ከወ/ት ብርቱካን ወላጅ እናትና ከልጇ ህጻን ሐሌ ጋር የተደረገ ቃለምልልስ
"እናቴ ናት፣ እወዳታለሁ! ስሄድ እቅፍ አደርግና እስማታለሁ፤ እሷም ትወደኛለች" ህጻን ሐሌ
"ለእኔ ከላይ ከታች ያለችኝ፣ ጧሪ ቀባሪዬ እሷው ናት" ወ/ሮ አልማዝ
የአንድት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ሊቀመንበር ብርቱካን ሚደቅሳ ወላጅ እናት የ72 ዓመቷ ወ/ሮ አልማዝ ገ/እግዚያብሔር በእስር ላይ ስለምትገኘው ልጃቸው እንዲሁም የአራት ዓመት ልጇ ሐሌ ሚደቅሳ ከአዲስ አድማስ ዘጋቢ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርበዋለን።
ከወ/ት ብርቱካን ሌላ ልጅ የሎትም?
ከመጀመሪያ ባለቤቴ ደራ እያለሁ የወለድኩት አንድ ወንድ ልጅ አለኝ። አዲስ አበባ በትዳር መጣሁና ሚሚን እኔ ካረጀሁ (ወ/ት ብርቱካንን ማለታቸው ነው) ጃንሆይ ከሥልጣን በወረዱበት ጊዜ፣ እዚችው ቤት ወለድኳት።
አስተዳደጓ እንዴት ነበር?
በተወለደችም በዕድገቷም ጊዜ ምንም ችግር አልነበረብኝም፣ አባቷም አሥር አለቃ ሚደቅሳ ደሜ በፊት የክብር ዘበኛ አባል ነበሩ፤ በኋላ ጡረታ ወጥተው ነበር። ምንም እንኳን የኑሮ ደረጃችን በዝቅተኛ ደረጃ የሚመደብ ቢሆንም እሷን ተንከባክቦና አንቀባሮ ለማሳደግ አልቸገረንም። ብቸኛ በመሆኗም የተለያየ አትኩሮትና ፍቅር እየሰጠናት በጥሩ ሁኔታ አሳደግናት። ዕድሜዋ ለትምህርት እንደደረሰ ህዝባዊ ሠራዊት ነው የሚባለው ወይም ሚሽን ገብታ ተማረች። ተምራ ወደ ቤት ስትመጣ ጥናት አታቅም ደፍተሯን ውርውር ነው የምታረገው። ነገር ግን አንደኛ ነበር የምትወጣው። በትምህርት ቤቷ ውስጥም እንዲሁ እጇን እያወጣች “ጥያቄ አለኝ” እያለች አስተማሪዎቿን ስትጠይቅ ነው የምትውለው የሚለውን እሰማ ነበር። ከዓመት ከዓመት ጥሩ ውጤት ማምጣቷን እየሰማሁ ስምንተኛ ክፍክ 100 አምጥታ አለፈች ተባለ። ልጄ አንደኛ ወጣች ብዬ በጣም ደስ አለኝ። ከዚያም መነን ገባች፤ እሱንም ስትጨርስ አሁንም በአንደኛ ደረጃ ውጤት አመጣች አሉ፤ ከዛ ዩኒቨርስቲ ገባች። የዚን ግዜ በጣም ስለተደሰትኩ ድንኳን ጥዬ ነበር ያስመረኳት።
የልጅነት ፀባይዋስ?
ሚሚ ልጄ ስለሆነች አይደለም። የፈረንሣይ ሰው ሁሉ የሚመሰክርላት ነው። ከልጅም ከጎረቤት የማትጣላ፤ ሰው የምታከብር እንጂ የምትነቅፍ አይደለችም። ምንም እንኳን የሌለባት እንደጠጅ የተጣራ ፀባይ ነው የነበራት። አሁንም እንዲሁ ናት።
ዩኒቨርስቲ ከገባች በኋላ ግንኙነታችሁ እንዴት ነበር?
የገባችበት ዩኒቨርስቲ እዚሁ አዲስ አበባ ስለነበር በየሣምንቱ ትመጣ ነበር። በኋላ ሁለት ዓመት እንደተማረች አባቷ አረፉ፤ እኔ መቼም ይህን ሳያዩ በመሞታቸው ተገላገሉ ነው የምለው። ትምህርቷን አጠናቃ ስትመጣ ከኔ ጋር መኖር ጀመረች። ከዛ በቀጥታ ዳኛ ሆና ሥራ ነው ጀመረች። ጠበቃም ከሆነች በኋላ አልተለያየንም። ልጅ ወልዳ ዓይኔን በዓይኔ አሳይታኝ ነበር። ቤታችንን በማርጀቱም ፈርሶ ነበር። አፍርሳ እንደገና ሠርታ፣ ልጄ ልጅ ወልዳ ሳትቀመጥ፤ ሰዎች ልጄን ወስውሰው እንዲህ ያለ ነገር ውስጥ አስገቡብኝና እንዲሁ እንደታሰረች አለች።
ወ/ት ብርቱካን ስትታሰር “ሐሌ” የተባለች ህጻን ልጇ የስንት ዓመት ልጅ ነበረች?
የመጀመሪያውን ስትታሰር የስድስት ወር ልጅ አካባቢ ነበረች። እኔ ነኝ ያሳደኳት። እስር ቤትም አራስ ልጇን ነው ይዘንላት እየሄድን የምናስጠይቃት የነበረው።
በወቅቱ በእስር በነበረችበት ሁለት ዓመት ከአራስ ልጅ ጋር ስንቅ ማመላለስ አይከብድም ነበር?
ያኔ ደህና ነበርኩ። መኪናም ባላገኝም ባቡር ጣቢያ እሄድና በሎንችንም ተሳፍሬ እሄዳለሁ። ያሁኑን ግን አልቻልኩም ውስጤ እንዲሁ እንደተቃጠለና እንዳረረ አለ።
አሁን ያለችበት ሁኔታ እንዴት ነው?
የጤንነት ሁኔታዋን በተመለከተ፤ ብቻዋን መሆኗነው እንጂ፣ ደህና ነች፣ ጤነኛ ነች፣ በጥሩ ሁኔታ ነው ያለችው። እግዚያብሔር ከሷ ጋር ነው ማለት እችላለሁ። ነገር ግን እስር ቤት ያውም በወጣትነት ብቻ ታስሮ አንድ ሰው ተመችቶ ይኖራል ማለት አይቻልም። በርግጥ ገብተን ስንጠይቃት እኔንም ሆነ ልጇን ስታነጋግረን ጥንካሬዋ ከዱሮው ባልተለወጠ ሁኔታ ነው። አጫውታን አሳስቃን ነው የምትሸኘን። ይሄ ማለት እንደናትነቴ ሳየው ተመችቷታል ለማለት አያስችለኝም። ከኛ ተለይታ ወደ ውስጥ ስትገባ። በተዘጋ ቤት ውስጥ ብቻዋን ቁጭ ብላ ስትጨነቅ የምታረገው፣ ግራ ሲገባት፣ ወጣትነቷ ሲጨልም ይታየኝና ውስጤ እርር ይላል። እንደው እኔስ መሞቻዬ ደርሷል እንደው መንግሥት መሃሪ ነው፣ መንግሥትነቱን የሚያስተዳድሩትም ሰዎች ናቸው። እንደሰው ይሰማቸዋል፣ ቤተሰብ አላቸው ወዴት እንደሚኬድ ግራ ግብት ብሎኝ ነው እንጂ፤ እንደው ልጄ ከዚህ በኋላ የትም አትደርስ ሰብስቤ እይዛለሁ ብዬ ቃል ገብቼ ይቅርታ ቢያደርጉልኝ እጠይቅ ነበር። መቼስ እንኳን ምንም ጥፋት ያላጠፋችን አንዲት ሴት ይቅርና መንግሥት ስንትና ስንት ወንጀል የፈጸመን ቅር ብሎ ይፈታ የለ እንዴ።
መልዕክቶን ለሚመለከተው ሰው በዚህ ጋዜጣ ማስተላለፍም ይችላሉ
ከመጀመሪያው ብነሳ ብቻዋን መታሰሯና ከኔና ከልጇ ውጭ ከቤተሰብ አለመገናኘቷ ትክክል አይደለም አሉኝ። ከሰስን፣ ፍርድ ቤትም ከመጀመሪያው ጀምሮ እየተከተልኩ አይቻለሁ፤ ብቻዋን መታሰሯ ትክክል ነው ብሎ ሲወስን ቤተሰብ ግን ይግባና ይጠይቃት ብሎ ወሰነ። በውሳኔው ተደስቼ ነበር፤ ግን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ አልተከበረም። የሚያስገቡኝንም ሰዎች ስጠይቅ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አልደረሰንም፣ አልታዘዝንም አሉኝ። የት ሔጄ ልጠይቅ? የሚኬድበትም አላውቅ። ብቻ እንዲሁ በሁሉ ተቃጠይ ብሎኛል እንደተቃጠል አለሁ።
ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ ሁለት ተጨማሪ ሰው ተፈቅዶሎታል አይደል?
እሱ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ አይደለም የተፈቀደልኝ። እንደምታዩኝ እኔ አቅመ ደካማ ነኝ። ከታሰረች ጀምሮ እግዚያብሔር ይስጣቸውን የሚያስገቡኝ ሰዎች አንዳንድ ዕቃ ከሚይዙልኝ በስተቀር ስንቁን ይዤ ከግቢው መግቢያ ጀምሮ የታሰረችበት ክፍል እስክደርስ ያለውን ረዥም መንገድ ስንቅ ተሸክሜ መመላለሱ በጣም እየደከመኝና እያቃተኝ ስመጣ አምርሬ አቤት አልኩ። እባካችሁ የሚያግዘኝ እየተቀያየረ የሚገባ ሁለት ሰው ፍቀዱልኝ ብዬ ጠየኩ፤ ገና የፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ላይ እያለ ስም ስጪ ተባልና የሁለት ሰው ስም ሰጠሁ፤ በዛ መሰረት ተፈቀደልኝ። ነገር ግን ይሄ ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ ጋር አይሄድም፤ ፍርድ ቤቱ በማንም ሰው መጠየቅ መብቷ ነው ብሏል። በዚህ ላይ እነዚህ የተፈቀዱት ሁለት ሰዎች ይቀያየሩልልኝ ብል እንኳን አልሆነም መቼም ሰው ሁሌ አይመቸውምና ሳይመቻቸው ቀርተው ቢቀሩ እንኳን ስንቁን ብቻዬን ነው የማመላልሰው። ደሞስ ሌላ እስረኛ ሁሉ ወዳጅ ዘመዱ አይዞህ ከጎንህ ነን ሲለው ምነው ከሰው እንዳልተፈጠረ ሰው ብቻዬን መከራዬን የምበላው። ፍርድ ቤት የሁሉም የበላይ ነው አይደል? ምነው እሱ ያለውን ቢፈጽሙልኝ። ሰው ቢገባ ይዞ የሚወጣው ነገር የለ፣ ሁሉም ሲገባ ተፈትሾ ቢገባ ምን የሚጎዳው ነገር አለ? እስቲ ደግሞ ቅዳሜ ሲመጣ የሚሆነውን አያላሁ።
ልጇ “ሐሌ” ይዘዋት ሲገቡም ሆነ ሲወጡ አታስቸግሮትም?
እግዚያብሔር በስንቱ ልበድልሽ ብሎ ነው መሰለኝ ልጅቷስ ፊቱንም ከኔ ጋር ስለለመደች ብዙም አታስቸግረኝ። አወጣጧም እሷኑ ሊሆን ነው መሰለኝ ከትምህርት ቤቷ “ሐሌ በጣም ጎበዝ ልጅ ነች” ብለው ጽፈው ይልኩብናል። ደሞ በየወሩ የሚሰይሙት ነገር አለ መሰለኝ ሁሌም “ዛሬ የወሩ ኮከብ ሆና ተመርጣለች” እያሉ እጇ ላይ የኮከብ ስዕል እየሳሉ ይልኩልናል። እና እናቷ ጋር ስትሄድም አጫውታት ትስማትና፣ ሲመሽ ነው ወደቤት የምትመጪው ትላታላች፤ ብዙም አታስቸግራትም። አሁን አሁን ግን እቤት ውስጥ ምንም ነገር ሲሠራ “ለቡርቴ ነው?” ብላ ወጥራ ትይዘናለች። ክፍሏም ትገባና “መቼ ነው መጥታ የምትተኛው?” ብላ ትጠይቀናለች። እሷንም ትሄድና “ለመምጣት ስንት ቀን ቀረሽ? ሦስት ቀን ቀረሽ? ሁለት ቀን ቀረሽ?” እያለች ጣቷን እያሳየች ትጠይቃታለች።
ከዚህ በኋላ ምን ይፈጠራል ብለው ይጠብቃሉ?
እኔ እንግዲህ ምንም የማውቀውም የሚታየኝ ነገር የለም። አንድ ነገር ግን አጥብቄ እለምናለሁ። መቼም ሰው ሆኖ የማያጠፋ የለም። አጥፍታም ከሆነ፣ ለእግዚያብሔር ብለው፣ ለዘርና ለትውልዳቸው ብለው ቢለቁልኝ። ህጻን ልጅ ያለው ሰው ስሜቱ በደንብ ይገባዋል፤ እናት ለልጇ ምን ማለት እንደሆነች፤ ለዚች ለህጻን ልጇ ያለቻት እሷው ናት። እሷም ብትሆን ወጣትና የተማረች ተንኮል የማታውቅ ንጹህ ልጅ ናት፤ ለሀገር አትጠቅምም ብቻዋን ነፍስ እንዳጠፋ ሰው እዛ ተወስዳ የምትታሰረው፣ ለኔም ከላይ ከታች ያለችኝ ጧሪ ቀባሪዬ እሷው ናት። መንግሥት አስተያየት አድርጎ ቢፈቅድልኝ በእግዚያብሔር መንገድም ያስኬዳል። እስቲ እግዚያብሔር ልባቸውን ያራራልኝ።
የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ልጅ ሐሌ ሚደቅሳ ሳቂታና ተጫዋች ናት አያቷን ድምፅ መቅረጫ ደቅነን ስናናግር ተመለከተችና እኔም ላውራ ስትል እንደቀልድ ጠየቅችን። የጠየቀችው ይሳካ ብለን ድምፅ መቅረጫውን ከፈትንና አንዳንድ ነገር ጠየቅናት። በኮልታፋ አንደበቷ የሚከተለውን ምላሸ ሰጠችን። ስምሽን፣ ስንት ዓመትሽ እንደሆነና የት እንደምትማሪ ንገሪን?
ስሜ ሐሌ ሚደቅሳ ነው። አራት ዓመቴ ነው የምማረው “ዋን ፕላኔት” ነው።
ብርቱካን ሚደቅሳ ምንሽ ናት?
እናቴ ናት። እወዳታለሁ ስሄድ እቅፍ አደርግና እስማታለሁ፤ እሷም ትወደኛለች። ደኅና ነሽ ወይ እላታለሁ። እሷ ደግሞ የሚበላ ነገር የሚጠጣ ነገር ታመጣልኛለች።
ከማን ጋር ሄደሽ ትጠይቂያታለሽ?
ከእማማ ጋር፣ ከእሙሻ ጋር፣ ከደረጀ ጋር
ቤቷ ገብተሸ ጠየቅሻት?
አዎ! ሸውጄ አይቸዋለሁ። (አያቷ በመሃል ገብተው ኧረ! ሸውዳ አይደለም አንዴ ሳትሰናበታት ስለሄደች ስታለቅስ አስገብተዋት ነው። አንዴ ደግሞ ሽንቷ በጣም ስለወጠራት ልትሸና ገብታ ነው። እሷ ግን ጨዋታ ስለምትወድ ስትወጣ ጠባቂዎቹን “ሸውጃችሁ ገባሁ” አለቻቸው እነሱም ስቀው ዝም አሉ) ሁለቱንም ቤት ገብቼ አይቻለሁ። አንደኛውንም ሁለተኛውንም። አንደኛው ትልቅ ሆኖ ግን አልጋው የዱሮ ነው፤ ደሞ የቤት አልጋ ልብስ ነው ያለበት። ግን ሁለተኛው ጠባብ ነው። አልጋና ፍራሽ አለው።
ልትጠይቂያት ስትሄጂ ምን ብለሽ ታጫውቻታለሽ?
አንድ ቀን ሃፒ በርዝዴይ ስላት ቴንኪው አለችኝ። ግን ለመፈታት ስንት ቀን ቀረሽ ስላት ቀረኝ አትለኝም፣ እፈታለሁም አትለኝም። እኔ ግን ናፍቃኛለች።