበር ሥጋታችንን ይቀንሳል። ለብዙዎች መኖር አስተዋጽኦ እያበረከትን ስለመኾናችን ያስገነዝበናል።

በእርግጥም አታድርጉ የተባልነውን ባለማድረግ አብዝተን የምናተርፈው ትርፍ ዜጐችን ከሞት መታደግና ብሎም የአገርንም መከራ ይቀንሳል። ስለዚህ አሁንም ቫይረሱን ለመከላከል ከመንግሥት፣ ከሕክምና ባለሙያዎችና ከሃይማኖት አባቶች የሚተላለፉ መልእክቶችን አክብሮ ከመጓዝ ውጭ፤ አሁን ላይ ሌላ መፍትሔ የለንምና ለተወሰኑ ጊዜያት ይህንን በማድረግ ይቺን ጊዜ ማለፍ የግድ ይላል።

እንዳለፈው ሳምንት ያሉ ተፋፍጐ መገበያየት አደጋው ቀላል ካለመኾኑም በላይ፤ ማን አለብኝነት ያሻንን እናደርጋለን ብሎ መንቀሳቀስ ጠልፎ ይጥላል። እንደ ሕዝብም ኃላፊነት የሚሰማን፤ ዛሬ የተነፈግነው ነገር ነገ ልንደርስበት የምንችል መኾኑን አውቀን እንንቀሳቀስ።

ዛሬ የተመለከትነው አንፃራዊ መታቀብ እና የቆየ ልምዳችንን ትተን ማሳለፋችን፤ ከዚህም በኋላ ላሉ ቀናት የምንመለከተው ይኾን ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን! ነገራችንም ያዝ ለቀቅ እንዳይኾን ለመልካም የሚሰጡ ትእዛዞችን የማክበር ልምድም ልናዳብርበት የምንችልበት አጋጣሚ ይሁን።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!