Welelaye's yerob gitem y2 n52ወለላዬ በየሳምንቱ ረቡዕ ረቡዕ በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ላይ ለሁለት ዓመታት ያህል ሳያቋርጥ 104 ግጥሞች በመጻፍ አስነብቦናል። በነዚህ ግጥሞቹ እኛን ሆኖ ውስጣችን ገብቶ ያልተናገርነውን ተናግሮልናል። ታዝበን ያለፍነውን ገልጾልናል። የሸሸግነው አጋልጦ አውጥቶብናል። የረሳነው አስታውሶ ወይ ጉድ አሰኝቶናል።

ግጥሞቹ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ አገራዊና ተፈጥሮዋዊ ነገሮችን ይዘው የሚያጠነጥኑ፤ ጭብጣቸው የተለያየ መልዕክት የሚያስተላልፍ በመሆኑ በአዲስ ረቡዕ አዲስ ነገር ለማንበብ በጉጉት ያስጠብቃሉ። ረቡዕ እንደሌላው ሁሉ ቀን ቢሆንም በወለላዬ ግጥም ምክንያት አንባቢዎቹ ዘንድ ደምቆ የሚታይ ሆኗል።

ደራሲና ገጣሚ አለማየሁ ታዬ ወለላዬ የአንድ ዓመቱን ረቡዕ ግጥም ሲያጠናቅቅ ስለ ግጥሞቹ አስተያየት ሲሰጥ፤ “የወለላዬ ግጥሞች አብዛኞቹ ባራት መስመር የተቋጠሩ እጥር ምጥን ያሉ የዘመናችን መዝሙሮች የየዕለት ሕይወታችን ሂሶች ናቸው። ግጥሞቹ ግልጽና ቀጥተኛ ስለሆኑ አደናጋሪነት አይታይባቸውም። የየስንኞቹን ሃሳብ ለመረዳትም ጥልቅ ምርምርና ተመላልሶ ማንበብን አይጠይቁም” በማለት ገልጾታል።

ኢትዮጵያ ዛሬም ይህን አስተያየት የምትጋራ ሲሆን፣ ወለላዬ በየሣምንቱ የሚያቀርበውን የረቡዕ ግጥም ሁለተኛ ዓመትን ከላይ በሰፈረችው ግጥም ስላጠናቀቀ ስለ ግጥም ሥራውና ስለ ገጣሚነቱ ምን ይላል ከሚለው ሃሳብ በመነሳት ጥያቄዎች አቅርበንለት ነበር። የሰጠንን መልስ እንዳለ አስፍረናል። መልካም ንባብ!!

ኢዛ፣ ወለላዬ እስቲ ስለገጣሚነትህ አጫውተን የግጥም ሥራስ እንዴት ነው?

ወለላዬ፣ በአሁን ጊዜ ስለ ገጣሚነቴም ሆነ ስለግጥም ሥራ ብዙ የምነግርህ አይኖረኝም። ገጣሚ ነኝ ብዬ ለመናገር ያን ያህል አቅም ያካበትኩ ነኝ ለማለት አልደፍርም፤ በርግጥ በዝቺው ባለችኝ ተነስቴ መናገር እችላለሁ ያ ግን ብዙ አይመቸኝም።

ኢዛ፣ ለምን?

ወለላዬ፣ አየህ ድምጻዊ ያልሆነውን አንድ ዘፈን አወጣ ብለን ድምጻዊ እገሌ ስንል፣ ደራሲ ያልሆነውን ደራሲ ብለን ስንጠራ፣ ጋዜጠኛ ያልሆነውንም ጋዜጠኛ እከሌ እንደዘገበው ብለን በመናገር ያልሆኑትን ስም እየሰጠን አለሙያቸው ሙያ እየጫንባቸው አበላሽተናቸዋል። እነሱም አይደለንም ብለው አይሸሹትም ይቀበሉታል በኋላ ግን ያለ ችሎታቸው የተሸሸከሙትን ሙያ ወርውረው ለመጣል በመቸገር ሲንተፋተፉ ከርመው ይጠፋሉ። አንዳንዱ ደግሞ ስላልከው ነኝ ብሎ ስለሚያስብ ሙያውን እንደገልቱ ቡሀቃ ሲያጨማልቀው ይታያል። ሌላው ባለመሆንና በመሆን መሀል ተቀምጦ ተቀዣብሮበት ያቀባዥርሀል። አኩርፎ የሚጠፋም አለ።

ገጣሚ መሆን ደግሞ ከነዚህ ሁሉ የከበደ ልዩ ሙያ ነው። እያንዳንዱ ሕዝብ ግጥም ልቡ ውስጥ አለ። በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለግጥም ቅርብ ነው በሆያ ሆዬው በዘፈኑ በቀረርቶው በእሰጥ አገባው በእንካ ሰላምትያው ከግጥም ጋር ተዋህዷል፤ ባይገጥም እንኳን ስለግጥም ያውቃል ቅኔ ይፈታል መጥፎና ጥሩውን ይለያል እዚችጋ ሰበርካት ብሎ ይተችሃል። እና በዚህ ሕዝብ ፊት ገጣሚ ነኝ ማለት አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ ገጣሚ ስትባል መጠንቀቅ አለብህ። የገጣሚ ሸማ አጥልቀህ ገጣሚ ነኝ ብትል አይሆንም ስምህ ሕዝብ አፍ አይገባም። እስቲ ገጣሚ ፀጋዬ ገብረ መድህንን ጥራ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ በል ገጣሚ ኃይሉ ገሞራው ... ስማቸውን ገና ስትሰማ የግጥም ዶፍ ዙርያህን ያጥለቀለቀህ ያህል ይሰማሀል። እናም ገጣሚ ስትሆን ጥያቄና መልስ አያስፈልግህም ጥያቄውም መልሱም ሥራህ ውስጥ ይገኛል። የኔ ጉጉት እዛ ለመድረስ ስለሆነ አሁን ገጣሚ ነኝ ማለት ያስፈራኛል።

ኢዛ፣ ገጣሚ መባል ያስፈራኛል ካልክ እስከዛሬ የገጠምካቸውን ግጥሞች ምን ብለን እንጥራቸው?

ወለላዬ፣ እነሱንማ ግጥም ብለህ ልትጠራቸው መብትህ ነው። ሌላ ልበላቸው ልትል አትችልም፤ እኔም ገጠምኩ ብያለሁ፤ አንተም ግጥም ብለህ አትመሃቸዋል። በርግጥም የግጥሞቼ መበራከት ለመጽሐፍ ጥራዝ በቂ ሆነው እየተገኙ ነው። ብዙ ወዳጆቼም እንዳሳትማቸው ይፈልጋሉ። ይህን አደርገዋለሁ። የረቡዕ ግጥሞቼንም ለብቻቸው መታተማቸው አይቀርም። ይሄን ጊዜ ደራሲ የሚባል ስም ስለምጭን ምናልባት ገጣሚ ወደምትለዋ ምዕራፍ እሸጋገር ይሆናል። በርግጥም ግጥም አሳትሜ ሕዝብ እጅ ስላደረስኩ ገጣሚ ብለህ በሙሉ አፍህ ልትጠራኝ ትችል ይሆናል። ባትለኝም ቋ ብዬ ለመሰበር አልደርስም፣ ገጣሚ ብዬ ራሴ ስላልቆለልኩት በሕዝብ ሚዛን ስለካ ባንስ አላፍርም። ደግሜ መጻፍ እንደገና መጻፍ እንደሚገባኝ አውቃለሁ ደጋግሜም እጽፋለሁ ሥራዬ እንዲያነሳኝ እንጂ አንኮታኩቶ እንዲጥለኝ አልፈቅድለትም።

የረቡዕ ግጥሞቼ አንባቢያን አስተያየት እና የደራሲያን ግምገማ፤ የሥራዬ መለኪያ ይሆናል የሚል ግምት አለኝ። ለመጽሐፌም ሕትመት ገንቢ ምዕራፍ ከፋች ነው።

ኢዛ፣ (ወለላዬ ይሄን ቢለኝም ጥያቄዬን አልገታሁም።) ዛሬ አንድ ግጥም የጻፈ ሁሉ ገጣሚ በተባለበት ዘመን አንተ ስፍር ቁጥር የሌለው ግጥም ጽፈህ እየታየህ በአብዛኛውም ጥሩነቱን እየመሰከረ ገጣሚ አይደለሁም ስትል “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም” አይሆንም ወይ? አልኩት።

ወለላዬ፣ አየህ ያ አሞሌ እኮ አሞሌ ላይሆን ይችላል መጀመሪያ አሞሌ አለኝ ብሎ ድንጋዩን አሞሌ ቀብቶ ያቀርባል። አቤት አሞሌዬ ሲጣፍጥ ይላል፣ አሞሌው ሲጣፍጥ የሚሉም ያዘጋጃል አሞሌው አሞሌው ይባላል ... ያ ድንጋይ ላይ የተቀባ አሞሌ በአንድ ዙር ተልሶ ያልቅና ድንጋዩ ብቻ ይቀራል።

ይሄውልህ እዚችጋ እምታየው ኃላፊነት አለመሰማትን ነው። እኔ ምን ቸገረኝ ከገዙኝ ብለህ ድንጋዩን አሞሌ ነው ብለህ ታቀርባለህ፣ ትሸታጣለህ ልትከብር ሁሉ ትችላለህ፤ ያን የህሊና ዕዳ ከቻልክ ሥራውን አጋነህ አጋናዮችም አሰማርተህ ሰማይ ላይ ልትሰቅለው ትችላለህ። ቀጥታ በተረቱ ደግሞ ከመጣህ “እዩኝ እይኝ ያለ ደብቁኝ ደብቁኝ ማለቱ አይቀርም” የሚባልም አለ፤ ሥራህን አቀለልከውም ቆለልከውም ሕዝብ ሲደርሰው እንዴት አየው፣ በምን መመዘኛ ሰፈረው ነው እንዳልኩህ ለጊዜው ማጭበርበር ይቻል ይሆናል፤ ያ ማጭበርበር ግን ከማጭበርበርነቱ አይዘልም።

በዛ ሰሞን የተነሳው ዶ/ር ኢንጅነር ነኝ ያለውን እየው፣ እራሱን አሞሌ አድርጎ ቀረበ። ከፕሬዝዳንቱ ጋር ሳይቀር ቤተኛ ሆነ። ከብዙ ምሁራን ጋር ዋለ። ትምህርት ቤቶች መረቀ። በየቦታው ደሰኮረ አወያየ ... አሞሌ ሳይሆን አሞሌ መስሎ መላስን በሚገባ ቻለ። በኋላ ግን እጣን እጣን ይሸታል እንዳልተባለ ያህል እፍ ተብሎ ተባረረ።

የፖለቲካ ሥልጣን ጨባጮችም ችግር ውስጥ ተደፍቀው ችግር ውስጥ የሚደፍቁን በዚሁ ምክንያት ነው። መጀመሪያ ድንጋዩ አሞሌ ነኝ ብሎ እላይህ ላይ ተከምሮ የኖረውን ጣልንልህ ይሉሃል። እኛ ግን እውነተኛው አሞሌ ነን ብለው ይቀርቡሃል፤ አሞሌ አይደላችሁም እንዳይባሉ መንገድ ያጥራሉ። አሞሌ ናቸው የሚል ወሽካታ ይሰበስባሉ፣ ይሾማሉ፣ ዙርያቸው ይኮለኩላሉ። ከዛ በኋላ አሞሌ አይደላችሁም ብትል፤ “ነን ብለንሃል”፣ “ናቸው ብለህ እመን!” ይሉሃል፤ እንቢ ስትል ያስሩሃል፣ ይገድሉሃል። ይሄን በተለዋወጡት መንግሥቶቻችን ያየኸው ነው።

እኔንም ገጣሚ ነህ ስትለኝ ወይም በሌላ ሙያ ስትጠራኝ፣ መጀመሪያ ነኝ ብዬ ራሴን አሳምናለሁ፣ እኔን የሚመስሉ፣ እኔን የሚያወድሱ፣ ሙያዬን የሚመሰክሩ በያዝኩት ቦታ ላይ አሰባስባለሁ። ከኔ አትበልጡም እንጂ እናንተም ባለሙያ ናችሁ ብዬ አሳምናለሁ፣ ሙከራ ያለውን ሁሉ ሰብስቤ ጥቅምና ዝና ወደሚገኝበት ጎዳና እገሰግሳለሁ፣ ጥቅሙ በተገኘና በበዛ ቁጥር መለጠጡም የዛኑ ያህል ይጨምራል።

እይ! እንግዲህ ሙያ ምን ያህል አፈር ድሜ እንደምትግጥ። ምክንያቱም እዛ ላሉት ትልቁ እኔ ስለሆንኩ፣ መመዘኛቸው እኔ ነኝ። ወደ ላይ እንዲመለከቱ አላደርጋቸውም፤ እነሱም እኔን አልፈው መሄድ አይፈልጉም። የቆሙባት ያልጠነከረች ቆጥ ተሰባብራ እንዳይወድቁ ይሰጋሉ። አንድ መንጠራራት ደግሞ አብራ ትመጣለች፤ ከስሬ ብዙ ባለሙያዎች ተሰባስበው የል? ከነሱ እኩል መሆን የለብኝም ስሜ ላይ ሌላ ከፍ ያለች ማዕረግ እጨምርባታለሁ። ያን የት እንዳገኘሁ ጠያቂ የለም፣ ሙያውን ባውቅም ባላውቅም ማንም ግድ የለውም። ከኔ የሚፈለገው ተጠቅሜ መጥቀሜ ብቻ ነው።

እዚች ጋ አንድ የቆየች ጨዋታ ላጫውትህ፣ በደርግ ዘመን ነው። የኪነጥበብ ባለሙያውች ከያሉበት ለስብሰባ ተጠሩ። ጠሪው ባህል ሚኒስቴር ይመስለኛል። አዳራሹ ከአፍ እስከ አፍንጫ በኪነጥበብ ሰዎች ጢቅ ብሎ ሞላ። ሰብሳቢዎቹ ጸጥታው እንዲጠበቅ ካደረጉ በኋላ አንዱ መናገሪያውን ጨብጦ፣ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክቱን ካስተላለፈ በኋላ፤ መጨረሻው ጫፍ ላይ የተቀመጠ ሰው እጁን አወጣ፣ ተናጋሪው ግራ ተጋብቶ እሺ እዛጋ ምን ነበር ይላል።

“ጥያቄ አለኝ።”

“እንዴ! ስብሰባው ሳይጀመር ከምን ተነስተህ ነው ጥያቄ የምትጠይቅ?”

“ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት የሚጠየቅ መሪ ጥያቄ በመሆኑ ነው።” ሰብሳቢዎቹ እርስ በእርስ ከተናገሩ በኋላ እንዲጠይቅ ተፈቀደ፤

“ስብሰባው” አለ ጠያቂው፣ “ስብሰባው የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች ስብሰባ ተብሎ አይደለም እንዴ የተጠራው?”

”አዎን! ትክክል ነው።”

“አሁን ተሰብስቦ የሚታየው እኮ ከጥቂቶች በስተቀር አብዛኛው የትያትር ቤትና የባህል ሚኒስቴር ሠራተኛ እኮ ነው። በስህተት ነው የገቡት ወይስ የኪነጥበብ ሰዎች ስላነሱ ማሟያ ናቸው? ማለቴ ...” የአዳራሹ ሕዝብ ከጫፍ እስከጫፍ በሳቅ አውካካ። ለምን? ... እውነታ አለቻ! እንደምንም ጸጥታው ሲረጋጋ ጠያቂው እንደገና ድምጹን ጎላ አድርጎ፤ “በበኩሌ ይሄን ስብሰባ መሳተፍ ስለማልፈልግ እንድወጣ ይፈቀድልኝ።” መልስ እስኪሰጠውም አልጠበቀ ሹልክ ብሎ ወጥቶ ሄደ። ይህ ሰው በወቅቱ ለየለት አበደ ተባለ። እንደውነቱ ከሆነ ይህ ሰው በትያትርና ሥነጥበብ የሠለጠነ ውጪ አገርም ሄዶ በዚሁ ሙያ የመሠልጠን ዕድል ያገኘ ነው፤ ነገር ግን ቅድም እንዳልኩህ አሞሌ ሳይሆኑ አሞሌ ነን ብለው የሚላላሱ መኖራቸውን ያውቅ ነበር።

እያደር ግን ይቺን ያህል እንኳን የሚናገር ጠፍቶ፣ ለመሪነት መመረጥ ያለበት ተጥሎ፣ ታስሮ፣ ተሰዶ፣ ተዋርዶ እየኖረ፤ መሪ መሆን እማይገባው መሪ ሆኖ ይገዛሃል። ደራሲ ያልሆነው ደራሲ ነኝ እያለ ድርሰት እንድትሸሽ ያደርግሃል። ገጣሚ ያልሆነው ገጣሚ ነኝ ብሎ ይቃዥብሃል። ሁሉም አለቦታው ተቀምጦ አገራችንም እኛም መቀለጃ የሆነው ለዚህ ነው።

ዲሞክራሲ ሊያመጣልህ የተነሳውንም ታዘብ፤ እኩልነትን ሊያቀናጅህ ሰላምና መረጋጋት ሊፈጥርልህ መጣሁ አለ። ያላለህ ነገር አልነበረም፤ ግን አንዱንም አልፈጸመውም፤ ለምን ይመስልሃል? መጀመሪያ ሰውዬውና የሰበሰባቸው ሰዎች ምን አይነት ናቸው? እነዚህ ሰዎችስ ያሉትን የሚያስፈጽም ባህሪ አላቸው ወይ? በፍጹም የላቸውም! እንደውም ሰጪ ሳይሆኑ ንፉጎች፣ አዳኝ ሳይሆኑ ገዳዮች፣ አልሚ ሳይሆኑ አጥፊዎች፣ ቀጥተኛ ሳይሆኑ ጠማሞች ነበሩ። እንግዲህ እነዚህ ሰዎች እንዴት አድርገው ነው ዲሞክራሲ የሚያቀናጁህ? በማሰብህ እንኳን የሚስቁና የሚቀልዱ መሆናቸውን እመን። እንግዲህ ወይ መስለሃቸው እነሱን ሆነህ መኖር አንዱ አማራጭህ ነው፤ አለዛ ያስሩሃል ወይ ይገድሉሃል፤ አለዛም ዕድሉን ካገኘህ አገር ጥለህ ትሰደዳለህ።

አለቦታው መቀመጥና ያልሆንከውን ነኝ ብሎ ማሰብ ያሰበውንም በኃይል ወይም በዘዴ መያዝ በትልቁ ከተመለከትክ ይሄን ነው የሚያስከትል። በትንንሹም ስታይ ቦታውና ሁኔታው ይለያያል እንጂ ባህሪው ያው ነው። ስለዚህ ቅድም እንደነገርኩህ ሕዝብ ሁሉንም ያያል፣ ይሰማል፤ የት እንደሚያስቀምጥህ፣ ምን ብሎ እንደሚጠራህም ያውቃል። ያን መጠበቅ እያቃተን አስቀድመን እራሳችንን እንሰይምና ጥፋት እንፈጥራለን።

ኢዛ፣ አሁን ሕዝብ ምን ብሎ የሚጠራህ ይመስልሃል?

ወለላዬ፣ ገጣሚው ወይም ግጥም የሚጽፈው ብሎ የሚጠራኝ ይመስለኛል። ይሄን እንዲለኝም መንገድ ከፍቻለሁ። ይሄን ሳነሳ የጋሽ ጸጋዬ አባባል ትዝ አለችኝ፤ ጋሽ ጸጋዬ ገና በልጅነቱ በደራሲያን መዝገብ ላይ በመስፈሩ ይህን በዛ ዕድሜ ማግኘት ከሚገባው በላይ የተጫነበት ስም መሆኑን ሲገልጽ፤ አንድ የአርመን ሴት እናትን ጠቅሶ ነበር። አርመናይቱ ልጇን “ያንን ትልቅ ጎዳና ተሻግረህ ና፣ ሰዉ ያለህንም ስም ንገረኝ” አለችው ብሎ ጽፎልናል። ሰው መንገደኛን እንኳን ስም እንደሚሰጥ ለመግለጽ ነው። እንኳን አመላክተኸው ይቅርና፤ ይመስላልም ብሎ ስም ሊያወጣልህ ይችላል። እኔንም ግጥም የሚጽፈው እንኳን ቢለኝ ግጥሜን እንደ ግጥም አይቶታል ወይም ተቀብሎታል ማለት ነው። አለበለዚያ ያ ግጥም እጽፋለሁ የሚለው ብሎ ሊያሽሟጥጥም ይችላል። ማህል ላይ አስመሳይ ካቢዎችና አይ የኛ ገጣሚ የሚሉ ምቀኝነት የተጸናወታቸውም አይጠፉም። እነሱን ተመርኩዞ ሽው እልም ማለት ወይም ተስፋ ቆርጦ መቀመጥ አደጋ አለው፤ ይህ እንዳይሆን እራስን አውቆና መዝኖ መጓዝ ሙያህ እንዳይነጠልህ ያደርጋል።

ኢዛ፣ ብዙውን ጊዜ ለቃለ ምልልስ ክፍት አይደለህም ለምንድነው?

ወለላዬ፣ ይሄውልህ የመጀመሪያ ጥያቄህ ከምን ተነስተህ ይቺን ግጥም ጻፍካት የምትል ትሆናለች፤ መልሱ ከገጠምኩት ግጥም በላይ ነው የሚገዝፈው። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አካትቼ ሕልምና አስተሳሰቤን ለጥጬ ግጥሟ ከኔ የወጣች ሳትሆን መለኮት ሹክ ብሎኝ እንደጻፍኳት ያህል እሰቅላታለሁ። እዝቺ ጋ እንግዲህ ለውሸት መንገድ ከፈትክልኝ ማለት ነው።

ጥያቄህ ይቀጥላል ብዙ ጊዜ ግጥሞችህ ነጻነትና ዲሞክራሲን የሚያንጸባርቁ የሚናፍቁና የሚጠይቁ ናቸው። ሌሎችም ይሄን ይናገራሉ አንተስ ስለግጥሞችህ ምን ትላለህ?

ይቺ ቁልፍ ራስ መግለጫና እራስን ለመስቀል የተመቻቸች የብረት መሰላል ናት። እንዲህ እላለሁ፤ ነጻነት ይናፍቀኛል! ዲሞክራሲ ይርበኛል! ርሃብና ጥማቴን በግጥሞቼ የምወጣ ስለሚመስለኝ ብዙ ጊዜ ኡ ኡ እላለሁ፣ እጣራለሁ፣ እዘምራለሁ፣ ልቤ ከነጻነት ጋር አብሮ ይበራል። ከኩልነት ጋር ይንሳፈፋል ... እቀጥላለሁ አንተም ጥያቄህ አያቋርጥም ለመሆኑ ግጥሞችህን ምን ጊዜና የት ቦታ ነው የምትጽፈው ትላለህ?

መሸትሸት ሲል ደመናን ረግጨ፣ የሰማይን ግድግዳ ተደግፌ በጨረቃ ብርሃን እየተመራሁ ከጻድቃን ሰማትን ብዕር ተቀብዬ መጻፍ ደስ ይለኛል ልልህ እችላለሁ። ይቺን አንተ ደግሞ ነፍስ አድርገህ ትጽፋታለህ። ርዕሷን እራሱ “ደመና ረግጦ ሰማይ ተደግፎ ከሚጽፈው ገጣሚ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ ...” ብለህ ታሳምራታለህ፤ መጧጧዝ እንዴት እንደምንጀምር ልብ በልልኝ። ከጡዘቱ ጋር ጦዘህ ያልሆነውንከውን እንደሆንክ አድርህ በስካር ፈረስ እየጋለብክ በትንሽ ያገኘሃትን ዝና በብዙ እየመነዘርክ መኖር ከጀመርክ ምንም ነገር ለማድረግ እንደማትመለስ እወቅ።

”ፀረ-ኮሎኒያሊስት” የምትል ትያትር አይተሃል? በደርግ የሥልጣን ዘመን ብሔራዊ ትያትር ቤት የወጣች በመንግሥቱ ለማ የተደረሰች ትያትር ነበረች። ጭብጧን ላቀብልህ። ጣሊያን ኢትዮጵያን ይዟል። የጠላት ዘመን የምንለው ነው። ጉልበት ጉልበት ያለውን መርጦ መንገድም ቤትም ያሠራል። የቤት ውስጥ ሠራተኛም የሆኑ አሉ አንድ ቤት የሚኖሩ አራት ጓደኛሞች ይታያሉ። ከነዚህ መሃል አንዱ ለጣሊያን አሽከር መሆን ሰለቸኝ። ካልሲ ማጠብ አስመረረኝ፣ ሽታዋን ሁሉ ይጠቅሳል ... የግንባታውንም ሥራ እንዳልሠራ ጉልበት የለኝም አንድ ዘዴ ፈጥረን ከዚህ ሥራ መገላገል አለብን የምትል ሃሳብ ያቀርባል። በጉዳዩ ላይ ከተወያዩ በኋላ አንድ መንገድ ቀየሱ፤ እሱ ጠንቋይ ሊሆን ሌሎቹ የሱ አጋፋሪ ሊሆኑ ተስማሙ።

ቤት ይዘው ጥንቆላው ተጀመረ። አጋፋሪዎቹ አስጠንቋዩ የሚፈልገውን ቀድመው ጠይቀው ይነግሩታል። ዋናው ጠንቋይ ችግርህ ታይቶኛል እያለ የሰማትን እየተናገረ ይፈርዳል። ጥንቆላው ሰመረ ሀብት መጣ። ጣሊያን እራሱ እየመጣ ያስጠነቁል ጀመር። እዚች ጋ ጠንቋዩ በምክር የተሰየመበት ጥንቆላ ሳይሆን ራሱን ጠንቋይ እንደሆነ ገመተ። ከጓደኞቹም ጋር መገናኘቱን ቀስ በቀስ አቋረጠ። ብዙ የጣሊያን ሹማምንት ጓደኖች አፈራ። ስለ ሚስቶቻቸው የሚያስጠነቁሉ፣ በግ የሚያርዱ፣ ወርቅ የሚሰጡ ... በዚህ መሃል ጓደኞቹ የሚበሉት እስከማጣት ደረሱ። እንደምንም ሰው ጭር ሲል አገኙትና ምነው? አብረን ተማክረን አንተን ጠንቋይ ባደረግን እኛን ትከዳናለህ? ለዚህ ባደረስን እንዴት ትጥለናለህ? ብለው ወቀሳ አቀረቡ።

ጠንቋዩ ቱግ አለ፤ ከመለኮት የተሰጠኝን ሥልጣን ግፈፉኛ! ብላችህ ብላችሁ አታውቅም በሉኛ! ንዴቱን ማን ይቻለው፤ እንደውም አርፈው ካልተቀመጡ እንደሚያስለቃቅማቸው ዛተ። ይሄውልህ እንግዲህ ያልሆንከውን ሆነህ ስትነሳ፤ በማይገባህ ደረጃ ላይ ስትወጣ የምትሆነው ይሄንን ነው። ታላቁ መጽሐፍ “ትእቢት ከመጣች ውርደት ትከተላለች” እንዳለው በመጨረሻ ውርደትን መከናነብ አይቀሬ ነው።

ይሄን ስልህ ግን ሁሉም እንዲህ ነው ወይም ይሆናል ማለቴ አይደለም። ስንት የወገን ፍቅር የሕዝብ አክብሮት ያላቸው የኢትዮጵያዊነት ኩራታቸውን ጠብቀው የኖሩ አሁንም ያሉ ሞልተዋል። አገራችን ስንት ምርጥ ሰዎችን ያፈራች አገር እንደሆነች ወደፊትም እንደምታፈራ መካድ አይቻልም።

ስለ ወንድምነት ስለሰው ልጅ ፍቅር ራሳቸውን አሳልፈው እስከመስጠት የደረሱ ሰዎች እንዳሉ የሰማሁትን ላጫውትህ፤ በንጉሡ ዘመነ መንግሥት ሥርዓቱን የሚወቅስና የሚተች ጽሁፍ ከተማ ውስጥ ተሰራጭቶ ይገኛል። ጽሁፏ መንግሥት እጅ እንደገባች ይቺን ማንም ሊጽፍ አይችልም ያ ጸጋዬ ነው ተብሎ፤ ጸጋዬ ገ/መድህን ተፈልጎ ይታሰራል። ጸጋዬ ጣቢያ ውስጥ ኩርምት ብሎ እንደተቀመጠ አንድ ሰው ሰተት ብሎ ወደ ግቢው ገባ። ይህ ሰው ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) ነበር። የጸጋዬን መታሰር ሲሰማ ስንቅ ለማቀበል አልነበረም የመጣው፤ ራሱን ሰንቆለት ነበር ገስግሶ የደረሰው። ጽሁፉን የጻፈው እሱ ነበር። ጸጋዬ ከደሙ ንጹህ ነው። ይህንን ተናግሮ ጸጋዬን በማስፈታት እሱ የእስር ቤቷን ወለል ያዘ። ይኽን ቀናነት ባስታወስኩት ቁጥር እውስጤ ድረስ ዘልቆ የሚገባ ትልቅ የፍቅርና የእውነተኛነት እንዲያድርብኝ ያደርገኛል። በሰው ልጅ ላይ ያለኝንም እምነት እና ፍቅር እንዳጠናክርም አግዞኛል።

ሌላ አንድ ልጨምርልህ። ይሄ ደግሞ ለእውነት መቆምንና ሐቀኛነትን የሚያጠናክር ነው። የአሁኖቹ ገዢዎች መንግሥታቸውን በማጠናከር ላይ እንዳሉ ብሔራዊ መዝሙር እንዲሠራ ፈለጉ። ለዚህም የግጥም ጸሐፊዎች ግጥማቸውን ይዘው እንዲቀርቡ ጥሪ ተደረገ። አንድ ወዳጄ በጥሪው መሰረት እንዴት ያለች ግጥም ይዞ ቀረበ። ግጥሟ ሞገስ አግኝታ በአንደኝነት ተመረጠች። አንደኛ ሆና የምትጸድቀው ግን እነሱ ያልፈለጓትን አንድ ቃል መዞ አውጥቶ ሌላ ከተካበት ብቻ መሆኑ ተነገረው። ደራሲው እንዲህ አለ “ይቺን ቃል በሌላ ለውጨ ግጥሙ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር እንዲሆን አልፈልግም። ያላመንኩበትን አድርጌ መጸጸት አልሻም ... ተዉት” አላቸው። ተዉት!

የዚህ ግጥም አንደኛ መሆን በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ተመዝግቦ የመቀመጥን ክብር ያስገኛል ተብሎ የሚገመት ነው። ሽልማትና ሹመትም ሊያመጣ መንገድም መክፈቱ አይቀርም። ለማንም ያጓጓል፤ እሱ ግን አልፈለገም። ከዚህ ሁሉ ክብርና ዝና ያመነበትን መረጠ፤ ይህ ጥቂቶች ብቻ የሚፈጽሙት ራስን የማሸነፍ ጀግንነት ነው። በአሉን ውሰድ ያያትን እውነት ለሕዝብ ዘርግፎ አወጣ። ሞት ባይሆን እስራት እንደሚጠብቀው አላጣውም! ግን አደረገው። የያዘው የሥልጣንና መደላደል ይሄን እውነት አፍኖ የሚያስቀር ኃይል ነበረው። አልፈለገም። ይሄን ሁሉ አገላብጠህ ማየት ስትጀምር ከመንጠራራት እንድትድን ያደርግሃል።

ኢዛ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግጥም ያውቃል ብለሃል፤ ደራሲያኑ ደግሞ የግጥም መጽሐፍ እንደማይሸጥ ሲያማርሩ ይታያል፤ ይሄ ለምን ይመስልሃል?

ወለላዬ፣ ቅድም እንደነገርኩህ ነው፤ የራሱን ግጥም ሰብስበህ፣ አሻሽለህ የምታቀርብለት ስለሚመስለው ሊገዛህ ይዘገያል። አይቶ ቀምሶ ሲያጣጥመው መግዛቱ አይቀርም። ሌላው ግጥም ሲነበብለት እንጂ ማንበብ የማይወድ ሞልቷል። ስለዚህ ማንን አንብብ ብዬ ልጠራ ነው የምገዛው በማለት ለመግዛት እጁን ይይዘዋል። አንዳንዱም በግጥም የሚተላለፍ መልዕክት ውስን ይዞታ ያለው ስለሚመስለው ይሸሸዋል። በግጥም ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ቢሆን የማንበብ ልምድም ችግር እንዳለ አትዘንጋ። ያም ሆኖ ደራሲያን ከመጽሐፌ ትርፍ አላገኘሁም ብለው ቅር ሊላቸው አይገባም፤ መልዕክታቸውንና ሊያስተላልፉት ያሰቡትን ሃሳብ አውጥተው ሕዝብ እጅ እንዲገባ ማመቻቸታቸው እራሱ በቂ ነው።

ኢዛ፣ ሰውን ስታማርር አትሰማም ተግባብተህ የመኖር ሚስጥርህ ምንድነው ?

ወለላዬ፣ ይህ ከቤተሰብ አኗኗሬ የመጣ ይመስለኛል። ያደኩበት ቤተሰብ ግቢ ውስጥ ከአያት እስከ የልጅ ልጅ የሚኖርበት ነው። ያለው የሰው አይነት፣ የዕድሜ መበላለጥ፣ የጾታ መቀያየጥ ይታይህ የዕውቀት ትልቅነትና ትንሽነት አለች። ተመሳስለህ ከነሱ ጋር መኖር ብዙ ነገር ውስጥህ እንድታስቀር ይረዳሃል። አኩርፈሃቸው የማያኮርፉህ ስላሉ ይቅርታን ትለምዳለህ። በአንድነት መብላትና መጠጣት፣ መቀበልና መስጠት ትማራለህ። ለታናሽ ምን እንደሚወራ ለታላቅ ምን እንደሚነገር ታውቃለህ።

በርግጥ ሁሉም ጥሩ ላይሆኑ ይችላሉ፤ መካሪም ደስኳሪም አይጠፋም። ሙያቸውም ፍላጎታቸውም የተለያየ ነው ... ከነዚህ ሁሉ ጋር አብረህ ስትኖር የምታካብተው ልምድ ግን ብዙ ነው። ከዕለታት በአንዷ ቀን ከቤት ስትገባ አያቶችህን ታገኛለህ፣ ንጹህ ፍቅራቸው አብሮ አለ። ትመከራለህ ምክሩ ራሱ ምንግዜም ከውስጥህ የማይጠፋ ነው “ምነው! ብዙ ስታውቅ ይሄንን አደረክ ...” ነው የምትባል፤ ለካ ብዙ አውቃለሁ! ይቺን ነው የማላውቃት ነው ብለህ ታስባለህ። አትከፋም በጥፋትህ ቁጡና ነጭናጫ እንዳትሆን በንዲህ ያለ ውብ አቀራረብ ይረዱሃል። እኩዮችህ ጋር ስትገናኝ ትከራከራለህ ልምድ ትለዋወጣለህ፣ ትበሻሸቃለህ ... ይሄ የኩያ ጨዋታን ያስተምርሃል። አንተም በተራህ ታናኛሾችህን ልትመክርም ልትገስጽም ትችላለህ፤ ይሄ የአኗኗር ልምድ ተከትሎኝ የመጣ ይመስለኛል። ትህትናና ሰው ማክበርን በዚህ ሁኔታ ከቤተሰቤ ተምሬአለሁ።

በርግጥ ከቤተሰብ ወደ ሕብረተሰብ ስትሸጋገር የመግባቢያ ይዞታው የተለያየ ነው። ቢሆንም አብሮ የመኖር እርሾ ካለህ ይጠቅምሃል። በዚህ ባለንበት የውጪው ዓለም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሊገጥምህ ይችላል። በተለይ ከሁሉም ጋር ተግባብቼ እኖራለሁ ላለ ግራ ቢገባው አያስገርምምም። ያንዱ ያልሆነ የሁሉም አይሆንም የምትባለዋ አባባል እግር አውጥታ ስትሄድ በዓይንህ ታያታለህ። ያንዱ ካልሆንክ የሌላ ነህ ስለምትባል ባሉት ቡድኖች ሁሉ የሌላ ሆነህ ትገመታለህ። ይህ ሁኔታ ከገባህ በራስ መተማመን ልታቀለው ትችላለህ። እነሱም የሚረዱህ ጊዜ እሩቅ ስለማይሆን አክብሮትና ፍቅራቸውን አይነፍጉህም። ሌላው እንኳን ባትሆን ለአስታራቂነት ትታጫለህ። እንደ ግራዋ ባትመርም የሰው ጸባይ ለማጽዳት ብቸኛው አማራጭ ሆነህ ትገኛለህ። ይሄን መሰሉ ነገር ውስጤ ስላለ ከሰው ጋር ለመኖር ያለውን የማያቋርጥ የጉዞ መንገድን ያቀለለልኝ ይመስለኛል።

አንድ ደግሞ ሌላ ሚስጢር አለችኝ፤ ሁሉንም ትንሽ ትልቅ ሳትል የሚገባቸውን አክብሮት አለመንፈግ። ይህ በጣም ጠቃሚ ነው፣ ለማስመሰል ሳይሆን ከልብህ ልታደርገው ይገባል። መታጠቢያ ቤት ወረፋ ላይ እባክህ ወንድሜ አንተ ቅደም ብትል ትጠቀማለህ እንጂ አትጎዳም፤ ያ ሰው ሌላ ቀን የምግብ ሰልፍ ላይ እባክህ ወንድሜ ቅደም ሊልህ ይችላል። አክብሮትህን ውስጡ ይዞ ስለሚኖር ላንተ ልቡ ክፍት ነው። በር የከፈትክለት ወይንም ከፍተህ የጠበከው በምንም አይነት ላንተም አይዘጋብህም። ከሰው ጋር ለመኖር እነዚህን የመሳሰሉ ትናንሽ ነገሮች ሰውዬው ግን ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ለማድረግ ተፈጥሮዬ አግዞኛል።

ኢዛ፣ ብዙ ጊዜ አትስቅም ፈገግታህ ቁጥብ ነው ለምን ይሆን? እንደዛ መሆንህንስ ታውቀለህ?

ወለላዬ፣ በደንብ አውቃለሁ፣ ለነገሩ የሚያስቁና ሳቅ የሚጭሩ ነገሮች ደስ ይሉኛል። የማልስቀው ግን ሳቅ ያመጣው ነገር ወይም የተነገረው ቀልድ ጀርባ ሄጄ የመመሰጥ አመል አለኝ። እሱን ስመራመር ሰው ሁሉ የሳቀበት ቀልድ ያመልጠኛል። ከዚህ ጋር የተገናኘ አንድ ሁኔታ ገጥሞኛል። ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ አሜሪካን አገር ከገባች በኋላ ወደ ስዊድን ለኢትዮጵያን አዲስ ዓመት በእንግድነት ትጋበዛለች። በዛ ዝግጅት ላይ ንግግር ስታደርግ በደል ሲፈጸም ማየት ከልጅነቷ ጀምራ እንደሚሰማት ገልጻ፤ ሴቶች ለዓመት በዓል ከሚያወጡት የአበባዬሆሽ ግጥም መሃል ጥቂቱን አነሳች፤ እንዲህ ነበር ያለችው፤

... ኮከብ ቆጥሬ ስገባ ቤቴ
ትመታኛለች የእንጀራ እናቴ
ከጎኔም ጎኔን ኩላሊቴን
እሷን ጥሩልኝ መድኃኒቴን

ግጥሙ ውስጥ በደል ቁልጭ ብሎ ይታያል። ትንሿ ብርቱካን ያ ጥቃት ይሰማት ነበር ለምድነው ኩላሊቷን የምትመታው እያለች በልጅነት አዕምሮዋ ታስባለች፤ በዚህን ጊዜ በርግጠኝነት የሚያወርዱትን ግጥም የመቀበል ኃይል የላትም። እሷ የልጅቷን መረገጥ እያሰበች ስለሆነ ያልፋታል። የኔም ሳቅ የሚያልፈኝ ጀርባውን ስመለከት ይመስለኛል። አለበለዚያም አንድ ክፉ የቤተሰብ አባል ምን ትገለፍጣለህ ብሎ ጮሆብኝ ሳቄን አድርቆት ሊሆን ይችላል። ለነገሩ ውጪ ወጥተህ ሁለት ዓመት ከቆየህ በኋላ ሳቅህ ይደርቃል፤ ይሄ ለምን እንደሆነ ባላውቅም በብዙዎች አይቼዋለሁ። ለማስመሰል ይሳቅ ይሆናል። እኔ ግን ለማስመሰል ከምስቅ ድርግም ብሎ ቢጠፋብኝ እመርጣለሁ።

ኢዛ፣ የመጀመሪያ ግጥምህን ታስታውሰዋለህ?

ወለላዬ፣ በድንብ የተጻፈ የመጀመሪያ ግጥሜን አላስታውስም። በእንካ ሰላምትያ የጀመርኳት ግጥም ግን ትዝ ትለኛለች። እንካ ሰላምትያን እኔና ጓደኞቼ ትንሽ ከፍ አድርገናት ነበር። ይኼን እየነገርኩህ ግዛቸው ፊቴ ድቅን አለ። ግዛቸው ትናንሽ ዓይኖች ያሉት ልጅ ነው፤ ማየታቸው ራሱ ያጠራጥርሃል። የዶሮ ዓይን ነው የሚያካክሉት። ግዛቸው ዓይን ቢነሳውም አፍ ሰቶታል። አንዴ የለጠፈብህ ነገር እላይህ ላይ ተጣብቆ ሲከተልህ ነው የሚኖር። ግዛቸውና እኔ እንከባበር ነበር፤ በኋላ ግን እንዲህ አለህ፣ እንዲህ አለህ አሉትና እላዬ ላይ ሰፈረብኝ። ግዛቸውን ብሸሸውም አልተወኝም። በመጨረሻ ግን አንድ ግጥም ይዤ መጣሁ፤

“ገደል ሜዳ መስሎት ወድቆ ተሰበረ

ዓይናማው ግዛቸው እንደወጣ ቀረ” የምትል ይቺ የመጀመሪያ ግጥሜ ትመስለኛለች። የሚገርመው ነገር ይሄ ካለፈ ከብዙ ጊዜ ብኋላ ግዛቸው ወታደር ሆኖ ተቀጥሮ ጦር ሜዳ እንደሄደ ሳይመለስ ቀረ። መርዶው ሲመጣ ግጥሟን እያሰብኩ ለቅሶ ደረስኩ።

ኢዛ፣ ወለላዬ በመጨረሻ የምታክለው ነገር አለ?

ወለላዬ፣ የለኝም

ኢዛ፣ በምን ብንቋጨው ደስ ይልሃል?

ወለላዬ፣ በደህና እደር

ኢዛ፣ ደህና እደር!

ወለላዬ፣ ደህና እደር!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ