አምባ የጥናት እና ምርምር ክፍል ያቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ

Map of Barara and its surrounding.
Map of Barara and its surrounding. The places shown on the map and others are identified by Marco. From Marco Vigano, “The Names Lost, the Map Grasped,”

በሀቅ ላይ የተመሰረተ ታሪክ ጽኑ የአንድነት መሰረት ነው። ፍትህንም ለማስፈን ወሳኝ ሚና አለው። ታሪክ የራሱ የሆነ የሙያ ስነምግባር አለው። የታሪክ ባለሙያ ለሙያው ፍቅርም ሲል ህይወቱን መስዋዕት ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለበት። የሚያስከፋም ሆነ የሚያስደስት፣ የሚያስነቅፍም ሆነ የሚያስወድስ በመረጃ የተመሰረተ ሀቀኛ ታሪክን መቀበል የስልጡንነት ምልክት ነው። ታሪክን መፍራት፣ መካድ እና ማድበስበስ ኋላቀርነት ነው። ታማኝ መረጃ እስከተገኘ ድረስ ታሪክ ያለምንም ገደብ ይጻፋል። ያስከፋል ወይም ያስነቅፋል ብሎ በታሪክ ላይ ሀጢያት መስራት ጉዳቱ ከባድ ነው። የታሪክ ዕውቀት ያድጋል፣ ይሰፋል ይቀየራል። ይህ የሚሆነው ደግሞ አዳዲስ መረጃዎች በአይነትና በመጠን ሲገኙ ነው።

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነው በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ሚኒስትሮች ምክር ቤት “ኦሮሚያ” የሚባለው ክልል የአገሪቱ ርዕሰ መዲና ከሆነችው ከአዲስ አበባ ስለሚያገኘው ልዩ ጥቅም ያስተላለፈው ረቂቅ አዋጅ ነው። አዋጁ የወጣው የሀገሪቱ “ህገ መንግስት” ስለዚሁ ልዩ ጥቅም ጉዳይ የደነገገውን መሰረት በማድረግ እንደሆነ ተገልጿል። በዚህ ጽሁፍ ለማስገንዘብ የምንሞክረው የዛሬዋ አዲስ አበባ ከ600 ዓመት በላይ ታሪክ እንዳላትና በረራ በመባል በ15ኛው እና 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና እንዳገለገለች ነው።

ይህ ጽሁፍ ሁለት አላማዎች አሉት። አንደኛው የበረራን ወይም የአዲስ አበባን የኋላ ታሪክ ከአህመድ ግራኝ (1529-1543) ጦርነት በፊት እና ኦሮሞ ወደ ሸዋ፣ ዳሞት እና ጋፋት ከመስፈሩ በፊት ያለውን ዘመን መዳሰስ ነው። ሁለተኛው ስለ በረራ በኢትዮጵያውያን እና በውጭ ሀገር ጸሓፊዎች የተጻፉ የታሪክ ማስረጃዎችን ለአንባቢ ማስተዋወቅ ነው። በተለይም የቦታው ተወላጆች ስለበረራ በሰጡት ምስክርነት ላይ ተመስርተው የተጻፉትን የጽሁፍ መረጃዎች እና ካርታዎች ለማቅረብ ይሞክራል።

በረራ የኢትዮጵያ የነገስታቱ ዋና መቀመጫ በመሆን ከአጼ ዳዊት ቀዳማዊ (1380-1413) ጀምሮ እስከ አጼ ልብነ ድንግል (1508-1540) ከመቶ ዓመት በላይ አገልግላለች። በረራ ወረብ በሚባል አውራጃ ስር ትተዳደር ነበር። ወረብ ታላላቅ አብያተ ክርስትያናት እና ቤተ መንግስት የነበሩበት በጣም ሀብታም አውራጃ ነበር። በ16ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ብዙ የውጭ አገሮችን የጎበኙት አባ ዳንኤል የተባሉ ኢትዮጵያዊ መነኩሴ ወረብን በኢየሩሳሌም መስለው ጽፈዋል። በዚሁ ዘመን የግራኝ አህመድን ጦርነት የዘገበው ከሰራዊቱ ጋር በመሆን ወረብንና በረራን ያየው አራብ ፈቂህ ወረብን የሀበሾች ምድራዊ ገነት ይላታል።

ሆኖም ከግራኝ ከ1529 ዓመተ ምህረት ሽምብራ ኩሬ ጦርነት በኋላ የንጉሱ ቤተመንግስት በረራና በወረብ የሚገኙ ታላላቅ አብያተ ክርስትያናት በግራኝ ወታድሮች ተዘርፈዋል፤ ወድመዋል። ከኦሮሞ ፍልሰት በኋላ ደግሞ ወረብና ዋና ከተማው በረራ ብቻ ሳይሆን በሰሎሞናዊያን ዘመን የአገሪቱ የሀይማኖት፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የአስተዳደር እና የህዝብ ማዕከል የነበሩ ቁልፍ ቁልፍ አውራጃዎች በኦሮሞ ቁጥጥር ስር ውለዋል። ከነዚህም ባሌ፣ ፈጠጋር፣ ዳሞት፣ ወረብ፣ ጋፋት፣ ሸዋ እና ጉራጌ ይገኙበታል። ይህም የኢትዮጵያን ፖለቲካ፣ የህዝብ ስብጥር እና አስተዳደር ከግራኝ በበለጠ ሁኔታ እና በዘላቂነት ቀይሮታል።

አጼ ምኒልክ ወደ ወጨጫም ሆነ ወደ እንጦጦ የሄዱበት ምክንያት የአጼ ዳዊትን ከተማ በረራን ፍለጋ ነው። ስለዚህ አጼ ምኒልክ አዲስ አበባን አልመሰረቱም። ምኒልክ አንድ ስንዝር የኦሮሞ ርስት መሬት አልወሰዱም። የሸዋ መኳንንትም ሆነ አጼ ምኒልክ ወደ እናርያ፣ ወደ አሮጌው ዳሞት እና ጋፋት የዘመቱት አዲስ አገር ለማቅናት አይደለም። ባለ አገሮቹ የጋፋት ዘሮች እና አማሮች ቋንቋቸው ተወልዶ ያደገበትን እና ለብዙ ሺህ አመታት የኖሩበትን አጽመ ርስታቸውን እንደ አዲስ አገር የሚያዩበት ምንም ምክንያት የላቸውም።

ለፍትህ እና ለአንድነት ሲባል በታሪክ ሂደት ጉዳት የደረሰባቸውን ህዝቦች እውቅና መስጠት ከጉዳታቸው እንዲያገግሙ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ድጋፍ ማድረግ ተገቢና ፍትሃዊ ነው። በሃገራችን ኢትዮጵያ የምናየው ግን ከዚህ ተቃራኒ ነው። ርስታቸው የፈለሰባቸው እና ቋንቋቸው የተደመሰሰባቸው ሰዎች ወራሪ ተብለው ዳግም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ‘በፊት የበቀለን ጀሮ በኋላ የበቀለ ቀንድ በለጠው’ እንዲሉ የጋፋት እና የዳሞት ዘሮች፣ ጉራጌዎች እና አማሮች ቋንቋቸው ተወልዶ ካዳገበት፣ አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው ትናንት በእየሩሳሌም ከመሰሉት ከጥንት አጽመ ርስታቸው አገራችሁ አይደለም ተብለው ተባረዋል። ለዘላቂ ሰላም እና ፍትህ ሲባል ኢትዮጵያ እንደ አሜሪካና ካናዳ ካሉ አገሮች መማር አለባት።

ሁላችንንም ባለርስት የሚያደርግ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት እናልም። ... (ሙሉውን የአምባ የጥናት እና ምርምር ክፍል ጽሑፍ በፒዲኤፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!