የወያኔ ባለሥልጣናት

የወያኔ ባለሥልጣናት

(በወያኔአዊ ቋንቋ የተጣፈ ስላቅ)

ዘጌርሳም

ከደደቢት በመነሳት አራት ኪሎ ለመድረስ ረጅምና አድካሚውን ጉዞ የጀመርነው ገና ጎሕ ሳይቀድ ነበር። ከፊት ለፊታችን የተንጣለለ የአርብቶና አርሶ አደር ልማታዊ እንቅስቃሴ ይካሄዳል። እንስሳቶች ሳይቀሩ ደፋ ቀና ይላሉ። ልማታዊውና አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊው መንግሥት በመልሶ መደራጀት ያሰባሰባቸው ናቸው። አብዛኞቹ ተጋዳሊቶችና ተጋዳዮች ሲሆኑ፤ በተለጣፊነት የተሰለፉም አሉበት። ተለጣፊዎቹ በአብላጫ የሚያገለግሉት በእቃ ተሸካሚነትና መንገድ መሪነት ሲሆን፣ ፈንጂ እንዲመክኑም ይታዘዛሉ። ተለጣፊዎቹ በአብላጫው ከአናሳ ብሔረሰቦች የመጡ ሲሆኑ፣ የተማረኩና የጥቅማጥቅም ተስፋ የተሰጣቸው፣ ከትምክህተኞችና ጠባብ ብሔረተኞች የመጡ በቁጥር ብዝኀትነት አላቸው። ሕጉ አሁንም በረሃ ላይ እንደነበረው ስለሆነ ዕንስታትና ተባዕታት አብረው እንዲታዩ ቅቡልነት የለውም። ይህ ተጥሶ ቢገኝ ወደ ባዶ ስድስት ያስወረውራል። በአንፃራት ግን ዕንስት ከዕንስት፣ ተባዕት ከተባዕት መገናኘት ትግሉን ለመሸርሸር እስካልተንቀሳቀሱ ድረስ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ መብታቸው ነው። እነሱም ቢሆን ይህ በሕገመንግሥቱ ቅቡልነቱ ታውቆ እንደተረጋገጠ ያውቃሉ። ጉዳዩን አስመልክቶም የትሃድሶ ሥልጠና በየደረጃውና ዘርፉ ተሰጥቷል።

ምንም እንኳን በልማቱ እንቅስቃሴ ላይ ብዝኀን ተግዳሮቶች ቢሸነቆሩብንም፤ የግልና የቡድን ግምገማ ከማድረግ ተጨማሪ፤ ጥልቅ ትሃድሶ በመውሰድ ከተዘፈቅንበት የሙስና አዘቅትና የብቃት ማነስ ለመመለስና በጥልቀት ለመታደስ ቆርጠን ተነስተናል። ለወዳጆቻችንም ይህንኑ ስላስታወቅን የረድኤት እጃቸውን እንዳያሳጥሩብን ከወዲሁ ተማፅነናል። ይህን ታሳቢ በማድረግ ተመሳሳይ ሥልጠና በየደረጃው ከቀበሌ እስከ ላዕላይ አካሉ በየክልሉ እንዲካሄድ በምልአተ ድምፁ ተቀባይነትና አፅንዖት ተሰጥቶት ውሳኔው ተላልፏል። በዋነኛነትም የተለያዩ የቢሮ ኃላፊዎች፣ ከመከላከያ የተወከሉ ከፍተኛ ባለማዕረግ ኢንስፔክተሮች፣ ኮሚሽነሮች፣ ኮማንደሮች፣ ሳጅኖችና ኮንስታፕሎች እንዲሳተፉ ተደርገዋል። ሥልጠናው እንዳለቀም መርኀግብሩን በማይጣረስ መልኩ በተግባር እንዲፈጽሙና እንዲያስፈጽሙ ጉባኤ በማያሻማ መልኩ በማስረገጥ ወስኗል። ከየብሔር ብሔረሰቡ የተውጣጡ ልሂቃን በጋራ አጥንተው ካቀረቡት ግምገማ በመነሳት የመተካካት አስፈላጊነት ያለምንም ተቃርኖ ጉባኤውን አስማምቷል።

ምንም እንኳን ጠባቦችና ትምክህተኞች ባልተጠበቀ ሁኔታ ከጭድና እሳትነት ብዥታ ተላቀው ዘር-ተኮርና ብሔርተ-ኮር እንቅስቃሴ በጋራ ለማካሄድ ሲንቀሳቀሱ ቢታዩም፤ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ የመከላከያ ኃይላችን የማያዳግምና ቆራጥ እርምጃ በመውሰድ ጥቃቱን አምክኖታል። መከላክያ ኃይላችን የወሰደውን እርምጃ አስምልክቶም፤ ሕጋዊ ሽፋን ስለሚሻው ለተከበረው የሕዝብ ምክር ቤት በማቅረብ የሙሉ ድጋፍ ድምፅ በማሰጠት መከላከያው የማጥቃት ምኅዳሩን እንዲያሰፋ ረድቶታል። የደህንነት መዋቅራችንም በበኩሉ የዱሮ ባንዲራ ናፋቂዎችና በአዲስ ቤተመንግሥት ለመግባት ከሚያቆበቁቡት ጠባቦች ጎን በመሰለፍ፤ የዘረጉትን የግንኙነት መረብ ለመበጠስ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። አሁን አሁን መርዛማ ራስ ምታት የሆነችብን ኦሮማራ የተባለች የማትታይና የማትዳሰስ ፈጣን የነውጥ ቡድን ናት። ጉልበትና ፍጥነቷም ከጃፓን ላንድክሩዘርና ፓጃሮ ይልቃል። ይህች ቡድን ፍጥነቷ ከወዲሁ ካልተገታ፤ አይደለም አራት ኪሎ መቐለ ያለውን ቤተመንግሥት ተቆጣጥራ፤ እኛንም ከራሳችን እስር ቤት ደደቢት ትጨምረናለች የሚለው ስጋታችን ከፍተኛ ነው።

የዕድገታችን መፃዒ እድል የሚወሰነው ያስመዘገብናቸውን እሴቶች ታሳቢ በማድረግ መሆኑን በማስረገጥ መናገር ቢቻልም፤ የሙስና መስፋፋትና ብልሹ አስተዳደር ተደምሮበት፣ የሙሰኞች ድብቅ ሴራ በኢኮኖሚያችን ብቻ ሳይሆን፤ በሁለንተናችን ላይ ተጣራሽነት ያለው አኀዛዊ ጣራ ነክ ግሽበትን አስመዝግቦብናል። ይህ ደግሞ ዕድገታችን የኋልዮሽ ጎተተው ማለት ነው። ይህ በመሆኑም ወዳጅ አገሮች ሳይቀሩ አመልካች ጣቶቻቸውን በትውፊቶቻችን ላይ መቀሰር ጀምረዋል። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ደግሞ ተላብሰነው የቆየነው ድባባችን ቀልቡ ይገፈፍና ምክነትን በመጎናፀፍ መፃዒ ዕድላችንን ፀሊም ያደርገዋል። እስካሁን የታገልንለት ራዕያችንና መፃዒ ጉዟችን፤ አንድም በሁሉም ዘንድ ቅቡልነትን በውዴታ ማግኘት፤ ካልተሳካም ሕገመንግሥቱን ተገን በማድረግ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ተፅዕኖ መፍጠር፤ ይህ ሳይሳካ ቢቀር ደግሞ የአገሪቱ አንድነት እንዲበታተን ማድረግ ይሆናል። ዓላማው እንዲሳካ ደግሞ እስከ ሦስት ዘር የሚቆጠር የመሪው ፓርቲ የደምና ሥጋ ዝርያ ያላቸውን፣ ስማቸውንና የብሔር ብቅለታቸውን እየቀየሩ በቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች ውስጥ ተሸጥሽጠው እንዲቀመጡ ማሰማራት ታስቧል። አንድ ሊሰመርበት የሚገባው ከጅምሩ ስንገባ በአገሪቱን ሙሉ ካፒታሊዝም እስኪገነባ መግዛትና ኢኮኖሚውን ማሳደግ በመሆኑ፤ ይህ ገቢር ሳይሆን ቢቀር ሥልጣን እንደማንለቅ በማስረገጥ መናገራችን በማያሻማ መንገድ ሁሉም ከወዲሁ ሊያውቅ ግድ ይላል።

ከጅምሩ የአንድ ለአምስት ጥርነፋውን ፖሊሲ ስናወጣ፣ ጠላቶቻችንንና ተቃዋሚዎቻችንን በቀላሉ መደፍጠጥ እንዲያስችለን ነበር። ካድሬዎችና የደህንነት አባላት ባሳዩት ድክመትና የሙሰኝነት ንቅዘት ከመጠርነፍ ወደተጠርናፊነት አድርሶናል። ያስተማርናቸውና የሾምናቸው ሳይቀሩ እኛኑ መልሰው እየደፈቁን ይታያሉ። ክህሎቶቻችንና ስኬቶቻችን ትቢያ እየለበሱ ይታያሉ። የሕዳሴው ግንባታም በጠላቶች ሴራ እንፍሽፍሽ ሆኖ ቀርቷል። እስካሁን የተከናወነው የግንባታ ሥራም ከተራ የውሃ ማቆር ተግባር የላቀ አይደለም። የግንባታው ዘገምተኝነት በዚህ ከቀጠለም የግብፅና ሱዳን ሲሳይ መሆኑ አይቀሬ ይሆናል። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ከንቅዘት በወረደ ደረጃ በስብሰናል፤ በጥልቅ ለመታደስ የተገደድነውም ወደን ሳይሆን፤ ትናንት ነፍጥ እንስጣችሁና ውጉን ያልናቸውን ሁሉ ብዙ ደረጃ ወርደን ለሰላም ስንል እንደራደር ለማለት ነው። ለሰላምና የመፍትሔው አካል ለመሆንም ጠቅላይ ሚንስትሩን ሳይቀር በፍቃዱ ከሥልጣኑ እንዲወርድ አድርገናል። በኛ በኩል ይቅርታ እንድንጠየቅ ብንፈልግም ባለመሳካቱ፤ ተከታዩን ስጋት ለመሸወድ ይረዳል ከሚል እሳቤ በመነሳት፤ ሁሉንም እስረኞች ያለቅድመ ሁኔታ በምሕረት ለቀና።

ኢኮኖሚያችን ያስመዝገበው እመርታ ብለን ያቀርብነው ሪፖርት፣ የወዳጆቻችን እጅ በረዥሙ እንዲዘረጋ አርጎ ነበር። ለዚህ የረዳን ደግሞ የክልል አንድ ዕድገትና ስኬት አንድና አንድ በመሆኑ ሌሎቹን ክልሎች በማስረጃነት ብናቀርብ ትዝብት ላይ ስለሚጥለን፤ የሁሉንም ድምር በጀት ወደ ክልል አንድ ማዛወሩ ለስኬቱ አወንታዊ ቅቡልነት ይሰጣል ብለን በማመናችን ነው።

በየጊዜው በልሂቃኖቻችን አቅራቢነት በተካሄዱት አውደ ጥናት መሰረት፣ ለወዳጆቻችንና ለጋሾቻችን አኀዙን ለነሱ ዕይታና ግምገማ በሚስማማ መልኩ በመቀመር፤ ለአንዳንዶቹም ከሰጡት ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ወደኪሶቻቸው መልሰን በመሸጎጥ ይበልጥ ቅቡል የሆነ እምነታቸውንና ድጋፋቸውን እንዲያጎለብቱ አግዞናል። በዚህ ዘዴ ተግቶ በመሥራትም የግዛት ዘመናችን በትንሹ መቶ ዓመት ሊያስቆጥር ይችላል የሚል ምኞትና ተስፋ አለን።

ለተግዳሮቶቻችን ጉልበት እየሰጡ ያሉት ከራሳችን ንቅዘቶች በተጨማሪ ሃይማኖተኞችና ባንዲራ አፍቃሪዎች በመሆናቸው፤ ትምክህተኞችንና ጠባቦችን ለማንበርከክ የልማታዊ መከላከያ ኃይል አባላትን የግል ኑሮና ምቾት በማሟላት፤ በማንኛውም ጊዜ የሚቀሰቀስን ጉድኝትና ሕዝባዊ ነውጥን በቀላሉ መደፍጠጥ ቀላል ይሆናል። በመሆኑም ገደብ የለሽ ሥልጣን ለሠራዊቱ መስጠት አስፈላጊነቱ ታምኖበታል። ምንም እንኳን የትምህርት ደረጃቸው እጅግ የወረደ ቢሆንም፤ ለማበረታቻና ለማነቃቂያ ሲባል በዓለም ላይ ማንም አገር የሌለው የጀኔራሎች ቁጥር ሠራዊታችን እንዲኖረው ተደርጓል።

የመሬት አጠቃቀምን በተመለከተ ባለቤትነቱን ለመንግሥት በማድረግ፤ ሽያጩ በሊዝ ግብይት በተቀላጠፈ ሁኔታ እየተከናወነ ሲሆን፣ መርኀ ግብሩ የመንግሥትን የካፒታል አቅም በስፋት ሊያጎለብት ችሏል። ይህ የሊዝ ፖሊሲ አተያይ የከፈተው በር መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚ ያረገው፤ በርካታ የማኅበረሰቡን አባላትና ሆድቀለብ ባለሥልጣናትን የደለቡ ቱጃሮች አድርጓል። ይህ ዐይነቱ የጥቅም ትስስር ደግሞ እየተካሄደ ላለው ልማታዊ ግንባታ ተጨማሪ ጉልበት ሰጥቶታል። በተለይ የጨረቃ ቤቶች ግንባታና ገበያው ወደር ያልተገኘለት የኢኮኖሚያችን እመርታ በር ከፋች ቁልፍ ነገር ሆኖ በመገኘቱ፤ በሁሉም ክልሎችና ከተሞቻቸው ግብይቱ በመጧጧፍ ላይ ይገኛል።

ምንም እንኳን ጠላቶቻችን የሚያናፍሱብን ቱሪናፋ ዐመፅ ቀስቃሽና አሉታዊ አቅጣጫ አመልካች መስሎ ቢታይም፤ ወዳቀድነው የካፒታሊዝም ኢኮኖሚ ግንባታ ከመገስገስ ለአንዴ እንኳን ሰከን ለማለት አላሰብንም ነበር። ታዲያ ምን ያደርጋል ”ቁጭ ብለው የሰቀሉት፤ ቁሞ ለማውረድ ይቸግራል” እንዲሉ፤ ሐቁ የፈናጅራ፤ ጉዟችንም ቁልቁለት ሁኗል። ትናንት ቁጭ ብድግ ሲሉልን የነበሩት፣ ዛሬ ይጎረብጡን ጀምረዋል። የመዋቅር ለውጥ፣ የውጥረት መላላት፣ የሹመት ሽግሽግ ቢደረግም፤ ወይ ፍንክች ካይቀሬው የውድቀት ዋዜማ ላይ በመድረሳችን ቃለ ኑዛዜ ማድረግ የግድ ስለሚል፤ እነኾ የሚከተለው የመጨረሻ ቃላችን ነው። ለኛ ያደሩና የትውፊቶቻችን ተካፋይ የነበሩ ከዘመድ አዝማድ ጀምሮ በሆዳቸው እስከገዛናቸው ድረስ የማይታጠፍ ቃላችን ቃላችሁ እንዲሆን ታማኝነትና ታዛዥነታችሁ ቃልኪዳኑን እንደጠበቀ እንዲኖር አደራ በማለት የሚከተለውን ቃለ ኑዛዜ ለታሪክ ትተናል።

በሰው ልጆች ታሪክ ሲወርድ ሲዋረድ እንደታየው፤ ኑሮ ኑሮ ወደምሬት ከሥልጣን ወርዶ ወደ እስር ቤት ነውና፤ እነኾ ፅዋው ለኛ ደረሰና ወደ አይቀሬው ዓለም በቃኝ መወርወሪያችን ጊዜ በመቃረቡ ወራትና ቀናት እያስቆጠሩ ይገኛሉ።

እያወቅን በድንቁርና፣ እየተለመንን በትዕቢት ሕልማችንን ወደ ደደቢት በማድረጋችን የሰማዩ መግቢያችን ከወዲሁ በሩ ቢዘጋም፤ የምድሩም በጠራራ ፀሐይ ሊከረቸምብን መቃረቡ እኛን ብቻ ሳይሆን፤ ጠቅላላ ትውልዱን በመጉዳታችን ጥልቅ ኀዘንና ፀፀት ላይ ዘፍቆናል። ይቅርታ ብንጠይቅ እንኳን ግፉ ሞልቶ ስለፈሰሰ የግፉ ሱናሚ ማዕበል በቁማችን ጠራርጎ እንጦረጦስ እንደሚደፍቀን ምልክቶች እየታዩ ነው።

አባታችን ሰይጣን ሆይ! ነፍስና ሥጋችን አንተን አምና ወዳንተ መጥታለችና፤ በደም ዋዥተው ወደ አንተ እንደተመለሱ ልጆችህ እኛንም ተቀብለህ ከተከታይ አሪዎሶችህ አጠገብ በስቃይ አሳርፋት። ስናሰቃየው የኖርነውን ሕዝብና ስናደማት የቆየችውን አገርም የሰላም እስትንፋስ ስጣቸው።

አሜን!

ዘጌርሳም (ኢትዮጵያ ዛሬ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!