ሰሎሞን ተሠማ ጂ.

በመጀመሪያ፣ አንድ ሰው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመጓዝ ላይ ሳለ፣ በአጋጣሚ አንድ ወርቃማ-ቁልፍ ቢጥል በዚያው መንገድ እንደሚመለስ አያጠራጥርም። ሰውዬው የጠፋበትን ቁልፍ ለማንሳት የፈለገውን ያህል ጊዜ (ዘመን) ቢቆይም እንኳ፣ ቁልፉን ፍለጋ በዚያው በተጓዘበት መንገድ ይመለሳል። እንጂ በሌላ አቋራጭ-መንገድ አይሄድም።

 

 

ቁልፉን የጣለው ሰው፣ የጣለበትን መንገድ ይዞ ካልተመለሰ ግን፣ ሌላ ሰው አንስቶ የራሱ (የግሉ) ያደርገዋል። በሌላ አነጋገር፣ አንድ ሕዝብ የመጣበትን መንገድ ተከትሎ የዘመኑን ችግርና ድቀት ፈቺ የመፍትሔ-ቁልፍ ለመፈለግ ካልተመለሰ፣ ያ ሕዝብ ከራሱ ታሪክ ምንም ነገር አይማርም። ሌሎች በተጓዙበት መንገድ የፈለገውን ያህል ቢማስን የጣለውን “ወርቃማ ታሪኩን-ራሱኑ” ሊያገኘው አይችልም።

 

በሁለተኛ ደረጃም፣ አንድ ጅረት ውስጥ የሚገኝ ውኃ ሲሞላም ሆነ ሲጎድል፣ ውኃውን የሚያይዘው ረቂቅ ኃይል አለ። ቀድሞ ያለፈውን ውኃ፣ አሁን ከሚተመውና ከወደኋላ እየመጣ ካለው ጋር የሚያይዛቸው አንዳች ረቂቅ ሰንሰለት አለ። የወንዙ መሙላትም ሆነ መጉደል ሰንሰለቱን ፈፅሞ ሊበጥሰው አይችልም። እንደዚሁ ሁሉ፣ ያለፈውን ትውልድ ከአሁኑና ከመጭዎቹ ትውልዶች ጋር የሚያይዛቸው ሰንሰለት አለ። እርሱም ሥልጣኔ ነው። በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበሩትንና በአሁኑም ዘመን ያሉትን፣ እንዲሁም ወደፊት የሚመጡትን ትውልዶች የሚያይዛቸው ኃይል ነበረ፤ አለም። እርሱም፣ ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያውያን ሥልጣኔ የመሻት፣ የመጓጓትና የመቅናት ኃይል ነው። (ሆኖም፣ ያንን ረቂቅ የሥልጣኔ ዘይቤ ሳይረዱ ነገሥታቱንም ሆነ ቀደምቶቹን ለመተቸት መሞከሩ ከንቱ ድካም ነው።) ስለሆነም፣ “ኢትዮጵያ” በተባለችው ጅረት ውስጥ የምንፈሰው ሕዝቦች፣ የሚያይዘንን ረቂቅ ኃይል ተረድተን በዘመናት ውላጤ ውስጥ በማይበጠስ ሰንሰለት እንደተያያዝን መዘንጋት የለብንም። የሰንሰለቱም ቅጥልጥል አምላክ ወደተለመው ልዩ ብርሃን እንደሚወስደን ጥርጥር የለውም። (ቀሪውን ሃተታ ወደኋላ እንመለስበታለን።)

***************************************

ለመሆኑ “ታሪክ” ስንል ምንድነው? የታሪክን ዘይቤና ፋይዳውን እንዲከተለው አቀርባለሁ። በግዕዝ “ታሪክ” ማለት፣ መጀመሪያ “ዘመን” ማለት ሲሆን፣ ሁለተኛው ትርጉሙ ደግሞ “ዜና መዋዕል” ወይም በቁሙ “ታሪክ” ነው። “መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሀዲስ” መፅሐፋቸው ውስጥ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ “ታሪክ ማለት ያለፈ የተጣፈ ወሬ፣ ዜና” ነው ይሉናል (ገጽ - 903)። ሁሉም ትርጓሜዎች ከታሪክ ዘይቤ የወጡ አይደሉም። ቀዳሚዎቹ ደንጋጊዎች እንደወሰኑት ታሪክ ሲባል ስለሰዎች (ሕዝቦች) ስራ የሚናገር ነው።

 

በተጨማሪም፣ ታሪክ የሥልጡን ሕዝብ ስራ ነው። ይህንኑም ወደፊት የሚያንቀሳቅሰው እርምጃ አለ። እርሱም ለውጥ ነው። የፊቱን ለውጥ ከኋለኛው የሚያስተሳስረው ቋሚ መሳሪያ አለ። መሳሪያው፣ ረቂቅ ነው። ኃያል ነው። ጥልቅ ነው። ርቀቱን-ጥልቀቱንና-ኃያልነቱን ሳይመረምሩ ታሪክ ለመጻፍ መነሳትም ዘይቤውን ያጎለድፈዋል። ወይም የታሪክን ዘይቤ እንደማውተፍተፍም ይቆጠራል።

 

የታሪክ ዘይቤ እንዳይጎለድፍ፣ ከአውጉስሚኖስ ጀምሮ የተነሱትን ዋና-ዋና ሊቃውንትን መራሄ-ኃሳቦች አንድ ባንድ እስቲ እናጥናቸው። “የታሪክ ፍልስፍናና ዘይቤ አባት” ተብሎ የሚጠቀሰው አውጉስሚኖስ፣ “የእግዚአብሔር አገዛዝ” በተባለው መጽሐፉ፣ ታሪክን “መንግሥት መቆሙንና መፍረሱን፣ ሕዝቦችም ማደጋቸውንና መውደቃቸውን” በዝርዝር ከገለጠ በኋላ፤ ይህም የሚሆንበት ምክንያት “አምላክ በአቀደው መሠረት የሰውን ዘር ወደ እውነተኛው ብርሃን ለመምራትና ለማዳን፤” ሲል ነው ይላል። ሊቁ፣ ይህን ሃሳብ የመሰረተው በክርስቲያናዊ እምነቱና ዕውቀቱ ነው። ቶይንቢ ደግሞ፣ “የሕዝብ መነሳትና መውደቅ ዋናው ምክንያት፣ እውነተኛ የሃይማኖት ጥልቀት መገለጽ ነው” ይለናል።

 

ቶይንቢ እንደሚለው፣ “የሰውን የነፍስ ሁናቴና የሥልጣኔ ዕድገት ከዳር እስከዳር ለማርካት የሚቻለው፣ የነፍስን ቀጥተኛ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እምነት ካለ ነው። “ጥያቄው በቀዘቀዘበት ወቅት፣ ያን ጊዜ የሥልጣኔ ሕንፃ ወደመፍረስ ይቃረባል። የሕንፃውም መፍረስ የእምነትን መገለጽ ያመጣል፤” በማለት ሃሳቡን ያጠናክራል።

 

የሄግልም አስተያየት ከቶይንቢ ሃሳብ እምብዛም አይርቅም። “አእምሮ በታሪክ ውስጥ” በሚለው መጽሐፉ ቃል-በቃል እንዲህ ይላል። “አንድ ሰው ማመንንና ማሰብን በታሪክ ውስጥ ማዳበር ይገባዋል። የሕሊና ዓለም ወደዚህ ዓለም በዕድል የመጣ አይደለም። በሰዎች ተሰጥዖ ውስጥ የመጨረሻው ትልቅ ዓላማ፣ የበላይ የሆነውን የዓለም ታሪክ (አእምሮን) ማጎልበት ነው፤” ይለናል።

 

ይኸውም “አእምሮ” የተባለው ስያሜ የአንድን ፍጡር ብቻ ለማለት ሳይሆን “አምላካዊውን ፍፁም አእምሮ” ለመግለጽ የተጠቀመው ቃል ነው። ሄግል ለማለት የፈለገው፣ ሰው አምላካዊ አመጣጥ እንዳለውና ዓላማውም ወደዚያ የሚመለከት ሲሆን ታሪክም የዚሁ ጥረት ውጤት ነው። ስለዚህም፣ “የሰው ስራ ሕያውነት አለው፤” ለማለት ነው።

 

ሁሉም እንደሚስማሙት፣ ታሪክ ዓላማ አለው። ዓላማውም የራሱ ሳይሆን፣ ከላይ የተሰጠው ነው። ሰጪውን ኃይል አውግስሚዎስ “እግዚአብሔር ነው” ይለዋል። ቶይንቢ ደግሞ “ሃይማኖት ነው” ይላል። ሄግልም “ፍጹም የሆነ አእምሮ ነው” ብሎታል። ሁሉም፣ ዓለም በጥፋትና በድቀት ውስጥ ብትሆንም እንኳን ወደ ደህንነት እንደምታመራ ይቀበላሉ።

 

ከላይ እንደጠቀስነው፣ ታሪክ ያለፈውን የሰው ሥራ የሚገልጽ ነው። ሆኖም፣ ያለፈ ነገር ሁሉ ታሪክ አይደለም። ያለፉ ነገሮች በታሪክ ዓምድ ተቀርጸው ለመኖር ሦስት መስፈርቶች የግድ ያስፈልጋሉ።

 

አንደኛ፣ እርግጠኝነትና ድርጊቱ በተወሰነ ቦታና ጊዜ ለመፈጸሙ ምርመራና ማስረጃ ሊኖረው ይገባል። በዚህም ከአፈ-ታሪክ (Myth) እና ከትውፊት (Legend) ይለያል። አፈ-ታሪክ የሚነገረው ከአንደበት ወደ አንደበት ስለሆነ፣ ሰሚውን ለማስደሰት ሲባል የቀለለና ተአማኒም ያልሆነ ነው። ትውፊትም ስያሜው እንደሚያመለክተው አማናዊ ያልሆነና መላምትን ተመርኩዞ ዕረፍትን ለማግኘት ሲል ሰው ከልቡ የሚያፈልቀው ነው። ትውፊት እየጎላ የሚነገርና ምሳሌነትም አለው። ልብ ወለድ ቀመስ ነው። “ታሪክ” እነዚህን ሁለቱን በጭራሽ አይክዳቸውም። እርግጠኛውን ፈልፍሎ ማግኘት ግን የአንድ ታሪክ ፀሐፊ ግዴታው ነው። እዚህ ላይ ፖሊቭዮስ የሚባል የጥንት ታሪክ ፀሐፊ የተናገረውን መጥቀስ ያስፈልጋል። “እንስሳ ሁለት አይኖቹ ከጠፉ ህልውናው በሞላ የማይረባ እንደሚሆን፣ ከታሪክም ላይ እውነት ከተቀነሰ (ከጠፋ) የቀረው ሁሉ የማይረባ “ወሬ” ይሆናል፤” ብሏል።

 

ሁለተኛ፣ ድርጊቱ በቀጥታም ሆነ በጎንታ ማኅበራዊ ኑሮንና የዛሬውን ዘመን አኳኋን ማመልከት አለበት። ማለትም ድርጊቱ ከጠቅላላው ከሰው ሕይወት ጋር የተያያዘ መሆን ያስፈልገዋል። ሦስተኛም፣ የታሪኩን መተረክ ምን ያህል አስገላጊነት አለው? ማለትም፣ የመንፈስና የብዕልን ሕይወት የሚነካ ነወይ? ወይስ ዝንጓኤ ያጠቃው ነው? አነሰም በዛ ድርጊቱ ተከታዩን ሁናቴና የኋለኛውንም ዕድገት ፈልጎና አፈላልጎ ማግኘትም አለበት።

 

እነዚህ ሦስቱ መለያዎች ከሌሉት አንድ ድርጊት “ታሪክ” ሊሆን አይችልም። በአንድ አጠቃሎ ሦስቱን ለመግለጽ ተስማሚው ቃል “ለውጥ” የሚለው ነው። በማኅበርዊ ኑሮና በልዩ ልዩ ተሰጥዎች በዘመናት መካከል የሰው ዘር በዓለም ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴና የፈፀማቸውን ለውጦች ታሪክ ያለውላጤ የማውሳት ዓይነተኛ ዓላማ አለው። የሰው ሕይወት ሁልጊዜ የሚንቀሳቀስና የማይቋረጥ ለውጥ ነው። ስለዚህ አንድ የታሪክ ፀሐፊ የአንድ ሕዝብን ታሪክ ለመፃፍ ሲነሳ በአሮጌው ፈንታ የተተካውን አዲሱን ዘይቤ መወቅ ይገባዋል። በአዲሱ ዘይቤ ምክንያት፣ ሰው የውስጡንና የውጭውን ሁኔታዎች ለውጦ ራሱን የሚያድስበት ኃይል መኖሩ ፈፅሞ ቸል ሊባል አይገባም። ለውጡ ከስር መሰረቱ አለመሆኑንና የማይለወጥ አንድ ፅኑ ነገር እንዳለ ማወቅም የተገባ ነው። (ያንን የማይለወጥ፣ ፅኑና ረቂቅ ኃይል ምንነት ኋላ እንመለስበታለን።)

 

ሕይወት በጠቅላላው በምክንያትና ውጤት ሰንሰለት የተያያዘ ነው። ስለዚህም ምክንያት-ምክንያትን እየተካና እየቀጠለ ይሄዳል። ለምሳሌ፣ የውሃ ሙላትና ጎርፍን እንመልከተው። አንዱ ከአንዱ መጠኑ የበዛና ያነሰም ቢሆን የኋለኛው ከፊተኛው ጋር የተያያዘ ነው። የፊተኛውንና የኋለኛውን የሚያያይዝ ረቂቅ ነገር አለ። ረቂቅ ግን ጠንካራ ነው። እንደሚታወቀው ሁሉ፣ የአንድን ዘመን ሰው ከሌላው ዘመን ሰው ጋር በማይለወጥና በማይበጠስ ኃይል የተያያዘ ነው። የአንድ ዘመን ትውልድ ምክንያቱ ከርሱ በፊት የነበረው ትውልድ ነው። ሕይወት በጠቅላላው ሰንሰለታማ ነው። በዚህ አኳኋን ሰው ያለፈውን በመካድና በማጥፋት ፍጹም አዲስ ነገር ለመጀመር አይችልም። የሕይወት ሰንሰለት የዕድገትንና የጊዜን ረቂቅ እርዳታ የሚጠይቅ ነው።

 

የዕድገቱና የመሻሻሉ ጉዳይ፣ ለሰው ችሎታና ብርታት የተተወ ነው። አንድ ሕዝብ እንደብርታቱና ዓላማውን እንደመከተሉ መጠን እርምጃውም የተፋጠነ ይሆናል። የዚህን ጊዜ በታሪክ አደባባይ ላይ ለመዋል ይችላል። ስለሆነም ታሪክ ያለው ሕዝብ ከፍተኛ የመንፈስና የብዕል (የብልጽግና) ደረጃ ላይ የደረሰ ሕዝብ ነው። የቀረው በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚኖር ሕዝብ፣ እርሱ ገና በታሪክ ሸንጎ ላይ አይገኝም። ምክንያቱም፣ በሕይወቱ ገና ደንበኛ ለውጥ (ውላጤ) የለውምና ነው።

 

የአንድ ሕዝብ መነሳትና መውደቅ ከታሪክ ጽኑ መሣሪያ ጋር ምን ግንኙነት እንዳለው ቀጥሎ እናንሳ። መጀመሪያ ግን የአንድ አገር ሥልጣኔ ተቀባይም ሰጪም መሆኑን እንስማማ። አንድም አገር ከሌላ ሕዝብና ባሕል ጋር ሳይገናኝና ሳይጋባ የሥልጣኔን መሰላል የተወጣጣ ከቶም አይገኝ። (ለምሳሌ የአሜሪካንንም ሆነ የሕንድ ወይም የቻይናን ስልጣኔ መውሰድ ይቻላል። ከሌላ ያስገቡት ባሕል አለ።) ሰው ወደእርምጃ የሚያመራው ከብጤው ጋር ሐሳቡን ሲቀባበልና፣ በራሱ ላይ መጨመርና ማዳበርም ሲችል ነው። ከራሱ ያፈለቀውንና ከሌሎች ተወዳጅቶ ያገኘውን አንድጋ ሲያፃምረው አንድ አይነት ሥልጣኔ ይፈጠራል። የራሱን ሐሳብ ከባዕዱ አኃዝ ጋር ሲያፃምረው ከሁለቱ አንዱ እየበረታ ሄዶ፣ ከችሎታና ፍላጎቱ (በጠቅላላው ከነፍሱ ሁናቴ) ጋር የተያያዘ እንደሆነ በርትቶ ይገለጣል።

 

በምሳሌ እናስተንትነው። በአብዛኛዎቹ የምስራቅ አገሮች ተመሳሳይ የስልጣኔ ቅርስ እናያለን። የእነዚህ አገሮች ሕዝብ እምነት እውቀትና ሥነ-ጥበብ የአንዱ ከሌላው በጣሙን የተመሳሰለ ነው። የራሳቸውን የጥረት ውጤት ከውጭ በአገኙት ሐሳብ ላይ አልጨመሩበትም። ስለዚህ ከውጭ የተገኘው ሥልጣኔ የነርሱን ስለደበቀው የውጭው ጎልቶ ይታያል። የዚህም ምክንያቱ የራስን ነፍስ ሰውቶ፣ በሌላ ስጋ ውስጥ ከመወሸቅ የመነጨ ነው። የምስራቃውያኑ የነፍስ ሁኔታ “የእኔ” የሚለውን አኃዝ “የአንተ” ለሚለው የሚሰዋ ነው። ነፍሳቸው ከሌላው የተቀበለውን አኃዝ እንደገና እንደነበር ይጠብቀዋል። (ለአብነትም የሰርጉን አኃዝ እንውሰድ። ዳስ ተጥሎ፣ ጠላው ተጠምቆ፣ ጠጁም ተጥሎ፣ በግልገል ሙሽራውና በበቅሎ ጀርባ ዳገት ቁልቁለቱን ወጥቶና ወርዶ ይደረግ የነበረው ቀርቶ፤ በቬሎ፣ በሱፍና በገበርዲን፣ በቢራና በሻምፔኝ፣ በኮክቴልና በኬክ፣ በማርሴዲስና በሊሞዚንም ተተካ። “እኔ”ነትን እርግፍ አርጎ ትቶ፣ “አንተ”ነት ውስጥ ተወሸቀ። (የምስራቃውያኑ የከፋ እዳ! ይኼው ነው።)

 

በምዕራቡ ሥልጣኔ ውስጥ ግን ተቃራኒው ተከሰተ። ለምሳሌ፣ የጥንት ግሪኮች ከእነርሱ በፊት በሥልጣኔ ከፍ ካሉት ከምስራቁ አገሮች ብዙ-ብዙ ነገሮችን ወስደዋል። ከግሪክ ሥልጣኔ እንደራሴዎች መካከል ብዙዎቹ የምስራቁን ሥልጣኔ ጎብኝተዋል። ለምሳሌ ሶሎን፣ የአቴንስን ሕግ ለማሻሻል ከመጀመሩ በፊት ብዙዎቹን የምስራቅ አገሮችና አሰራራቸውን ጎብኝቷል። ፕሌቶም ዲያሎጎቹን ከመፃፉ በፊት ግብፅንና ሕንድን ጎብኝቷል። “የአቶም አባት” የሚባለው ዲሞክሪቶስም እስከ ኢትዮጵያ ድረስ መጥቶ እንደነበር ታውቋል። እነዚህ ሊቃውንት ከዳበረው የምስራቅ ሥልጣኔ ብዙ ነገሮችን እንደቀዱም አያጠራጥርም።

 

ሆኖም፣ ከጉብኝታቸው በኋላ በደነገጉት ሕግም ሆነ በአሻሻሏቸው የማህመራዊ ኑሮና የአስተዳደር እርምጃዎች ውስጥ የምስራቁ አ ኃዝ እንደሌለ ሆኗል። ምክንያቱም፣ የራሳቸው የሆነው አኃዝ ጎልቶ ስለሸፈነው ነው። የምስራቆቹ “እኔያቸውን” ሁሉ “አንተነህ” ለሚባለው ሰውተውት አረፉ። ምዕራባውያኑ ግን “እኔያቸውን” በማበርታት “አንተነህ” የሚሉትን የማይታይና ጥገኛ አደረጉት። ስለሆነም ከውጪ የተገኘው አኃዝ እንደሌለ ሆነ።

 

ይኼ ሁሉ ዝርዝር የቀረበው፣ አንድ ሥልጣኔ ተቀባይም ሰጪም መሆኑንና የሚቀበለውም ሆነ የሚሰጠው እንዴት እንደሆነ ለመግለፅ ነው። በዚህ ሁናቴ አንድ ስልጣኔ በዓይነቱ ከሰጠ አይጠፋም። የቦታና የዘመን አቀማመጥም አያሰናክለውም። አንድ ምሳሌ እንውሰድ። የእህል ዘርን አንድ ትጉህ ገበሬ ከሩቅ አገር አምጥቶ ያለማል። ከጥቂት አመታት በኋላ ዘሩ ከመጣበት አገር ቸነፈር ገባን/ወደቀና አዝመራውን ሁሉ አጠፋው። ሆኖም፣ የእህሉ ዘር አንደኛውን ጠፋ ማለት አይደለም። ሩቅም ቢሆን ዘሩ አለ። ስለዚህ ከሩቅ አገር አምጥቶ እንደገና ዘሩን የማልማት ችሎታ አለ ማለት ነው።

 

በአንፃሩም አንድ ሥልጣኔ አንድ አገር ላይ ጠፍቶ ሌላ አገር ቢለማ በአይነቱ ሥልጣኔው ጨርሶ አልጠፋም። መዘንጋት የማይገባው የሰው የጋራ አመጣጥ አንድ ነው። ስለዚህ ሥልጣኔው የትም ቢለማ የቦታ መለዋወጡ ዋጋ የለውም። ዋነው ነገር በጭራሽ አለመጥፋቱ ነው።

 

አብዛኛውን ጊዜ ሥልጣኔ የሚደመሰሰው በጦርነት ነው። አሸናፊው ኃይል የተሸናፊውን አገር የመንፈስና የብዕል ብልፅግናን ዘርፎ ይመለሳል። ነዋሪዎቹን እራሳቸውንም ጭምር ማርኮ ይሄዳል። ስለሆነም ስልጣኔው ተዛወረ እንጂ አልጠፋም።

 

በአንድ አገር ስልጠኔ ማበብና መክሰም ከስነፍጥረት ህግ ጋር የተያያዘ ነው። ቦታ እየለወጠ ያለማቋረጥ እየተሻሻለ ወደፊት መቀጠሉም የታሪክ ሕግ ነው። በታሪክ ውስጥ አንድ ጽኑ መሳሪያ እንዳለና እርሱም “ስልጣኔ” መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

 

የታሪክ ጥቅሙ ምንድነው?

የአንድን ነገር ዋጋ ለማወቅ ማመዛዘን ያስፈልጋል። ሲመዘንም መሰሉን ከተቃራኒው ጋር አነፃፅሮና አመዛዝኖ መሆን ይገባዋል። ማመዛዘኑም ያለፉትን ከአሁኖቹ ጋር በማነፃፀር ነው። በዚህም ያለፈው ዘመን ሁኔታ ከአሁኑ፣ (ወይም የአሁኑ ካለፈው) ጋር ተናፅሮ ምን ያህል ከፍታ እንዳለው ለማወቅ ይረዳል። የታሪክ ዋጋው ለዘመኑ ብቻ ሳይሆን ለተከታዩም ጭምር ነው።

 

አንድ ሰው ከእርሱ ቀድሞ የኖሩት ወገኖቹ እነማን እንደነበሩ ምንስ እንደፈጸሙ ለማወቅ መጠበብ ሰብዓዊ ሕግ ነው። ሰውዬው ከአንድ ለሃገሩና ለወገኑ ታላቅ አገልግሎት የፈፀመና የታመነ ቤተሰብ አባል ከሆነ ኩራት ይሰማዋል። የከሃዲና የባንዳ ልጅም ከሆነ ሃፍረቱ የትየለሌ ነው። ለኩሩው ሰው ሌሎችም የሚገባውን ክብር ይሰጡታል። ለሃፍረታሙም እንደዚያው የሚገባውን አይነፍጉትም። የታላቅ ቤተሰብ ልጅም በበኩሉ ከቤተሰቡ በላይ ለመጨመር ይፍጨረጨራልም። ስለዚህም ታሪክ የወደፊት እርምጃዎችን አነሳሽና አትጊ ሆኖ እናገኘዋለን።

 

የታሪክን ጥቅም ለመግለፅም ያህል ፖሊቪዮስ የተባለው የግሪክ ጸሐፊ፣ “ከታሪክ ሌላ ምንም የተዘጋጀ የሰዎች ማረሚያ (ወህኒ) የለም። የአለፉትን ሰዎች ስራ ከማጥናት በስተቀር ማን አራሚ አለ!” ይለናል። ሴሴሮ የተባለው የታሪክ ፀሐፊም፣ “ታሪክ የሕይወት አስተማሪ ናት!” ይለናል። እንዲሁም ኳንቲሊኒውስ የተባለው ሊቅ፣ “ታሪክን ማወቅ የሚረዳው ስለዚህ ነው። ራሳችንም በአለፉት ዘመናት እንደኖርን ይሰማናልና፤” ይላል። ሊዮናርዶም ታሪክን “የበጎ ስራ ጠባቂ፣ የክፉ ሥራ መስካሪ፣ ለጠቅላላው ለሰው ዘር ደግ አድራጊ” ናት ይላታል።

 

ቲኦፊያክቶስ የሚባለው ግሪካዊም ታሪክን “የወል መምህርት! የሁሉም ሰዎች አስተማሪ ናት፤” ብሏታል። አስከትሎም፣ “የሽማግሌን እጅ ይዛ የምትመራ ምርኩዝ ናት። ለወጣቶችም ጽኑ አሰልጣኝ ማለት ታሪክ ብቻ ናት፤” ይለናል።

 

የታሪክ ዋና ፋይዳዋ ባለፈው ጊዜ የነበረውን ዕድገትና እርምጃ ያሳየናል። በማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ምን ደግና ክፉ እንደተደረገም ይገልጻል። በዚያን ዘመን የነበረውን ደስታና መከራ ምክንያት ምን እንደሆነ የተገኘውንም ዕውቀትና ሰዎች የነበራቸውን ተስፋና ዕምነት ሳይቀር ታሪክ ያስረዳል። በዚህም ስሌት መሰረት፣ የዛሬው ትውልድ ክፉውን መቀጣጫ አድርጎ፣ መልካሙን ደግሞ አርአያ እንዲያደርግ ይጠቅመዋል። በቂ የታሪክ እውቀት ያለው ሰው፣ በቀጥታ ፍርድ ለሚገባው ተገቢውን ዋጋ ለመስጠት፣ የአሁኑን ችግር ለማቃለልና ለመጪውንም ዘመን በደህና ሁናቴ ለማዘጋጀት ይችላል።


ሰሎሞን ተሠማ ጂ. (semnaworeq.blogspot.com)

 

(ይህ መጣጥፍ በአዲስ ጉዳይ መፅሔት ሐምሌ 07 ቀን 2004 ዓ.ም ቁጥር 121 ዕትም ላይ ወጥቶ ነበር።)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ