Protest in Amhara region over student abductions, January 28, 2020

“እኅቶቻችን ይፈቱ!” በማለት በአማራ ክልል የተካሔደው ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ (ማክሰኞ ጥር ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 28, 2020)

"የሕግ የበላይነትን በማጠናከር የዜጎችን ደኅንነት እናስጠብቃለን!" የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት

የአገራችን ሕዝቦች በአብሮነትና በአንድነት በሕብረ ብሔራዊነት ለበርካታ ዓመታት ድርና ማግ ኾነው፣ ለሌሎች ዓለማችን ሕዝቦች በልዩነት ተቻችሎ በመኖር ተምሳሌት የኾኑ ሕዝቦች ናቸው። በተለይም ደግሞ ለሰላምና የሕግ የበላይነት ልዩ ክብርና ግምት በመሥጠት ባለፉት ሺህ ዓመታት ሕገ-መንግሥት ሳይኖር በሕገ-ልቦና በሰላማዊነት ተከባብረው በልዩነት አንድ ኾነው የኖሩ ሕዝቦች ናቸው።

የአማራ ሕዝብ በአገራችን የሺ ዓመታት ታሪክ ውስጥ አገረ መንግሥት በመመሥረት ደማቅ አሻራ ያሳረፈ ድንቅ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ እንደሌሎቹ የአገሪቱ ሕዝቦች በመላው አገሪቱ ተሰራጭቶ የሚገኝ ሥራ ወዳድና ሕግ አክባሪ ሕዝብ ነው። ይሁን እንጂ በአማራ ጠል የውሸት ትርክት ምክንያት በአብሮነትና በአቃፊነት የሚታወቀው የአማራ ሕዝብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማንነቱ የተነሳ ልዩ ልዩ ጥቃት በተደራጁ ቡድኖች እየደረሰበት ያለ ሕዝብ ነው። የሚደርሰው ጉዳት በተለያየ መልኩ ቢሆንም፤ በተለይም ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች በማንነታቸው የተነሳ እየደረሰባቸው ያለው ጥቃት ለቆየው አገራዊ አንድነትና አብሮነት ሲባል በሆደ ሰፊነት ብናልፈውም፤ አሁንም ድረስ የችግሩ ገፈት ቀማሽና ሰለባ እየኾነ ይገኛል።

አሁንም ድረስ በፀረ አማራ ኃይሎች የተሠራውና በአማራ ሕዝብ ላይ የተቃጣው የሐሰት ትርክትና የጥፋት ዒላማ ሕዝባችንን ለሞትና ለስደት ሲዳርግ መቆየቱና አሁንም ድረስ የዚህ የጥላቻ ትርክት ሰለባ ኾኖ መቀጠሉ ሁሉም የሚረዳው እውነታ ከኾነ ውሎ አድሯል። እኛ የአማራ ሕዝቦች በጥቃቅን ጉዳዮች የምንከፋፈልና የምንተላለቅ ታሪክ አልባ ሕዝቦች ሳንሆን የሰላምን ክቡርነትና ታላቅነት ጠንቅቀን የምናውቅ ሕዝቦች በመኾናችን እየገጠመን ያለውን ችግር ከሌሎች ሰላምና አብሮነት ወዳድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በጋራ ታግለን እንፈታዋለን የሚል እምነት ይዘን እየሠራን የምንገኝ ሕዝቦች ነን።

ይሁን እንጂ ለዓመታት በፀረ አማራ ኃይሎች የተሠራውና በአማራ ሕዝብ ላይ የተቃጣው የሐሰት ትርክትና የጥፋት ዒላማ ሕዝባችንን ለሞትና ለስደት እየዳረገ ይገኛል፤ አሁንም ድረስ የዚህ የጥላቻ ትርክት ሰለባ ኾኖ መቀጠሉን ሁሉም የሚረዳው እውነታ ከመኾኑም በላይ በጋራ የሚደረገው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት እያመጣ አይደለም።

በቅርቡ በደንቢደሎ ዩኒቨርስቲ ሲማሩ በነበሩ ተማሪዎቻችን ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ፀረ አማራ ኃይሎች የተፈጸመ እገታ እንዳለ መረጃው ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ የሚደረግ ጥረት እንዳለ የሚሰማ ቢሆንም፤ ውጤት ባለመገኘቱ የክልሉ ሕዝብ ቅሬታውንና የድርጊቱን ሁኔታ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ የመንግሥትን ቸለልተኝነትና ዝምታ በማውገዝ፤ ዛሬ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች ተካሒደዋል። ሰልፉም ከ52 ቀናት በላይ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በታጠቀ ቡድን ታግተው በሰቆቃና በስቃይ የሚገኙ የአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ይፈቱ፤ በአማራ ላይ እየተቃጣ ያለው ብሔር ተኮር ጥቃት ሊቆም ይገባል፤ በተለያዩ የአገሪቱ ዩነቨርሲቲዎች ሲማሩ የነበሩና ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመለሱ፤ ኢ-ሰብዓዊና ከሞራል ያፈነገጠውን ድርጊት የፈጸሙት አካላትም ተጠያቂ ይሁኑ፤ መንግሥትም የሕግ የበላይነትን ያስከብር ወንጀለኞችንም ለሕግ ያቅርብ፤ የአማራ ክልል መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ለሕዝቡ አለማሳወቁና የፌደራልም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት የተጣለባቸውን ሕዝባዊ ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣታቸው፤ በሚመለከታቸው አካላት የተናበበ መረጃ ለሕዝብ አለመሠጠቱ ሕዝቡን እንዳሳዘነና ታጋቾቹ እንዲለቀቁ በተካሔዱት ሰልፎች የተላለፉ መልእክቶች ሲሆኑ፤ ሰልፉም ፍጹም ሰላማዊ በኾነና በሠለጠነ መልኩ ተካሒዷል።

በዚህ አጋጣሚ ለሰልፉ አስተባባሪዎች፣ ለመላ የክልላችን ሕዝቦችና የሕግ አስከባሪ አካላት የክልሉ መንግሥት ምስጋናውን እያቀረበ፤ ሰልፈኞች ያቀረቧቸው የፍትሕና የሕግ የበላይነት ይከበር ጥያቄዎች ትክክልና ተገቢ ስለኾነ የታገቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዲለቀቁ ከአሁን በፊት በጀመርነው መሠረት ከፌደራልና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጋር በጋራ እንደምሠራ ለማረጋገጥ እንወዳለን።

ጥቃቱ የተቃጣውና እየተፈጸመ ያለው በአማራና በአማራ ተወላጅ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን፤ በሰብዓዊ ፍጡርና በዜጎች ላይ መኾኑን በመገንዘብ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ደግሞ ጥቃቱ የተፈጸመበት ክልል የኦሮሞ ሕዝብ ከጎናችን ቆሞ ሊያወግዝና ልጆቻችን እንዲለቀቁና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያችን እናስተላልፋለን።

በመጨረሻም የአማራ ክልል ሕዝብ ቀጣይም በተናጠልም ኾነ በቡድን በአማራ ክልል ተወላጆች ላይ የሚደርስን ጥቃት በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በሚደረገው ጥረት ከመንግሥት ጎን በመቆም ለአንድነታችንና ለሰላም ዘብ እንዲቆም ጥሪውን ያስተላልፋል።

የሕግ የበላይነትን በማጠናከር የዜጎችን ደኅንነት እናስጠብቃለን!
የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት
ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም.
ባሕር ዳር

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!