“ኢሕአዴግ ሃገሪቱን ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳይከታት እሠጋለሁ” ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ናቸው፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት በአሜሪካ ኖረዋል፡፡ የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑና ሆነውም የማያውቁት ዶ/ር ዳኛቸው በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ግን ምሁራዊ አስተያታቸውን በየጊዜው ይሰጣሉ፡፡ ከዶ/ር ዳኛቸው ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሎሚ አዘጋጅ ቶማስ አያሌው ያደረገው ቆይታ ይህንን ይመስላል፡-



ሎሚ፡- የሃገሪቱን ወቅታዊ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዴት እየተመለከቱት ነው?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- በእኔ አመለካከት አሁን ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ከኢህአዴግ አካሔድ አንፃር ስናየው የስልጣን ሽግግር ወቅት ነው፡፡ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ካረፉ በኋላ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ተሹሟል፡፡ ከጀርባ የኃይል ወይም የበላይነት የማግኘት ትንቅንቅ እየተካሄደ ለመሆኑ አንዳንድ ምልክቶችም ይታያሉ፡፡ ያለፉትን አስር ዓመታት ፓርቲው ከለመደው የቡድን (ኮሌክቲቭ) አመራር ወጥቶ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ብቻቸውን በበላይነት ስላስተዳደሩት ያንን ክፍተት መተካት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ የበላይነት ቦታውን ለመውረስ ግብግብ እየተካሄደ ነው፡፡ ኢሕአዴግ በጣም ምስጢራዊ ስለሆነ በፊት ለፊት ምን እንደሚካሄድ ማወቅ አይቻል ይሆናል፡፡ ምልክቶች ግን አሉ፡፡ የበላይነት ለማግኘት በፓርቲው አመራር መካከል ትንቅንቅ እየተካሄደ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም ግን በርግጠኝነት ዘርዘር አድርጎ ’እንደዚህ እና እንደዚያ’ ነው ብሎ በድፍረት ለመናገር በጣም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

ሎሚ፡- መንግስት ከኃይማኖት ተቋማት ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቷል፤ “አክራሪነት” የሚለው ቃል ምክንያትና ተገቢነትን እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- በጣም አሳሳቢ፣ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ በቅርቡ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም በተከታታይ የፃፉትን አንድ ፅሁፍ አንብቤያለሁ፡፡ ፅንፈኝነትን የሚመለከት ሦስት መሠረታዊ ችግር ያለው ፅሁፍ ነው ያስነበቡን፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ፡- በኦርቶዶክስ ኃይማኖት ላይ ትልቅ ጫናና የማይሆን ትችት አቅርበዋል፡፡ “ብዙ ሺህ ዓመት ቆየን ብለው ይከራከራሉ” የሚል ትችት አላቸው፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ብዙ ሺህ ዓመት አልቆየም እንዴ? ታሪኩ እንደሚያመለክተው ሮም ክርስትናን ሳትቀበል፣ ክርስትና የተቀበለ ሕዝብ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ረዥም የፅናት የክርስትና ታሪክ አንድ ሕዝብ ቢኮራ እንዴት እንደ ትምክህት ይቆጠርበታል? 

ሁለተኛ ሚኒስትሩ ወደኋላ ሔደው ’የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኃይማኖት የመንፈሣዊና፣ የአስተዳደር ልዕልና የለውም ነበር’ ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን የቅርብ ታሪክን እንኳን በጥቂቱ ቢመለከቱ፤ የዛሬ መቶ ዓመት በዘመናዊ ትምህርት ዙሪያ ሊቃውንቱ ነገስታቱን የሞገቱበትን፣ የፓትርያርክ መንበርን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያኗ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች መሆኗን ይረዱ ነበር፡፡ በተጨማሪም ዶ/ር ሽፈራው አይወዱት እንደሁ እንጂ ፤ በቅርቡ በታተመ የብላቴን መርስኤ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ መፅሀፍ ላይ ታላቁ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ሊቅ አለቃ ታዬ ከዚህ ዓለም በሞት በተለዩ ጊዜ ’አባቶቼ መቃብር አሳርፉኝ’ ብለው ቢናዘዙም “ፕሮቴስታንት ሆነዋል” ተብሎ ስለነበር (በንግሥተ-ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት መሆኑ ነው) በጊዚው የነበሩ ካህናት “ኃይማኖቱን ስለለወጠ ሥላሴ አይቀበርም” ብለው ከለከሉ፡፡

እቴጌዋ “እባካችሁ” ብለው ቢለምኑ “በኃይማኖታችን ደንብና ሥርዓት ውስጥ አይግቡብን” ብለው ምልጃቸውን ሳይቀበሏቸው ቀሩ፡፡ መቼም መንፈሣዊና አስተዳደራዊ ልዕልና የሌለው ቤተክህነት ይህን ማድረግ አይችልም፡፡ ሦስተኛ በቅርቡ በተካሔደው የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ከጳጳሳቱ አንዱ እንዳሉትና እኔም እንደምጋራው አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኦርቶዶክስ ከሆነ ስለ ኦርቶዶክስ፣ ሙስሊም ከሆነ ስለ ሙስሊም፣ ፕሮቴስታንት ከሆነ ስለ ፕሮቴስታንት ይናገር እንጂ፤ ከቆምንበት ሃይማኖት እየተነሳን በማንከተለውና በማናውቀው ሃይማኖት ላይ ትችት ባንሰነዝር ጥሩ ይመስለኛል፡፡ 

ሚኒስትሩ በተከታታይ ስለ አክራሪነትና ፅንፈኝነት የፃፉትን ፅሁፎች አጠቃለን ስንመለከተው ለወጉ ያህል የሌሎቹን ሃይማኖቶች ስም ዘረዘሩ እንጂ በአክራሪነት ተፈርጀው ዋናው ቀስት የተነጣጣረባቸው ግን እስልምናውና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሀዶ ሃይማኖት ላይ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ኢህአዴግ የሃይማኖት ጉዳይ በትልቅ ጥንቃቄ መያዝ ያለበት ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ይኖርበታል፤ እዚህ ላይ ሰር ዊንስተን ቸርችል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ስለ ጄኔራሎቻቸው “war is too serious a subject to be left for the Generals” (“ጦርነት በትኩረት፣ በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ጉዳይ ስለሆነ ጄኔራሎች ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም፡፡”) ብለው ነበር፡፡ ከዚህ አባባል የምንማረው በአንድ ሀገር ወሳኝ የሆኑ እንደ ሃይማኖት ባሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ’ሙያቸው ነው’ ተብሎ ብቻ ጉዳዩን ለካድሬዎች መተዉ ስህተት ላይ እንደሚጥል ነው፡፡ በተጨማሪም የሃይማኖትን ጉዳይ በትልቅ ሃላፊነት መያዝ ብቻ ሳይሆን ከመንግስት ፖለቲካዊ ጥቅም ጋር በማያያዝ ብቻ በልዕልናቸው ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ ተገቢ አይደለም፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ ብዙ ጊዜ እንደሚያደርገው የራሱን ፖለቲካዊ ጥቅም አስከብራለሁ በሚል ፈሊጥ አገሪቱን ወደ እርስ በርስ ግጭት እንዳይከታት እሰጋለሁ፡፡

ሎሚ፡- በኢህአዴግ ውስጥ የአመራር ችግሮች እየተስተዋሉ ነው ብለው ያስባሉ? 

ዶ/ር ዳኛቸው፡- አቶ ኃይለማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ በአማካሪ ስም በአራትና በአምስት አንጋፋ ኢህአዴጐች መከበባቸው አንድ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ አንድ የአገራችን ሽማግሌ በአንድ ወቅት ሲያጫውቱኝ “አንዱ የልጅ ኢያሱ ችግር የመካሪው መብዛት ነበር” ያሉኝ ትዝ እያለኝ በአቶ ኃይለማርያም ዙሪያ የተሰለፉትን የአማካሪዎች ቁጥር ሳይ የልጅ ኢያሱ ሁኔታ ተመሳሳይ መልክ ይዞ በዐይነ ሕሊናዬ ይመላለሳል፡፡ ሌላው የኢህአዴግ ችግር ሥርዓቱ የፈጠረውን የምዝበራና የሙስና ችግር መፍትሄ ሊያበጅለት አለመቻሉ ነው፡፡ አሁን እንደምናየው አንድ የፖለቲካ ሥርዓት ከሕግ በላይ የሆኑ አይነኬዎችን ካወጣ ያ ሥርዓት አደጋ ላይ ነው ያለው ማለት ነው፡፡ የሙስናው ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አልፎ አልፎ በመገናኛ ብዙሃን መንግስት ራሱ እየነገረን ነው፡፡ በአቀራረብ ደረጃ ስናየው ግን ለጉዳዩ ተገቢ አትኩሮት ሳይሰጠው ለይስሙላ የተዘጋጀውን ቴአትር ያቀርቡልናል፡፡ ሙስናን በሆነ ዘዴ ለመከላከል መሞከር ነው እንጂ ቴአትር ማዘጋጀት ተገቢ አይደለም፡፡ 

ሎሚ፡- የአፍሪካ መሪዎች አይ.ሲ.ሲ ጫና ይፈጥርብናል ይላሉ፡፡ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ይህን ጉዳይ በሚመለከት በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ በአንክሮ ገልፀዋል፡፡ ይህንን ነገር እንዴት ታዘቡት?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- መቼም አንዳንድ ጊዜ ሙሉ እውነት፣ ሙሉ ውሸት የሚባል ነገር የለም፡፡ በተወሰነ ደረጃ እነኚህ ሰዎች (ፈረንጆቹ) ትንሽ የራሣቸው ጫና የሚፈጥሩበት ነገር አላቸው፡፡ ይሄ ማለት ግን የሚመሰርቱት የክስ ሂደት በሙሉ ሀሰት ነው ማለት አይደለም፡፡ የአፍሪካ መሪዎችን ስጋት በምናይበት ጊዜ የ17ኛው ክ/ዘመን ትልቁ ፈላስፋ ቶማስ ሆብስ “ሳይኮሎጂካል ኢጎይዝም” በሚለው ሃልዮቱ ላይ ሲያስረዳ ያለው ትዝ ይለኛል፡፡ “አንዲት የ14 ዓመት ልጅ የጓደኛዋ እናት ስትሞት ስቅስቅ ብላ ሀዘንተኛዋን አቅፋ የምታለቅሰው ከልብ አዝና ሳይሆን የራሷ እናት ሞት በዓይነ ህሊናዋ እየታያት ነው፡፡” አሁን ከአይ ሲሲ ጋር አተካራ የገጠሙት የአፍሪካ መሪዎች በጥቁርነታችን አድልዎ ደረሰ ብን ብቻ ብለው ሳይሆን ነግ በኔ በሚል እሳቤ የራሳቸው ዕጣ ፈንታ እየታያቸው ነው፡፡ 

ሎሚ፡- ተቃዋሚዎች በኢህአዴግ ጫና በዝቶብናል ይላሉ፡፡ ይህ ባለፈው ከተደረጉ
ሰልፎችና ከተፈጠረው ሁኔታ አንፃር የሚታወስ ነው፡፡ ያለተቃዋሚ ሃገር መምራት የሚፈልግ ስርዓት ምን ዓይነት ነው?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- ጫና ማብዛት ብቻ ሣይሆን ኢህአዴግ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፀረ ዴሞክራሲ መሆኑን እያስመሰከረ ነው፡፡ ድሮ ትንሽ የማስመሰል ሁኔታ ነበር፤ አሁን ግን ፈፅሞ የለም፡፡ አሁን ’እኛ እየሰራን ነው፤ ዝም ብላችሁ አድንቁን፤ እነዚህ ተቃዋሚዎች መሰናክሎች ናቸው’ ብለው ያምናሉ፡፡ ተቃዋሚ የሚባል ፈፅሞ መስማት አይፈልጉም፡፡ ይሄ የፖሊሲ ለውጥ አይመስለኝም፡፡ እርግጠኝነት ጠፍቷቸዋል፡፡ ብዙ ቅሬታ አለ፡፡ በዚህ ጊዜ አመጽ ሊያቀጣጥሉብን የሚችሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው ብለው ስለሚያስቡ ትልቅ የክትትል ጫና ያደርሱባቸዋል፡፡ እንደድሮው ቢሆን ኖሮ በልበ ሙሉነት ሰላማዊ ሰልፍ ውጣ፣ ሂድ ፃፍ ነበር የሚሉት፡፡ አሁን ላይ ግን የኃይል ሚዛናቸው ላይ እርግጠኛ ባለመሆናቸው ከበፊቱ በባሰ በእንጭጩ አለች የሚሏት ዴሞክራሲ እንኳን እስትንፋሷን እያፈኗት ነው፡፡ በመሆኑም ተቃዋሚ ፓርቲውን በደንብ አድርገው እየተከታተሉት ነው፡፡ ነገር የሚቀሰቅስባቸው ይመስላቸዋል፡፡ የአረቡ ዓለም አብዮት እንደ ልምድ ይታወቃል፤ ይህንን ሳስብ እንደ ፖለቲካዊ የአመለካከት ለውጥ አይደለም የማየው፤ የፍርሃት ሁኔታ ነው የሚመስለኝ፡፡ 

ሎሚ፡- ምን ዓይነት መንግስታዊ ስጋቶች አሉ? የኢህአዴግ ስጋትስ የትኛው ጋር ይመደባል?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- የታሰበው፣ የተነገረው ነገር አልደርስ ሲል ያለመደሰትና ያለመርካት አለ፡፡ የብክነትም ችግር አለ፡ ፡ በአፄ ኃ/ሥላሴ ጊዜ አንድ ደጃዝማች ስታይ ምን ዓይነት ሕይወት እና የሃብት መጠን እንዳለው ትገምታለህ፡፡ በደርግም ጊዜ ሀብታሙን መገመት ትችላለህ፡፡ አሁን ግን በግለሰቦች እጅ የሚታየው የሀብት መጠን ከእኛ የግምት አድማስ ውጪ ነው እየሆነ ያለው፡፡ እከሌ 20 ሺህ፣ 30 ሺህ ብር ሰረቀ ድሮ የሚያስደነግጥ ዜና ነበር፡፡ አሁን እኮ በ30 ሚሊዮኖች ነው የሚወራው፡፡ በሂደት ወደ ቢሊዮን ነው የሚያመራው፡፡ እንደውም ይሄ የሽግግር ክፍለ ጊዜ ስለሆነ አብሮ የሚመጣ ነገር ነው ይሉሀል፡፡ አንድ ስርዓት እንደዚህ የሚያስብ ከሆነ ስርዓቱ ተበላሽቷል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ 

ሎሚ፡- ኢህአዴግና ምሁራን ምን ዓይነት ግንኙነት አላቸው? ለምሁራን የተሰጠው ቦታ ምን ዓይነት ነው? 

ዶ/ር ዳኛቸው፡- ጭምት ምሁራን አሉ፤ “እኔ አልናገርም፤ በደርግም ጊዜ ብዙ አይቻለሁ” የሚሉ፡፡ ኢህአዴግን የሚያገለግሉ ምሁራን አሉ፡፡ ለነዚህ ቦታና ድጐማ ይሰጣል፡፡ በጥቅማ ጥቅም ለመያዝ ይሞክራሉ፤ እንጂ የራሣቸው ኤክስፐርት፣ የራሣቸው ምሁራን ግን አሏቸው፡፡ ምሁራኑ ወደዚህ ጎራ አልቀላቀል ሲሉ የራሣቸውን ምሁራን ፈጠሩ፤ በየቦታው ያለውን የጥናት ተቋማትን ደረጃ አወረዱት፡፡ ድሮ አፄ ኃ/ስላሴ ሊወርዱ ሲሉ (እኔ እንደሰማሁት) “እንዴት ነው ፊውዳሊዝምን የምንመታት” አሉና መከሩ አሉ፡፡ በመጨረሻ ሹመቷን እናርክሰው ተባለ፡፡ ወደ ዘጠኝ ሺህ ደረጃ አወጡ፡፡ ፊታውራሪ፣ ቀኛዝማች…፡፡ ኳስ ተጫዋቹ ’ፊታውራሪ’፣ ታክሲ ነጂው ’ቀኛዝማች’ እየተባለ ስያሜ ሲሰጥ ይሄ ደረጃ ቀደም ሲል የነበራቸው በሙሉ በጣም ተበሣጩ፡፡ እኔ አሁንም የምመለከተው በትምህርት ዘርፍ ማስትሬት ዲግሪ አለኝ የማይል ሰው አታገኝም፡፡ ቢኤማ መጫወቻ ሆኗል፡፡ ልክ ያኔ የፊውዳሉን ዘመን እንደመቱት እነኚህ ደግሞ ትምህርትን መቱት፡፡ ስሰማ ’የማንንም ገበሬ ልጅ ማስተርስ አስይዘናል’ እየተባለ ነው፡፡
ከአስራ አንድ ሰው በላይ ሁሉንም እግር ኳስ ተጫዋች ማድረግ አይቻልም፡፡ ዲግሪውን ትርጉም አልባ አደረጉት፡፡ እኔ ዶክትሬቴን ሰጥቼ ፊታውራሪነቴን መቀበል ነው የምፈለገው፡፡ አያቴም ፊታውራሪ ነበሩ፡፡ ይህንን የተመኘሁት ግን ወድጄ አይደለም፤ ከብስጭት ነው፡፡ እስቲ እግዚአብሔር ያሣይህ የተልዕኮ ፒ.ኤች.ዲ (“PHD”) የሚባል ነገር አለ? ማንም እንደሚያውቀው ትምህርት ውይይት ይጠይቃል፡፡ ከአንተ ጋር ያደረግኩትን ቃለ መጠይቅ በስልክ ብናደርገው አያምርም፡፡ ፊት ለፊት እየተነጋገርን ሲሆን ግን የተለየ ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ የትምህርት ጥራትን አውርዷል፡፡ ምሁሩን በማውረድ፣ ማንም ሊያገኘው ይችላል በሚያስብል መልኩ 50 ሺህ ኤም.ኤ፣ አስር ሺህ ፒ.ኤች.ዲ አወጣለሁ ይላል፡፡ በሦስት ሴሚስተር ኤምኤ እየሰጠ ነው፡፡ በክረምት ሁለት ሁለት ወር ይማሩና፣ በስድስተኛው ወር ማስተርስ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ በስድስት ወሩ ተማሩና የትምህርት ጥራት መጣ ማለት ይቻላል፡፡

ሎሚ፡- የሀገሪቱን ተቃዋሚ ፓርቲዎችስ እንዴት ይመለከቷቸዋል?

ዶ/ር ዳኛቸው፡- በሃገሪቱ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቅ ችግር ውስጥ ነው ያሉት፡፡ የኢህአዴግ ጫና ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ ስለራሣቸው ማሰብ አለባቸው፡፡ ባለ ራዕይ መሆን አለባቸው፡፡ አርቀው ማሰብ፣ መስማማት፣ የግል ንትርካቸውን መተው፣ ጣት መቀሳሰር ማቆም አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄንን እየጠየቃቸው ነው፡፡ ከመንግስት በኩል ያለባቸው ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ዋናው ግን የራሣቸውን ችግር መፍታት ነው፡፡ ልጅ ሆኜ አንድ የሰማሁት የእንግሊዝ ሃገር ተረት አለ፡፡ “ጠላት አለን ብለው የአንድ መንደር ሰዎች ጫካ ገቡ አሉ፤ በኋላ ሲፈልጉ ሲፈልጉ አንዱ ወደ ሰማይ ተኮሰ፤ ጐበዝ ጐበዝ ጠላታችንን አገኘሁት አለ፡፡ የታለ የታለ ሲሉት፣ ጠላታችንማ እኛ ራሣችን ነን፤ ሌላ ጠላት የለንም” አላቸው፡፡ የተቃዋሚው ጠላት ራሱ ተቃዋሚውም ጭምር ነው፡፡ 

ሎሚ፡- ዶክተር ካለዎት ሰዓት አጣብበው ለሰጡን ምላሽ አመሰግናለሁ፡፡

ዶ/ር ዳኛቸው፡- አመሰግናለሁ፡፡

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ