እንኳን ለዘመነ ዮሐንስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

ልደት የሚከበረው በታኅሣሥ 29፥ በሠግር ዓመት ግን በታኅሣሥ 28 ስለሆነ ዘንድሮ የሚከበረው በታኅሣሥ28 ቀን ነው።

 

 

በሀገራችን የሠግር ዓመት መቼ እንደሆነ የማያውቁ ሰዎች ልደት የሚከበርበት ቀን ይምታታባቸዋል። አባቶቻችን ለዚህ መፍትሔ ሲፈልጉ ለአራቱ ወንጌላውያን አንድ አንድ ዓመት ሰጥተው ዓመቱን "ዘመነ ማቴዎስ"፥ "ዘመነ ማርቆስ"፥ "ዘመነ ሉቃስ"፥ "ዘመነ ዮሐንስ" እያሉ ያስኬዱና ዓመቱ እንደ ዘንድሮው ዘመነ ዮሐንስ ሲሆን ልደት የሚውለው በታኅሣሥ 28 ነው ይሉናል - በአራት ዓመት ወይም በየአራት ዓመቱ አንዴ ማለታቸው ነው።

 

ዓመቱ ለምን "ሠግር" ተባለ? "ሠገረ" ፥ "ተሻገረ" የሚሉት የአማርኛ ቃላት "ሠግር" ከሚለው የግዕዝ ቃል ጋር ዝምድና አላቸው። "ሠግር" ማለት "ተሻጋሪ"፥ "ዘላይ" ማለት ነው። ዓመቱ 365 ቀናት መሆኑ ቀርቶ 366 ቀን ሲሆን ምዕራባውያን "Leap Year" ይሉታል፤ ያው "ዘላይ ዓመት" ማለታቸው ነው። በእኛ የአቈጣጠር ዘዴ ጳጒሜ 5 ቀናት መሆኗ ቀርቶ 6 ቀን ስትሆን ማለት ነው። ቈጠራው የሚምታታው "የሠግር ዓመት" የሚባለው ዘመነ ሉቃስ ነው ወይስ ዘመነ ዮሐንስ ከሚለው ጥያቄ ላይ ነው። ምክንያቱም ጳጒሜ 6 ቀናት የምትሆነው በዘመነ ሉቃስ ነው። ልደት በታኅሣሥ 28 የሚውለው ግን በዘመነ ዮሐንስ ነው።

 

እኛ ያየነው ጳጒሜ በዘመነ ሉቃስ 6 ቀናት ስትሆን ዘመነ ዮሐንስ የሚጀምርበትን፥ መስከረም 1ን፥ በአንድ ቀን ማስዘግየቷን ነው። አንድ ቀን ታስዘልለውና እንደሌሎቹ ዓመታት በ1 መጀመሩን ትቶ፥ 2 ሊሆን በሚገባው ቀን ይጀምራል። በአዘቦት ዓመታት መስከረም 2 ሊሆን የሚገባውን ቀን መስከረም 1 አለው ማለት ነው። መስከረም አንድ በአንድ ቀን ዘግይቶ ከጀመረ ("ከጀመረ" በማለት ፈንታ "ከባተ" ይላሉ)፥ ወራቱ ሁሉ (ታኅሣሥን ጨምሮ ማለት ነው) አንድ ቀን እያሳለፉ መጀመር (መባት) ግድ ይሆንባቸዋል። ልደት አብሮ አይዘገይም፤ ቦታውን እንደያዘ ይኖራል። ስለዚህ በሠግር ዓመት ታኅሣሥ አንድ ቀን ዘግይቶ እ2 ላይ ከጀመረ ልደት የሚውልበት ታኅሣሥ 29 ቀደም ብሎ በታኅሣሥ 28 ቀን ይውላል። የሠግር 28 ቀንና የአዘቦቱ 29 ቀን ሁለቱም እኩል ዮናርዮስ 7 (January 7) ናቸው።

 

ልደትን የምታከብሩ ሁሉ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በሰላም ያደረሳችሁ!

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!