”ሀገሬን ትቼ አልቀርም” ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ
“ኢትዮጵያን ሪቪው የተባለው ድረ-ገጽ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አውሮፓ እንደሚቀሩ መዘገቡን ተከትሎ ሀገር ቤት ያሉ ጋዜጦችም ይህንኑ ማውጣታቸውን ሰማሁና ወዳሉበት ጀርመን ሀገር ስልክ ደውዬ አገኘኋቸው፤ ለጥያቄዎቼም ምላሽ ሰጥተውናል” የሚለን ያሬድ ክንፈ ከስዊድን ነው።
ኢትዮጵያን ሪቪው የተሰኘው ድረ ገጽ፤ በአውሮፓ እንደምትቀሩ እና ጥገኝነት እንደምትጠይቁ ዘግቧል። የትኛው ሀገር ነው ለመቅረት ያሰቡት?
የተባለው ድረ ገጽ ላይ የተዘገበውን አንብቤዋለሁ። እናም አንድ ታሪክ ነው ያስታወሰኝ። በደርግ ጊዜ ዶ/ር ጌታቸው ቦሎዲያ ለትምህርት ወደ ውጭ ሀገር በሚኼድበት ጊዜ፤ በውጭ ኼዶ ላለመቅረት የ500 ብር ዋስትና እንዲያሲዝ በኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ተጠየቀ። ”እንዴ ለምንድን ነው ዋስትና የማስይዘው፤ ሀገሬን ለአስር አለቆቹ ትቼ ነው ወይ የምሄደው?” ብሎ እንደተቆጣ ሰምቼ የነበረውን ነው ያስታወሰኝ። ... ዘገባው የሚያስቅ ነገር ነው ማለት ይቻላል።
ዘገባው ሙሉ ለሙሉ ሐሰት ነው? ...
አዎ! ሐሰት ነው። ሀገሬን ትቼ አልቀርም። ድረ ገጹን የሚስተዳደረው ሰው ምናልባት ፍላጎቱን ጽፎ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም አንድነት በሀገር ውስጥ የሚያደርገውን ትግልም ሆነ፤ በአጠቃላይ ሠላማዊ ትግሉን የሚቃወም አቋም ስለያዘና ፈጽሞ በሀገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን የፖለቲካ እንቅስቃሴ መቆም አለበት ብሎ የሚያምን በመሆኑ፤ ያንን ፍላጎቱን በዜና መልኩ ገልጾት ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ።
በአውሮፓ ጉዟችሁ በዕቅድ ከያዛችኋቸው ሠባት ሀገሮች ውስጥ ስንቱን ጎበኛችሁ?
እስካሁን አምስት ሀገሮች ደርሰናል። በእንግሊዝ ሀገር ጀምረን፣ ቤልጅየም፣ ስዊድን - ስቶክሆልም፣ ሆላንድ - ዘሔግ ከተማ፣ አሁን ደግሞ ጀርመን ነው ያለነው።
ሆላንድ ምንም ዓይነት ስብሰባ አላካኼዳችሁም። እንዲያውም ሆላንድ እንዳልኼዳችሁ ነበር አንዳንድ ዘገባዎች የጠቆሙት፤ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?
ሆላንድ የነበረው የቀድሞው የቅንጅት የድጋፍ ድርጅት በተለያዩ ምክንያቶች አሁን የሚሠራ ድርጅት ኾኖ አልተገኘም። ዝግጅቱ ሲተባበር የነበረው ፈቃደኛ በሆኑ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ነበር። በተያዘው ዕቅድ መሠረት ጊዜው ሲደርስ ጉዳዩን የሚያስተባብሩት ወገኖች የግል ችግር ገጠማቸውና በዚያ ምክንያት ሕዝባዊ ስብሰባውን ማድረግ አልተቻለም። መጀመሪያውኑ ይሄ ታሳቢ ኾኖ፤ በዋናነት ሆላንድ ላይ አትኩረን ስንሠራ የነበረው፤ ከሀገሪቷ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በሚደረገው ውይይት ላይ ስለነበረ ከስዊድን ወደ ዘሔግ ነው የሄድነው። እዚያም በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳይ ኃላፊውንና የኢትዮጵያ ዴስክ ኃላፊዋን ለረዥም ሰዓታት አነጋግረናቸዋል። በዚህ ላይ ደግሞ አጥጋቢ ውይይት አድርገናል። እሱን እንዳጠናቀቅን ወደዚህ ወደ ጀርመን ተመልሰናል።
ቤልጅየም ብራስልስ ማንን አገኛችሁ?
ብራስልስ ላይ የአውሮፓ ኮሚሽን ሰዎችን አግኝተናል። እዚያም የምሥራቅ አፍሪካን ጉዳይ የሚከታተሉትን ኃላፊ፣ የአፍሪካ ዴስክ ኃላፊን፣ የፓርላማ አባላትን አግኝተን አነጋግረናል። እንዲሁም ከኢትዮጵያውያን ጋር ሕዝባዊ ውይይት አድርገናል።
አሁን ያላችሁት ጀርመን ነው። ጀርመን ከገባችሁ ጀምሮ ምን ሠራችሁ?
ጀርመን በርሊን የገባነው ማክሰኞ ነው። በዕለቱ በበርሊን የሚገኙ የፓርቲያችን ድጋፍ ሰጪ አባላቶቻችንንና ጠንካራ ደጋፊዎቻችንን ባደረጉት የእራት ግብዣና መጠነኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተን በጣም ሠፊ ውይይት አድርገናል። በአጠቃላይ የሀገሪቷ የፖለቲካ ሂደት ምን ይመስላል? ወዴት ይሄዳል? አሁን እየሄድንበት ያለው ሁኔታ ምን ዓይነት መልክ ይኖረዋል? ... አንድነት ደግሞ ምን ዓይነት አስተሳሰቦችና ምን ዓይነት የወደፊት ዕቅዶች አሉት? በሚለው ላይ በጣም ሠፊ ውይይት አድርገናል። እናም ብዙዎቹ በተለያየ ምክንያት የድጋፍ ሁኔታቸው ቀንሶ የነበረበት መልክ እንደነበረ ገልጸውልን፤ ከዚህ በኋላ ከድርጅቱ ጋር የጠነከረ የሥራ ግንኙነት እንደሚኖራቸው፣ ድጋፋቸውንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያረጋገጡበት ጊዜ ነበር። በጣም ጥሩ ጊዜ ነው ያሳለፍነው።
በጀርመን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የምሥራቅ አፍሪካ ኃላፊውን ለሁለት ሰዓት ተኩል አነጋግረናቸዋል። በአጠቃላይ ሀገሪቷ የምትገኝበትን ሁኔታ የማስረዳትና ሃሳቦችን የመለዋወጥ ሁኔታ ነበር። ገንቢ ውይይት ነበር ማለት ይቻላል። በተለይም ኃላፊው አሁን ያሉብንን የፖለቲካ ችግሮች በበቂ መረጃና በበቂ ግንዛቤ ጨብጠውት ነው ያገኘነው። ... የበርሊኑን ሥራችንን አጠናቅቀን አሁን ወደ ሙኒክ ከተማ እየ¤ድን ነው። እዚያም ያሉትን ደጋፊዎቻችንን እናገኛለን። በዚህ የጀርመን ደጋፊዎቻችን ከተለያየ ከተማ መጥተው የአዳራሽ ስብሰባው የሚደረገው በኑርንበርግ ከተማ የፊታችን ቅዳሜ ነው።
እስካሁን ድረስ ያለው የአውሮፓ ጉዟችሁ ምን ያህል የተሳካ ነበር? ምንስ የጎደለው ነገር ነበረ?
በሁለት መልኩ በጣም ስኬታማ ጉዞ ነው ማለት ይቻላል። ከምርጫ 97ና ከቅንጅት ጋር ተያይዞ፤ ከዚያም በመቀጠል ከእኛ እስርም ጋር በተያያዘ በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንደነበር ይታወቃል። ያም እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነት ሠፍኖ የዲሞክራሲ ሥርዓት ተመሥርቶ ለማየት ከመጓጓትና ያንን ሂደት ከማገዝ ፍላጎት የመነጨ ነበር። ከተፈታን በኋላ በቀድሞው የቅንጅት አመራር ውስጥ ተፈጥሮ በነበረው ችግር መነሻነት የድጋፍ መቀዝቀዝ ታይቶ ነበር። ይህንን ሁኔታም ደጋፊዎቻችን በብዙ መልኩ በዚህ የሥራ ጉብኝት ገልፀውልናል። እኛም በበቂ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተናል።
በዋናነት ችግሩ መፈጠሩ የሚያሳዛን ቢሆንም፤ በተፈጠረው ችግር የዛሬው አንድነት በርካታ ትምህርቶችን ወስዶ የወጣ ፓርቲ መሆኑን፣ ይህ ችግር መልሶ እንዳይፈጠር ተቋማዊ ማረጋገጫና ተቋማዊ ቼክ ኤንድ ባላንስ እንዲኖር አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ የወሰነ ድርጅት መሆኑን፤ ከዚህ በኋላም በግለሰቦች ላይ ሳይሆን በአሠራር፣ በሕግ፣ በደንብ፣ በተቋማዊ አተገባበር ላይ ያተኮረ ፓርቲ ይዘን መምጣታችን ባለፈው ያጋጠመው ዓይነት ችግር የመፈጠሩ ሁኔታ በጣም አነስተኛ መሆኑን ለማስረዳት ችለናል። ከዚህም ሌላ ሀገሪቷ ያለችበት ሁኔታ ለተቃውሞ ፖለቲካ ያለው ሥፍራ እጅግ ጠባብ ቢሆንም፤ ያንን ለማስፋት አንድነት አባላትን በስፋት የማደራጀት፣ የማሰባሰብ፣ የሚኖረውን ተፅዕኖ በየጊዜው የመጨመር፣ የጠበበውንም ሥፍራ በሂደት የማስፋት ተግባሩን በቁርጠኝነት የጀመረ መሆኑን ስናስረዳቸው፤ እንደገና መልሶ ድጋፉን ለመቀጠል ያለ ተነሳሽነት እንዳለ ነው የተመለከትነው። እና ጥሩ ውይይት ነው ያደረግነው ማለት ትችላለህ በየቦታው። ለንደን ብንወስድ፣ ስቶክሆልም ብንወስድ፣ ... ብዙ ጥያቄዎች ቀርበዋል፣ ብዙ ክርክሮች ተደርገዋል። የስብሰባዎቹ የመጨረሻ ውጤት ግን በስምምነት መንፈስና በተለይም በደጋፊዎቻችን በኩል በአብዛኛው በእርካታ፣ ተስፋ በሚሰጥ ሁኔታና ድጋፉን በማጠናከር መልኩ የተገለጸ ነበር ማለት ይቻላል። ከዚህ አንፃር በጣም ስኬታማ ነበር።
ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ባደረግናቸው ውይይቶች፤ ፓርቲያችንን ለማስተዋወቅ ችለናል። ሀገሪቷ ዛሬ የምትገኝበትን የፖለቲካ ሁኔታ የተወሰነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርገናል። አብዛኞቹ በእርግጥ ቀድመው የሚያውቁበት ሁኔታ እንደነበራቸው ነው የተረዳነው። በተለይም የሲቪል ማኅበረሰቡ ረቂቅ ሕግ በአብዛኛው ሃሳባቸውን ይዞ ስላገኘነው፤ በዚያ ላይም ገንቢ ውይይት አድርገናል። ከዚያም አንፃር እንደፓርቲም እንደሀገርም ያለንበትን የፖለቲካ ሁኔታ ከማስረዳት አንፃር በጣም ጥሩ ውጤት ያገኘንበት ሁኔታ ነበር ማለት ይቻላል።
በሆላንድ የድጋፍ ሰጪ ማኅበር የላችሁምና ስለእሱ ምን አስባችኋል?
ለነገሩ በሆላንድ ብቻ አይደለም፤ በአውሮፓ ብዙ ኢትዮጵያውያን በሚገኙባቸው ከተሞች የድጋፍ ማኅበራት ያልተቋቋሙባቸው ከተሞች አሉ። በፓሪስ፣ በጣሊያን ሮምም እንዲያሁ ተመሳሳይ ሁኔታ አለ። በእርግጥ በሆላንድ አምስተርዳም ቀደም ሲል የድጋፍ ሰጪ ድርጅት የነበረበት ሁኔታ ነበር፤ በተለያየ ሁኔታ የድጋፍ ድርጅቱ ባጋጠመው ችግር አሁን የድጋፍ ድርጅት የሌለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ የጉዞ ድምዳሜ ላይ ከየድጋፍ ሰጪ ድርጅቶቹ ወኪሎች በሚገኙበት ሠፊ ውይይት ለማድረግ ዕቅድ ይዘናል። በዛ ውይይት ላይ በአውሮፓ አህጉር ውስጥ ያሉ የድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች የሚጠናከሩበት፣ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች በሌሉበት ቦታ እንደ አዲስ የሚፈጠሩበትንና እነዚያ የድጋፍ ድርጅቶቹ በጋራ የሚያስተሳስራቸውን ሁኔታ ለመፍጠር ነው ዕቅዳችን። በዚህ ጉዞ መጨረሻ ላይ የድጋፍ ድርጅቶቹ በሚወስዱት የጋራ እርምጃና በሚደርሱበት የጋራ ስምምነት ላይ መሠረት በማድረግ በአምስተርዳምም ሆነ የድጋፍ ሰጪ ድርጅቶቹ በሌሉባቸው ቦታዎች በአፋጣኝ አስኳሉ እየተጣለ የድጋፍ ድርጅቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚቋቋሙበት ሁኔታ ነው የሚኖረው።
በአውሮፓ የቀድሞው የቅንጅት ድጋፍ ድርጅቶች በርካታ ደጋፊዎችን ሲያበሳጩ፣ ሲያነታርኩና ሲያናቁሩ እንደነበሩ ይታወቃል። የአንድነትስ የድጋፍ ሰጪ ማኅበራት ምን ያህል በውጭ የሚኖሩትን ደጋፊዎቻችሁን አንድ የሚያደርጉ፣ የሚያሳትፉ፣ ከስደተኛው ማኅበረሰብ (ዳያስፖራ) ጋርስ ተባብረው የሚሠሩበት ሁኔታ ይፈጠራል ወይ?
ከውስጥ የዲሞክራሲ ባህል፣ ከተቋማዊ አሠራር፣ ከግልጽነት፣ ከተጠያቂነት፣ ... አንጻር፤ እንኳን የፓርቲው ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ራሱ ፓርቲውም ቢሆን ብዙ ጉድለቶች እንደነበሩት የሚታወቅ ነው። እነዚያ ጉድለቶች የፈጠሯቸውን ጉድለቶች በዓይናችን ያየናቸው ናቸው። የተፈጠሩት ችግሮች በተለይም በውጭ ሀገር ያለውን ደጋፊ በጣም ያሳዘኑ፣ ምናልባትም በአንዳንድ ሁኔታ ተስፋ እስከማሳጣት የደረሱ እንደነበሩ ይታወቃል። በውይይቶቻችን የችግሮቹ መነሻ ምክንያቶቻቸውን ተለይተው ታውቀዋል፤ ከዚህ በኋላ መልሰው እንዳይከሰቱ የድጋፍ ሰጪ ድርጅቶቹ የሚቋቋሙበትን፣ የሚሠሩበትን መንገድ በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት የሚሠሩ፣ አመራሩም በደንቡ መሠረት በተወሰነለት ጊዜ በየጊዜው የሚመረጥ ሆኖ፤ አሠራሩም ግልጽነትና ተጠያቂነትን የተከተለ መሆን እንዳለበት ተገንዝበናል። ይኼ ደግሞ ለሚደግፉት ፖርቲም ሆነ ለደጋፊ ድርጅቶቹም ለራሳቸው ለስኬታቸውም ሆነ፤ ከዚህ በኋላ እንደተቋም ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ዋስትና የሚሰጥ ይኼ ብቻ እንደሆነ መግባባትና መረዳት ላይ ተደርሷል።
ስለዚህ ከዚህ በኋላ በሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲህ ዓይነት እርምቶች ስለሚደረጉ፤ አሁን አንተ እንደጠቀስከው ከዚህ በፊት እንደተፈጠሩት ዓይነት ደጋፊዎችን የሚያበሳጩ ድርጊቶች፣ አላግባብ የሚፈጠሩ መጎሻሸሞች ይኖራሉ ብለን አንገምትም። ብዙ ትምህርት የተቀሰመበትና ከዚህ በኋላ የሚኖረው ኺደት መሻሻሎች የሚታይበት እንደሆነ የሚጠቁሙ ግንዛቤዎች በአባላቱ መሃከል ተፈጥሯል።