ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ (ግራ)፣ ገርማሜ ነዋይ (ቀኝ) Mengistu and Germame Newayሰሎሞን ተሰማ ጂ.

በ1900 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መንግሥታት ስምምነት፣ “በልዩ የቆመ ፍርድ ቤት” የሚል ስያሜ የተቋቋመ ፍርድ ቤት ነበር። ፍርድ ቤቱ የመጀመሪያ ሥራውን በ1914 ዓ.ም. ሲጀምር፣ የመጀመሪያው የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደ ሥላሴ ነበሩ። ከርሳቸውም ቀጥለው የተሾሙትም ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ ናቸው። የዚህ ፍርድ ቤት ዋነኛው ተግባር የውጭ ዜጎች እርስ-በራሳቸው ሲጋጩና/ወይም የውጭ አገር ዜጎችና ኢትዮጵያውያን በተጋጩ ወይም በተካሰሱ ጊዜ ፍርድ መስጠት ነበር።

በፍርዱም ላይ የከሳሹ/የተከሳሹ የውጭ አገር ዜጋን የሚወክል ቆንስል/ኤምባሲ ወኪል እንደአንድ ዳኛ ሆኖ ይቀመጥ ነበር። ይህ ፍርድ ቤት ከ1928 ዓ.ም. በኋላ፣ “በልዩ የቆመ ፍርድ ቤት” መባሉ ቀርቶ፣ “ከፍተኛው ፍርድ ቤት” ተባለ። ይህም ፍርድ ቤት፣ ከ1928 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ ታሪካዊ ስሕተቶችን ፈፅሟል። በዚህ ወቅትም፣ ከ52 ዓመታት በፊት የፈፀመውን ግዙፍ የሕግ ስሕተት እናወሳለን። አንዴ “በልዩ የቆመው”፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ የ“ከፍተኛው” ፍርድ ቤት እየተባለ ቢጠራም፣ ፍርድ ቤቱ ፍትሐዊነት የጎደለውና በገዢዎች ጥቅሻ የሚሰራ መሆኑን አንድ አብነት ጠቅሰን እንነጋገራለን።

ወደዋናው ጉዳያችን ከመግባታችንም በፊት በሰኔ-1934 ዓ.ም. የተከሰተ አንድ የ”ከፍተኛው”ን ፍርድ ቤት የፍርድ ሂደት ማሳያ እንጥቀስ። ዝቃርጋቸው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ 1964 ዓ.ም. “ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ ዘብሔረ ዘጌ” ባሉት የጥናት ጽሑፋቸው፣ በገጽ 30-31 እንዳወሱት ከሆነ፣ የቀድሞው “በልዩ የቆመ ፍርድ ቤት” ሁለተኛው ፕሬዝዳንት አፈወርቅ ገብረ የሱስ፣ ለፋሺስት ጣሊያን ሠርተሃል፣ ሀገርህንም ከድተሃል ተብለው በትልልቆቹ አርበኞች ፊት ቀረቡ። አርበኞቹም ራስ ስዩም መንገሻ፣ ራስ አበበ አረጋይና ራስ ካሳ ሀይሉ ነበሩ። ችሎቱ ተሰይሞ፣ ክሱ ተደመጠ። አፈወርቅ መከላከያ ምስክሮቻቸውን እንዲያቀርቡ ተጠየቁ። ነገሩ ሁሉ ወደአንድ አቅጣጫ መትመሙን የተረዱት “ነቄው” አፈወርቅ፣ “አልከላከልም!” አሉ። አርበኞቹም የችሎቱ ዳኞች፣ “የማትከላከል ከሆነማ፣” አሉና በሞት እንዲቀጡ በየኑባቸው። የመኻል ዳኛውም፣ “አፈወርቅ! እንዴት ነው ጥፋተኝነህን ታምናለህ ወይስ አታምንም?” ቢሏቸው፤ “ምንም ጥፋት የለብኝም። የፊውዳል ፍርድና የጉንዳን መንገድ አንድ ዓይነት ናቸው። አንዱ ባለውና አንዱ በሄደበት ተከትላችሁ ‘አዎን! አዎን!’ ማለት ትወዳላችሁ፤” ሲሉ ፍርዱን አጣጣሉት። አማኑኤል አብራሃ እንደሚያወሱት ከሆነ ደግሞ፣ አፈወርቅ በችሎቱ ፊት የተናገሩት እንዲህ የሚል ነበር፤ “ተሠለጠነና፤ ዳኞች ተሰየሙና! ተሠለጠነና፤ ችሎት ቆመና! ፍርድ ተሰጠ ማለት ነዋ?!” ሲሉ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ተሳልቀውበታል።

አፈወርቅ፣ እድሜያቸው ከሰባ ዓመት በላይ ስለነበረና በዘመኑም እድሜው የገፋ ሰው በሞት እንዳይቀጣ ፍትሐ-ነገሥቱ ስለሚያዝ፣ የዳኞቹን ውሳኔ ንጉሠ ነገሥቱ አሻሽለው፣ “ወደዕድሜ ልክ እስራት ለውጠንልሃል” አሏቸው። አፈወርቅም ስሜት-አልባ ሆነው ተቀምጠው ቀሩ። የዚህም ጊዜ፣ ከመኳንንቶቹም አንዱ፣ አፈ-ንጉሥ ዘውዴ የተባሉት፣ “ምነው ነጋድራስ፣ ምህረት ሲደረግልህም እጅ አትነሳም እንዴ?” ቢሏቸው፤ አፈወርቅም፣ “ይታሰር ተባለ እንጂ፣ ይፈታ ተባለ እንዴ?! ለምን ብዬ ነው እጅ የምነሳው? ለኔ ሞቱ ይሻለኝ ነበር። ይህ ምህረት ሳይሆን ከሞትም የከፋ የቁም ስቃይ እንድቀበል የተደረገ የግፍ ፍርድ ነው።” ሲሉ አማረዋል። ከዚያም ጅረን በሚባል በጅማ ከተማ አቅራቢያ ባለ ቦታ ታሰሩና መስከረም 15/1939 ዓ.ም. በ79 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን የነበረው የከፍተኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔም ሆነ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ብዙዎች በፍትሐዊነቱ አይቀበሉትም። “የሞተ-ተገላገለ!” የሚባልበት ዘመን ነበር። ከነዚህም ሰለባዎች መካከል፣ በ1953ቱ ስዒረ/መፈንቅለ መንግሥት መሪነታቸው አንደኛ ተከሳሽ የነበሩት ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ አንዱ ናቸው።

መፈንቅለ መንግሥቱ የተጀመረው ማክሰኞ ታኅሣሥ 4 ቀን 1953 ዓ.ም. ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ነበር። ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይና ወንድማቸው ገርማሜ ነዋይ ከፍተኛዎቹን የንጉሠ ነገሥቱን ባለሥልጣኖች ሰብስበው ማሰር ጀመሩ። ሜ/ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ብ/ጄኔራል ጽጌ ዲቡን ለመታሰር የቀደማቸው የለም። ከዚያም ራስ አበበ አረጋይንና ልዑል ራስ ስዩምን፣ አባ ሃና ጂማን፣ ብ/ጄኔራል መኮንን ደነቀን ተራ በተራ አሰሯቸው። ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ የክብር ዘበኛ ሦስት ቡድኖች ሜ/ጄኔራል ከበደ ገብሬ ቤት ኼዱ። ከቤታቸው አጧቸው። ወታደሮቹ አጥተዋቸው ሲመለሱ፣ ጄኔራሉ ደግሞ ስዊድን ኤምባሲ ራት ግብዣ ላይ ቆይተው ሲመለሱ በተቃራኒ አቅጣጫዎች ለጥቂት ተላለፉ። ሜ/ጅኔራል መርድ መንገሻ ቤት የኼዱት ወታደሮችም፣ ጄኔራሉ ምጥ-ይግቡ-ስምጥ አጥተዋቸው ተመለሱ። ተጠራጣሪው ጀኔራል ግን፣ ግቢያቸው ውስጥ ጭለማን ተገን አድርገው ተሸሽገው ነበር-ወታደሮቹ ያጧቸው። ያን ጊዜ ሜ/ጄኔራል ኢሳያስ ገብረ ሥላሴ የት እንደነበሩና ምን እንደተከሰተ መዛግብቱ አይገልፁም።

በታኅሣሥ 5 ቀን 1953 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ የወትሮውን እንቅስቃሴዋን አጣች። ረፋዱ ላይ ግርግሩና የወታደራዊ ተሽከርካሪዎቹ ፍጥነት አይሎ ነበር። አሳሪዎቹ የክብር ዘበኛ ኃላፊዎችና ለእስር የሚፈለጉት የምድር ጦር ሹማምንት በየፊናቸው እያሴሩ ነበር። ክብር ዘበኞቹ፣ ከግብጽ ኤምባሲ ጎን ባለው ግቢ (የዛሬው ፕላንና ኤኮኖሚ ሕንፃ ውስጥ) ሲሆኑ፤ የጦር ሠራዊት መሪዎች ደግሞ መሻለኪያ በሚገኘው የአራተኛ ክፍለ-ጦር ግቢ ውስጥ፣ “እንዴት ቀድመው ድል እንደሚያደርጉ” ዕቅዶቻቸውን እየነደፉ ነበር። (ዝርዝር ሃተታውን ተከስተ መላከ THE 1960 COUP D’ETAT IN ETHIOPIA (June 1990) ብሎ በፃፈው የሁለተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናቱ ላይ ገልፆታል። ሙሉውን ሃተታ ለማወቅ የሚፈልጉ አንባቢያን ያንን ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲያነቡት እየጋበዝን፣ ከዚህ ቀጥሎ፣ የፍትሕ ሥርዓቱ እንዴት ያሉ ግድፈቶችን እንደፈጸመ ለማየት ንባባችንን እንቀጥላለን።

ይህ ስዒረ መንግሥት ሙከራ፣ አንዳንዴ “የታኅሣሥ ግርግር” ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ “የነዋይ ልጆች አመጽ”፣ በሌሎች ዘንድ ደግሞ “የክብር ዘበኛ ክሕደት” እየተባለ ይጠራል። ከላይ እንዳወሳነው ማክሰኞ ታኅሣሥ 4/1953 ዓ.ም. ተጀምሮ ታኅሣሥ 7/1953 ዓ.ም. ድረስ የቆየ ስዒረ-መንግሥት ነበር። በአራት ቀናት ውስጥ 64 የንጉሠ ነገሥቱ ሹማምንቶችና ወታደሮች ሲሞቱ፣ 91 ሹማምንቶችና ወታደሮች ቆስለዋል። ከሲቪሉ ማሕበረሰብ በኩልም 76 ሰዎች ሲሞቱ፣ 106 ያልታጠቁ ሰዎችም ቆስለዋል። ይህ አኃዝ ደግሞ ጉዳዩን “ከግርግርም፣ ከአመጽና ከክሕደትም” በላይ እንደነበርና ወደጦርነት የተጠጋ እንደነበር ያሳያል። በጠቅላላው 140 ዜጎች የሞቱበትና 197 ሰዎች የቆሰሉበት ክስተት ነው። የንጉሠ ነገሥቱ ክብር ዘበኛ ከምድር ጦርና ከአየር ሃይሉ ጋር ያደረገው የርስ-በርስ ጦርነት ነበር። አስራ አራት ሚኒስትሮችና አንድ ጠቅላይ ገዢም በግፍ ተገድለውበታል። ማን ገደላቸው? የሚለው ጥያቄ እስካሁን አልተመለሰም። ሁሉም ነገርና ሃጢያቱም ሁሉ፣ ዞሮ-ዞሮ ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይና ገርማሜ ነዋይ ላይ አነጣጥሯል።

ከ52 ዓመታት በኋላ፣ የነበረውን የፍርድ ሂደትና የምስክሮቹን ቃል፣ እንዲሁም የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ስንመረምራቸው፣ ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ የአረንጓዴውን ሳሎን ግድያ ስለማድረጉ አያረጋግጡም። “መንግሥቱ ንዋይና ግብረ አበሮቹ” የቂም-በቀልና የፖለቲካዊ ፍርድ/ውሳኔ የተፈፀመባቸው ዜጎች ናቸው። “ጄኔራሉ ለምን ፍትሐዊ ባልሆነ ችሎት ተዳኘ?” ትክክል አልነበረም ስንል፣ በአረንጓዴው ሳሎን ውስጥ በግፍና በጭካኔ ለተገደሉትም ኢትዮጵያውያን ቆሽታችን ያራል። ክፉኛ በሀዘን ፍላፃም እንመታለን። በተለይም፣ ይህንን የግፍ አካኼድ በወቅቱ ባለማውገዛችንና ባለማረማችን፣ “መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ግብረ አበሮቹ” ስድሳ ሚኒስትሮችንና ከፍተኛ የሀገር ባለውለታዎችን በግፍና በጭካኔ ገደሉ። የትም ቦታና በማንኛውም ጊዜ የሚፈፀምን ግፍና ኢ-ፍትሐዊነትን በወቅቱ ማውገዝ ሥነ-ምግባር ግዴታችን ነው።

በመጋቢት 20 ቀን 1953 ዓ.ም. የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በገጽ 1 እና 3 ላይ እንዲህ የሚል ዜና አውጥቶ ነበር። “የኢትዮጵያና የሕዝቧ ደመኛ መንግሥቱ ነዋይ በስቅላት እንዲሞት ተፈረደበት” ይልና፣ “ከከፍተኛው ፍርድ ቤት የተገኘ ወሬ” ነው ይላል። እውነቱን ለመናገር፣ የዳኞቹን የውሳኔ ቃለ-ጉባኤ ሙሉውን ነበር ያወጣው። ከችሎቱ ቃለ-ጉባኤ እንደምንረዳው ከሆነ በርካታ ጥያቄዎችን የሚያስነሱ ክስተቶች አሉበት። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ተከሳሾቹ ሦስቱ የክብር ዘበኛ መኮንኖች ብቻ ለምን ሆኑ? አንደኛው ተከሳሽ፣ ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ሲሆኑ፣ መንግሥት አቶ ዮሐንስ ፕሮታን ጠበቃ አቁሞላቸዋል። ሁለተኛው ተከሳሽም፣ ሻምበል ክፍሌ ወልደ ማርያም ሲሆኑ፣ ጠበቃቸው ደግሞ አቶ ታደሰ ድልነሣሁ ነበሩ። ሦስተኛውም ተከሳሽ፣ የመቶ አለቃ ድጋፍ ተድላ ናቸው፤ ጠበቃቸውም አቶ ተሾመ ገላግል የተባሉ ሰው ነበሩ። ሌሎቹ በሕይወት የተረፉት በመፈንቅለ መንግስቱ ዓይነተኛ መሪዎች (Ring Leaders) እና ሌሎች የክብር ዘበኛ ከፍተኛ መኮንኖች፣ ለምሳሌ እንደኮሎኔል ቃለ-ክርስቶስ አባይ የመሳሰሉት፣ በጭራሽ አልተከሰሱም። በአንፃሩ ግን ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይና ሁለቱ ረዳቶቹ ብቻ ተከሰሱ። “ለምን?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

በተለይም፣ መጋቢት 18/1953 ዓ.ም. አስችሎ በነበረው የከፍተኛው ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት የቀኝ ዳኛ የነበሩት ባለሕሊናው ኮሎኔል አበበ ተፈሪ፣ በፍርድ ሂደቱ ላይ የነበራቸውን ጥርጣሬና የዐቃቤ ሕጉን፣ የተከሳሽ ጠበቆችንና የምስክሮቹን ተዓማኒነት ጥያቄ ላይ የሚጥል የልዩነት አቋም አንስተዋል። ኮሎኔሉ እንዲህ አሉ፤ “ከብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ በስተቀር ሁለተኛውና ሦስተኛው ተከሳሽ ምንም ዓይነት የፖሊስ ምርመራ አልተደረገባቸውም። ሁለተኛም፣ ምስክር ሆነው የመጡት አብዛኞቹ ሰዎች የበቀል ስሜት አልነበራቸውም ብሎ ለመጠርጠርም ይከብዳል። ለምሳሌ፣ በ12 ጥይት ተመትተውና ሁለት እግሮቻቸውን ቆስለው ከሆስፒታል ለምስክረነት የመጡትን የ7ተኛውን ምስክር የብ/ጄኔራል መኮንን ደነቀን የምስክርነት ቃል ለማመን ይከብዳል። በገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥት የምድር ቤት ኃላፊ የነበሩትን የ5ተኛውን ምስክር የአቶ ተፈራ ኃይሉንም ሆነ ሳይምል የመሰከረውን የ10ኛውን ምስክር የአቶ ፍቃዱ ጮሌን ምስክርነት ፍርድ ቤቱ ቀብሏል። በተለይም 4ተኛው ምስክር ደጃዝማች በዛብህ ስለሺና 6ተኛው ምስክር ሻምበል ዳንኤል ሙሉነህ ቢያንስ ሁለት-ሁለት የቅርብ ዘመዶቻቸውን ያጡ ናቸው። ሆኖም ...” አሉ ኮሎኔል አበበ ተፈሪ፣ “ፍርድ ቤቱ ያለማመንታት ምስክርነታቸውን ተቀብሎታል፤” ሲሉ በሰፊው ወቅሰው ነበር።

ኮሎኔል አበበ ተፈሪ ላሳዩት ቁርጠኝነትና ወኔ ክብር ይገባቸዋል። “የፊውዳልን ፍርድና የጉንዳንን መንገድ” አልከተልም ብለው በምልዐት ስለተገኙ “ውድ ኮሎኔል አበበ ሆይ፣ ክብረት ይስጥልን!” ልንልዎት እንወዳለን። እደግመዋለሁ፣ “ክብርና ምስጋና ይገባዎታል!” (እንደርሳቸው ዓይነት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኞች አልፎ-አልፎ ብቅ ባይሉ ኖሮ፣ ስንቱ ወገናችን በግፍ ይፈረድበት ነበር?!) ኮሎኔል አበበ ተፈሪን የልዩነት አቋም ብቻ እንኳን ይዘን፣ ነገሩን በታሪክ ሕሊና እየተመራን ብንመረምረው፣ ብ/ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ የማይገባውን ፍርድ ተቀብሏል። ለዚህም በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ እንችላለን። በመጀመሪያ፣ የፍርድ ሚኒስትር ሆነው በየካቲት 2/1953 ዓ.ም. የተሾሙትን ደጃዝማች ዘውዴ ገብረ ሥላሴን ማንነት እናጢነው። ሚኒስትሩ/ዐቃቤ ሕጉ ዘውዴ በተከሳሾቹ ሰበብ፣ አያታቸውን ልዑል ራስ ስዩምን አጥተዋል። ዐቃቤ ሕግ አድርገው የላኳቸውን ኮሎኔል ተፈራ ገብረ ማርያምን ምን ያህል ጫና አሳድረውበቸው እንደነበረ ለመገመት አይከብድም። በዚያም ላይ-ደጃዝማች ዘውዴ፣ ተገደው በታኅሣሥ 5/1953 ዓ.ም. በሬዲዮ ንግግር ያደረጉት፣ የልዑል አልጋ-ወራሹም የእንጀራ ልጅ ናቸው። የእንጀራ አባታቸው ተጽዕኖ እንደሚኖርባቸው አያጠራጥርም።

ወደ ሌሎቹ ብርቱና ኃያላኑ የብ/ጄኔራል መንግሥቱ ተበቃዮች ማንነት እንለፍ። ዋናውና እጃቸውን ከማስረዘም የማይታቀቡት ፀሐፌ-ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ-ወልድና ወንድማቸው አቶ አካለወርቅ ናቸው። አክሊሉና አካለወርቅ ታላቅ ወንድማቸውን በአረንጓዴው ሳሎን ግድያ ወቅት አጥተዋል። በተለይ አክሊሉ፣ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ከኅዳር 22 እስከ ታኅሣሥ 8/1953 ዓ.ም. ድረስ ምዕራብ አፍሪካና ደቡብ አሜሪካን በውጭ ጉዳይ ም/ሚኒስትርነታቸው አብረው ሲጎበኙ ነበር። ለንጉሠ ነገሥቱም የነበራቸው ቅርበት፣ “እጅ ለአፍ፣ አሳብ ለልብ” ያህል ነው። ከ1928 ዓ.ም. ጀምሮም፣ ለሃያ አምስት ዓመታት ያህል የዘለቀ መታመንና ቅርብነትን አግኝተዋል። ጃንሆይ ደግሞ ከሌለ ፀባያቸው፣ ሌሎች የርሳቸውን ጉዳይ እንዲፈጽሙላቸው ያደርጋሉ እንጂ፣ ፈፅሞ በግልጽ ጣልቃ አይገቡም። ለዚህም ይሆናል፣ መጋቢት 21/1953 ዓ.ም.፣ አክሊሉ ተልኳቸውን በፈጸሙ ማግሥት፣ ፀሐፊ-ትዕዛዝ ተብለው የተሾሙት (አዲስ ዘመን፣ መጋቢት 22/1953 ዓ.ም.፣ ገጽ 1)። የራስ አበበ አረጋይ ልጅ፣ ደጃዝማች ዳንኤል አበበም ቢሆኑ (የመጀመሪያው የግል አይሮፕላን ባለቤት ነበሩ)፣ ቀላል ተፅእኖ ፈጣሪ አልነበሩም። ከላይ ያነሳናቸው ሦስቱ ሰዎች እጆቻቸው ረጅም ከመሆናቸውም በላይ፣ የፈለጉትን ለማስደረግ (Make-Belive) አቅሙም ችሎታውም ነበራቸው። በዚያ፣ በቂምና በበቀል በሚያከፍል ዘመን፣ ያንን ቢያደርጉ ደግሞ አያስደንቅም ይሆናል።

ንጉሠ ነገሥቱ ፍርድ ሚኒስትራቸውን የካቲት 2/1953 ዓ.ም. ሾመው፣ የ“ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይንና የግብረ አበሮቹ” ክስ የካቲት 13/1953 ተጀመረ። ከዚያም በጣም በፍጥነት (በየቀኑ ለማለት በሚያስችል ኹናቴ) በየካቲት 20፣ በ21፣ በ24፣ በ25፣ በ28፣ እና በ29 ቀን ምስክሮች ፍርድ ቤት ቀርበው መሰከሩ። ጄኔራሉ፣ ለይግባኝ አቤቱታም በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በየካቲት 27/1953 ዓ.ም. ቀርቦ ነበር። በመጋቢት 18/1953 ዓ.ም. የመጨረሻው ፍርድ ተሰጠ። የሞት ፍርድ ነበር። የዳኞቹም ውሳኔ (ቃለ-ጉባዔ) በመጋቢት 19/1953 ዓ.ም. ተፈረመ። በመጋቢት 20/1953 ዓ.ም. ከጠዋቱ በ12 ሰዓት ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ፣ ተክለ ሃይማኖት ቤተ-ክርስተያን ፊትለፊት ባለው አደባባይ ላይ ተሰቀለ። (አንቀው ከገደሉት በኋላ ነው የሰቀሉት የሚሉም አልታጡ።) በርካታ ጥርጣሬ የሚያጭሩ፣ ብሎም የንጉሠ ነገሥቱን ያልተገባ ሥነ-ምግባር የሚያመለክቱ ቁም-ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው፣ ብ/ጄኔራል መንግሥቱ የይግባኝ መብቱን በቃል ተጠይቆ-“ይግባኝ አልጠይቅም” ቢልም ቅሉ፤ በ48 ሰዓታት ውስጥ እንዲገደል መደረጉ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ብልሽት፣ “የአሣ ግማቱ፣ ከወደ አናቱ!” እንደሚባለው መሆኑን ያረጋግጣል። ከላይኛው ባለሥልጣን ጀምሮ፣ ፍትሕን የመደፍጠጥ አባዜ ገዢዎቹን ሁሉ የተጠናወታቸው በሽታ እንደሆነም ያሳብቃል። (የሌሎቹን ገዢዎች፣ ፍትሕን የመደፍጠጥ ነቀርሳና ደዌ ወቅቱን ጠብቀን በጊዜው እንመለስበታለን።)

ጃንሆይ፣ “ለምን የአንበሳ ዋሻቸው ውስጥ ያለውን “ድንቢጥ”፣ በ48 ሰዓታት ውስጥ ለማስወገድ ፈለጉ?” ብለን ብንጠይቅ፣ የመኳንንቱና የቤተሰቦቻቸው “ጫና በዝቶባቸው ነው!” የሚሉ ወገኖች አይጠፉም። እርሱስ ይሁን፣ ለምን ጄኔራሉ ገለልተኛ የውጭ አገር ጠበቃ ቅጥሮ እንዳይከላከል ዘጋጉበት? ለምንስ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ላይ፣ “ዐይኔ እስከሚድንና ራሴን መከላከል እስከምችል ድረስ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ?” ሲል ጠይቆ እንቢ ተባለ? ለምንስ፣ መንግሥት ያቆማቸው የተከሳሾቹ ጠበቆች አንድ እንኳን አጥጋቢ መስቀለኛ ጥያቄ ሳይጠይቁ፣ በዝምታ ተከሳሹን ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይን ለሞት ፍርድ ዳረጉት? ኧረ ለምን ተብሎ፣ በምንስ መስፈርት፣ ከነዚያ ሁሉ የመፈንቅለ መንግሥቱ ተዋንያን መካከል መንግሥቱ ነዋይ፣ ሻምበል ክፍሌና መቶ አለቃ ድጋፍ ተድላ ብቻ ሊከሰሡ ቻሉ? በምንስ ተጨባጭ የፖሊስ ምርመራና ማስረጃ ነው፣ በሚያዝያ 3/1953 ዓ.ም. “ጥፋተኛ ያለመሆናቸው ተጣርቶ፣” 89ኙ የክብር ዘበኛ መኮንንኖች፣ ጃንሆይ ፊት ቀርበው “አባታዊ መህረት” የተደረገላቸው?(አዲስ ዘመን፣ ሚያዝያ 4/1953 ዓ.ም.፣ ገጽ-1።) ከሁሉም-ከሁሉም ደግሞ፣ ብ/ጄኔራሉን በስቅላት ከገደሉ በኋላ፣ በጥር 1957 ዓ.ም.፣ የጄኔራሉን የደረሰ ጎረምሳ ልጅ (ያኔ 17 ዓመቱ ነበር) ቴድሮስ አደባባይ በጠራራ ፀሐይ በሞተር ሳይክል ሲሄድ በሽጉጥ የገደሉት ወገኖች፣ ለፍርድ ሳይቀርቡ የቀሩት? (እነዚህንና ሌሎቹንም ጥያቄዎች የሚመልስ፣ እጅግ ልባም የሆነ የታሪክ ተመራማሪንና የርሱን ጥረት ይፈልጋሉ።) የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ጉዳይ ገና ብዙ ማስረጃዎች አልተገለጡም። አቶ ብርሃኑ አስረስ በቅርቡ የሚያሳትሙት መጽሐፍ መጠነኛ መረጃዎችን ሊሰጠን እንደሚችል እናምናለን። ብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ 15ቱን ባለሥልጣኖች እንዳልገደለም ማረጋገጫ ይሠጡናል ብለን እንጠባበቃለን። እስከዚያው ድረስ ግን የተከስተ መላከን ያልታተመ ጥናታዊ ጽሑፍ የሚፎካከር አላገኘንም። (ቸር እንሰንብት)


ሰሎሞን ተሰማ ጂ. (www.semnaworeq.blogspot.com)

(ይህ መጣጥፍ በአዲስጉዳይ መፅሔት 13/04/2005 ዓ.ም. ቁጥር 143 ዕትም ላይ ወጥቶ ነበር።)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!