የአሜሪካ ምርጫ በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ዕይታ
![]() |
አቶ ቡልቻ |
አቶ ቡልቻ ማንም ይመረጥ ማን ለሳቸው ግድ የሚሰጣቸው አይመስሉም እንደውም ”… ምን አገባኝ …” ብለው ነገሩን ትተውታል።
በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ጥቅምት 25፣ በፈረንጆቹ ደግሞ ኅዳር 4 ቀን ነገ ማክሰኞ የሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ፣ የመላውን ዓለም ቀልብ የሳበ ሲሆን፤ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ምርጫም የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ እጩ ባራክ ኦባማ ናቸው።
ባራክ ኦባማ ቢመረጡ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታራምደው ፖሊሲ ይቀየራል በሚል እምነት ድጋፋቸውን የሚሰጡ በርካቶች የመኖራቸውን ያህል፣ ጥቁር በመሆናቸው ብቻ በሚሰማቸው ጥሩ ስሜት ድጋፋቸውን የሚገልጹ አልታጡም።
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ አልሠፈነም፣ ነፃ የመንግሥትና የግል ሚዲያ፣ ነፃ የፍትህ ሥርዓት፣ ነፃ ምርጫ ቦርድ፣ … የለም በሚል ይከራከራሉ።
የአሜሪካው የኮንግረስ አባልና የኢትዮጵያን መንግሥት አጥብቆ የሚቃወመው የኤች.አር. 2003 አርቃቂው ዶናልድ ሌቪን ደግሞ፣ ባራክ ኦባማ ከተመረጡ ከምርጫ 97 በኋላ በኢትዮጵያ የተከሰተው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያከትማል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚያስገድድ ፖሊሲ አሜሪካ ይኖራታል ብለው ያስባሉ።
![]() |
ፕ/ር መረራ ጉዲና |
የአሜሪካን ህዝብ የሀገሩን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚቃወም መሆኑንና፣ የተቀረው ዓለምም ከመቼውም ጊዜ በላይ የአሜሪካኖችን ጣልቃ ገብነት በመኮነን ላይ እንደሚገኝ አውስተዋል።
ከቀናት በፊት በአሜሪካ እንደነበሩ ያወሱት ዶ/ር መረራ የአሜሪካ መኪኖች፣ ጣራና ግርግዳዎች፣ መሬቱና አየሩ ሁሉ በባራክ ኦባማ ምስል ተጥለቅልቀው ማየታቸውን ገልፀው፣ የምርጫው አሸናፊ ማን ይሆናል የሚለውን ለመለየት ሁለት ካርዶች እንዳሉ ጠቁመዋል።
አንደኛው፡- የአሜሪካ ህዝብ በቀጣይ ዓመት የሚኖረው ኢኮኖሚ አሁን ካለበት የተሻለ ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ ከፈለገ ባራክ ኦባማን ለመምረጥ የሚያወጣው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በቀላሉ የማይበገሩት የአሜሪካ ኮንሰርቫቲቮች ባሉበት የተከናወነን ምርጫ ማሸነፍ ባለመቻሉ ምክንያት የሚሆነው የዘር ካርድ ነው። በዚህ የዘር ካርድ ማክኬይን በርካታ ሥራ ሊሠሩ ቢችሉም ኦባማ ግን በእስካሁኑ አካሄድ የተሻለ ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ዶ/ር መረራ ይገልፃሉ።
![]() |
አቶ ልደቱ አያሌው |
አያይዘውም ”… ለኢትዮጵያ ጥቅም ማን ምን ሊሠራ ይችላል የሚለው መታየት ካለበት፣ ኢትዮጵያ ብዙ የውጭ ዕርዳታ ያገኘችው በሪፐብሊካኖች ዘመን ሲሆን፣ በተቃራኒው ዲሞክራቶች ግን ለፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ድጋፍ ሲሰጡ እንደነበር፣ የሶማሊያን ወረራ ወደ ኋላ ሄዶ ማስታወስ ይገባል” ይላሉ።
እንደ አቶ ልደቱ አባባል ባራክ ኦባማ በዘር ላይ የተመሠረተ ዘመቻ ባለማድረጋቸው ነጭ ደጋፊዎችን ማግኘታቸው ራሱን የቻለ ድል ሲሆን፣ ሪፐብሊካን ፓርቲ ላለፉት ስምንት ዓመታት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ባሳየው ክፍተት፣ በአሜሪካውያን ዘንድ ጥሩ አመለካከት እንዳይኖረው በማድረጉ፣ ምናልባት የኦባማ ፓርቲ ሊመረጥ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።
የኦባማ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ በምርጫው አሸናፊ እንደሚያደርጋቸው፣ የህዝብ አስተያየት በመሰብሰብ ደረጃ የሚያወጡ የተለያዩ ተቋማትና ሚዲያዎች እየገለፁ ነው። ኦባማ ከ95 በመቶ በላይ የጥቁሮችን ድጋፍ ማግኘት የቻሉና አክራሪ የነጭ ዘረኞችን ሳይቀር ወደ ራሳቸው እየሳቡ ነው።
የሪፐብሊካን ደጋፊዎች ባሉበት በርካታ ቢሮዎችን በመክፈት እና ቅስቀሳ በማድረግ ውጤታማ ሲሆኑ፣ ለዚህ አብነት የሚሆነውም የሪፐብሊካን አባልና የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑት ኮሊን ፖል ለኦባማ ድጋፋቸውን መግለጻቸው ነው።
በመጪው ማክሰኞ በሚደረገው ምርጫ ኦባማ ቢያሸንፉ፣ አማካሪዎቻቸው እንደ ዶናልድቼይን በአፍሪካ ላይ ያላቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እውቀት ከፍተኛ በመሆኑ፣ HR 2003 እንዲፀድቅ የሚያደርጉት ዲሞክራቶች፣ ኦባማ ቢመረጡ አሜሪካ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ ላይ የምትከተለውን ፓሊሲ ለመቀየር እንደሚቻል ደጋግመው ይናገራሉ።
![]() |
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ |
በአሜሪካ የምርጫ ታሪክ ጥቁር ለፕሬዝዳንትነት ተመርጦ እንደማያውቅ የተናገሩት ዶ/ር ነጋሦ፣ ኦባማ ከጥቁርነታቸው ይልቅ ይዘውት የተነሱት አጀንዳ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳስገኘላቸውና እስካሁን የወጡት የመራጮች መለኪያ (ፑል) እንደሚያመለክቱት ኦባማ እየመሩ መሆኑንና፣ ከሀገራቸውም አልፈው እንደ ጀርመን ባሉ ሀገራት፣ ኦባማ ታላቅ ሰው መሆናቸውን ምስክርነት እንዳገኙ መረጃዎችን ዋቢ አድርገው አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
![]() |
ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ |
ኦባማ ለአሜሪካ ህዝብ እሠራለሁ ብለው ቃል የገቧቸው የሥራ አጥነት መቀነስ፣ የጤና ሁኔታን ማሻሻልና የትምህርት ፖሊሲያቸው ከፍተኛ ግምት እንዳሰጣቸው ፕሮፌሠር በየነ ይናገራሉ።
የኦባማ መመረጥ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ስላለው ፋይዳ አስተያየት የሰጡን ፕሮፌሠር በየነ፣ ሪፐብሊካኖች በእስካሁኑ አመራራቸው ለኢትዮጵያ ዕርዳታ አደረግን የሚሉት ከሌሎች ትናንሽ የአውሮፓ ሀገራት ጋር ሲነጻጻር ዝቅተኛ መሆኑንና ዋነኛ ትኩረታቸው የፀረ-ሽብርተኝነት ጉዳይ መሆኑ ሀገሪቱ ከነርሱ ልታገኝ የሚገባው ጥቅም አላገኘችም።
እንደ ፕሮፌሠሩ ማብራሪያም ዴሞክራቶች በውጭ ጉዳይ ፓሊሲያቸው፣ ከሪፐብሊካኖች ብዙም ባይለዩም ዲሞክራቶች በኦባማ አማካይነት በኢትዮጵያም ይሁን በአፍሪካ የሚከተሉት ፖሊሲ ከሪፐብሊካኖች የተሻለ እንደሚሆን ይታመናል ብለዋል።
ፕሮፌሠር በየነ ከባራክ ኦባማና ከማኬይን የማንኛው ደጋፊ ነዎት? ብለን ለጠየቅናቸውም ”እኔ ማንንም በስሜት ተነሳስቼ አልደግፍም፤ ነገር ግን ኦባማ እሠራዋለሁ ብለው ከተነሱባቸው ጉዳዮች አንፃር፣ የተሻለ መሪ እንደሚሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።