PM Meles Zenawi ጠ/ሚር መለስ ዜናዊጠ/ሚር መለስ ዜናዊ ከእንግሊዙ “ፋይናንሽያል ታይምስ” ጋዜጣ (የጁን 23, 2009 ዕትም) የአፍሪካ ዴስክ አዘጋጅ ዊልያም ዋሊስ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ባደረጉት ቃለምልልስ፤ በኢትዮጵያ በፈቃድ ሥልጣን የመልቀቅ ባህልን መስበር እንደሚፈልጉና የመጀመሪያው በፈቃደኝነት ሥልጣኑን ለቀቀ የሀገሪቱ መሪ ለመሆን እንዳቀዱ ገልፀዋል። በርካታ ኢትዮጵያውያን የጠ/ሚ/ሩን አባባል በጥርጣሬ ከመመልከታቸውም ባሻገር “ሐሰት ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው ይታመናል። ይኸው ቃለምልልስ ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ ስለታሰሩት፣ በፀረ-ሽብር ረቂቅ ሕጉ፣ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ... ጉዳዮች ላይ አተኩሯል። ቃለምልልሱን በሀገር ውስጥ የሚታተመው “ሪፖርተር” ጋዜጣ እንደሚከተለው ወደ አማርኛ ተርጉሞታል። መልካም ንባብ!

 

አፍሪካ በቡድን ሃያ ጉባዔ ላይ የተሻለ ውክልና በማግኘት ጥሩ ሥራ የሠራች ይመስል ነበር። በስምምነቱ ላይ የተባለው ይፈፀማል በሚለው ረክተዋል?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ አዎ ከሌሎቹ ጊዜያት በተለየ መልኩ የተሻለ ቃል ተገብቷል። 50 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ በአይ.ኤም.ኤፍ. በኩል ይታደላል። ከስፔሻል ድሮዊንግ ራይት ከምናገኘው 17 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ከወርቅ ሽያጭ ይገኛል። የአይ.ኤም.ኤፍ. ማኔጂንግ ዳይሬክተር ይህንን ለመፈፀም እየሠሩ ነው። የሀብት ክፍፍሉም ይህ ዓመት ሳያልቅ እንደሚሰራ ይጠበቃል። የ6 ቢሊዮን ዶላር ወርቅም ለሽያጭ እንደሚቀርብ ለሁሉም ሚኒስትሮች አስታውቀዋል። የወርቅ ሽያጩ ቀስ ብሎ መከናወንም ይችላል። በአሁኑ ወቅት 23 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ አካባቢ ለመከፋፈል ዝግጁ ነው። ቃል የተገባልን 50 ቢሊዮን በመሆኑም ቀሪው 27 ቢሊዮን በቀጣይነት መከፋፈል አለበት። እስካሁን ያገኘነው ከጠበቅነው አንፃር በጣም የተሻለ እና ከተጠበቀው በላይ ፈጣን ነው።

 

ለጋሽ መንግሥታት ከሁለት ሦስት ዓመታት በፊት ትችት ይሰነዝሩ ነበር። አንዳንድ ሕጎችንም ተቃውመው ነበር። አሁን ግን ከእርስዎ ጋር አብረው እየሄዱ ይመስላሉ

 

ጠ/ሚ መለስ፦ አይደለም። አሁንም እየተቃወሙ ነው። በግልጽነትም እንደማይስማሙ እየነገሩን ነው። ይሁን እንጂ እስካሁን አወጣጥ ላይ አንዳንድ ነገሮች አስቀምጠዋል እኛም ያሉንን የፖሊሲ አማራጮች እየተጠቀምን እየሰራን ነው። ፖሊሲያችንም ትክክለኛ መሆኑን ከአማካዩ በላይ ማሳየት አለብን። ሃሳባችን አሁን ከበፊቱ በተሻለ መልኩ በተጨባጭ ለውጦች እየተደገፈ ነው።

 

ከተለያዩ የውጭ ኃይሎች ጋር የተለያዩ የዲፕሎማሲ ጨዋታዎችን በመጫወት ተክነዋል። ለምሳሌ ከምዕራቡ ዓለም ጋር

 

ጠ/ሚ መለስ፦ መካን የሚለው ምን እንደሆነ አላውቅም። ከየትኛውም የዓለም ክፍል ዕርዳታ ማግኘት እንፈልጋለን። ምክንያቱም የምናገኘውን ድጋፍ ሁሉ ስለምንፈልገው ነው። ሕንዶችን፣ ከእናንተ ምንም አንፈልግም ከቻይና እንጂ ብንል ይህ አሳፋሪ ነው። እንግሊዛዊያን ሊረዱን ሲፈልጉ ቻይናዊያን አንዳንድ የመንገድ ፕሮጀክቶች እየሰሩልን ስለሆነ የእናንተን ገንዘብ አንፈልግም ብንልም አሳፋሪ ይሆናል። ትርጉምም አይኖረውም። የምንችለውን ያህል ድጋፍ ለማግኘት እንፈልጋለን። ይህ ማለት በዕርዳታ ላይ እንንጠላጠላለን ማለት ሳይሆን ባገኘነው መንገድ ሁሉ በመጠቀም የተሻለ ነገር መስራ እንፈልጋለን።

 

ከምዕራባዊያን ሀገራት የሚገኝ ዕርዳታ ብዙውን ጊዜ የተለያዩ መስፈርቶች ይቀመጡለታል። በቻይና እና በሕንድ ይሄ የለም። ከምዕራባዊያን ይልቅ ምስራቅ ሀገራት የበለጠ ይመቹዎታል፣

 

ጠ/ሚ መለስ፦ እያንዳንዱ ለጋሽ የራሱ ጥንካሬና ደካማ ጎኖች ይኖሩታል። በምዕራባዊያን ዕርዳታ ላይ የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ለምዕራባዊያን ዕርዳታ ሰጪዎች ብላ ኢትዮጵያ አንድም የፖሊሲ ቅድመ ሁኔታ ሳይመቻት ተቀብላ አታውቅም። በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያደረግናቸው ተሃድሶዎች ለእኛ ጠቃሚ ናቸው ብለን ስላመንን የወሰድናቸው ናቸው።

 

ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና መንግሥታት ይህንን ማድረግ አልቻሉም። ይህንን ማድረግ ለእርስዎ እንዴት ተቻለዎት?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ ምናልባት እኛ የተሻለ ግፊትና ጫናን ስለምንቋቋም ይሆናል።

 

በአፍሪካ ቀንድ ምንም ዓይነት ችግር ቢኖር ኢትዮጵያ ተረጋግታ ትቀጥላለች ይባላል። ሱዳን፣ ሶማሊያ ኤርትራ ሁሉም ጎረቤት ሀገር ናቸው። ያለው ሁኔታ ለኢትዮጵያ የተሻለ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነፃነት የሰጠ ይመስላል

 

ጠ/ሚ መለስ፦ ጆሴፍ ስትግሊዝ የዓለም ባንክ ቺፍ ኢኮኖሚ ከሆኑ ከ10 ዓመታት ወዲህ ከባንኩ ጋር መልካም መግባባት አለን። ይህ መግባባት ደግሞ ጠንካራ ነው። ይህም የምናገኘው ዕርዳታ በመጠኑ ቢያንስም የተሻለ የፖሊሲ ቦታ ይሰጠናል። ባለፉት ዓመታት ያገኘነውን የፖሊሲ ክፍተትም በሚገባ ተጠቅመንበታል። የትኛውም የለጋሽ ሀገር መንግሥት በኢኮኖሚ ልማታችን ላይ ቅሬታ የለውም። ደሃ አገዝ የዕድገት ኢንቨስትመንት አካሄዳችን ከአፍሪካው አማካይ የበለጠ ነው። ከበጀታችን 70 በመቶው ለደሃ አገዝ ኢንቨስትመንት ይውላል። ይህ በአፍሪካ የትኛውም ሀገር እየተሰራበት አይደለም። ለሥራችን ማሳያ እያቀረብን ስለሆነ ለጋሾች አልሰራችሁም ብለው ሊናገሩን እንዳይችሉ ሆነዋል። እነሱ የሚሉት የተሻለ ሥራ ሰርተን ውጤት ማስመዝገብ እንደምንችል ይናገራሉ። የአውሮፓ ኅብረት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ያነሰ የነፍስ ወከፍ ገቢ ለኢትዮጵያ ይሰጣል። የአውሮፓ ኅብረት በዚህ ረገድ በነፍስ ወከፍ ገቢ ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ለኤርትራ በአራት እጥፍ የበለጠ ይሰጣል።

 

ለጋሽ ሀገራት የማይክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ችግር እንዳለበት ይገልፃሉ። የውጭ ምንዛሪ ችግር፣ የዋጋ ግሽበትና የግሉ ዘርፍ በመንግሥት ብድር ተይዘዋል።

 

ጠ/ሚ መለስ፦ አዎ! ትክክል ነው ተከታታይ የዋጋ ግሽበት ገጥሞናል። ይህም መስተካከል አለበት። ከአይ.ኤም.ኤፍ. ጋር ይህንን ለማስተካከል ቀጠሮ ይዘናል። የክፍያ ሚዛን ችግር አለ። ይህም መፈታት አለበት። እነዚህ የሚታዩ ሁኔታዎች ናቸው። እኛም ልንፈታቸው ይገባል። የግሉ ዘርፍን በብድር ማጥለቅለቅ በጀታችን ዜሮ ሆኖ አይታሰብም። ላለፈው አንድ ዓመት የሚያበድር ባንክ የለንም። በዚህ ዓመት የሚያበድር ባንክ ዜሮ ይገባል። ይህ የበጀት ዓመትም ሰኔ 30 ያበቃል። ከዚህ በፊት ይታዩ የነበሩ የበጀት እጥረቶቹ ለኢንቨስትመንትና ለመሰረተ ልማት ይበሉ ስለነበር ነው። የኢኮኖሚ አማካሪዎቼ የግሉን ዘርፍ እንደወረርን ሳይሆን ለግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረግን ያምናሉ።

 

በቅርቡ ብዙ ሰዎች ታስረዋል። የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለመግደል፣ በሚል። አዲስ የሲቪል ማኅበረሰብ ሕግ፣ አዲስ የፀረ-ሽብር ሕግ ወጥቷል። ከውጭ ለሚያይ መንግሥትዎ በጠላት የተወረረ ይመስላል። የሚያሰጋዎት ጠላት አለ ወይስ ለምንድነው እነዚህ ሕጎች የወጡት?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ሊያስቡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ያነሳሃቸውን ነጥቦች ተመልከት። በአፍሪካ ኅብረትና በተባበሩት መንግሥታት ስምምነት መሰረት የፀረ ሽብር ሕግ ማውጣት ይጠበቅብናል። የፀረ ሽብር ሕጉን ማውጣት ያለብን ጥቂት ዓመታት ቀደም ብለን መሆን ነበረበት። በሌሎች ጉዳዮች ተጠምደን በመክረማችን ይህንን ማድረግ አልቻልንም። ይህን አሁን ወደማጠናቀቁ ቀርበናል። ረቂቁን አይተኸው ከሆነ ሕጉን የተለያዩ የፀረ ሽብር ሕጎችን በማጣቀስ የእንግሊዝን ጨምሮ የተሳ ነው።

 

አንዳንድ የሕጉ ክፍሎች በእንግሊዝ ቢሆን አይፀድቁም፣

 

ጠ/ሚ መለስ፦ ሕጉን እንድታነበው እመክርሃለው። ምክንያቱም የሰማኸው ምናልባትም ከምታነበው ጋር ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል። ይህ በኢትዮጵያ የተለመደ ነው። የእኛ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ከየትኛውም የአውሮፓ ሀገር ሕግ የበለጠ ወግ አጥባቂ አይደለም። በሕጉም ልናሳቅቀው ያሰብነው አካል የለም ያሉን የወንጀል ፍርድ ቤቶች ሽብርተኝነትን ለመመከት በቂ በመሆናቸው የፀረ ሽብር ሕጉን ለማውጣት አልተጣደፍንም ነበር። ይህንን ሕግ ለማርቀቅም በቂ ጊዜ ወስደናል። የታሰሩትን ሰዎች በተመለከተ የታሰሩት ሰዎች አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለመግደል ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸው ነው።

 

እርስዎም ለመገደል ከታሰቡት መካከል ነበሩበት?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ ይህንን በተመለከተ ግልጽ ነገር የለም። እውነቱን ይንገሩን አይንገሩን ማወቅ አይቻልም። አንዳንዶቹ የለም ይላሉ ሌሎቹ አዎን ይላሉ። ይህ ከዓላማቸው ጎን የሚነሳ ነው።

 

ቃላቸውን ሰጥተው አምነዋል?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ አዎን። እነዚህ የሽብር መንጋዎች ከአልሽባብና ከአል ኢታሃድ በተለየ መልኩ ያልሠለጠኑና አማተር ሽብርተኞች ናቸው። ለመግደል ሲያቅዱ ኦፕሬሽናቸው እጅግ ኋላ ቀር ነበር።

 

ይህ ግን በጦር ኃይሉ ውስጥ ከባድ ችግር እንዳለ አያሳይም? አንዳንድ ሰዎችም ይህንን ይጠረጥራሉ፣

 

ጠ/ሚ መለስ፦ በፍፁም የሲቪል ማኅበራትን ሕግ ለማፈን የወጣ ነው የሚሉ አሉ፤ እኛ ግን የበለጠ የሚያግዝ ነው እንላለን። በእኛ ሕግ የተሰየሙ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ብለን ሲቪል ማኅበረሰቡን መክፈላችን ነው። የውጭ ድርጅቶችና በውጭ ኃይሎች የሚረዱ በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ አይሰሩም። አንዳንዶች ይህ ማፈን ነው ይላሉ። እኛ ደግሞ ሲቪል ማኅበራትን ማበልፀግ ነው እንላለን። ሲቪል ማኅበራት የአባላቱን ፍላጎት ማሳየት አለበት። ለዚህም ነው የአሜሪካ የውጭ ሲቪል ማኅበራት መሳተፍ የማይችሉት።

 

በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በውጭ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ የሰብዓዊ መብትና የዲሞክራሲ ደጋፊ ድርጅቶች አሉ። ከሀገር ውስጥ በቂ ፈንድ ማግኘት በኢትዮጵያ አይቻልም። ይህ ማለት ደግሞ እነዚህ ድርጅቶች ይጠፋሉ ማለት ነው?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ ይህ አሳፋሪ አባባል ነው። ይህንን ንግግርህን ብትገፋበት የሚወስድህ ደሃ ሰዎች ሃብታሞች ካልከፈሉላቸው ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ማራመድ አይችሉም ልትል ነው። እነዚህ መብቶች ለድሆች አስፈላጊ ናቸው ካልን ደሃ ህዝቦች እነዚህን ዓይነት መብቶቻቸውን ተሰባስበው ማስከበር፣ የራሳቸውን ሀብት ማውጣት ይችላሉ። ምክንያቱም እነዚህ መብቶች ጠቃሚ ናቸው። በዚህ ሀገር ለማስተማሪያ የሚሆን ታሪክ አለን። በገጠር የሚኖሩ አርሶ አደሮች በትንሽ ትምህርት፣ ከውጭ ፈንድ ሳያገኙ በኢትዮጵያ የመሬት ላራሹን እንቅስቃሴ አድርገዋል። የንጉሡን አገዛዝም ያለ ውጭ ዕርዳታ እነዚህ አርሶ አደሮች ጥለውታል። ይህ በ1970ዎቹ የሆነ ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ይህ የማይሆንበት ምክንያት የለም ብለን እናምናለን። በሌላ መልኩ ለሲቪል ማኅበራት የውጭ ዕርዳታ የሚሰጥ ከሆነ ሲቪል ማኅበራቱ ዲሞክራሲያዊ ፀባያቸውን ያጣሉ። ምክንያቱም ሲቪል ማኅበራቱ በማኅበራት አባል ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አይደለም። አመራሩ የኤምባሲዎች ጥገኛ ይሆናል።

 

መንግሥታችሁም የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና ኤምባሲዎች እንደ መንግሥትነታችው ጥገኞች ናችሁ እኮ፣

 

ጠ/ሚ መለስ፦ ለልማት እንቅስቃሴዎች ከሆነ፣ አዎ!

 

ዕርዳታ አላቂ ነው። በፖለቲካ እንቅስቃሴም በእነሱ ላይ ጥገኞች ናችሁ?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ መደበኛ ባጀታችን በሀገር ውስጥ ገቢ የተመረኮዘ እንደሆነ ግልጽ አቋም ይዘናል። ይሄም ለጤንነታችን አስፈላጊ መሆኑን እናምናለን። ለልማት እንቅስቃሴዎች ግን የውጭ ዕርዳታ እንፈልጋለን። የውጭ መያዶችም በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ልማታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ እየጠየቅን እንገኛለን። በእነዚህ ዘርፎች የውጭ የተራድኦ ድርጅቶች መንቀሳቀስን አልከለከልንም።

 

በመልካም አስተዳደርስ ታዲያ ለምሳሌ?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ ያ ፖለቲካ ነው። ፖለቲካ ደግሞ የዜጎች ጉዳይ ነው።

 

እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ሰዎች ሃሳባቸውን በነፃ የማይገልፁበት ሁኔታ ለመፍጠር አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፦

 

ጠ/ሚ መለስ፦ የሀገር ውስጥ ጋዜጦች አንብበሃል? ስለ መንግሥት ሲናገሩ ቃል እንኳን ሲያጥራቸው አይተሃል?

 

ፓርቲያችሁ ልክ አንዳንድ የሀገሪቱ ነፃ አውጪ ንቅናቄዎች የመጀመሪያ ዓላማቸውን ስተው ሥልጣን ለራሳቸው የሚል ጥቅም ለማስፈፀም በማሰብ ህዝብ የራሱ ዓይነት የማጋጠም አደጋ አለባችሁ ወይ?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ አዎ! ምንም ዋስትና የለንም። እያንዳንዱ ንቅናቄ በየዕለቱ ራሱን ማደስ ይኖርበታል። አለዚያ ደግም የመሰባሰብ አደጋ ያጋጥማል።

 

አመራሩን መለወጥ ጨምሮ?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ በሚገባ!

 

ቀደም ሲል ሥልጣን እንደሚለቁ ተናግረዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አዲስ ነገር እና እርምጃ አለ?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ ቢያንስ በፓርቲያችን ውስጥ እየተወያየንበት እንገኛለን። በድርጅታችን የምናካሂደው ውይይት ደግሞ ሰዎች ከሚሰጡት ቦታ በላይ የበሰለ እንደሆነ እንገምታለን። እያወራን ያለነው ስለ መለስ ብቻ አይደለም። እያወራን ያለነው ስለቆየው አመራር ነው፣ ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ስላለው አመራር ማለትም ድርጅቱ በትጥቅ ትግል ጊዜ ያልነበረ አዲስ አመራር ይፈልጋል ነው። ይሄ ለድርጅቱም ታክቲክን በተመለከተ መልስ መስጠት አስቸጋሪ ይሆናል፤ ስለተቀረው ጊዜ ሊያከራክር ይችል ይሆናል። የቀድሞው አመራር ተወግዶ በአዲስ አመራር መተካት አለበት በሚል መርኅ ላይ ግን ምንም ዓይነት አለመግባባት የለም። ይሄ የመፍትሔው አንድ አካል ነው፣ የብቸኛ መፍትሔ ግን አይደለም። ድርጅታችን ሌሎች ነፃ አውጪ ንቅናቄዎች የገጠማቸውን የመበስበስ አደጋ በእጅጉ ያስወገደ ይመስለኛል።

 

በመጪው ዓመት ምርጫ ላይ አልሳተፍም እያሉኝ ነው?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ እኔ እያልኩ ያለሁት በእኔ እምነት “ሥልጣን” በቃኝ። እኔ ብቸኛ ተዋጊ አይደሉም። ጠ/ሚኒስትር ሆኜም ቢሆንና ከጊዜ ወደ ጊዜ በድምፅ እየተበለጥኩኝ የማልፈልጋቸውን ነገሮች ፈጽሜያለሁኝ። በተለይ የኤርትራን ጦርነት በተመለከተ እኔ ያልተስማማሁበትን የድርጅቱ አቋም ተግባራዊ አድርጌአለሁ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ደግሞ ሁለት አማራጮች ብቻ ነው ያሉኝ። ድርጅቴን በፍቃዴ መልቀቅ ወይም የአብላጫውን ድምፅ መቀበል። ስለዚህም፣ እኔ ጉዳዬን ይዤ እየተከራከርኩ ነው። ሌሎችም ጉዳያቸውን ይዘው እየተከራከሩ ነው። በመጨረሻም ሕይወቴን በሙሉ የተዋጋሁበት ድርጅቴን ለቅቄ የማልወጣበት የጋራ መግባባት ላይ እንደርሳለን የሚል ተስፋ አለኝ። ከመንግሥት ሥልጣኔን ከለቀቅኩ በኋላም በድርጅት አባልነቴ ለመቀጠል እፈልጋለሁ። ተስፋዬ ግን አንድ መግባባት እንደርሳለን የሚል ነው። ያሉን ልዩነቶች እጅግ ከፍተኛ ናቸው ብዬ አላስብም።

 

ይሄ የሚሆነው መቼ ነው? በቅርቡ የሚካሄድ የድርጅቱ ጉባዔ አለ፣

 

ጠ/ሚ መለስ፦ አዎ መስከረም ላይ ጉባዔ ይኖራል።

 

ይሄ ውሳኔ በዛ ወቅት ክርክር ይደረግበታል?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ አዎ! ግን ከዛም በፊት ውይይት ይደረግበታል።

 

ለማጥራት ያህል እርስዎ እያሉት ካለ ተሃድሶ ለማድረግ የያዙት እቅድ በድርጅትዎ አብላጫ ድምፅ ድጋፍ ካላገኘስ በፍቃድዎ ይለቃሉ?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ ሁለት አማራጮች ይኖሩኛል። በቀጣይ አንድ ወቅት ላይ ለማሳመን እችላለሁ ወይም እለቃለሁ። ተስፋ የማደርገውና የምገምተው ግን ያለን ልዩነት ሰፊ ስላልሆነ የምንስማማበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን የሚል ነው።

 

ማን እንዲተካዎ ይፈልጋሉ?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ ይህንን ለድርጅቱ ውሳኔ መተው እፈልጋለሁ።

 

እዚህ ያሉት ግደባዎች እንዳሉ ሆኖ የሚያደርጉት እርምጃ ከቻይና ሞዴል ጋር የሚመሳሰል ነው፣ ከምዕራባውያን በምርጫ የመቀያየር ሞዴል ደግሞ ያለው ግንኙነት እስከዚህም ነው?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ የአንተም ሀገር ጭምር ይህን ያደረጉ ይመስለኛል፤ ቢያንስ ሌበር ፓርቲ። የአንድ ድርጅት ተሃድሶ በምዕራብም ይሁን በምስራቅ አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ጊዜ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሌሎች የበለጠ በሥልጣን ላይ ይቆያሉ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የአመራር ለውጥ ማድረግ የበለጠ አስፈላጊ ይሆናል። በሌላ ጊዜ ምርጫ ራሱ የፖለቲካ ድርጅቶችን ይቀያይራል።

 

ኢትዮጵያውያን እርስዎ ሥልጣን ይለቃሉ የሚል እምነት የሌላቸው ለምን ይሆን?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ከዚህ በፊት ተደርጎ ስለማያውቅ።

 

እርስዎ የመጀመሪያ ለመሆን ፈልገዋል?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ አዎ! ቢያንስ ያንን ባህል ለመስበር እፈልጋለሁ።

 

ሥልጣን ለቀው ከወረዱ ምን መሥራት ነው የሚፈልጉት? ላለፉት 34 ዓመታት ዕረፍት ወጥተው እንደማያውቁ ይገባኛል፣

 

ጠ/ሚ መለስ፦ የእኔ ምርጫና ፍላጎት ማንበብ ምናልባትም መፃፍ ነው። ያም ሆኖ ግን ይህም ራሱ በፓርቲው ውሳኔ ላይ የተመሰረተ ነው። አንድ የማላደርገው ነገር ግን ድርጅቴም ሊያስበው (ከቁጥር ሊያስገባው) የማይችለውን በማንኛውም የመንግሥት አስተዳደር ሥራ ውስጥ መግባቴን ነው።

 

እና በቃ ጠቅለው ይወጣሉ?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ ያማ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው። ከዚህ ውጭም የአመራር ለውጥ ሊኖር አይችልም። ይህንን ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ካበቃን በኋላ ድርጅቴ አንድም፣ ቁጭ ብዬ አጠናና እጽፍ እንደሆነ አለዚያም ሌላ ፓርቲ ሚና ይሰጠኝ እንደሆነ የድርጅቴ ውሳኔ ነው።

 

እንደ የድርጅቱ ሊቀመንበር ማለት ነው?

 

ጠ/ሚ መለስ፦ አይመስለኝም። አይደለም። ምክንያቱም የድርጅቱ ሊቀመንበር የሚሆነው ጠ/ሚኒስትሩ ነው። ይህ ቦታ (የሊቀመንበርነት ሥልጣን) ጡረታ የወጣ ሰው ሥልጣን አይደለም።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ